የእስራኤል እና ኢራን ግጭት “መስፋፋት ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል እሳት ሊያቀጣጥል ይችላል” ተመድ

ስምንተኛ ቀኑን የያዘው የእስራኤል እና ኢራን ግጭት “መስፋፋት ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል እሳት ሊያቀጣጥል ይችላል” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሳሰቡ።ዋና ጸሐፊው በአገራቱ መካከል ያለው ግጭት መቀጠል አለምን ወደ ቀውስ የሚከት ነው ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

  • እስራኤል እና ኢራን ግጭት "መስፋፋት ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል እሳት ሊያቀጣጥል ይችላል" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሳሰቡ
  • ኢራን በእስራኤል ያልተጠበቀ ጥቃት የተፈጸመባት "ከአሜሪካ ጋር የኒውክሌር አቅምን አስመልክቶ ተስፋ ሰጪ ዲፕሎማሲያዊ ሂደት ላይ በነበረችበት ወቅት" መሆኑን አስታወቀች።
  • የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከእስራኤል ጋር ያለውን ግጭት ለማስቆም ፈረንሳይን ጨምሮ አውሮፓውያኑ አገራት ለኢራን የዲፕሎማሲ ፕሮፖዛል እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
  • ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን እና በእስራኤል ግጭት ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ መግባት አለመግባቷን ይወስናሉ- ዋይት ሐውስ
  • ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ላይ ለመወሰን ሁለት ሳምንት ጊዜ ሲሰጡ ዩኬ እና የአውሮፓ ኅብረት ከኢራን ጋር ሊነጋገሩ ነው
  • የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ለቢቢሲ አሜሪካ በግጭቱ ውስጥ የምትሳተፍ ከሆነ ቀጠናው "ሲኦል" ይሆናል ሲሉ ተናግረው ነበር
  • ኢራን በትናንትናው ዕለት በፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት ከሆስፒታል አቅራቢያ ያለ ወታደራዊ ስፍራ ማነጣጠሩን ገልጽላች
  • ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች በደቡባዊ እስራኤል ባርሺባ ከተማ የሚገኘውና በእስራኤል ትልቁ ከሚባሉት አንዱ ሶሮካ ሆስፒታል መመታቱን እስራኤል አስታወቀች።
  • የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በእስራኤል እና ኢራን ግጭት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው
  • የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን ለማጥቃት ዕቅድ ቢያጸድቁም ነገር ግን የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አለመድረሳቸው ተዘገበ።
  • አሜሪካ የጦር ጄቶችን ጨምሮ የጦር መሳሪያዎችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እያንቀሳቀሰች ነው
  • ፑቲን በኻሜኒ ላይ የታቀደውን ግድያ አስመልክቶ "በፍጹም በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየት አልፈልግም" አሉ
  • የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ "ኢራናውያን እጃቸውን የሚሰጡ ሕዝቦች አይደለም" ሲሉ ተናገሩ።
  • እስራኤል በኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት እስከ እሁድ ምሽት ድረስ 224 ሰዎች ሲገደሉ 1 ሺህ 277 መጎዳታቸውን ኢራን አስታውቃለች። እስራኤል በበኩሏ በጥቃቶቹ 20 ሰዎች ተገድለውብኛል ብላለች።
  • ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት መፈጸምን በተመለከተ "ላደርገው ወይም ላላደርገው እችላለሁ" አሉ
  • ፎርዶ ኢራን ካሏት ሁለት ወሳኝ የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያዎች መካከል አንዱ ሲሆን የእስራኤል መከላከያ ኃይል የአየር ጥቃት ቢያደርስበትም ጉዳት ሊደርስበት አልቻለም።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ነዋሪዎች ቴህራንን ለቀው እየወጡ ነው

    ከኢራን መዲና ቴህራን ነዋሪዎች ለቀው እየወጡ መሆኑን ከአገሪቱ የሚወጡ ምስሎች አሳይተዋል። በመዲናዋ የሚገኘው ካራጅ ቻሉስ የተሰኘው ጎዳና ወደ ምዕራብ አቅጣጫ እያቀኑ ባሉ መኪኖች መጨናነቁን አሳይቷል።

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው “ነዋሪዎች በሙሉ ከቴህራን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቀዋል።

    የእስራኤል ጦር ከዚያ ቀደም ብሎ ነዋሪዎች ከሰሜን ምስራቅ ቴህራን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

  2. በእስራኤል የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ዜጎቹ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበ

    በእስራኤል እና ኢራን መካከል የቀጠለው የአየር እና የሚሳኤሎች ጥቃት መባባሱን ተከትሎ በእስራኤል የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ዜጎቹ “በተቻለ ፍጥነት” አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል።

    “በእስራኤል ያለው የቻይና ልዑክ ቻይናውያን ለግል ደህንነታቸው ዋስትና ቅድሚያ በመስጠት በተቻለ ፍጥነት በመሬት የድንበር ማቋረጫዎች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ያሳሳስባል” ሲል ኤምባሲው ዊ ቻት በተሰኘው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

    “በዮርዳኖስ አቅጣጫ መሄድ ይመከራል” ሲል አክሏል።

    የቻይና ኤምባሲ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግጭት “እየተባባሰ ቀጥሏል” ሲል ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

    “በርካታ የሲቪል መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፤ የዜጎች ሞት እየጨመረ ነው እንዲሁም የጸጥታው ሁኔታም አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል” ብሏል።

  3. ኢራን ዛሬ ጠዋት በፈጸመችው ጥቃት አምስት ሰዎች መቁሰላቸው ተዘገበ

    ኢራን ዛሬ ከጠዋቱ ጀምራ ተከታታይ ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል መተኮሷን የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ሲያስታውቅ፣ አምስት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።

    በዚህም የተነሳ የአየር ጥቃት ማስጠንቂያ ደወል በመላዋ አገሪቱ የተሰማ ሲሆን፣ የመከላከያ ኃይሉ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ከጦር ኃይሉ የሚሰጡትን መመሪያዎች እንዲከተሉ ጠይቋል።

    በኢየሩሳሌም እና ቴል አቪቭ የሚገኙ የቢቢሲ ዘጋቢዎችም ዛሬ ረፋድ ላይ በርካታ የፍንዳታ ድምጾችን መስማታቸውን ገልጸዋል።

    የጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወሉን ተከትሎ ቢያንስ አንድ ሚሳዔል ማዕከላዊ እስራኤልን መምታቱ ተዘግቧል።

    የእስራኤል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ባወጣው መረጃ ረፋድ ላይ ከኢራን በተወነጨፉ ሚሳዔሎች ምክንያት በሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል።

    በማዕከላዊ እስራኤል በሚገኝ የአውቶብስ ማቆሚያ ስፍራ ላይ በደረሰ ጥቃት አምስት ሰዎች በፈንጣሪ ተመትተው ቀላል የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው የእስራኤል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ቃል አቀባይ ማጊን ዴቪድ አዶም ተናግረዋል።

  4. እስራኤል ልትገድላቸው ያቀደችው የኢራኑ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል የኢራኑን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሉ ኻሜኒ ለመግደል የነበራትን ዕቅድ ውድቅ ማድረጋቸው ተዘግቧል።

    ሆኖም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከኤቢሲ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጉዳዩን እያጤኑበት መሆኑን ጠቁመዋል። የኻሜኒ ግድያ “ግጭቱን ይቋጨዋል እንዲሁም የኒውክሌር ጦርነትን ይከላከላል” ብለዋል።

    ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን የማበልጸግ መብት እንዳላት በተደጋጋሚ በአጽንኦት የሚናገሩት የኢራን የረዥም ጊዜ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ጥያቄ ፈጥሯል።

    “የአገዛዙ የመቀጠል ህልውና የእሳቸው ቀዳሚ ግብ ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ መሪውን አግኝተው የነበሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች የቀድሞ ረዳት ሚኒስትር ጄፍሪ ፌልድማን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    “የአገዛዙን የመቀጠል ህልውና አንዳንድ ጉዳዮች እንዲፈጽሙ የሚያደርጋቸው ከሆነ ለምሳሌ ያህል እሳቸው በሚገልጹበት ቋንቋ ከሰይጣን (አሜሪካ) ጋር መቀመጥ፤ ያንን ለማድረግ ፈቃደኛ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ” ይላሉ።

    ሆኖም ፌልድማን አክለውም ኻሜኒ በዚሄ ቀጥለው ኢራን “[የኒውክሌር] ቦምብ እንድታመርት ሊያነሳሳት ይችላል” ይላሉ።

    ጠቅላዩ መሪ በቀጣዩ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር የሁለቱ አገራት ግጭት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት” ከትልልቅ ጥያቄዎች አንዱ ነው” ብለዋል።

  5. አምስተኛ ቀኑን የያዘው የእስራኤል እና ኢራን ግጭት

    በእስራኤል እና ኢራን መካከል የተነሳው ግጭት አምስተኛ ቀኑን ይዟል፤ የአገራቱ የአየር እና የሚሳኤል ጥቃት ልውውጥ እንደቀጠለ ነው።

