"የአሜሪካ ጥቃት ኢራንን የማንበርከክ እንጂ ከኒውክሌር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም"- አያቶላህ ኻሜኒ

አሜሪካ በኢራን የፈጸመችው ጥቃት "ኢራንን እጅ የማሰጠት" እንጂ በጭራሽ ከኒውክሌር ማበልጸግ ጋር ፍጹም ግንኙነት እንደሌለው የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ ተናገሩ።ከሳምንት በኋላ የታዩት ጠቅላይ መሪው “ሁልጊዜም ቢሆን አንድ ነገር ብቻ ነው ፍላጎታቸው፤ ኢራን እጇን እንድትሰጥ” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

  • እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ሳኢድ ኢዛዲ መገደላቸውን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ማረጋገጡን የአገሪቱ ሚዲያ ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
  • የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን ከአሜሪካ ጥቃት በፊት የበለጸገ የዩራኒየም ክምችቷን ከፎርዶ የኒውክሌር ጣቢያ አዛውራለች የሚለውን ሪፖርት አስተባበሉ።
  • በኳታር የአሜሪካ የጦር ሰፈርን ለመከላከል የቀሩት 44 ወታደሮች ብቻ እንደነበሩ አሜሪካ ገለጸች
  • አሜሪካ 'ኦፕሬሽን ሚድናይት ሐመር' በሚል ስያሜ በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት ለ15 ዓመታት የታቀደበት እንደሆነ የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ዳን ኬይን ገለጹ።
  • በኢራን ላይ የተፈጸመው "የተሳካ ታሪካዊ ጥቃት ነበር" ሲሉ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ገለጹ
  • አሜሪካ በኢራን የፈጸመችው ጥቃት ኢራንን እጅ የማሰጠት እንጂ በጭራሽ ከኒውክሌር ማበልጸግ ጋር ፍጹም ግንኙነት እንደሌለው የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ ተናገሩ
  • ትራምፕ፤ የአሜሪካ ጥቃት የኢራን ኒውክሌር ይዞታዎችን አላወደመም የሚለውን የደህንነት ግምገማ ውድቅ አደረጉ
  • የአሜሪካ ጥቃት የኢራን ኒውክሌር ይዞታዎችን እንዳላወደመ የደህንነት ግምገማ አሳየ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በሰሜናዊ ኢራን ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ 33 ጉዳት ደረሰባቸው

    እስራኤል በሰሜናዊ ኢራን በፈፀመችው ትቃት ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ አራት ቤቶች መውደማቸውን ባለስልጣናት ገለፁ።

    በጊላን የሚገኘው አስተዳደር ቢሮ 33 ሰዎች መጎዳታቸውን ጨምሮ ገልጿል።

    የአካባቢው አስተዳደር የ”ሽብር ጥቃት” በአስታኔህ ዬ አሽራፊዬ ጥቃት መድረሱን አስታውቋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ከጥቃቱ ጀርባ እስራኤል አለች ሲሉ ዘግበዋል።

    የጊላን ምክትል አስተዳዳሪ ከተገደሉት ወይም ከተጎዱት 16ቱ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው ብለዋል።

    የተወሰኑ መገናኛ ብዙኃን ከተገደሉት ሰዎች መካከል የኒውክሌር ሳይንቲስቱ ሞሐመድ ረዛ ሴዲቂ ይገኙበታል ሲሉ ዘግበዋል።

    የእስራኤል መንግሥት ትናንት በፈፀመው ጥቃት የኒውክሌር ሳይንቲስት መግደሉን አስታውቋል።

  2. እስራኤል የአሜሪካን የተኩስ አቁም ሃሳብ መቀበሏን አስታወቀች

    የእስራኤል የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በኢራን ሚሳዔል ከወደመ ሕንጻ ውስጥ የሰው ሕይወት ለማትረፍ ሲጥሩ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የእስራኤል መንግሥት በዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን የተኩስ አቁም ሃሳብ መቀበሉን ገለፀ፥

    ዛሬ ማለዳ ላይ ባወጣው መግለጫ “እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተጣሰ ጠንካራ ምላሽ ትሰጣለች” ብሏል።

    የእስራኤል መንግሥት በኢራን ላይ ያደረሰው ጥቃት "ዓላማውን" ማሳካቱን በመግለጽ የተኩስ አቁም ሃሳብን ተቀብያለሁ ብሏል።

    እስራኤል አክላም ኢራን በኒውክሌር ጦር መሳሪያ እና በባለስቲክ ሚሳኤሎች የደቀነችውን “ሁለት ፈጣን የኅልውና ስጋት” አስወግጃለሁ ብላለች።

