የእስራኤል እና ኢራን ግጭት “መስፋፋት ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል እሳት ሊያቀጣጥል ይችላል” ተመድ

ስምንተኛ ቀኑን የያዘው የእስራኤል እና ኢራን ግጭት “መስፋፋት ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል እሳት ሊያቀጣጥል ይችላል” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሳሰቡ።ዋና ጸሐፊው በአገራቱ መካከል ያለው ግጭት መቀጠል አለምን ወደ ቀውስ የሚከት ነው ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

  • እስራኤል እና ኢራን ግጭት "መስፋፋት ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል እሳት ሊያቀጣጥል ይችላል" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሳሰቡ
  • ኢራን በእስራኤል ያልተጠበቀ ጥቃት የተፈጸመባት "ከአሜሪካ ጋር የኒውክሌር አቅምን አስመልክቶ ተስፋ ሰጪ ዲፕሎማሲያዊ ሂደት ላይ በነበረችበት ወቅት" መሆኑን አስታወቀች።
  • የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከእስራኤል ጋር ያለውን ግጭት ለማስቆም ፈረንሳይን ጨምሮ አውሮፓውያኑ አገራት ለኢራን የዲፕሎማሲ ፕሮፖዛል እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
  • ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን እና በእስራኤል ግጭት ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ መግባት አለመግባቷን ይወስናሉ- ዋይት ሐውስ
  • ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ላይ ለመወሰን ሁለት ሳምንት ጊዜ ሲሰጡ ዩኬ እና የአውሮፓ ኅብረት ከኢራን ጋር ሊነጋገሩ ነው
  • የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ለቢቢሲ አሜሪካ በግጭቱ ውስጥ የምትሳተፍ ከሆነ ቀጠናው "ሲኦል" ይሆናል ሲሉ ተናግረው ነበር
  • ኢራን በትናንትናው ዕለት በፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት ከሆስፒታል አቅራቢያ ያለ ወታደራዊ ስፍራ ማነጣጠሩን ገልጽላች
  • ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች በደቡባዊ እስራኤል ባርሺባ ከተማ የሚገኘውና በእስራኤል ትልቁ ከሚባሉት አንዱ ሶሮካ ሆስፒታል መመታቱን እስራኤል አስታወቀች።
  • የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በእስራኤል እና ኢራን ግጭት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው
  • የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን ለማጥቃት ዕቅድ ቢያጸድቁም ነገር ግን የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አለመድረሳቸው ተዘገበ።
  • አሜሪካ የጦር ጄቶችን ጨምሮ የጦር መሳሪያዎችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እያንቀሳቀሰች ነው
  • ፑቲን በኻሜኒ ላይ የታቀደውን ግድያ አስመልክቶ "በፍጹም በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየት አልፈልግም" አሉ
  • የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ "ኢራናውያን እጃቸውን የሚሰጡ ሕዝቦች አይደለም" ሲሉ ተናገሩ።
  • እስራኤል በኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት እስከ እሁድ ምሽት ድረስ 224 ሰዎች ሲገደሉ 1 ሺህ 277 መጎዳታቸውን ኢራን አስታውቃለች። እስራኤል በበኩሏ በጥቃቶቹ 20 ሰዎች ተገድለውብኛል ብላለች።
  • ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት መፈጸምን በተመለከተ "ላደርገው ወይም ላላደርገው እችላለሁ" አሉ
  • ፎርዶ ኢራን ካሏት ሁለት ወሳኝ የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያዎች መካከል አንዱ ሲሆን የእስራኤል መከላከያ ኃይል የአየር ጥቃት ቢያደርስበትም ጉዳት ሊደርስበት አልቻለም።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በየዕለቱ በእስራኤል ላይ የሚወነጨፉት የኢራን ሚሳዔሎች

    እስራኤል እና አሜሪካ በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ያደረጉት በአየር ላይ ባላቸው የበላይነት ሲሆን፣ ኢራን ደግሞ ረጅም ርቀትን ተጉዘው በሚያጠቁ ሚሳዔሎች ላይ ነው። ባለፉት ጥቂት ቀናትም በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢራን ሚሳዔሎች እስራኤልን ዒላማ አድርገው ተተኩሰዋል።

