ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባሉት አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ደኅና መሆናቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ ጉዳት ደርሶባቸዋል መባሉን ተከትሎ የኢራን ፕሬዝዳንት ልጅ “በደኅና ሁኔታ” ላይ እንደሚገኙ አስታወቀ።
የፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ወንድ ልጅ ይህንን የጠቅላይ መሪውን ደኅንነት የሚያረጋግጥ መረጃን ያወጣው አዲሱ ጠቅላይ መሪ ጉዳት ደርሶባቸዋል የሚል ዜና መሠራጨቱን ተከትሎ ነው።
ዩሱፍ ፔዜሽኪያን በቴሌግራም ገጹ ላይ ጠቅላይ መሪው ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚገልጹ “ሪፖርቶችን አይችላሁ” በማለት፣ ነገር ግን ሞጅታባ ደኅና መሆናቸውን ማረጋገጡን ጽፏል።
"የቅርብ ግንኙነት ያላቸውን በርካታ ጓደኞቼን ጠይቄ እንደነገሩኝ፣ በፈጣሪ ጸጋ ያለምንም ችግር በደኅና ሁኔታ ላይ ናቸው” ሲል ቴሌግራም ላይ አስፍሯል።
ነገር ግን ጠቅላይ መሪው ሥልጣኑን እንዲረከቡ በሊቃውንት ጉባዔ ከተሰየሙ በኋላ በይፋ ለሕዝብ አለመታየታቸው፣ ንግግር አለማድረጋቸው እና መግለጫ አለመስጠታቸው በደኅንነታቸው ላይ ጥያቄን አስነስቷል።



