    በተጨማሪም እስራኤል "በወታደራዊ አመራር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። እንዲሁም በርካታ የኢራን መንግሥት ዒላማዎችን አውድሜያለሁ" ብላለች።

    የእስራአል መንግሥት መግለጫ በመቀጠል የእስራኤልኃይሎች በመጨረሻውቀን በወሰዱት እርምጃ “በቴህራን ማዕከላዊ ክፍል በሚገኝ የመንግሥት ዒላማዎችን በመቶዎች የሚቆጠሩ የባሲጅ አባላትን” ማስወገዳቸውን ገልጿል።

    የባሲጅ ታጣቂዎች የኢራን መንግሥት ተቃውሞን ለማፈን የሚጠቀምባቸው ሚሊሻዎች ናቸው።

    መግለጫው አክሎም በዚሁ ጥቃት "ሌላ ከፍተኛ የኒውክሌር ሳይንቲስትን ተገድሏል" ብሏል።

    “እስራኤልፕሬዝዳንት ትራምፕን እና አሜሪካን በመከላከያ ላደረጉት ድጋፍ እና የኢራንን የኒውክሌር ስጋት ለማስወገድ ላሳዩት ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል” ሲል መግለጫው ገልጿል።

  3. የእስራኤል አምቡላንስ አገልግሎት በኢራን የሚሳኤል ጥቃት አራት ሰዎች መሞታቸውን ገለፀ

    በኢራን የሚሳዔል ትቃት የተመታ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, MDA

    የእስራኤል አምቡላንስ አገልግሎት በኢራን የሚሳኤል ጥቃት አራት ሰዎች መሞታቸውን እና 22 መጎዳታቸውን አስታወቀ።

    በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሁለቱ መለስተኛ 20ዎቹ ደግሞ አነስተኛ ጉዳት ገጥሟቸዋል።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ቴህራን የተኩስ አቁሙተግባራዊ መሆን ከመጀመሩ በፊት "የመጨረሻ ዙር ሚሳዔሎች አስወንጭፋለች" ሲል ዘግቧል።

  4. “የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል"- ትራምፕ

    ትራምፕ በኢራን እና እስራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆን መጀመሩን ገለፁ።

    ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ “የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። እባካችሁ አትጣሱት!” ሲሉ ተማጽነዋል።

    እስራኤል እስካሁን ድረስ በይፋ የተኩስ አቁም ስምምነቱን መቀበሏን ያልገለፀች ሲሆን የኢራን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣብያ ግን የተኩስ አቁም በእስራኤል ላይ “ተጭኖባታል” ሲል ዘግቧል።

  5. ኢራን ሚሳዔል ማስወንጨፏን አለማቆሟን የእስራኤል ጦር ገለፀ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን እና እስራኤል የ12 ቀን ጦርነትን ለማስቆም ሙሉ ለሙሉ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን ከገለፁ በኋላ ከኢራን በተተኮሰ ሚሳዔል ሦስት ሰዎች መሞታቸውን የእስራኤል ጦር አስታወቀ።

    በደቡባዊ እስራኤል ቴል አቪቭ እና ቤርሳቤህ አካባቢ ፍንዳታዎችን መሰማታቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጦር ኢራን ስድስት ዙር ሚሳኤሎች ማስወንጨፏን ሲገልጽ፣ የእስራኤል ብሔራዊ አምቡላንስ አገልግሎት በቤርሳቤህ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቋል።

    ይህም ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ካወጁ በኋላ በእስራኤል የተመዘገበ የመጀመሪያው ሞት ሆኗል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የዋይት ሐውስ ከፍተኛ ባለስልጣንን ጠቅሶ ትራምፕ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ባደረጉት ውይይት የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማድረግ መስማማታቸውን ዘግቧል።

    አንድ የኢራን ባለስልጣን ቴህራን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መስማማቷን ቀደም ሲል አረጋግጠዋል።

    ነገር ግን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ጥቃቷን እስካላቆመች ድረስ ጦርነቱ ማቆም እንደማይቻል ተናግረዋል።

  6. ትራምፕ ኢራን እና እስራኤል በተመሳሳይ ጊዜ ሰላም እንደሚፈልጉ እንደጠየቋቸው ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል እና ኢራን “በተመሳሳይ ጊዜ ማለት ይቻላል ሰላም [እናውርድ] አሉኝ” ሲሉ ጽፈዋል።