    እስራኤል ደግሞ በዋናነት ትኩረት የሰጠችው እነዚህን የኢራንን የሚሳዔል ማስወንጨፊያ ማዕከላትን በማውደም ላይ ነው። በዚህም ምክንያት አሁን የእስራኤል አየር ኃይል በአብዛኛው የአገሪቱ የአየር ክልል ላይ የበላይነትን እንደያዘ እየተነገረ ነው።

    ምንም እንኳን የኢራን የሚሳዔል ማዕከላት ጉዳት ቢደርስባቸውም አሁንም በእስራኤል ላይ ጥቃት እየፈጸመች ነው።በዚህም የተለያዩ የእስራኤል ክፍሎች ዒላማ ሆነዋል።

    ለመሆኑ ኢራን ምን ዓይነት ሚሳዔሎች አሏት? ምን ያህል ርቀትስ መጓዝ ይችላሉ?

  2. ‘ጥቃቱ ሲያበቃ ኢራን ኒውክሌር እና ባለስቲክ ሚሳዔል አይኖራትም’ - ጠ/ሚ ኔታኒያሁ

    እስራኤል በኢራን ላይ የምታካሂደው ዘመቻ ሲጠናቀቅ ለኅልውናዋ ስጋት የሚሆን የጦር መሳሪያ በኢራን እጅ ላይ አይኖርም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከኢራን በኩል ያሉ የኒውክሌር ስጋቶችን “ታስወግዳለች” ብለዋል ዛሬ ማለዳ ላይ በኢራን ሚሳዔል የተመታውን ሶሮካ ሆስፒታልን በጎበኙበት ወቅት።

    "ይህ ተልዕኮ ሲያበቃ ለእስራኤል ስጋት የሚሆኑ የኒውክሌር ስጋቶች እንዲሁም የባለስቲክ ሚሳዔል ስጋቶች በሙሉ አይኖሩም” በማለት ኔታኒያሁ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ኔታኒያሁ ጨምረውም እስራኤል በኢራን ላይ ባለፉት ሰባት ቀናት በፈፀመቻቸው ጥቃቶች የኒውክሌር ፕሮግራሟ “እጅጉን" እንደተጎዳ አመልክተዋል።

    የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በእስራኤል ጥቃት ዒላማ ሊደረጉ እንደሚችሉ ተጠይቀው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም “ማንም ከዒላማችን ውጪ አይሆንም” ብለዋል።

    ከአሜሪካ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው እና ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ያላቸው ወዳጅነትም “ድንቅ” መሆኑን የገለጹት ኔታኒያሁ፤ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር “ከሞላ ጎደል በየዕለቱ” እንደሚወያዩ ተናግረዋል።

  3. የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአውሮፓ አቻዎቻቸው ጋር ሊገናኙ ነው

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከፈረንሳይ እና ከጀርመን አቻዎቻቸው ጋር አርብ በጀኔቫ ላይ ሊገናኙ እንደሆነ የኢራን የመንግሥት የዜና ወኪል (ኢርና) ዘገበ።

    የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስም በውይይቱ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ለመገናኛ ብዙኃኑ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ንግግሩ እንደሚካሄድ ያረጋገጡት የኢራን ልዑካን እና የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንደሚገናኙ በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት ከተወራ በኋላ ነው።

    አራግቺ በስብሰባው ላይ ስለኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር እንደሚወያዩ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

  4. አያቶላ ኻሜኒ ሕዝባቸው “በጥንካሬው ጸንቶ እንዲቀጥል” ጥሪ አቀረቡ

    የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ለኢራን ሕዝብ "ጠላት እንደምትፈሩት ከተሰማው አይለቃችሁም" ሲሉ ሕዝባቸው በጥንካሬው እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

    መሪው በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ሕዝባቸውን “እስከ ዛሬ ድረስ በነበራችሁ ባህርይ ቀጥሉ፣ ይህንንም ባህርያችሁን በጥንካሬ በመያዝ ጸንታችሁ ቀጥሉ” ብለዋል።

    ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ እስራኤል ኢራን ውስጥ የፈጸመችው ጥቃት ተከትሎ ሁለቱ አገራት አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ አውዳሚ ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።

