የእስራኤል እና ኢራን ግጭት “መስፋፋት ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል እሳት ሊያቀጣጥል ይችላል” ተመድ

ስምንተኛ ቀኑን የያዘው የእስራኤል እና ኢራን ግጭት “መስፋፋት ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል እሳት ሊያቀጣጥል ይችላል” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሳሰቡ።ዋና ጸሐፊው በአገራቱ መካከል ያለው ግጭት መቀጠል አለምን ወደ ቀውስ የሚከት ነው ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

  • እስራኤል እና ኢራን ግጭት "መስፋፋት ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል እሳት ሊያቀጣጥል ይችላል" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሳሰቡ
  • ኢራን በእስራኤል ያልተጠበቀ ጥቃት የተፈጸመባት "ከአሜሪካ ጋር የኒውክሌር አቅምን አስመልክቶ ተስፋ ሰጪ ዲፕሎማሲያዊ ሂደት ላይ በነበረችበት ወቅት" መሆኑን አስታወቀች።
  • የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከእስራኤል ጋር ያለውን ግጭት ለማስቆም ፈረንሳይን ጨምሮ አውሮፓውያኑ አገራት ለኢራን የዲፕሎማሲ ፕሮፖዛል እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
  • ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን እና በእስራኤል ግጭት ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ መግባት አለመግባቷን ይወስናሉ- ዋይት ሐውስ
  • ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ላይ ለመወሰን ሁለት ሳምንት ጊዜ ሲሰጡ ዩኬ እና የአውሮፓ ኅብረት ከኢራን ጋር ሊነጋገሩ ነው
  • የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ለቢቢሲ አሜሪካ በግጭቱ ውስጥ የምትሳተፍ ከሆነ ቀጠናው "ሲኦል" ይሆናል ሲሉ ተናግረው ነበር
  • ኢራን በትናንትናው ዕለት በፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት ከሆስፒታል አቅራቢያ ያለ ወታደራዊ ስፍራ ማነጣጠሩን ገልጽላች
  • ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች በደቡባዊ እስራኤል ባርሺባ ከተማ የሚገኘውና በእስራኤል ትልቁ ከሚባሉት አንዱ ሶሮካ ሆስፒታል መመታቱን እስራኤል አስታወቀች።
  • የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በእስራኤል እና ኢራን ግጭት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው
  • የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን ለማጥቃት ዕቅድ ቢያጸድቁም ነገር ግን የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አለመድረሳቸው ተዘገበ።
  • አሜሪካ የጦር ጄቶችን ጨምሮ የጦር መሳሪያዎችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እያንቀሳቀሰች ነው
  • ፑቲን በኻሜኒ ላይ የታቀደውን ግድያ አስመልክቶ "በፍጹም በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየት አልፈልግም" አሉ
  • የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ "ኢራናውያን እጃቸውን የሚሰጡ ሕዝቦች አይደለም" ሲሉ ተናገሩ።
  • እስራኤል በኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት እስከ እሁድ ምሽት ድረስ 224 ሰዎች ሲገደሉ 1 ሺህ 277 መጎዳታቸውን ኢራን አስታውቃለች። እስራኤል በበኩሏ በጥቃቶቹ 20 ሰዎች ተገድለውብኛል ብላለች።
  • ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት መፈጸምን በተመለከተ "ላደርገው ወይም ላላደርገው እችላለሁ" አሉ
  • ፎርዶ ኢራን ካሏት ሁለት ወሳኝ የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያዎች መካከል አንዱ ሲሆን የእስራኤል መከላከያ ኃይል የአየር ጥቃት ቢያደርስበትም ጉዳት ሊደርስበት አልቻለም።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ ይህንን ጦርነት የማስቆም አቅም አላቸው - የቀድሞ የእስራኤል ዲፕሎማት

    እስራኤል እና በኢራን መካከል ያለውን ግጭት የማስቆም አቅም በአብዛኛው በዶናልድ ትራምፕ እጅ ነው ሲሉ ለሁለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትሮች አማካሪ የነበሩት የቀድሞ ዲፕሎማት አሎን ፒንካስ ተናገሩ።