    በዚህ ጊዜ "ጊዜው አሁን እንደሆነ አወቅኩ" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

    ሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በመጥቀስ “ዓለም እና መካከለኛው ምሥራቅ እውነተኛዎቹ አሸናፊዎች ናቸው። ሁለቱም አገራት ወደፊት ታላቅ ፍቅር፣ ሰላም እና ብልጽግናን ያያሉ" ብለዋል።

    ኢራንም ሆነች እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ስለመደረሱ ቤእፋ ያሉት ነገር የለም።

    ቴህራን እስራኤል ኢራንን መደብደቧን ካቆመች እርሷም ሚሳዔሎቿን ማስወንጨፍ እንደምታቆም ገልጻለች።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ ሁለቱ አገራት “ በርካታ የሚያገኙት ነገር አለ።እንዲሁም ከፍትህ እና ከእውነት መንገድ ከራቁ የሚያጡትም አለ” ብለዋል።

    ልጥፋቸውን ሲያጠናቅቁም የእስራኤልና የኢራን የወደፊት ዕጣ ፈንታ “ያልተገደበና በታላቅ ቃል ኪዳን የተሞላ ነው። እግዚአብሔር ሁለታችሁንም ይባርክ!” ብለዋል።

  7. የአሜሪካው ፕሬዚደንት በኢራን እና እስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሷል አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን እና እስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን ገለፁ።

    ሁለቱ አገራት ግን በይፋ የተኩስ አቁም ስለመደረሱ ያሉት ነገር የለም።

    ኢራን እስራኤል የምትፈጽመውን ጥቃት የምታቆም ከሆነ እርሷም ሚሳዔሎችን ማስወንጨፍ እንደምታቆም ተናግራለች።

    ትናንት ምሽት ኢራን በኳታር ወደሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ሚሳዔሎችን አስወንጭፋ ነበር።

    ይህ ከሆነ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው ትራምፕ በኢራን እና እስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሳወቁት።

    ትራምፕ ሁለቱም አገራት በ24 ሰዓታት ውስጥ ጥቃት መፈጸማቸውን ያቆማሉ ብለዋል።

    ነገር ግን ከዚያ በኋላም እስራኤል በኢራን የሚገኙ ዒላማዎች ላይ ድብደባ መፈፀሟ ተሰምቷል።

    እስራኤል ሁለቱ አገራት በቀጣዮቹ 24 ሰዓታት ውስጥ ተኩስ ያቆማሉ ለሚለው የትራምፕ መግለጫ ይፋዊ ምላሽ አልሰጠችም።

  8. ኢራን ዒላማ ስላደረገችው የአሜሪካ ጦር ሰፈር የምናውቀው በአጭሩ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ አል ኤዴይድ ጦር ሰፈርን ባለፈው ግንቦት በጎበኙበት ጊዜ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ አል ኤዴይድ ጦር ሰፈርን ባለፈው ግንቦት በጎበኙበት ጊዜ

    በኳታር የሚገኘው እና በኢራን የሚሳዔል ጥቃት ዒላማ የተደረገው አል ኡዴይድ የተባለው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ከዋና ከተማዋ ዶሃ አቅራቢያ የሚገኝ ነው።

    ይህ የጦር ሰፈር ወደ ስምንት ሺህ የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮች የሰፈሩበት ሲሆን፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ የአየር ኃይል ክፍል ዋና መዘዣ ነው።

    አልፎ አቡ ናኽላ በሚል መጠሪያው በሚታወቀው በዚህ ጦር ሰፈር ውስጥ የብሪታኒያ ወታደሮች እየተፈራረቁ ለአገልግሎት ይቆያሉ።

    በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ረጅሙ የአውሮፕላን መንደርደሪያ ሜዳ ያለው ይህ የጦር ሰፈር በአሁኑ ወቅት አሜሪካ በኢራቅ ውስጥ ለምታካሂደው ወታደራዊ ተልዕኮ ዋና ማዘዣ እና የአቅርቦት ማዕከል ነው።

    ኳታር የአል ኡዴይዳ ጦር ሰፈርን እንድትጠቀምበት የፈቀደችው ከ25 ዓመት በፊት ነው። ሁለቱ አገራት ስምምነት ተፈራርመው ጦር ሰፈሩ በአሜሪካ እጅ ከገባ በኋላ ኳታር በይፋ በግዛቷ ውስጥ የአሜሪካ ወታደሮች እንዲሰፍሩ ዕውቅና ሰጥታለች።