    በእስካሁኑ ጥቃት የኒውክሌር ማዕከላት፣ ወታደራዊ እና የመንግሥት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ እና ተቋማት ጉዳት ደርሶባቸዋል። በሁለቱም ወገን በመቶቹ የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን እና ሺዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እየተነገረ ነው።

  5. “ራሳችንን መከላከላችንን እንቀጥላለን” የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰኢድ ኻቲብዛዴህ ኢራን ራሷን መከላከሏን እንደምትቀጥል ለቢቢሲ ተናገሩ።

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ስላጸደቁት ወታደራዊ ዕቅድ እና ኢራን ከዚህ ምን እንደምትጠብቅ በቢቢሲ የተጠየቁት ኻቲብዛዴህ፣ እስራኤል ወደ ኢራን ጥቃት ከመፈፀሟ በፊት ኢራን በኒውክሌር ጉዳይ ላይ ንግግር ለማድረግ ከአሜሪካ ጋር ለመስማማት ጫፍ ላይ ደርሳ እንደነበር አስታውሰዋል።

    ኢራን አርብ ዕለት በእስራኤል ለተፈፀመባት ጥቃት አጸፋ ለመስጠት በመፈለጓ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ንግግር የሰረዘችው ባለፈው እሁድ እንደሆነም ተናግረዋል።

    ኻቲብዛዴህ ጨምረውም ዋሽንግተን በጥቃቱ ከበስተጀርባ እጇ እንደሌለበት እና ጣልቃ መግባት እንደማትፈልግ ስትገልጽ ነበር ብለዋል።

    ሆኖም የትራምፕ የአደባባይ መልዕክት “ግራ የሚያጋቡ እና እርስ በርሳቸው የሚጋጩ እንዲሁም የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት የሚጠቁሙ ነበሩ" ብለዋል ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

    ኻቲብዛዴህ ኢራን እስካሁን ድረስ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር እንዳልተገናኘችም ተናግረዋል።

    ትራምፕ ግን የኢራን ተደራዳሪዎች ዋይት ሐውስ መሄድ እንደሚፈልጉ ረቡዕ ዕለት ተናግረው ነበር።

    ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጦርነቱን ለማብቃት ምን አማራጭ እንዳለም በቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

    “ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ከተፈፀመባት በኋላ ራሷን እየተከላከለች ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ጨምረውም እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅትም የኢራንን ከፍተኛ የጦር አዛዦች መግደሏን ጠቅሰዋል።

    “ራሳችንን እየተከላከልን ነው . . . አጥቂዎች ሌላ አገርን ማጥቃት እንደማይችሉ እስኪገባቸው ድረስ ራሳችንን መከላከላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

  6. “የኢራኑ መሪ ከዚህ በኋላ በሕይወት መኖር የለበትም” የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር፣ የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ “ከዚህ በኋላ እንዲኖር ሊፈቀድለት አይገባም” አሉ።

    ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ኢራን በፈፀመችው የሚሳዔል ጥቃት እስራኤል ውስጥ የሚገኘው ሶሮካ ሆስፒታል ከተመታ በኋላ መሆኑን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን እና ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግበዋል።

    የመከላከያ ሚኒስትሩ ኢዝራኤል ካትዝ፣ ከቴል አቪቭ አቅራቢያ በምትገኘው ሆሎን ለጋዜጠኞች ሲናገሩ “ኻሜኒ እስራኤል እንድትጠፋ እንደሚፈልግ በግልጽ አውጇል። በሆስፒታሎች ላይ ጥቃት እንዲፈፀም ትዕዛዙን የሰጠው ራሱ ነው” ብለዋል።

    “የእስራኤልን መንግሥት ማጥፋት እንደ ግብ ይዞታል። እንዲህ ዓይነቱን ሰው ከዚህ በኋላ እንዲኖር መፍቀድ አይቻልም” ብለዋል ሚኒስትሩ።

    ቀደም ብሎ የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን "ዛሬ ጠዋት የተፈፀመው የሚሳዔል ጥቃት ዒላማ በሶሮካ ሆስፒታል አቅራቢያ የሚገኝ ወታደራዊ ሥፍራ እንጂ ሆስፒታሉ አይደለም" ብሏል።

