ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ኢራን መደራደር ብትፈልግም አሜሪካ ዝግጁ አይደለችም አሉ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አሜሪካ ሁለተኛ ሳምንቱን የደፈነውን የኢራን ጦርነት ለመቋጨት የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ አይደለችም አሉ። ኢራን ስምምነት መፈጸም ፈልጋለች ሲሉ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ነገር ግን “የቀረቡት የድርድር ነጥቦች ገና በቂ ስላልሆኑ” ንግግር ለማደረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦርነቱ የሚቋጨው ከኔትያናሁ ጋር በሚተላለፍ “የጋራ” ውሳኔ መሆኑን ተናገሩ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትያናሁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን ጦርነት መቼ ይጠናቀቃል የሚለው ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትያናሁ ጋር “በጋራ” የሚወሰን እንደሆነ መናገራቸውን ታይምስ ‘ኦፍ ኢስራኤል’ ዘገበ።

    ስለ ጦርነቱ ከኔትያናሁ ጋር “እየተነጋገሩ” መሆኑን በስልክ በተደረገ ቃለ መጠይቅ ለእስራኤሉ መገናኛ ብዙኃን የገለጹት ትራምፕ፤ “ትክክለኛው ጊዜ ላይ ውሳኔ እንደሚያሳልፉ” ተናግረዋል ተብሏል።

    አሜሪካ ጥቃት መፈጸም የምታቆም ከሆነ ኢራን ጦርነቱን መቀጠል ትችል እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ይህ የመሆን እድል የመኖሩ ጉዳይ ላይ ከመናገር ተቆጥበዋል። “ይሄ አስፈላጊ ይሆናል ብዬ አላስብም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    የቀድሞው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ልጅ የሆኑት ሞጅታባ ኻሜኒ የኢራን ጠቅላይ መሪነትን ሥልጣን ስለ መረከባቸው ለቀረበላቸው ጥያቄም ግልጽ ምላሽ ሳይሰጡ አልፈዋል። “የሚፈጠረውን እናያለን” ብለዋል።

    ከዚህ ቀደም ትራምፕ “ለእኔ የኻሜኒ ልጅ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ሞጅታባ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተው ነበር።

  2. የአያቶላህ ኻሜኒ ልጅ ሞጅታባ አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሆነው ተመረጡ

    ሞጅታባ ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    88 አባላት ያሉት የኢራን የሃይማኖት ሊቃውንት ጉባኤ፤ የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ሁለተኛ ልጅ የሆኑት ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸውን ቦታ በመተካት አዲሱ የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ እንዲሆኑ መረጠ።

    ሞጅታባ ኻሜኒ፤ አሜሪካ እና እስራኤል ከሳምንት በፊት ኢራን ላይ በከፈቱት የመጀመሪያ ዙር ጥቃት የተገደሉትን አባታቸውን ቦታ በመተካት የአገሪቱ መንፈሳዊ መሪነትን እና ከፍተኛውን የሥልጣን ቦታ ይቆጣጠራሉ።

    አዲሱ ጠቅላይ መሪ የአባታቸውን አክራሪ ፖሊሲዎች እንደሚያስቀጥሉ ብዙዎች ይጠብቃሉ።

    የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ የአዲሱን ጠቅላይ መሪ መመረጥ ባበሰረበት ዘገባ፤ “ከባድ የጦርነት ጊዜ ሁኔታ እና በዚህ ታዋቂ ተቋም ላይ የጠላቶች ቀጥተኛ ዛቻ ቢኖርም” ውሳኔው መተላለፉን ገልጿል።

    የቴሌቪዥን ዜና አቅራቢው፤ የሊቃውንት ጉባኤው “የመረጣ እና የእስላማዊ ስርዓቱን መሪ የማስተዋወቅ ሂደቱን ለደቂቃ እንኳ አላቋረጠም” ብሏል። አክሎም፤ “አላሁ አክበር፣ አላሁ አክባር መሪው ኻሜኒ ናቸው” ሲል ተደምጧል።

    ሹመቱን እንደሚቃወሙ የሚጠበቁት አሜሪካ እና እስራኤል እስካሁን ድረስ ውሳኔውን በተመለከተ አስተያየት አልሰጡም።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኢራን አዲስ መሪ የመምረጥ ሂደት ውስጥ ሚና መጫወት እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።

    ከቀድሞው የአገሪቱ አመራር ጋር ግንኙነት ያለው ሰው ቢመረጥ ሊቀበሉ እንደሚችሉ የጠቆሙት ትራምፕ፤ ሞጅታባ ኻሜኒ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በግልጽ አስቀምጠዋል። “ለእኔ የኻሜኒ ልጅ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ተናግረዋል።

    ሹመቱ ይፋ ከመደረጉ ከሰዓታት አስቀድሞ ደግሞ ያለ እርሳቸው ይሁንታ ሥልጣኑን የሚረከብ ማንም ሰው “ረጅም ጊዜ እንደማይቆይ” በመጥቀስ ዝተዋል።

    እስራኤልም በተመሳሳይ የጠቅላይ መሪነቱን ሥልጣን የሚረከበውን “ሁሉንም ተተኪ ማደኗን እንደምትቀጥል” ተናግራለች።

    የ56 ዓመቱ ሞጅታባ ኻሜኒ ከአባታቸው በተቃራኒም ሕይወታቸውን የመሩት ራሳቸውን በመሸሸግ ነው። ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው አገሪቱን ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ሰዎች እንዱ እንደሆኑ ይገመታሉ።

    በፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች ላይ እጅቸውን እንዳስገቡ፣ የባስጂ ታጣቂዎችን እንደሚያዝዙ እንዲሁም ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ይገለጻል።

    በአገሪቱ ውስጥ ከፍ ያለ ተጽዕኖ እንዳላቸው ቢነገርም በእስላማዊ ሪፐብሊኩ ውስጥ አንድም የመንግሥት ሥልጣን ይዘው አያውቁም።

    አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና የእስላማዊ ሪፐብሊኩ መሪ ሩሆላህ ኾሜኒ በአገሪቱ ሥልጣን ላይ በዘር መተካካት ይተቹ ነበር።