እስራኤል ከየመን ሚሳዔል እንደተተኮሰባት ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ከየመን ሚሳዔል መተኮሱን እንደለየ አስታወቀ። የዜና ወኪሎቹ ሮይተርስ እና አጃንስ ፍራስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ)፤ አንድ ወር የሞላው የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከየመን ወደ እስራኤል ሲተኮስ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ዘግበዋል።
የእስራኤል ጦር በቴሌግራም ገጹ ባሰፈረው መልዕክት፤ መከላከያ ሠራዊቱ ከየመን ወደ እስራኤል ግዛት ሚሳዔል መተኮሱን ለይቷል፤ የአየር መከላከያ ስርዓቶች ስጋቱን ለመቀልበስ እየሰሩ ነው” ብሏል። ከ15 ደቂቃ ካነሰ ቆይታ በኋላም በመላ አገሪቱ የሚገኘው ሕዝብ ጥብቅ ከሆኑትን ስፍራዎች መውጣት እንደሚችሉ አስታውቋል።
እስራኤል ሚሳዔል እንደተተኮሰባት የገለጸችው በኢራን የሚደገፈው የየመኑ ሁቲ ቃል አቀባይ ቴህራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ አማጺው ቡድን የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትን እንደሚቀላቀል ከተናገሩ በኋላ ነው።
የመኑ ጦር ኃይሎች የተባለው የሁቲ ወታደራዊ ክንፍ ቃል አቀባይ የሆኑት ያህያ ሳሪ ቴሌግራም ላይ ባወጡት መግለጫ፤ ሦስት ሁኔታዎች የሚፈጸሙ ከሆነ “ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለማድረግ ጣቶቻችን ቃታው ላይ ናቸው” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ የገለጿቸው ሦስት ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፦
- አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ሌላ አገር የሚቀላቀል ከሆነ
- አሜሪካ እና እስራኤል “ቀይ ባሕርን በኢራን እስላማዊ ሲፐብሊክ እና ማንኛውም ሙስሊም አገር ለሚፈጸመው ጠበኛ ዘመቻ የሚጠቀሙ ከሆነ”
- ኢራን ላይ የሚካሄደው “ግጭት የሚባባስ” ከሆነ
መግለጫው አክሎም፤ ይህ እርምጃ "ጠላቶቹ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ፣ በፍልስጤም እና ጋዛ፣ በኢራቅ እንዲሁም በሊባኖስ ላይ ለሚፈጽሙት የቀጠለ ጥቃት" የተሰጠ ምላሽ መሆኑን ገልጿል።




