  7. በኢራን ግጭት የአሜሪካ ጣልቃ መግባት “አጠቃላይ ሁኔታውን እንደሚያባብስ” ሩሲያ አስጠነቀቀች

    አሜሪካ በእስራኤል እና በኢራን ግጭት መካከል የምታደርገው ጣልቃ ገብነት "ወደ ተባባሰ ሁኔታ" ሊመራ እንደሚችል የክሬምሊን ቃል አቀባይ ለሩሲያ የመንግሥት የዜና ወኪል ተናገሩ።

    በግጭቱ ሩሲያ እና አሜሪካ የተለያየ ወገኖችን እየደገፉ ነው።

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እጇን እንድትሰጥ ከመፈለጋቸው በተጨማሪ ለመፈፀም እያጤኑ ቢሆንም ሞስኮ ግን ቴህራንን እንደ አጋሯ ነው የምታያት።

    በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ቭላድሚር ፑቲን ከኢራኑ አቻቸው መሱድ ፕዝሽኪያን ጋር የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል።

    ከስምምነታቸው ውስጥ አንቀጽ አንድ የመከላከያ እና የደኅንነት ትብብራቸውን ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ያስረዳል።

    ኢራንም ለሩሲያ ሻሂድ ድሮኖችን አቅርባለች። እነዚህ ድሮኖች በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።

    የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስራኤል በኢራን ላይ የፈፀመችውን ጥቃት ያወገዘ ሲሆን፣ ረቡዕ ዕለት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ርያብኮቭ፣ አሜሪካ ለእስራኤል ወታደራዊ ድጋፍ እንዳታደርግ አስጠንቅቀዋል።

    ምክትል ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጣልቃ መግባት “ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ያባብሰዋል” ብለዋል።

    ይህም ሞስኮ እና ዋሽንግተን በእስራኤል እና ኢራን ውዝግብ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጋቸው ሲሆን፣ ትራምፕ በድጋሚ ፕሬዚደንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ እየተሻሻለ መጥቶ ለነበረው የሩሲያ እና የአሜሪካ ግንኙነት ትልቅ እንቅፋት ሊሆን ይችላል።

  8. ኢራን ዛሬ በፈጸመቻቸው የሚሳኤል ጥቃቶች 89 እስራኤላውያን መጎዳታቸው ተነገረ

    ኢራን በዛሬው ዕለት በፈጸመቻቸው የሚሳኤል ጥቃቶች የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ወደ 89 ከፍ ማለቱን የእስራኤል የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ማጌን ዴቪድ አዶም አስታወቀ።

    በተጨማሪ በቴልአቪቭ እና በደቡብ የሃገሪቱ ክፍል የተወነጨፉ ሮኬቶች ሶስት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውን እንዲሁም ሁለቱ ደግሞ በመካከለኛ ሁኔታ ላይ ናቸው ብሏል።

    አብዛኛዎቹ የተጎዱት በፍንዳታዎች እንዲሁም በስብርባሪ እና ፍንጣሪዎች መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

    በእስራኤል ደቡባዊ ክፍል ቤርሼባ በተሰኘች ከተማ የሚገኝ ሆስፒታል በኢራን የሚሳኤል ጥቃት ተመትቷል።ኢራን የሚሳኤል ጥቃቱ ኢላማ በሆስፒታሉ አቅራቢያ የሚገኝ ወታደራዊ ይዞታ መሆኑን አስታውቃለች።

  9. “እነዚህን ፈታኝ ቀናት እናልፋቸዋለን” የኢራን ፕሬዚዳንት

    እስራኤል ጥቃት የከፈተችባት የኢራኑ ፕሬዚዳንት “በአምላክ ቸርነት፣ በመተሳሰብ እና በጋራ በመቆም እነዚህ ፈታኝ ቀናት እናልፋቸዋለን ሲሉ ተናገሩ።

    የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መስኡድ ፔዜሽኪያን እያንዳንዱ የመንግሥት አካል “ኢራንን እንዲያገለግል” መመሪያ መስጠታቸውን ለህዝቡ በማህበራዊ ድረገጽ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አስፍረዋል።