    የአገራቱ የስምምነት ጊዜ ባለፈው ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ሌላ ስምምነት ተደርሶ የአሜሪካ ወታደሮች ለተጨማሪ 10 ዓመታት በኳታር እንዲቆዩ ከስምምነት መደረሱን ሲኤንኤን ዘግቦ ነበር።

  9. ኳታር የኢራንን የሚሳዔል ጥቃት አወገዘች

    ኳታር በአል ኡዴይድ በሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሠፈር ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በጥብቅ አወገዘች።

    የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጂድ አል አንሳሪ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ጥቃቱ “የኳታርን ሉዓላዊነት፣ የአየር ክልል፣ ዓለም አቀፍ ሕግ እና የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት ጥሰት እንደሆነ እንቆጥረዋለን” ብለዋል።

    የኳታር የአየር መከላከያ ሥርዓት “ጥቃቱን በተሳካ ሁኔታ መመከቱን እና የኢራንን ሚሳዔሎች ማክሸፉን” የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ የጦር ሠፈሩም ቀደም ብሎ ከአካባቢው ወጥቷል ብለዋል።

    “በጦር ሠፈሩ ላይ የነበሩ ሠራተኞችን ደኅንነት ለማረጋገጥም ሁሉም አስፈላጊ እርምጃዎች ተወስደዋል” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በጥቃቱ የተከሰተ “ሞትም ሆነ ጉዳት እንደሌለ” አረጋግጠዋል።

    “ኳታር ለዚህ ጭካኔ ለተሞላበት ጥቃት የሚመጣጠን ምላሽ የመስጠት መብቷ የተጠበቀ ነው” ሲሉም አክለዋል።

  10. “በአገራችን ላይ የተፈፀመን ጥቃት በዝምታ አናልፈውም” የኢራን አብዮታዊ ዘብ

    አመሻሹ ላይ ኢራን የሚሳዔል ጥቃት የሰነዘረችባት ኳታር በምሽት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, አመሻሹ ላይ ኢራን የሚሳዔል ጥቃት የሰነዘረችባት ኳታር በምሽት

    የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ኢራን በአሜሪካ ለተፈፀሙባት ጥቃቶች “ኃያልና ለድል የሚያበቃትን” ምላሽ መስጠት መጀመሯን ዘገበ።

    በመንግሥት የሚመራው ታስኒም የዜና ወኪል እንዳለው የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ በኳታር እና በኢራቅ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሠፈሮች ላይ የሚሳዔል ጥቃቶችን ከፍቷል።

    ታስኒም እንደዘገበው “በአገር ላይ ጥቃት ሲፈፀም ዝም ብሎ መመልከት አይቻልም” ብሏል አብዮታዊ ዘቡ።

    ጨምሮም በጥቃቱ ኢራን ለዋይት ሐውስ እና ለአጋሮቿ ያስተላለፈችው መልዕክት “ግልጽ” ነው ብሏል።

    ኢራን በሉዓላዊነቷ፣ በግዛት አንድነቷ እና በደኅንነቷ ላይ የተፈፀመባትን ጥቃት በምንም ዓይነት ሁኔታ ዝም ብላ እንደማትመለከትም ገልጿል።

    ቀደም ብሎ ኢራን በኳታር በሚገኘውና በአሜሪካ በሚመራው የጦር ሠፈር ላይ ጥቃት ልትፈፅም እንደምትችል ቢቢሲ “ተጨባጭ መረጃዎችን” አግኝቶ ነበር።

    የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ዋይት Hውስ እና መከላከያ መሥሪያ ቤት ስለ ስጋቱ ያውቁ እንደነበር እና በቅርበት እየተከታተሉ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።

  11. ኢራን በኳታር እና በኢራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ ሚሳዔሎችን ተኮሰች

    ካርታ

    የኢራን መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን አሜሪካ ለፈጸመችው ጥቃት ምላሽ ኢራን “ግዙፍ እና ድል የሚያቀዳጅ” ጥቃት መሰንዘር መጀመሯን አስታውቀዋል።

    የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ‘ታስኒም’ እንደዘገበው በኳታር እና በኢራቅ ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሚሳዔሎችን ተኩሷል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ ፍንዳታዎች መሰማታቸው ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።

    በኳታር አል ኡዳይድ በሚገኘውና በአሜሪካ በሚመራው ጥምር የአየር ኃይል ኦፕሬሽን ማዕከል ላይ ጥቃት ሊደርስ ይችላል የሚል "ተጨባጭ ስጋት" መኖሩን ቢቢሲ መረጃ አግኝቶ ነበር።