    • የእስራኤል ጦር “ወታደራዊ መሰረተ ልማቶች” ላይ ያነጣጠረ ዕቅድ ለመፈጸም በሚል ነዋሪዎች ከሰሜናዊ ምስራቅ ቴህራን ለቀው እንዲወጡ አዟል።
    • ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራም “ነዋሪዎች በሙሉ ከቴህራን ለቀው መውጣት አለባቸው” የሚል ማስጠንቀቂያ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ አስተላልፈዋል።
    • ከሁለቱ አገራት ግጭት ጋር ተያይዞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በካናዳ እየተካሄደ ያለውን የቡድን 7 ጉባኤ ሳይጠናቀቅ ቀደም ብለው ተመልሰዋል።
    • ማክሰኞ ማለዳ በቴህራን ከፍተኛ ፍንዳታ እና ከባድ የአየር መከላከያ እሳት መነሳቱን የኢራን መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸውን ሮይተርስ አስፍሯል።
    • ከኢራን በርካታ ሚሳኤሎች መወንጨፋቸውን ተከትሎ የእስራኤል ባለስልጣናት በርካታ ግዛቶችን የሸፈነ ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።
    • ከዚያ ቀደም ብሎ እስራኤል በቀጥታ ይተላለፍ የነበረ የኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥን ላይ ጥቃት ፈጽማ ፕሮግራሙ ከመቋረጡ በተጨማሪ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
    • ኢራን የአየር ክልሏን መዝጋቷም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያሳያል።
  6. የኢራን እና የእስራኤል ግጭት መባባሱን ተከትሎ ትራምፕ የቡድን 7 ጉባኤን አቋርጠው ወጡ

    የኢራን እና የእስራኤል ግጭት ተባብሶ አምስተኛ ቀኑን መያዙን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በካናዳ እየተካሄደ ያለውን የቡድን 7 ጉባኤ ከመጠናቀቁ በፊት አቋርጠው መመለሳቸው ተገለጸ።

    በኢራን እና በእስራኤል መካከል እየተባባሰ ከመጣው ግጭት ጋር ተያይዞ ፕሬዚዳንቱ ወደ ዋሽንግተን መመለስ አለባቸው ሲል ዋይት ሐውስ አስታውቋል።

    "ግልጽ በሆኑ ምክንያቶች ቀደም ብዬ መመለስ አለብኝ" ሲሉ ትራምፕ የተናገሩ ሲሆን የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት እንዲሰበሰብ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ሪፖርቶች ወጥተዋል።

    አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን "የመከላከል አቅም ለማሳደግ" ወደ ቀጣናው ተጨማሪ መሳሪያ እንደምታሰማራ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት ተናግረዋል።

    ነገር ግን አሜሪካ፤ እስራኤል በኢራን ላይ እየፈጸመች ያለችውን የማጥቃት ዘመቻ ልትቀላቀል ትችላለች የሚሉ አስተያየቶችን የአሜሪካ ባለስልጣናት ውድቅ አድርገዋል።

  7. ፕሬዚዳንት ትራምፕ “ነዋሪዎች ከቴህራን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ” አስጠነቀቁ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ 17 ሚሊዮን ነዋሪዎች ከሚኖሩባት የኢራኗ መዲና “ቴህራን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

    የፕሬዚዳንቱ አስተያየት የተሰማው የእስራኤል ጦር በመቶ ሺዎች ከሚኖሩባት ከሰሜን ምስራቃዊ ቴህራን እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ነው።

    ትራምፕ በዚሁ ልጥፋቸው ላይ ኢራን በቅርቡ በተካሄደው የአሜሪካ እና የኢራን የኒውክሌር ድርድር ላይ ያቀረቡትን ስምምነት መፈረም እንደነበረባት አስፍረዋል።

    “ኢራን የኒውክሌር መሳሪያ ሊኖራት አይችልም። ደጋግሜ ተናግሬዋለሁ” ብለዋል

    አክለውም “ ሁሉም ነዋሪ በአስቸኳይ ቴህራንን ለቆ መውጣት አለበት” ሲሉ ትዕዛዛቸውን አስፍረዋል።

  8. የኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ በእስራኤል ጥቃት ደረሰበት

    የኢራን መንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ አካል የሆነው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ኒውስ ኔትወርክ በእስራኤል ጥቃት እንደደረሰበት ተገለጸ።