    “ሁሉም ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች እና የመንግሥት ተቋማት ኢራንን በሙሉ አቅማቸው እና ገንዘባቸው እንዲያገለግሉ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል። ይህም ያለ እናንተ ትዕግስት እና ድጋፍ አይከናወንም” ብለዋል።

  10. ኢራን በኒውክሌር ማበልጸጊያዎቿ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት በተመለከተ ለዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ቅሬታ አቀረበች

    ኢራን እስራኤል በኒውክሌር ማበልጸጊያዎቿ ላይ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት በተመለከተ ለዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ቅሬታ አቀረበች።

    እስራኤል “በኒውክሌር ማዕከላት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የሚከለክሉ አለም አቀፍ ህጎችን በጣሰ መልኩ ጥቃቶችን መፈጸሟን ቀጥላለች” ስትል ኢራን ለኤጀንሲው ከሳለች።

    በዛሬው ዕለት እስራኤል አገልግሎት በማይሰጠው በአራክ የኒውክሌር ማብላያ እንዲሁም የናታንዝ የኒውክሌር ማበልጸጊያ ተቋም ጥቃት መፈጸሟ ተገልጿል።

    ኤጀንሲው በአራክ የኒውክሌር ይዞታ ላይ በደረሰው ጥቃት በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ገልጿል።

  11. ጥቂት በዛሬው ዕለት ጥቃት ስለተፈጸመባቸው የእስራኤሉ ሆስፒታል እና የኢራን የኒውክሌር ማብላያዎች

    በእስራኤል

    • በሃገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ቤርሼባ በተሰኘች ከተማ የሚገኝ ሆስፒታል በኢራን የሚሳኤል ጥቃት ተመትቷል።
    • ኢራን የሚሳኤል ጥቃቱ ኢላማ በሆስፒታሉ አቅራቢያ የሚገኝ ወታደራዊ ይዞታ መሆኑን አስታውቃለች።
    • ኢራን ትናንተና ባስወነጨፈቻቸው የሚሳኤል ጥቃቶች በርካቶች መቁሰላቸው ተነግሯል።
    • የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኢራን “ዋጋ ትከፍላለች” ብለዋል።

    በኢራን

    • የእስራኤል ጦር በኢራን የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቀዋል። ከእነዚህም መካከል አራክ የኒውክሌር ማብላያ እና ናታንዝ የዩራኒየም ማበልጸጊያ ጣቢያዎች ይገኙበታል።
    • ኢራን ለዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ቅሬታ አቅርባለች።

    በአሜሪካ

    • ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤል ጋር ተሰልፈው ኢራንን የማጥቃት ዕቅዶችን ቢያጸድቁም የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አለመደረሱን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘግቧል።
  12. ኢራን የሚሳኤል ጥቃቷ ከሆስፒታል አቅራቢያ ያለ ወታደራዊ ስፍራ ማነጣጠሩን ገለጸች

    ኢራን ዛሬ ጥዋት የፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት ኢላማ ያደረገው ቤርሼባ በተሰኘችው ከተማ ከሚገኘው ሆስፒታል አጠገብ የሚገኝ ወታደራዊ ስፍራ እንጂ ሆስፒታሉ እንዳልሆነ የኢራን የመንግሥት ሚዲያ ዘገበ።

    እንደ ዜና ወኪሉ ከሆነ ጥቃቱ ያነጣጠረው የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት “የትዕዛዝ እና የመረጃ ዋና መስሪያ ቤት” አንዲሁም በጋም ያም ቴክኖሎጂ ፓርክ ውስጥ የሚገኘው የመረጃ ማዕከል ላይ መሆኑን ነው።

    “ሆስፒታሉ የተጋለጠው ለፍንዳታዎቹ ብቻ ነው እንዲሁም ከባድ ጉዳት አልደረሰበትም። ነገር ግን ቀጥታ ኢላማ የነበረው ወታደራዊ መሰረተ ልማት ነው” ሲል ዘገባው አክሏል።

    የጋቭ ያም ኔጌቭ የቴክኖሎጂ ፖርክ “ከቤን ጉሪዮን ዩኒቨርስቲ ካምፓስ እንዲሁም የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት “የትዕዛዝ እና የመረጃ ዋና መስሪያ ቤት” አቅራቢያ እንደሚገኝ” በድረገጹ አትቷል።