    ቀደም ሲል የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ኢራን በኳታር ውስጥ በሚገኝ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈር ላይ ሚሳዔሎችን ለመተኮስ እየተዘጋጀች ነው ብለው ነበር።

    አገሪቱ አሁን ላይ በጊዜያዊነት የአየር ክልሏን የዘጋች ሲሆን የጦር ሠፈሩም በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ የቢቢሲ የደኅንነት ዘጋቢ ተነግሮኛል ብሏል።

    ስጋቱ የመጣው ኢራን በአየር ኃይል የጦር ሠፈሩ ላይ የሚሳዔል ጥቃት ትሰነዝራለች ከሚል ነው።

    አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ማዕከላት ላይ ጥቃት ከፈፀመች በኋላ ኢራን “ተመጣጣኝ እርምጃ” እንደምትወስድ ዝታለች።

    የአሜሪካን ጨምሮ በኳታር የሚገኙ የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎችም ዜጎቻቻው እንዲጠነቀቁ እያሳሰቡ ነው።

    አል ኡዳይድ ከኳታር መዲና ዶሃ ወጣ ብሎ የሚገኝ ግዙፍ የጦር ሰፈር ሲሆን፣ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ለምታደርጋቸው የአየር ዘመቻዎች የማዕከላዊ ዕዝ ዋና መሥሪያ ቤት መገኛ ነው። የብሪታንያ ወታደሮችም በዚሁ የጦር ሰፈር እየተቀያየሩ ያገለግላሉ።

  12. ኢራን ለአሜሪካ ጥቃት “ተመጣጣኝ ምላሽ” እንደምትሰጥ የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ተናገሩ

    ኢስፋሃን የኒውክሌር ማብለያ ጣቢያ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ የሚያሳይ የሳተላይት ምስል

    የፎቶው ባለመብት, Maxar Technologies / EPA

    የምስሉ መግለጫ, ኢስፋሃን የኒውክሌር ማብለያ ጣቢያ ከአሜሪካ ጥቃት በኋላ ጉዳት እንደደረሰበት የሳተላይት ምስሎች አሳይተዋል።

    ኢራን ለአሜሪካ ጥቃት "ተመጣጣኝ ምላሽ" እንደምትሰጥ የአገሪቷ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ተናገሩ።

    ኢታማዦር ሹሙ ይህን ያሉት የደረሰው የጉዳት መጠን በውል ባይታወቅም አሜሪካ በሦስት የኢራን የኒውክሌር ማብለያ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ነው።

    አብዶልራሂም ሙሳቪ ይህን ማለታቸውን የዘገበው ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ነው።

    ሜጀር ጀነራል አብዶልራሂም ሙሳቪ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት “ የትራምፕ እርምጃ ከተስፋ መቁረጥ የመነጨ እና እስራኤልን እና ኔታንያሁን ለመታደግ ያለመ ነው” ብለዋል።

    ኢታማዦር ሹሙ ጨምረውም "ትራምፕ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትርን “ውድቀት” ባዩ ጊዜ ኢራንን በመደብደብ “ሰው ሰራሽ እስትንፋስ” ሊሰጡት ወስነዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

    ሞሳቪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሆነው የተሾሙት የተኳቸው መሐመድ ሁሴን ባግሄር እስራኤል በኢራን ላይ በፈፀመችው የመጀመሪያው ጥቃት ከተገደሉ በኋላ ነው።

  13. በኳታር የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ ከእንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ አሳሰበ

    በዶሃ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ

    የፎቶው ባለመብት, U.S. Embassy Doha

    በኳታር መዲና ዶሃ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በድረገጹ ላይ ባወጣው ጽሑፍ ዜጎቹ ሌላ መረጃ እስከሚሰጣቸው ድረስ ከእንቅስቃሴ ተቆጥበው ቤት ውስጥ እንዲሆኑ አሳሰበ።

    ኤምባሲው ለዚህ የሰጠው ምክንያት “ለጥንቃቄ” የሚል ነው።

    በድረገጹ ላይ የተሰጠ ተጨማሪ መረጃ የለም።

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥትም ለዜጎቹ ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፏል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የብሪታኒያ ዜጎች ከመንግሥታቸው የሚተላለፍላቸውን የጉዞ መመሪያ በቅርበት መከታተል እንደሚገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ላሚይ አሳስበዋል።

    “መንግሥት አሁን ላይ በኳታር የሚገኙ የብሪታንያ ዜጎች ሌላ መረጃ እስከሚሰጣቸው ድረስ ከእንቅስቃሴ ተቆጥበው በቤት ውስጥ እንዲሆኑ ይመክራል” ብለዋል።

    የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በድረ ገጹ ላይ ባወጣው መረጃም ይህ መመሪያ የተላለፈው አሜሪካ "ለጥንቃቄ" ስትል ለዜጎቿ ተመሳሳይ መልዕክት በማውጣቷ ምክንያት ነው ብሏል።

    የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም በርካታ ኤምባሲዎች ዜጎቻቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እያሳሰቡ መሆናቸውን ተናግረው፤ ይህ ግን በአገሪቷ ውስጥ “የተለየ ስጋት መኖሩን የሚያመለክት” አለመሆኑን ገልጸዋል።

    ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው በአገሪቷ ያለው የፀጥታ ሁኔታ የተረጋጋ መሆኑን ጠቅሰው ማስጠንቀቂያ አሊያም እርምጃ የሚያሻቸው ጉዳዮች ሲኖሩ ለኅብረተሰቡ እናሳውቃለን ብለዋል።

  14. ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ማበልጸግ እንደሌለባት አባላቱ መስማማታቸውን የኔቶ ኃላፊ ተናገሩ

    የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ኃላፊ ማርክ ሩት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ በሄግ ከሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ አስቀድመው ለጋዜጠኞች መግለጫ እየሰጡ ነው።

    ዋና ፀሐፊው የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብርን በተመለከተ የኔቶን አቋም አብራርተዋል።

    “የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብርን በተመለከተ ወደ ኔቶ አቋም ስንመጣ፤ አጋሮች ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ማበልጸግ እንደሌለባት ተስማምተዋል” ብለዋል።

    ከዚህም በተጨማሪ የኔቶ አባል አገራት ‘የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መስፋፋትን ለመከላከል’ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ኢራን ግዴታዋን ማክበር እንዳለባት ሲያሳስቡ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

    ጨምረውም ኢራን በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ተሳትፋለች ሲሉ ከስሰዋል።

    “ኢራን ሩሲያ ሰላማዊ ዩክሬናውያንን ለመግደል የምትጠቀምበትን ድሮኖችን አቅርባለች” ብለዋል።

  15. እስራኤል በቴህራን የሚገኘውን ታዋቂ እስር ቤት ለምን ዒላማ አደረገች?

    በቴህራን የሚገኘው ኤቪን እስር ቤት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በኢራን የሚገኘው ኤቪን እስር ቤት በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን እንደያዘ ይገመታል።

    እስራኤል በቴህራን የሚገኘውን እና ታዋቂ የሆነውን ኤቪን እስር ቤት ዛሬ አዲስ በፈፀመቻቸው ጥቃቶች መምታቷን ገልጻለች።

    ኢራን ጥቃቱን ለማጣጣል ብትሞክርም ከሕግ አካላት ጋር ግንኙነት ያለው 'ሚዛን ኒውስ' የተባለው የዜና ወኪል ግን “የእስረኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ አስፈላጊው እርምጃ ተወስዷል” ሲል ዘግቧል።

    ለመሆኑ ይህ ታዋቂ እስር ቤት ምን ያህል ወሳኝ ነው?

    ኤቪን እስር ቤት በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን የያዘ ሲሆን፣ በኢራን ዋነኛው የፖለቲካ እስር ቤት ነው።

    እስር ቤቱ ምን ያህል እስረኞችን እንደያዘ ይፋዊ መረጃዎች ባይኖሩም በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች እንዳሉበት ይገመታል። የእስር ቤቱ አቅምም 15 ሺህ እስረኞችን መያዝ እንደሚችል ይታሳበል።

    እስር ቤቱ የብሪታኒያ እና የኢራን ጥምር ዜግነት ያላት ናዛኒን ዛጋሪ ራትክሊፍ በስለላ ተጠርጥራ አራት ዓመት የታሰረችበት ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንድትመለስ ተፈቅዶላታል።

    አሁንም በተቃውሞ፣ በጥምር ዜግነት፣ በስለላ የተጠረጠሩ የውጭ ዜጎች እንዲሁም የሃይማኖት እና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ማኅበረሰብ አባላት እስር ቤቱ ውስጥ ታስረው ይገኛሉ።

    ቢቢሲ ኢራን በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ያቀረበችውን ክስ በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።

    እስር ቤቱ በምዕራባውያኑ የሰብዓዊ መብት ቡድኖች ሲተች ቆይቷል። ሂውማን ራይትስ ዎች የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት ማሰቃየት፣ ያልተወሰነ ጊዜ እስራት፣ የተራዘመ ምርመራ እንደሚፈፅሙበት እንዲሁም እስረኞች የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ ክልከላ ይፈፅማሉ ሲል ከስሷል።

    ኢራን ግን እነዚህን የቀረቡባትን ክሶች ውድቅ አድርጋለች።

  16. እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ጣቢያና እስር ቤት ላይ አዲስ ጥቃት ፈፀመች፤ አሁናዊ መረጃዎቹ ምንድን ናቸው?

