
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግዝ እና የአሜሪካ ጦር ኃይል የጋራ ዕዝ ሊቀ መንበር ጄኔራል ዳን ኬይንአሜሪካ በኢራን ሦስት የኒውክሌር ተቋማት ላይ ስለፈጸመችው ጥቃት የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር እንዲሁም የአሜሪካ ጦር ኃይል የጋራ ዕዝ ሊቀ መንበር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት በፈፀመችው ጥቃት "አስደናቂ እና የማይቀለበስ ስኬት" ተገኝቷል ብለዋል።
ፒት ሄግዝ በፔንታጎን መግለጫውን ለመከታተል ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ከዋና አዛዣችን [ትራምፕ] የተቀበልነው ትዕዛዝ ትኩረት ያለው ነበር፤ኃይለኛ እና ግልጽ ነበር። የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብርን አውድመናል” ብለዋል።
አሜሪካ ጥቃቱን ለመፈጸም ለረዥም ጊዜ ስትዘጋጅ
መቆየቷን የተናገሩት መከላከያ ሚኒስትሩ "ለወራት እና ለሳምንታት ቦታ
መያዝን እና መዘጋጀትን የጠየቀ እቅድ ነው" ብለዋል።
ለጥቃቱ ቢ-2 ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ጥቅም ላይ መዋሉን የተናገሩት ፒት ሄግዝ
“ቢ-2 ቦምብ ጣይ አውሮፕላናችን ዓለም ሳይሰማ ወደ ኒውክለር ተቋሞቹ ገብቶ መውጣት ችሏል" ብለዋል።
ሄግዝ እንደተናገሩት አሜሪካ እኩለ ሌሊት ላይ በኢራን፣ ፎርዶ፣ ናታንዝ እና ኢስፋሃን በሚገኙ ሦስት የኒውክሌር ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አድርሳለች።
"የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብርን አውድመናል፣ ነገር ግን ኦፕሬሽኑ የኢራን ወታደሮችን እና የኢራንን ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል" ሲሉ ሄግዝ አክለዋል።
ሄግዝ አክለውም “ይህ ተልዕኮ የስርዓት ለውጥ አልነበረም፤ አይደለምም” ብለዋል።
በፔንታጎን ከመከላከያ ሚኒስትሩ ጋር በመሆን መግለጫ የሰጡት ጄኔራል ዳን ኬይን፣
የአሜሪካ ጦር ኃይል የጋራ ዕዝ ሊቀ መንበር፣ ኢራን ላይ የተፈጸመው ጥቃት በተለያዩ የመከላከያ ክፍሎች “የታቀደ እና ተግባራዊ
የሆነ” መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም ቢ-2 ቦምብ ጣይ አውሮፕላን አርብ ዕለት ከአሜሪካ ተነስቶ ለ18 ሰዓታት
ወደ ዒላማው መብረሩን ገልፀዋል።
ዘመቻው “ኦፕሬሽን ሚድ ናይት ሐመር” ተብሎ እንደተጠራ የተናገሩት ጄነራሉ፣ በርካታ
“የማሳሳቻ እና የማደናገርያ” ስልቶችን መጠቀማቸውን አብራርተዋል።
ስለ ኦፕሬሽኑ ዝርዝር ሁኔታ የተናገሩት ጄነራል ኬይን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቹ ከአሜሪካ ተነስተው አንዳንዶቹ ወደ ምዕራብ ፓሲፊክ ውቅያኖስ እንደ "ማታለያ" መብረራቸውን ገልጸዋል።
ኬይን 75 “ዒላማቸውን
በሚገባ አነጣጥረው የሚለዩ መሳርያዎች”፤14 "ግዙፍ ኦርዳንስ ፔኔትሬተርስ" እንዲሁም "ምሽግ ደርማሽ" በመባልም የሚታወቁት ቦምቦችን ጨምሮ ጥቅም ላይ መዋላቸውን አስረድተዋል።
ከኢራን መከላከያ ምንም ዓይነት የመከላከል እርምጃ እንዳልገጠማቸው ሲገልፁም “ምንም የተተኮሰ ነገር የለም” ብለዋል።
ኬይን “የኢራን ተዋጊዎች በአየር ክልሉ ላይ አልነበሩም። እናም የኢራን የሚሳዔል ስርዓቶች አላዩንም”
ብለዋል።
ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቹ ወደ አሜሪካ በመመለስ ላይ መሆናቸውንም አክለው ተናግረዋል።