    የቴሌቪዥን ጣቢያው ጥቃት የደረሰበት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር "የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ለመጥፋት ተቃርቧል” ሲሉ ከዛቱ በኋላ ነው።

    የወጡ ቪዲዮዎች በስቱዲዮው ውስጥ ፍርስራሽ ሲወድቅ እና ዜና አንባቢዋ ተነስታ ስትሄድ አሳይተዋል።

    ለኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሚሠራ ጋዜጠኛም ጥቃቱን ተከትሎ ቴሌቪዥን ጣቢያ ያለበት ሕንጻ በእሳት ተያይዞ የሚያሳይ የመጀመሪያ ቪዲዮ አጋርቷል።

    በቪዲዮው ላይ ጋዜጠኛው ዩንስ ሻድሉ በጥቃቱ ምን ያህል ባልደረቦቹ እንደተገደሉ እንደማያውቅ ሲናገር ይሰማል።

    ጣቢያው ከጥቃቱ በኋላ ለጥቂት ደቂቃዎች ከተቋረጠ በኋላ በቀጥታ ሥርጭት ወደ አየር ተመልሷል።

    ጣቢያው በቴሌቪዥኑ ላይ ባስተላለፈው የጽሑፍ መልዕክት "ፕሮግራሞቹ ያለምንም መቋረጥ ወደ ቀጥታ ሥርጭት መመለሳቸውን" ገልጿል።

    በሌላ የጽሑፍ መስመርም እስራኤል "ጭካኔ በተሞላበት ጥሰት የኢራን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከሚገኙበት ሕንጻ መካከል አንዱን ዒላማ አድርጋለች” ብሏል።

    እስራኤል ጥቃት በመፈፀም "ሐቅን ለማፈን" እየሞከረች ነው ሲልም ከሷል።

  9. “የማጣው ምንም የቀረኝ ነገር የለም” የኢራን ነዋሪ

    እስራኤል ባለፈው አርብ በኢራን ላይ ጥቃት መፈፀም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የቢቢሲ ፐርሽያ አገልግሎት ነዋሪዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለፉ እንደሆነ እያነጋገረ ነው።

    በኢራን አብዮት ወቅት እንደ አውሮፓውያኑ በ1979 የተወለደች አንዲት ሴት "በልጅነቴ ያየኋቸው አስፈሪ ቅዠቶች እንደገና ተመልሰው መጥተዋል” ስትል እያሳለፈች ያለውን ሁኔታ ተናግራለች።

    "በእነዚህ ባለፉት ሁለት ሦስት ምሽቶች እያንዳንዱ የሚሰማው ትንሽ ድምጽ ያስደነግጠኛል - በመንገድ የሚያልፍ የሞተር ሳይክል ድምጽ፣ የሆነ እቃ ሲወድቅ አሊያም እኔ ራሴ የሆነ ነገር ስጥል የሚሰማው ድምጽ ያሸብረኛል” ብላለች።

    “በጣም ተጨንቄያለሁ።ለዓመታት በሕይወት የደረሰብኝ ጫና እና ያሳለፍኩት ፈተና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ውስጥ ከቶኛል።”

    “በጣም ደክሞኛል፣ የማጣው ምንም የቀረኝ ነገር የለም” ብላለች።

    ከቴህራን 50 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ፓክዳሽት ከተማ ነዋሪ የሆነ ግለሰብም እየተካሄደ ባለው ምንም ዓይነት ስሜት ሊሰማው እንደማይችል ተናግሯል።

    "በእስላማዊ ሪፐብሊክ የአገዛዝ ዘመን ከባድ መከራዎችን ነው ያሳለፍነው። ይህን አብዛኛው ሰው የሚጋራው ይመስለኛል። እውነቱን ለመናገር በውስጣችን የቀረ ትክክለኛ ስሜት የለም።ፍርሃት እና ደስታን ለመረዳት እንኳን የሚያስችል ጥሩ ስሜት የለንም።" ብሏል።

  10. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስራኤል የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስራኤል የሚያደርጋቸውን በረራዎች እስከሚመጣው እሁድ ድረስ ማቋረጡን አስታወቀ።

    ባለፈው አርብ እስራኤል በኢራን ላይ የጀመረችውን ጥቃት ተከትሎ ሁለቱ አገራት አንዳቸው በአንዳቸው ላይ የአየር እና የሚሳዔል ጥቃት እየፈጸሙ ይገኛሉ።

    ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ወደ አገራቱ የሚደረጉ የአየር በረራዎች የተስተጓጎሉ ሲሆን፣አየር ማረፊያዎቻቸውም ሥራቸውን አቁመዋል።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድም በሳምንት ከ10 ጊዜ በላይ ወደ እስራኤሏ ከተማ ቴል አቪቭ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ማቋረጡን አስታውቋል።

    አየር መንገዱ ባወጣው ማስታወቂያ ከአዲስ አበባ ወደ ቴል አቪቭ እና ከቴል አቪቭ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጋቸውን በረራዎች እስከ ሰኔ 15/2017 ዓ.ም. ድረስ ማቋረጡን ለደንበኞቹ ገልጿል።

  11. ነዋሪዎች ከሰፊ የቴህራን ክፍል ‘በአስቸኳይ’ ለቀው እንዲወጡ የእስራኤል ጦር አስጠነቀቀ

    የእስራኤል ጦር ሠራዊት በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ በሚገኙ ሰፊ ቦታ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች “አሁኑኑ” ለቀው እንዲወጡ “አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ” አስተላለፈ።

    "በቀጣዮቹ ሰዓታት የእስራኤል መከላከያ ኃይል ባለፉት ቀናት በመላዋ ቴህራን ውስጥ ሲያካሂድ እንደበረው የኢራን አገዛዝ ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን ለመምታት በአካባቢው ዘመቻ ያካሂዳል” በማለት የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ አቪቻይ አድሬ ማስጠንቀቂያቸውን በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

    ቃል አቀባዩ ከማስጠንቀቂያ መልዕክታቸው ጋር ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ የሚፈለገውን እና ዒላማ ይሆናል ያሉትን የቴህራን ክፍል የሚያሳይ ካርታ አያይዘዋል።

    የጦር ሠራዊቱ ቃል አቀባይ ማስጠንቀቂያ "በእዚህ አካባቢ የምትቆዩ ከሆነ ሕይወታችሁን ለአደጋ ታጋልጣላችሁ" በሚል ማሳሰቢያ ይጠናቀቃል።

    ዋና ከተማዋ በ22 ወረዳዎች የተከፋፈለች ሲሆን አሁን የእስራኤል ጦር ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ ያዘዘበት አካባቢ ከከተማዋ ትላልቅ ወረዳዎች አንዱ ሲሆን ከ330 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ያሉበት ነው።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘውም በዚሁ አካባቢ ነው።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በቴህራን ምዕራባዊ ክፍል ውስጥ አመሻሽ ላይ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ፍንዳታዎች መሰማታቸው ተዘግቧል።

    ዒላማ ከተደረጉ በአካባቢው ከሚገኙ ተራሮች የሚወጣ ጭስን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ምሥሎች በኢራን የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ እየተዘዋወሩ ነው።

    የቴህራን የአየር መከላከያ ሥርዓት ምዕራባዊውን የከተማዋን ክፍል ለመከላከል መሰማራታቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን የዘገበ ሲሆን፣ ለኢራን አብዮታዊ ዘብ ቅርብ የሆነው ፋርስ ዜና አገልግሎት ደግሞ እስራኤል በአካባቢው ያለን ወታደራዊ ጦር ሰፈር ዒላማ አድርጋለች ሲል ዘግቧል።

  12. “ድል ወደ መቀዳጀት እያመራን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ “ድል ወደ መቀዳጀት እያመራን ነው” በማለት የጀመሩት ወታደራዊ እርምጃ እንደሚቀጥል ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገራቸው የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ውስጥ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ ዛሬ የተነገረውንና እስራኤል የኢራን ዋና ከተማ - ቴህራንን የአየር ክልል በቁጥጥሯ ሥር ማስገባቷን” ደግመው ተናግረዋል።

    በዚህ ጦርነት “ግባችን የሆኑትን ሁለት ጉዳዮች ለማሳካት እየሠራን ነው፤ እነሱም የኒውክሌር ስጋቶችን ማስወገድ እና የሚሳዔል ስጋቶችን ማጥፋት ናቸው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

    ኔታኒያሁ አሁን አገራቱ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ እየፈጸሙ ያሉትን ጥቃቶች በሁለት የለዩ ሲሆን፣ የእስራኤል ዒላማዎች የኒውክሌር እና የሚሳዔል ማዕከላት ናቸው ሲሉ፤ የኢራንን ደግሞ “ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረጉ ናቸው” ብለዋል።

    "ለቴህራን ነዋሪዎች ዒላማ የሚሆኑ ቦታዎችን ‘ለቃችሁ ውጡ’ እንላለን፤ ከዚያም እርምጃ እንወስዳለን” በማለት የአገራቸው ሠራዊት የሚወስደውን እርምጃ አብራርተዋል።

    በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአየር ኃይሉ ሠፈር ውስጥ ለሚሰሩት ዜጎቻቸው ምስጋና አቅርበው “በእግዚአብሔር ድጋፍ እርምጃ እየወሰድን ድል እስክንቀዳጅ ድረስ እንቀጥላለን።” ብለዋል።

    እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈተችበት ካለፈው አርብ ጀምሮ ቢያንስ 224 ሰዎች መገደላቸውን የኢራን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

  13. በምዕራባዊ ኢራን የሚገኝ ሆስፒታል በእስራኤል ጥቃት እንደተፈጸመበት ተዘገበ

    በዛሬው ዕለት [ሰኞ] እስራኤል በምዕራባዊ የኢራን ክፍል ላይ ጥቃት መፈጸሟን የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ይህንንም ተከትሎ የኢራን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጌል እንደተናገሩት ኬርማንሻህ በተባለች ከተማ ውስጥ የሚገኘው ፋራቢ ሆስፒታል በእስራኤል ጥቃት ዒላማ ሆኗል።

    ቃል አቀባዩ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ በሆስፒታሉ ላይ የተፈጸመው ጥቃት “ከባድ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት” እና “የጦር ወንጀል” ነው በማለትም ከስሰዋል።

    ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ከተወሰኑ ሁኔታዎች በስተቀር ጦርነት በሚካሄድበት ጊዜ ሆስፒታሎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም ያዛል። በሆስፒታሎች ላይ የሚፈጸም ጥቃትም እንደ ጦር ወንጀል እንደሚቆጠር ያስቀምጣል።

    ቢቢሲ በቪዲዮ ምሥል ላይ ባደረገው ማጣራት ሆስፒታሉ ላይ ጉዳት መድረሱን አረጋግጧል፤ ነገር ግን ጥቃቱ በቀጥታ ሆስፒታሉን ዒላማ ያደረገ ስለመሆኑ ማወቅ አልቻለም።

    ኢርና የተባለው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የዜና ወኪል በጥቃቱ በሰው ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ያለው ነገር ባይኖርም፤ የነፍስ አድን ሠራተኞች ወደ ሆስፒታሉ መላካቸውን ዘግቧል።

  14. በኢራን የኒውክሌር ማዕከላት ላይ ተጨማሪ ጉዳት አለመድረሱ ተነገረ

    እስራኤል ባለፈው አርብ ከፈጸመችው ጥቃት በኋላ ናታንዝ እና ፎርዶው በተባሉት የኢራን የኒውክሌር ማዕከላት ላይ ተጨማሪ ጉዳት አለመድረሱን የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ተናገሩ።

    ኃላፊው ራፋኤል ግሮሲ ለተቋማቸው የቦርድ አስተዳዳሪዎች እንደተናገሩት በሁለቱ የኢራን የኒውክሌር ማዕከላት ዙሪያ ያለው የጨረራ መጠን መደበኛ ነው ብለዋል።

    በናታንዝ ያለው ማዕከል ከመሬት በላይ ያለው ክፍል በእስራኤል ጥቃት የወደመ ቢሆንም፣ ከመሬት በታች ባለው ክፍል ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙ አመልካች ነገሮች የሉም ተብሏል።

    ነገር ግን የማዕከሉ የኃይል አቅርቦት መውደሙን እና ምናልባትም በዩራኒየም የማበልጸጊያ ማሽን ላይ ጉዳት ሳይደርስ እንዳልቀረ ኃላፊው ገልጸዋል።

    በተጨማሪም ኢስፋሃን በሚገኘው የኒውክሌር ማዕከል ውስጥ የሚገኙ አራት ሕንጻዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ከተራራ በታች ተቆፍሮ በተገነባው ፎርዶው የኒውክሌር ማዕከል ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ሪፖርት አልወጣም።

    የዓለም አቀፉ ኒውክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም ኃላፊው ግሮሲ ወታደራዊ ጥቃቱ የሚባባስ ከሆነ ከማዕከላቱ ጨረር አፈትልኮ የመውጣት ዕድል ስለሚኖረው የሰዎችን ሕይወት ለአደጋ ያጋልጣል በማለት ሁለቱም አገራት ግጭቱን ከማባበስ እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።

  15. ኢራን ለእስራኤል ሲሰልል አግኝቸዋለሁ ያለችውን ግለሰብ በሞት ቀጣች

    ኢራን የእስራኤል የደኅንነት ተቋም ለሆነው ሞሳድ በመሰለል ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ያለችውን ግለሰብ በሞት መቅጣቷን ገለጸች።

