በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለው ግጭት አሁን ላይ በሁለቱ አገራት መካከል የተገደበ ይመስላል፤ ነገር ግን ሁለቱ አገራት ግጭት እንዲያቆሙ የሚቀርበውን ጥሪ አንሰማም ቢሉስ? ግጭቱ ቢባባስ እና ቢስፋፋስ ምን አስከፊ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል?
የሚከተሉት ሊፈጠሩ የሚችሉ አስከፊ ሁኔታዎች ናቸው።
ምንም እንኳን አሜሪካ ብታስተባብልም ኢራን የአሜሪካ ኃይሎች ግጭቱን መደገፋቸውንና ቢያንስ ለእስራኤል ጥቃት ስልታዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በግልጽ ታምናለች።
በመሆኑም ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ የአሜሪካ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች። አሜሪካ ኢራቅ ውስጥ የልዩ ኃይል ካምፖች፣ በባሕረ ሰላጤው አገራት ደግሞ ወታደራዊ ሰፈሮች እና በቀጠናው የዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች አሏት።
በኢራን የሚደገፉት ሐማስ እና ሄዝቦላህ ብዙ የተዳከሙ ቢሆንም በኢራቅ የሚገኙት ደጋፊ ሚሊሻዎቻቸው ግን አሁንም ታጥቀውና አቅማቸውን አጠናክረው ነው የሚገኙት።
የባሕረ ሰላጤው አገራት ወደ ግጭቱ ሊሳቡ ይችላሉ
ኢራን አስተማማኝ መከላከያ ባለው የእስራኤል ጦር እና ሌሎች ኢላማዎች ላይ ጉዳት ማድረስ ካልቻለች፣በተለይ ጠላቶቿን ለዓመታት ይደግፋሉ በምትላቸው የባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ የሚሳኤል ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች።
እነዚህ አገራት የአሜሪካ አየር ኃይል ሰፈር የሚገኝባቸው ናቸው።በመሆኑም የባሕረ ሰላጤው አገራት ጥቃት ከደረሰባቸው ራሳቸውን ለመከላከል የአሜሪካ እና የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖችን ድጋፍ ሊጠይቁ ይችላሉ።
የኢራን አገዛዝ ሊወድቅ ይችላል፤ ይህም ክፍተት ይፈጥራል
እስራኤል የኢራንን እስላማዊ አብዮት ጥበቃ አገዛዝ የማፍረስ የረዥም ጊዜ ህልሟን ብታሳካስ ?
ትናንት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሰጡት መግለጫ ዋና አላማቸው አገዛዙን ማፍረስ እንደሆነ በግልጽ ተናግረዋል። የኢራንን መንግሥት መፍረስ በተለይ በአንዳንድ የእስራኤል ወዳጆች ሊደገፍ ይችላል። ግን ይህ ምን ክፍተት ሊፈጥር ይችላል? ምን ዓይነት ቀውስስ ሊያስከትል ይችላል? በኢራን የእርስ በርስ ጦርነት ምን ሊመስል ይችላል?
በርካቶች በኢራቅ እና በሊቢያ ማዕከላዊ መንግሥት ሲወድቅ ምን እንደተከሰተ ያስታውሳሉ።
በመሆኑም የኢራን አገዛዝ ቢወድቅ ምን ሊከሰት ይችላል የሚለው በቀጣይ ቀናት በሚኖረው የግጭቱ ሁኔታ ላይ ይወሰናል።
ኢራን እንዴት የከፋ አፀፋ ትመልሳለች ? አሜሪካስ እስራኤልን ልትደግፍ ትችላለች? በሚሉት ጥያቄዎች መልስ ላይም የሚመሰረት ይሆናል።