    የእስራኤል መገናኛ ብዙኃንም የእስራኤል መከላከያ አንድ ካምፓስ በስፍራው እየገነባ መሆኑን ከዚህ ቀደም ዘግበው ነበር።

  13. ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች በእስራኤል ትልቁ ከሚባሉት አንዱ ሆስፒታል ተመታ

    ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች በደቡባዊ እስራኤል ባርሺባ ከተማ የሚገኘውና በእስራኤል ትልቁ ከሚባሉት አንዱ ሶሮካ ሆስፒታል መመታቱን እስራኤል አስታወቀች።

    ሆስፒታሉ በቀጥታ በሚሳኤል መመታቱን የገለጸችው እስራኤል በዚህም ጥቃት 30 ሰዎች ተጎድተዋል ብላለች።

    ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች በተጨማሪም ሶስት የሲቪል ስፍራዎች መመታታቸውን አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ባለስልጣን ገልጸዋል።

    በስፍራው በርካታ ሚሳኤሎች መወንጨፋቸውን እና በቴልአቪቭ እና እየሩሳሌም ፍንዳታ መሰማቱ ተገልጿል።

    የሆስፒታሉ ቃል አቀባይ “ሆስፒታሉ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል” ብለዋል። በአካባቢው “አደገኛ ንጥረ ነገሮች ሊፈስ” ይችላል በሚል ስጋት ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲርቁ እየተጠየቁ ይገኛል።

    የእስራኤል የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ማጌን ዴቪድ አዶም እንዳለው ኢራን በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 32 ሰዎች መጎዳታቸውን ገልጿል።

    የኢራን የዜና ወኪል ኢርና በሆስፒታሉ አቅራቢያ የሚገኘው የእስራኤል ወታደራዊ ማዘዣ እና የስለላ ጣቢያ የዛሬ ጥዋት የሚሳኤል ጥቃት ዋና ኢላማ ነበር ብሏል።

    የእስራኤል ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሆስፒታሉ ላይ የደረሰውን ጥቃት “ሆን ተብሎ የተፈጸመ” እንዲሁም “ወንጀል” ሲሉ አውግዞታል።

    ጥቃቱ የተፈጸመው “በጦር ሰፈር ሳይሆን በሆስፒታል” ነው ያሉት ሚኒስትሩ ሻረን ሃስከል ይህ ሆስፒታል ለኔጌቭ ክልል ነዋሪዎች ዋነኛ የህከምና ማዕከል ነው ብለዋል።

    አክለውም “አለም ሊያወግዘው ይገባል” ብለዋል።

  14. የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በእስራኤል እና ኢራን ግጭት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በእስራኤል እና ኢራን ግጭት ላይ ለመወያየት አርብ፣ ሰኔ 12/ 2016 ዓ.ም አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ ተገለጸ።

    አስቸኳይ ስብሰባው የተጠራው በኢራን፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ፓኪስታን እና አልጀሪያ ጥያቄ መሆኑን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    በተባበሩት መንግሠታት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን እንደሚገኙ ተናግረዋል።

    ከዚህ ቀደም የእስራኤል ጥቃትን ተከትሎ ኢራን ባቀረበችው ጥያቄ በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ድርጅት ተሰብስቦ ነበር።

    በዚህም ስብሰባ ላይ እስራኤል የፈጸመችውን ጥቃቶች “አረመኔያዊ” እንዲሁም “ወንጀል” ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራን ተወካይ ሰኢድ ራቫኒ ወቅሰው ነበር።

    የጸጥታው ምክር ቤት የእስራኤልን ድርጊት እንዲያወግዝ እና ተጠያቂ እንዲያደረጋትም ጠይቀዋል።

  15. ትራምፕ የኢራን ጥቃት እቅድን ቢያጸድቁም የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አለመደረሱ ተዘገበ

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ፣ ሰኔ 10/ 2017 ዓ.ም ኢራንን ለማጥቃት ዕቅድ ቢያጸድቁም ነገር ግን የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አለመድረሳቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘግቧል።