    ባለሥልጣናት እንዳሉት እስማኤል ፍቅሪ የተባለው ግለሰብ በገንዘብ የተለያዩ መረጃዎችን ለማስተላለፍ ሲሞክር ተይዞ የታሰረው ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር።

    በኢራን በቅርብ ጊዜ ውስጥ መሰል ቅጣቶች ሲፈፀሙ ይህ ሦስተኛው እንደሆነ ይታሰባል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ለእስራኤል በመሰለል የተጠረጠሩ ሌሎች በርካታ ሰዎችም ከአርብ ዕለት ጀምሮ ታስረዋል።

    የአገሪቷ የፍትሕ ኃላፊ ጎላምሆሴን ሞህሲን ኢጀኢ እንዳሉት አሁን ካለው ግጭት አንጻር የተጠረጠሩት የእስራኤል ተባባሪዎች የፍርድ ሒደት በአፋጣኝ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ለኢራን የደኅንነት መሥሪያ ቤት በመሰለል የተጠረጠሩ ሁለት እስራኤላዊያንም እሁድ ዕለት ታስረዋል።

    ባለፈው ሳምንትም በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠረ የ13 ዓመት ታዳጊ በቴል አቪቭ መታሰሩ ተገልጿል።

  16. እስራኤል “የቴህራንን የአየር ክልል በሙሉ” መቆጣጠሯን ገለፀች

    የእስራኤል እና የኢራን ጥቃት በቀጠለበት በአሁኑ ሰዓት እስራኤል የቴህራንን የአየር ክልል መቆጣጠሯን አስታወቀች።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ እስራኤል “ የቴህራንን አየር ክልል ሙሉ በሙሉ መቆጣጣር ችላለች” ሲሉ ተናግረዋል።

    ብርጋዴር ጄኔራል ኤፊ ዴፍሪን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ላይ “የኢራን አንድ ሦስተኛ የምድር ለምድር የሚሳኤል ማስወንጨፊያዎችን አውድመናል” ሲሉ ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጦር ከ120 በላይ የሚሳኤል ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙን ገልጿል።

    እስራኤል አርብ ዕለት ጥቃት መሰንዘር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ኢራን ከያዘችው አጠቃላይ ማስወንጨፍያዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ማውደሟን ገልጻለች።

    የአየር ኃይሉ ትናንት ምሽት ብቻ ከ20 በላይ ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙን የገለፁት ቃል አቀባዩ፣ “ከደቂቃዎች በፊት” ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን ለማስወንጨፍ ጥቅም ላይ ውለው እንደነበር ዴፍሪን ተናግረዋል።

    እስራኤል በማዕከላዊ ኢራን ኢስፋሃን ውስጥ ወደ 100 የሚጠጉ ወታደራዊ ዒላማዎችን ላይ ጥቃት ለማድረስ 50 የሚጠጉ ተዋጊ ጄቶችን ማሰማራቷን ተናግረዋል።

    በዚህ ጥቃትም የሚሳኤል ማከማቻ ስፍራዎችን፣ ማስወንጨፊያዎችን እና የማዘዣ ማዕከሎችን አውድማለች ብለዋል።

  17. የኢራን ፕሬዝዳንት ዜጎች 'ወንጀለኞችን እንዲጋፈጡ' ጥሪ አቀረቡ

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ኢራናውያን "ኢራን የገጠማትን የወንጀለኞች ጥቃት በጋራ እንዲጋፈጡ፣በአንድነት እንዲቆሙ፣እንዲጸኑ" ጥሪ አቀረቡ።

    ሰኞ ዕለት ለኢራን ፓርላማ ንግግር ያደረጉት ፔዝሽኪያን፣ ኢራን "ለዲፕሎማሲ ዕድል ሰጥታ ለድርድር እና ለውይይት መንገድ ከፍታ ነበር" ብለዋል።

    "ጠላት ኢራንን እና ሕዝቦቿን በግድያ እና በሽብር ሊያጠፋቸው አይችልም። ከእያንዳንዱ ከታለሙ ጥቃቶች ጀርባ ዓላማውን አንግበው መንገዱን የሚቀጥሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጀግኖች አሉ" ብለዋል ።

    ፔዝሽኪያን አገራቸው "የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመታጠቅ እንደማትፈልግ" ነገር ግን "ከኒውክሌር ኃይል እና ሕዝቦቿን በሚጠቅም ምርምር የመጠቀም መብት እንዳላት" በድጋሚ ተናግረዋል።

