ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን የምታስከፍልበት ሕግ ልታወጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢራን ፓርላማ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከሚያልፉ መርከቦች ክፍያ ለመሰብሰብ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ሊወጣ መሆኑን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
የፓርላማው የኮንስትራክሽን ኮሚቴ ኃላፊ፤ “ረቂቅ ተዘጋጅቷ ነገር ግን ወደ ሙሉ አዋጅነት ደረጃ አልደረሰም” ብለዋል። ሕጉ የተዘጋጀው “ለሚያልፉ መርከቦች የደኅንነት ጥበቃ ለማቅረብ” እንደሆነም ተናግረዋል።
አንድ የአገሪቱ ሕግ አውጪ ደግሞ “ፓርላማው ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያላትን ሉዓላዊነት፣ ቁጥጥር እና የበላይነት በሕጋዊ መንገድ ለማረጋገጥ የተያዘውን እቅድ እየተከተለ ነው፤ በዚያውም ክፍያ በመሰብሰብ የገቢ ምንጭ ይፈጥራል” ማለታቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ የኢራን የዜና ወኪሎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
“ሸቀጦች በሌሎች ኮሪደሮች ሲያልፉ የትራንዚት ክፍያ እንደሚከፍሉ ሁሉ ይህ ሙሉ በሙሉ ተፈጥሯዊ ነው፤ የሆርሙዝ ወሽመጥም መተላለፊያ ነው” ብለዋል።
“እኛ ጥበቃ እናቀርባለን፤ መርከቦች እና የነዳጅ ጫኞች ይህንን አይነት ክፍያ መክፈላቸውም ተፈጥሯዊ ነው” ሲሉ የረቂቁን መነሻ አስረድተዋል።
በወሽመጡ ከሚያልፉ መርከቦች የሚሰበሰበው ክፍያ ምን ያህል እንደሚሆን እስካሁን አልታወቀም።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ትናንት ምሽት በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው፤ ቴህራን እስካሁን እንደ “ቻይና፣ ሩሲያ፣ ፓኪስታን፣ ኢራቅ እና ህንድ” ካሉ አገራት የቀረበላትን የመርከቦች ይለፉ ጥያቄ መቀበሏል ገልጸዋል።
ከኢራን አንጻር ሲታይ የሆርሙዝ ወሽመጥ “ሙሉ ለሙሉ አልተዘጋም፤ ለጠላቶች ግን ዝግ ነው” ብለዋል።


