    ፒንካስ ትራምፕ ሁለቱን አገራት ለማደራደር በሚያስችል ሁኔታ ላይ ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ኢራንን ለመታደግ እና በድርድር ላይ የተመሠረተ ሰላምን ለመቀበል የሚያስችላቸውን ሀሳብ ለቴህራን ሊያቀርቡ ይችላሉ።

    ነገር ግን ኢራን ያለችበት ሁኔታ ለመደራደር ደካማ የሚባል ስለሆነ ትግሏን ለመቀጠል እና በእስራኤል ላይ የበለጠ ጉዳት ማድረስ ትፈልግ ይሆናል ብለዋል።

    "በአንጻሩ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስልክ አንስተው ኔታንያሁ 'ይበቃል፤ ይህንን ለማቆም 24 ሰዓት አለህ' ሊሏቸው ይችላሉ።

    "ከሁለቱ አንዱን ያደርጉ ይሆን? አላውቅም" ብለዋል የቀድሞው ዲፕሎማት።

  2. የቴህራን ነዋሪዎች “ዋጋ ይከፍላሉ” ሲሉ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዛቱ

    ኢራን ሌሊቱን በፈጸመችው ጥቃት አምስት ዜጎቿ ከተገደሉ እና በርካቶች ከቆሰሉ በኋላ ለጥቃቱ አጸፋ የኢራን ዋና ከተማ ነዋሪዎች “ዋጋ ይከፍላሉ” ሲሉ የእስራኤል የመለካከያ ሚኒስትር ሲሉ ዛቱ።

    ሚኒስትሩ ኢዝራኤል ካትዝ “የኢራንን አቅም እያዳከመ ያለውን የእስራኤል ሠራዊት ከሚፈጽማቸው ጥቃቶች ለማደናቀፍ” የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ አካባቢዎችን ዒላማ እያደረጉ ነው ሲሉ የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ከስሰዋል።

    የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር የኢራኑን የበላይ መሪ አያቶላ ኻሜኒን “ፈሪ ነፍሰ ገዳይ” እና “ጉረኛ አምባገነን” ሲሉ ተችተዋቸዋል።

    አራተኛ ቀኑን በያዘው የእስራኤል እና የኢራን ድንበር ተሻጋሪ ግጭት በሁለቱም ወገን ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው እየተነገረ ሲሆን፣ ኢራን ሌሊቱን በእስራኤል ውስጥ ጥቃትን ፈጽማለች።

    በተለያዩ የኢራን አካባቢዎች ላይ ጥቃቶችን እያደረሰች ያለችው የእስራኤል ሚኒስትር ሌሊቱን ለተፈጸመው ጥቃት “ሳይዘገይ” አጸፋ እንደምትመልስ ተናግረዋል።

  3. ዋናው ጥያቄ ኢራን በከፍተኛ ደረጃ ያበለፀገችውን ዩራኒየም የት እንዳስቀመጠችው ነው - የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣን

    የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጥበቃ የቀድሞው ምክትል ዋና ዳይሬክተር የእስራኤልን ጥቃት ተከትሎ በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ውስጥ ነገሮች የት እንዳሉ በትክክል አናውቅም አሉ።

    ኦሊ ሄይኖን እስራኤል በቴህራን የኒውክሌር አቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሳ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። በናታንዝ የሚገኘው የኒውክሌር ተቋም "ዳግም ስራ ለማስጀመር ቢያንስ ዓመታትን ይወስዳል" ሲሉ ከሬዲዮ 4 ቱዴይ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።

    "እኔ እንደማስበው (የፎርዶው የኒውክሌር ተቋም) ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ከእነዚህ የቦምብ ጥቃቶች በኋላ በጣም መጥፎ ሁኔታ ላይ ነው።"

    ነገር ግን ቁልፉ ጥያቄ ይቀራል ይላል ያሉት ሄይኖን፣ ኢራን በከፍተኛ ደረጃ የበለጸገውን ዩራኒየም “ከ400 ኪሎ ግራም በላይ ይሆናል” የምትከማችበትን ቦታ የት ነው የሚለው አልታወቀም።