    ትራምፕ ጥቃት ለመጀመር ያልፈለጉት ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን እርግፍ አድርጋ ለመተው ከተስማማች በሚል እንደሆነ ከፍተኛ የመረጃ ምንጭን ዋቢ አድርጎ ሲቢኤስ ዘግቧል።

    ዜናው መጀመሪያ የተዘገበው በዋል ስትሪት ጆርናል ነው።

    ረቡዕ ዕለት አገራቸው ከእስራኤል ጋር ተሰልፋ ኢራንን ልታጠቃ ትችላለች ወይ በሚል የተጠየቁት ትራምፕ “ላደርገው ወይም ላላደርገው” እችላለሁ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

    ትራምፕ በተራራ ተከቦ ከመሬት በታች ከ80-90 ሜትር ጥልቀት ላይ የተሰራው የኢራን ዋነኛ የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ ፎርዶን ለመምታት እያጤኑት መሆኑን ሲቢኤስ ቀደም ሲል ዘግቧል።

    የፎርዶን የኒውክሌር ማብላያን መድረስ የሚችለው የአሜሪካው 14 ሺህ ኪሎግራም ገደማ የሚመዝነው ‘በንከር በስተር’ የተሰኘው ቦምብ እንደሆነ እየተነገረ ነው። ይህንን ቦምብ አሜሪካ ለእስራኤል ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነችም።

  16. ፑቲን በኻሜኒ ላይ የታቀደውን ግድያ አስመልክቶ “በፍጹም በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየት አልፈልግም” አሉ

    እስራኤል የኢራኑን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ለመግደል ወጥና አሜሪካ ውድቅ ማድረጓ በተሰማ ማግስት ይህንን በተመለከተ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን “በፍጹም በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየት አልፈልግም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

    የጠቅላዩ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ ሊገደሉ ስለሚችሉበት ሁኔታዎች የተጠየቁት የሩስያው መሪ “ ስለሚቻልበት ጉዳይ በጭራሽ መወያየት አልፈልም። በፍጹም አልፈልግም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

    “ይሄንን ሁሉ እሰማለሁ ነገር ግን ልወያይበት እንኳን አልፈልግም” ሲሉ በሴይንት ፒተርስበርግ በነበረው የኢኮኖሚ መድረክ የጎንዮሽ ውይይት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ቀደም ሲል በአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ኢራን የሩሲያን እርዳታ ጠይቃ እንደሆነ የተጠየቁት ፑቲን “የኢራን ወዳጆቻችን እርዳታችንን አልጠየቁም” ብለዋል።

  17. አሜሪካ የጦር ጄቶችን ጨምሮ የጦር መሳሪያዎችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እያንቀሳቀሰች ነው

    አሜሪካ ከእስራኤል ጋር ተሰልፋ ኢራንን ልታጠቃ ትችላለች የሚሉ መላምቶች በተበራከቱበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ በተለያዩ የጦር ሰፈሮች የሚገኙ የጦር ጄቶችን ጨምሮ የጦር መሳሪያዎች ወደ መካከለኛው ምስራቅ እያንቀሳቀሰች መሆኑ ተገልጿል።

    በቀጠናው ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮች እንዳሉ የአሜሪካ ባለስልጣን በቅርቡ ተናግረው ነበር።

    ባለፉት ጥቂት ቀናት ቢያንስ 30 ወታደራዊ አውሮፕላኖች አሜሪካ ከሚገኘው የጦር ሰፈሮች ወደ አውሮፓ ተንቀሳቅሰዋል።

    ሁሉም የጦር ጄቶች ተዋጊ እና ቦምብ ጣይ ጄቶችን ነዳጅ ለመሙላት የሚያገልግሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ታንከር መሆናቸው ተነግሯል።

    የአሜሪካ ኒሚትዝ የተሰኘው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ከበርካታ የሚሳኤል አውዳሚዎች ጋር ከደቡብ ቻይና ባህር ተነስቶ ወደ መካከለኛው ምስራቅ እየቀዘፈ ነው።

    ሌሎች የጦር መርከቦች በኦማን ባህረ ሰላጤ እና በፋርስ ባህረ ሰላጤ የሚገኙ ሲሆን እስራኤል የኢራን ሚሳኤሎችን እንድትመታ ረድተዋታል።

