የእስራኤል ጥቃት ሊጎዳው ያልቻለው የኢራኑ የኒውክሌር ማበልጸጊያ ፎርዶ
ከሰሞኑ እስራኤል በኢራን ላይ እያካሄደችው ካለው ጥቃት ጋር ተያይዞ ስሙ እየተጠቀሰ ያለው የፎርዶ የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ ነው።
ፎርዶ ኢራን ካሏት ሁለት ወሳኝ የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያዎች መካከል አንዱ ሲሆን የእስራኤል መከላከያ ኃይል የአየር ጥቃት ቢያደርስበትም ጉዳት ሊደርስበት አልቻለም።
ፎርዶ ከቴህራን በስተደቡብ በ200 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
የተገነባውም በተራራ ተከቦ ከመሬት በታች ከ80-90 ሜትር ጥልቀት ላይ ሲሆን ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ከደህንነት እና ከጥበቃ ጋር የተያያዘ ነው።
ኢራን ዩራኒየም- 235 የተሰኘውን ለማግኘት ከምትጠቀምባቸው ቁልፍ የማበልጸጊያ ጣቢያዎች አንዱ ነው።
የፎርዶን የኒውክሌር ማብላያን መድረስ የሚችለው የአሜሪካው 14 ሺህ ኪሎግራም ገደማ የሚመዝነው ‘በንከር በስተር’ የተሰኘው ቦምብ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
ቦምቡ ከመሬት ስር ያሉ ስፍራዎችን እንዲሁም ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግላቸውን የተቀበሩ የጦር መሳሪያዎችን ለማውደም ታልሞ የተሰራ ነው።
ቦምቡ ከመፈንዳቱ በፊት መሬት፣ አለት ወይም ድንጋይ ሰንጥቆ በመግባት ሳይፈነዳ መቆየት ይችላል።
ስድስት ሜትር እርዝማኔ እና 14 ሺህ ኪሎግራም ከመመዘኑ አንጻር የአሜሪካው ቢ-2 የተሰኘው መሳሪያ ነው ሊሸከመው የሚችለው።
እስራኤል ፎርዶን ብቻዋን ማውደም እንደማትችል እየተገለጸ ነው። አሜሪካ 'በንከር በስተር' የተሰኘውን ቦምብ ለእስራኤል ለመስጠት ከልክላለቸ።