    "ሚስጥራዊ ጣቢያ ካላቸው... በጣም ግዙፍ መሆን አይጠበቅበትም እና ዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ እይታ ውጪ ለጦር መሳሪያ የሚሆን [ዩራኒየም] ማበልጸግ ከቻሉ ያልፈታነው ትልቅ ችግር አለ ማለት ነው።"

  4. ኢራን በእስራኤል ያደረሰችው ጥቃት በምስል

    ኢራን ትናንት ምሽት በቴልአቪ የሚሳዔል ጥቃት የፈጸመች ሲሆን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከፍርስራሽ ውስጥ ሰዎችን ለማውጣት ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል።

    በትናንትናው የኢራን ጥቃት አራት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ይህም ከአርብ ጀምሮ በሚሳዔል ጥቃት የሞቱትን ሰዎች ቁጥር 19 መድረሱን የእስራኤል ብሔራዊ የድንገተኛ ጊዜ አገልግሎት አስታውቋል።

  5. ከአርብ ዕለት ጀምሮ ኢራን በእስራኤል በፈጸመችው ጥቃት 19 ሰዎች ተገደሉ

    ትናንት ሌሊት ኢራን በእስራኤል ላይ በፈጸመችው ጥቃት አራት ሰዎች መሞታቸውን የእስራኤል ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት አስታወቀ።

    ይህም በእስራኤል ከአርብ ዕለት ጀምሮ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር ወደ 19 ከፍ አደርጎታል።

    የብሔራዊ ድንገተኛ ጊዜ አገልግሎቱ በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁለት ሴቶች እና ሁለት ወንዶች መገደላቸውን አስተውቋል።

    አያይዞም 87 የተጎዱ ሰዎችን ወደ ሆስፒታሎች መውሰዱን እና ከነዚህም መካከል አንዲት የ30 ዓመት ሴት በፊቷ ላይ ከባድ ጉዳት እንዳጋጠማት፣ አምስት ሰዎች መካከለኛ እና 81 ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ገልጿል።

    የኢራን ጤና ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት ይፋ እንዳደረገው ሁለቱ አገራት በሚሳዔል ጥቃት ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ 224 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።

  6. ዛሬ ሰኞ ማለዳ የእስራኤል እና የኢራንን ግጭት ለመከታተል ወደ ገጻችን ከመጣችሁ

    • ኢራን በመላ እስራኤል በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች። በእስራኤል የሚገኝ የቢቢሲ ባልደረባ ጥቃቱ "እስካሁን ከደረሱት ትልቁ ነው የሚመስለው" ብሏል።
    • በማዕከላዊ እስራኤል የደረሰን የኢራን ጥቃትን ተከትሎ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
    • የእስራኤል ትልልቅ ከተሞችን ያናወጡት ፍንዳታዎች በቴል አቪቭ እና የሃይፋ የወደብ ከተማን 30 ሰዎችን አቁስለዋል።
    • የኢራን ጥቃት የደረሰው እስራኤል በኢራን ምድር ለምድር የሚምዘገዘጉ ሚሳዔሎችን በመጠቀም ጥቃት ሰንዝራ የኢራን ጦር ኃይሎች የስለላ ኃላፊንከገደለች በኋላ ነው።
    • ጦርነቱ ከተጀመረበት አርብ ጀምሮ ቢያንስ 224 ኢራናውያን እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት የተገደሉ ሲሆን 90 በመቶ የሚሆኑት ሟቾች ሰላማዊ ዚጎች መሆናቸውን የኢራን የጤና ሚኒስቴር አስታወቋል።
    • የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል እና ኢራን ስምምነት ላይ ሊደርሱ ይችላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ አገራት "መፋለምአለባቸው" ብለዋል። የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ትራምፕ እስራኤል የኢራንን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ኼሜኒን ለመግደል ያቀደችውን እቅድ አልተቀበሉም ሲሉ ዘግበዋል።
    • ጥቃቱ የተፈጸመው የቡደን ሰባት አገራት መሪዎች በካናዳ በሚሰባሰቡበት ወቅት ሲሆን ሁሉም ዓይናቸው በእስራኤል እና በኢራን ላይ እንደሚሆን የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ ዘጋቢ ገልጿል።
  7. ዕሁድ ዕለት እስራኤል እና ኢራን የፈጸሟቸው ጥቃቶች እና የደረሱ ጉዳቶች