  18. ኢራን የኒውክሌር ድርድር የሚቀጥል ከሆነ አሜሪካ የእስራኤልን ጥቃት እንድታወግዝ ጠየቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ትናንት ዕሁድ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የአሜሪካ እና ኢራን የኒውክሌር ድርድር ከተሰረዘ በኋላ፣ ድርድሩ እንዲቀጥል አሜሪካ እስራኤል እየፈጸመች ያለችውን ጥቃት "ማውገዝ" አለባት ብለዋል።

    ኢስሜል ባጋይ አሁን ባለው ሁኔታ ድርድሩን “ትርጉም የለሽ” በማለት በድጋሚ የገለፁ ሲሆን፣ ዩናይትድ ስቴትስ በጥቃቱ “ተባባሪ” ነች ሲሉ ወንጅለዋታል።

    በተጨማሪም የኢራን ፓርላማ ከኒውክሌር ስምምነት ለመውጣት የሚወስን ከሆነ ውሳኔው "አስገዳጅ" እንደሚሆን ተናግረዋል።

    ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል መሆኑን ስትገልጽ ብትቆይም፣ እስራኤል ግን በዚህ ሃሳብ አትስማማም።

  19. የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ባደረሰችው ጥቃት ላይ ለመነጋገር አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

    የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የቦርድ አባላት የእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ የሚያስከትለውን አደጋ ለመወያየት ዛሬ በኤጀንሲው ዋና መሥሪያ ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ያደርጋሉ።

    ስብሰባው የተጠራው በኢራን ሲሆን የሩሲያ፣ቻይና እና ቬንዙዌላን ድጋፍ አግኝቷል።

    ኢራን መጀመሪያ ላይ በሳምንቱ መጨረሻ የእስራኤልን ጥቃት የሚያወግዝ የውሳኔ ሃሳብ ማቅረብ ፈልጋ ነበር።

    ይሁንና ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዲፕሎማቲክ ምንጮች እንደገለፁት የውሳኔ ሃሳቡ የብዙሃኑን ድጋፍ ያስገኛል ተብሎ አይታሰብም።

    በዚህም ምክንያት ኢራን አሁንም የእስራኤልን ድርጊት ማውገዝን ያካተተ አጠቃላይ መግለጫ ለማቅረብ ተዘጋጅታለች።

    ይህ አስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው በኢራን እና በእስራኤል መካከል እየተካሄደ ያለው የሚሳዔል ልውውጥ መካከል፣ እስራኤል በናታንዝ እና ፎርዶው የሚገኙ የኢራን የኒውክሌር ቦታዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ ነው።

    የኒውክሌርን ስጋት ለመፍታት ወታደራዊ እርምጃ በኤጀንሲው አባል አገራት ስምምነት መሠረት ተቀባይነት ያለው መንገድ ሆኖ አያውቅም።

    ኢራን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የኤጀንሲው የቦርድ አባላት ጥቃቱን ማውገዝ እንዳለባቸው አጥብቃ ትናገራለች።

    ሆኖም፣ አሁን ካለው የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር፣ እንዲህ ዓይነቱ ውግዘት የሚጠበቅ አይደለም።

    በተጨማሪም ይህ ስብሰባ በሁለቱ ኃያላን አገራት መካከል በአፋጣኝ የተኩስ ማቆም እንዲደረግ መንገድን ስለ መክፈት አለመክፈቱ ግልፅ አይደለም።

    ሁለቱ አገራት አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጠንካራ የአጸፋ ጥቃት መስጠታቸውን ቀጥለዋል።

  20. በቴል አቪቭ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኢራን ጥቃት መጠነኛ ጉዳት ደረሰበት

    ትናንት እሁድ ምሽት ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳዔሎች በቴል አቪቭ በሚገኘው የኤምባሲያቸው ቅርንጫፍ “መጠነኛ ጉዳት” መድረሱን በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር አስታወቁ።

    ማይክ ሃካቢ በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ቆንስላው “በኢራን ሚሳዔሎች ንዝረት” ጉዳት ስለደሰበት ዝግ ሆኖ ይቆያል ብለዋል።

    የአሜሪካ ኤምባሲ በቴል አቪቭ እና በኢየሩሳሌም የሚገኙ ሠራተኞቹ መጠለያ ውስጥ እንዲቆዩ በትናንትናው ዕለት አሳስቦ ነበር።

    በሚሳዔል ጥቃቱ የተጎዳ የኤምባሲው ሠራተኛ እንደሌለም አምባሳደሩ ተናግረዋል።