የአሜሪካ ባሕር ኃይል በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መርከቦችን ለማጀብ “ዝግጁ እንዳልሆነ” ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የአሜሪካ ኢነርጂ መሥሪያ ቤት ሚኒስትር የሆኑት ክሪስ ራይት፤ የአገሪቱ ባሕር ኃይል ኢራን በምትቆጣጠረው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለማጀብ ዝግጁ አለመሆኑን ተናገሩ።
ሚኒስትሩ ማክሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ግን የአሜሪካ ባሕር ኃይል በወሽመጡ በኩል ያለፈን ነዳጅ ጫኝ በተሳካ ሁኔታ ማጀቡን ተናግረው ነበር።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ከዚህ ቀደም “አስፈላጊ ከሆነ” አገራቸው በወሽመጡ የሚያልፉ መርከቦችን እንደምታጅብ መግለጻቸው ይታወሳል።
የኢነርጂ ሚኒስትሩ ዛሬ ከአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ‘ሲኤንቢሲ’ ጋር በነበራቸው ቆይታ እጀባው “በአንጻራዊነት በቅርቡ ይሆናል፤ አሁን ግን ሊሆን አይችልም” ብለዋል።
“በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ወታደራዊ ኃይሎቻችን ትኩረታቸው የኢራንን የማጥቃት አቅሞችን እንዲሁም ለማጥቃት የሚሆን ግብዓት የሚያቀርበውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ማጥፋት ላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተከፈተባት ኢራን ከዓለም ነዳጅ አንድ አምስተኛው የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታለች። “ትዕዛዙን ተላልፈው” በአካባቢው የሚያልፉ መርከቦች ላይም ጥቃት እየፈጸመች ነው።
በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ አሳይቷል። የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ከአራት ዓመት ገደማ በኋላ 120 ዶላር ገብቶ የነበረ ሲሆን፣ ኋላ ላይ ግን ቀንሷል።
ዋይት ሐውስ የአሜሪካ ባሕር ኃይል በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብን እያጀበ አለመሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ግን ዋጋው ተመልሶ ጭማሪ አሳይቷል።




