    ከአርብ ጀምሮ ለሦስተኛ ቀን የቀጠለው የእስራኤል እና የኢራን ግጭት እየተባባሰ ነው። ዕሁድ ዕለት በሁለቱም ወገኖች የተፈጸሙ ጥቃቶች እና የደረሱ ጉዳቶችን በተመለከተ አጭር መረጃ፡

    በእስራኤል የተፈጸሙ ጥቃቶች

    • እስራኤል በኢራን ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን መምታቷን ቀጥላለች፤ የእስራኤል የመከላከያ ኃይል እንዳለው በዛሬው ዕለት 250 ዒላማዎችን መትቷል።
    • የኢራን የመገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት አስከ ቅዳሜ ዕኩለ ቀን ድረስ 128 ሰዎች ሲገደሉ 900 የሚደርሱት ደግሞ ተጎድተዋል።

    በኢራን የተፈጸሙ ጥቃቶች

    • ኢራን ሌሊት ላይ በእስራኤል ላይ የሚሳዔል ጥቃቶችን የፈጸመች ሲሆን፣ በዚህም ስድስት ሰዎች ከቴል አቪቭ በስተደቡብ በምትገኘው ባት ያም በምትባል ቦታ እንዲሁም አራቱ በሰሜናዊቷ ታምራ ከተማ ውስጥ በአጠቃላይ 10 ሰዎች ተገድለዋል። ከ100 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የእስራኤል ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
    • ዕሁድ ከሰዓት በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል በማስወንጨፍ ጥቃት ሰንዝራለች። የእስራኤል ጦር ሠራዊት እንዳለው አብዛኞቹ ሚሳዔሎች የከሸፉ ሲሆን፣ ጉዳት ስለመድረሱ የወጣ ዘገባ የለም።
  8. የቀጠለው የእስራኤል ጥቃት ኢራን ውስጥ ያደረሰው ጉዳት

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱን የጤና ሚኒስቴር በመጠቀስ እስከ ቅዳሜ ዕኩለ ቀን ድረስ እስራኤል በፈጸመቻቸው ጥቃቶች 128 ኢራናውያን መገደላቸውን እና 900 የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸውን ዘግበዋል።

    ካለፈው አርብ ጀምሮ ከተለያዩ ወገኖች በእስራኤል ጥቃት የተጎዱ ሰዎችን በተመለከቱ አሃዞች እያወጡ ነው።

    ቢቢሲ በኢራን ውስጥ ዘጋቢ ስለሌለው ከገለልተኛ አካላት ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ አልቻለም።

    በተጨማሪም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሚወጡት ቁጥሮች በተለያየ ወገኖች የሚወጡትን ያካተተ ወይም የተናጠል መሆኑን ለማወቅ አዳጋች ሆኗል።

    · የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ቅዳሜ ዕለት እስራኤል ቴህራን ውስጥ በአንድ ሕንጻ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 20 ሕጻናትን ጨምሮ 60 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።

    · ምሥራቃዊ አዘርባይጃን የምትባለው የኢራን ግዛት አስተዳዳሪ 30 ወታደሮች እና አንድ የኢራን ቀይ ጨረቃ አባል ተገድለዋል ብለዋል።

    · የኢራን ቀይ ጨረቃ እንዳለው በምዕራባዊ አዘርባጃን ግዛት ውስጥ አምቡላንስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።

    · በተባበሩት መንግሥታት የኢራን መልዕክተኛ አርብ ዕለት እንዳስታወቁት በመጀመሪያው ቀን ጥቃት 78 ሰዎች ሲገደሉ ከ320 በላይ ሰዎች መጎዳታቸውን ገልጸው ነበር።