    በኤቭን እስር ቤት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት የሚያሳይ ምስል

    የፎቶው ባለመብት, Masoud Kazemi

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኤቭን እስር ቤት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት የሚያሳይ ምስል አጋርተዋል

    እስራኤል እና ኢራን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ቀጥለዋል። ዛሬ [ሰኞ] እስራኤል በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ፈፅማለች። ለመሆኑ እስካሁን ስለተፈጠረው ምን እናውቃለን?

    የኒውክሌር ጣቢያ ላይ የተፈፀመ ጥቃት፡ እስራኤል ለኢራን የኒውክሌር ዓላማ ወሳኝ በሆነው እና ከምድር በታች በሚገኘው የፎርዶ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ጥቃት መፈፀሟን አሳውቃለች። የእስራኤል ጦር ጥቃቱን የሰነዘረው ወደ ጣቢያው የሚወስዱ መንገዶችን ለማውደም ነው ብሏል።

    ኤቭን እስር ቤት፡ በመዲናዋ ቴህራን የሚገኘው ኤቭን እስር ቤት በተፈፀመበት ጥቃት መውደሙን የፍትህ አካላት ተናግረዋል። የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ፣ እስር ቤቱ የኢራን አገዛዝ “ጠላቶችን” የያዘ ነው ብለዋል።

    በሌሎች ቦታዎች የተፈፀሙ ጥቃቶች፡ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ካትዝ የኢራን መንግሥት ብዙ ጊዜ ተቃውሞዎችን ለማፈን የሚጠቀምባቸው ሚሊሻዎች ዋና መሥሪያ ቤት ዒላማ መደረጉን ገልጸዋል። በኢራን የሚገኙ ነዋሪዎችም የኃይል መቋረጥ እንዳጋጠመ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    በእስራኤል፡ ኢራንም በእስራኤል ላይ በርካታ የአየር ድብደባዎችን ፈፅማለች። እስካሁን በጥቃቱ የደረሰውን ጉዳት ባለሥልጣናቱ አልገለጹም፤ ነገር ግን በደቡባዊ የእስራኤል ክፍል 8 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች የኃይል መቋረጥ እንዳጋጠማቸው አሳውቀዋል።

    ኃይለ ቃላት፡ እስራኤል "ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ" ኃይሏ ኢራንን እየደበደበች እንደሆነ የገለጸች ሲሆን፣ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕም ትናንት የአገዛዝ ለውጥ ሊፈጠር የሚችልበትን ዕድል እንዳለ አንስተው ነበር።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው “አሁን ያለው የኢራን አገዛዝ ኢራንን በድጋሚ ታላቅ ማድረግ ካልቻለ የአገዛዝ ለውጥ የማይኖረው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጽፈዋል።

  17. በኢራን 500 ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ

    በጥቃት ጉዳት የደረሰበት ህንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት መፈፀም ከጀመረችበት እንደ አውሮፓውያኑ ሰኔ 13 ጀምሮ ወደ 500 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቷ የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገበ።

    ከሟቾቹ በተጨማሪም ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ጣቢያው ገልጿል።

    በኢራን መንግሥት ገደብ ምክንያት የቢቢሲ ጋዜጠኞች አገሪቷ ውስጥ ሆነው መዘገብ ባለመቻላቸው በእስራኤል ጥቃት የደረሰውን ጉዳት ለመመልከት አዳጋች ሆኗል።

    ግጭቱን እየተከታተለ የሚገኝ ‘ሂውማን አክቲቪስትስ ኢን ኢራን’ የተባለ የሰብዓዊ መብት ቡድን የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከተገለጸው እጥፍ እንደሆነ ገልጿል።

  18. እስራኤል በፎርዶ የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ ላይ ጥቃት መፈጸሟ ተዘገበ

    የፎርዶ ጣቢያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል ኢራን ካሏት ሁለት ወሳኝ የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያዎች መካከል አንዱ የሆነውን የፎርዶ ጣቢያ ላይ ጥቃት መፈጸሟን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘገቡ።