    አሜሪካ ኤፍ- 16፣ ኤፍ- 22 እንዲሁም ኤፍ-35 ተዋጊ ጄቶችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ የጦር ሰፈሮች ማዛወሯን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

  18. ኢራን የሃይፋ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ አስጠነቀቀች

    ኢራን የእስራኤሏ ሃይፋ ከተማ በተወሰነው ክፍል ያሉ ነዋሪዎች ለህይወታቸው አደጋ ስለሚኖር አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ አስተላለፈች።

    ሃይፋ ባለፈው ሳምንት በኢራን የሚሳኤሎች ጥቃት ተፈጽሞባታል።

    የእስራኤል ጦር አብዛኞቹ ሚሳኤሎች እንደከሸፉ ቢያስታውቅም አንዳንዶቹ ግን የተለያዩ ስፍራዎችን መምታታቸውን አምኗል።

    ኢራን የእስራኤል ወታደራዊ ማዕከላትና የጦር ሰፈሮች ላይ ድሮኖች እንዲሁም ሚሳኤሎችን እያስወነጨፈች ትገኛለች።

  19. ከእስራኤል ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የሚታመኑ የመረጃ መንታፊዎች ከኢራኑ የክሪፕቶ ድርጅት 90 ሚሊዮን ዶላር ዘረፉ

    ከእስራኤል ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው ተብሎ የሚታመነው የመረጃ መንታፊዎች ቡድን ፕሪዳቶሪ ስፓሮው ከኢራኑ ትልቁ የክሪፕቶ ኩባንያ ኖቢቴክስ 90 ሚሊዮን ዶላር ዘረፈ።

    ቡድኑ ገንዘቡን ከዘረፈ በኋላ መገኘት ወደማይችልበት ስፍራ ልኮታል ተብሏል።

    መንታፊ ተሟጋች ነኝ የሚለው ቡድኑ ኢራንን ኢላማ ባደረገ መልኩ መረጃዎችን በመመንተፍ ይታወቃል።

    ቡድኑ ከአንድ ዓመገት በላይ ከባድ የሳይበር ጥቃቶችን ባይፈጽምም እስራኤል በኢራን የጀመረችውን ጥቃት ጠብቆ ብቅ ብሏል።

    ከእስራኤል ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት ቡድኑ ማክሰኞ በኖቢቴክስ ላይ የፈጸመው የሳይበር ጥቃት አዲስ የምንተፋ ማዕበል አካል ነው ብሏል።

    “ኖቢቴክስ ሽብርተኝነትን በመደገፍ እና ማዕቀቦችን በመጣስ ቁልፍ የገዥው አካል መሳሪያ ነው” ሲል ቡድኑ በቴሌግራም እና ኤክስ ላይ ለጥፏል

    በተጨማሪም በመንግሥታዊው ባንክ ሴፋህ ላይ ምንተፋ መፈጸሙን ተናግሯል።

    ፕሪዳቶሪ ስፓሮው በኢራን ላይ ለዓመታት የሳይበር ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።

    ከሶስት ዓመታት በፊት በኢራን የብረታ ብረት ስራዎች ላይ በፈጸመው የመረጃ ምንተፋ ከባድ የእሳት ቃጠሎ አስከትሎ የሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ የከተተ ነው።

  20. አሜሪካ በእስራኤል የሚገኙ ዜጎቿን ለማስወጣት ዝግጅት እያደረገች ነው

    የእስራኤል እና ኢራን ግጭት ስድስተኛ ቀኑን መያዙን ተከትሎ ከእስራኤል መውጣት ለሚፈልጉ ዜጎች እቅድ መውጣቱን በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሃክቤ ገልጸዋል።

    አምባሳደሩ በኤክስ ገጻቸው “አስቸኳይ ማስታወቂያ” በሚል ባጋሩት መልዕክት በእየሩሳሌም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ “ከአገር የመውጣት በረራዎችን እንዲሁም የመርከብ ጉዞዎችን” እያዘጋጀ ነው ብለዋል።

    ከአገር መውጣት ለሚፈልጉ እንዴት መመዝገብ እንደሚችሉና፣ የተመዘገቡም መረጃዎች ይደርሳቸዋል ብሏል።