ኢራን አሜሪካ ለፈጸመችው ጥቃት እንዴት ምላሽ ልትሰጥ ትችላለች?
አሜሪካ ሌሊቱን በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ለፈጸመችው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ከሦስት ስልታዊ ምርጫዎች አንዱን መምረጥ ይጠበቅባታል። እነዚህ ሦስት ስልታዊ አማራጮች ምንድን ናቸው?
እጅን አጣጥፎ መቀመጥ- ይህ ከተጨማሪ የአሜሪካ ጥቃቶች ሊጠብቃት ይችላል። እንዲያውም የዲፕሎማሲውን መስመር መምረጥ ከአሜሪካ ጋር እንደገና ድርድር ለመቀመጥ ያስችላታል። ነገር ግን ምንም ነገር አለማድረግ የኢራን አመራርን በተለይም አሜሪካ ጥቃት ከፈጸመች አስከፊ መዘዞች እንደሚደርሱ ካስጠነቀቀ በኋላ ደካማ ያስመስለዋል። አስተዳደሩ በሕዝቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት መቀዛቀዝ እና የአሜሪካ ተጨማሪ ጥቃቶች የሚያደርሱትን ኪሳራ በማመዛዘን ሊወስን ይችላል።
ጠንካራ እና ፈጣን ምላሽ መስጠት- ኢራን አሁንም ለዓመታት አምርታ የሸሸገቻቸው ከፍተኛ የባለስቲክ ሚሳኤሎች አሏት። ጥቃት ለመሰንዘር የምትወስን ከሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ ወደ 20 የሚጠጉ የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ይገኛሉ። እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ የባህር ኃይል መርከቦች ላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ፈጣን ጀልባዎችን በመጠቀም 'ተከታታይ ጥቃት' ልትፈጽም ትችላለች።
ጊዜ ጠብቆ እና አድብቶ ጥቃት መፈጸም- ·ይህ ማለት አሁን ያለው ውጥረት እስኪበርድ ድረስ መጠበቅ እና የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች በከፍተኛ ጥንቃቄ ላይ በማይሆኑበት ጊዜ ድንገተኛ ጥቃት መፈፀም ማለት ነው።




