    የኢራን ሪፐብሊክ የዜና ወኪል እና ታስኒም ፎርዶ ከሚገኝበት የቆም ግዛት የሚገኘው የአደጋ አስተዳደር ባለስልጣንን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።

    ባለስልጣኑ እስራኤል በጣቢያው ላይ ጥቃት ብታደርስም ነገር ግን በዚህ ምክንያት “በዜጎች ላይ ምንም አይነት ስጋት ወይም አደጋ አይኖርም” ብሏል።

    የአሜሪካ አየር ኃይል ‘በንከር በስቲንግ’ የተሰኘውን ቦምብ በመጠቀም ከመሬት በታች ያለው እዚህ ጣቢያ ላይ በትናንትናው እለት ጥቃት ፈጽሟል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው በኢራን ላይ የፈጸመችውን ጥቃቶች “በሁሉም የኒውክሌር ይዞታዎች” ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፤ እንዲሁም “ማውደም የሚለው” የሚገልጸው ነው ብለዋል።

    ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ አካል፣ አለም አቀፉ አቶሚክ ኤጀንሲ የደረሰውን ጉዳት በትክክል ማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጿል።

    ፎርዶ ከቴህራን በስተደቡብ በ200 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

    የተገነባውም በተራራ ተከቦ ከመሬት በታች ከ80-90 ሜትር ጥልቀት ላይ ሲሆን ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ከደህንነት እና ከጥበቃ ጋር የተያያዘ ነው።

    ኢራን ዩራኒየም- 235 የተሰኘውን ለማግኘት ከምትጠቀምባቸው ቁልፍ የማበልጸጊያ ጣቢያዎች አንዱ ነው።

  19. ኢራን ዛሬ የፈጸመችው ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያንን መብራት አልባ ማድረጉ ተነገረ

    በእስራኤል የደረሰው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢራን ዛሬ፣ ሰኔ 16/ 2017 ዓ.ም በፈጸመችው ጥቃት 8 ሺህ ያህል እስራኤላውያንን መብራት አልባ ማድረጉን የአገሪቱ የኃይል ሚኒስትር ገለጹ።

    “በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ለሚደርሱ ጉዳቶች አስቀደመን ተዘጋጅተናል፤ እናም በሚቀጥሉት ሶስት ሰዓታት ውስጥ የኃይል አገልግሎት ይመለሳል” ሲሉ ሚኒስትሩ ኤሊ ኮኸን ተናግረዋል።

    የእስራኤል ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን ቀደም ሲል በደቡባዊ እስራኤል “በስትራቴጂካዊ የመሰረተ ልማት ግንባታ አቅራቢያ ጉዳት ደርሷል” ሲል ሪፖርት አድርጎ፤ ይህም በበርካታ ነዋሪዎች ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ማስከተሉን ገልጾ ነበር።

    "ሰራተኞቻችን በተቻለ ፍጥነት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ለመመለስ በበርካታ ቦታዎች ላይ እየሰሩ ነው። የመሰረተ ልማት ጥገናዎችን ጨምሮ አደጋ ፈጣሪ ቁሶችን ማስወገድን ከጸጥታ ኃይሎቻችን ጋር በቅንጅት እያከናወኑ ናቸው” ብሏል።

  20. የተመድ ተቆጣጣሪ ቡድን የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎችን ለመመርመር እንዲቻል የግጭት አቁም ጥሪ አቀረበ

    አለም አቀፉ የአቶሚክ ኤጀንሲ (IAEA) ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ቡድን አለም አቀፉ የአቶሚክ ኤጀንሲ (IAEA) ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎችን ለመመርመር እንዲቻል የግጭት አቁም ጥሪ አቀረቡ።

    ኃላፊው በቪየና ለሚገኘው የአለም አቀፉ የአቶሚክ ገዥዎች ቦርድ በሰጡት መግለጫ

    “ለማንኛውም ስምምነት ቅድመ ሁኔታ በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ማረጋገጥ ነው፤ ይህም ሊሳካ የሚችለው በአለም አቀፉ አቶሚክ ኤጀንሲ ፍተሻዎች ብቻ ነው” ብለዋል።

    አክለውም “አስፈላጊው የደህንነት እና የጸጥታ ሁኔታ ተመቻችቶ ኢራን የአቶሚክ ኤጀንሲውን ቡድን ወደ ይዞታዎቿ አስገብታ ሁኔታውን ለመገምገም የግጭት ማቆም መሰረታዊ ነው” ብለዋል።