    · የኢራን መንግሥት ቃል አቀባይ ፋጢማህ ሞሐጄራኒ ባለፉት ሦስት ቀናት በእስራኤል ጥቃት ቢያንስ 30 ሴቶች እና ሕጻናት መገደላቸውን ያመለከቱ ሲሆን፣ አጠቃላይ ቁጥር ግን አልገለጹም።

    · በተጨማሪም አስካሁን ድረስ ኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የአየር ኃይል አዛዥን ጨምሮ 18 የአብዮታዊ ዘቡ ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ ጥቃቶች መገደላቸውን አንድ የኢራን ጦር ሠራዊት ከፍተኛ አመራር አስታውቀዋል።

    · በተጨማሪም ቢያንስ ሰባት የኢራን የኒውክሌር ሳይንቲስቶች በእስራኤል በተፈጸሙ የተናጠል ጥቃቶች ተገድለዋል።

  9. ኢራን እና እስራኤል ለምን ደመኛ ጠላቶች ሆኑ?

    ኢራን ከግብፅ ቀጥላ ለእስራኤል እውቅና በመስጠት ሁለተኛዋ እስላማዊ አገር ነበረች። ነገር ግን ከኢራን እስላማዊ አብዮት በኋላ ይህ ግንኙነት ተበላሽቶ ከአራት አስርታት በላይ በጠላትነት እየተያዩ ቆይተዋል። ለመሆኑ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደ ደመኛ ጠላትነት ለምን ተሸጋገረ?

  10. በኢየሩሳሌም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞቹ በመጠለያ እንዲቆዩ ሲያሳስብ ቤተሰቦቻቸው እንዲወጡ ፈቀደ

    በእስራኤል የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አሁን ባለው ሁኔታ ሁሉም ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው በመጠለያዎች እንዲቆዩ አሳሰበ።

    የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በእስራኤል ውስጥ ያሉ የቤተሰብ አባላት እና አንዳንድ የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞች ያልሆኑ ከፈለጉ ለቅቀው መውጣት እንደሚችሉ ገልጿል።

    አሁን በቴል አቪቭ አቅራቢያ ያለው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተዘግቷል።

    ይህ ማለት ብቸኛ መውጫው መንገድ በመኪና እንደ ዮርዳኖስ ወዳሉ ጎረቤት አገራት መሄድ ነው።

    አሜሪካ ኤምባሲ የሚገኘው በቴል አቪቭ ሳይሆን በኢየሩሳሌም ነው።

    በኢየሩሳሌም ኤምባሲ ካላቸው ጥቂት አገራት መካከል አንዷ አሜሪካ ናት።

    በኢየሩሳሌም የሚገኘው ኤምባሲም ሆነ በቴል አቪቭ የሚገኘው ቢሮ ለአደጋ ጊዜ የቆንስላ አገልግሎት ክፍት ናቸው።

  11. ዩኬ ዜጎቿ ወደ እስራኤል እንዳይጓዙ አስጠነቀቀች

    ዩናይትድ ኪንግደም በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለው ግጭት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ዜጎቿ ወደ እስራኤል እና የፍልስጤም ግዛቶች እንዳይጓዙ አስጠነቀቀች።

    አርብ ዕለት “ከአስፈላጊ ጉዞዎች በስተቀር” ማንኛውንም ጉዞ እንዳያደርጉ አስጠንቅቆ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ሙሉ በሙሉ ጉዞ እንዳያደርጉ አስጠንቅቋል።

    የውጪ ጉዳይ ቢሮ ቅዳሜ ዕለት ባሻሻለው የጉዞ መመርያ መሰረት ወደ እስራኤል ምንም ዓይነት ጉዞ እንዳያደርጉ አስጠንቅቋል።

    ኢራን ወደ እስራኤል ባስወነጨፈቻቸው ሚሳዔሎች አስር ሰዎች መሞታቸውን የእስራኤል ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

    በአሁኑ ወቅት ወደ እስራኤል የሚደረግ ጉዞ የማይቻል ነው ያለው ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ወደ አገሪቱ የሚገቡም ሆነ የሚወጡ በረራዎች መስተጓጎላቸውን ገልጿል።

    የዩኬ መንግሥት ኢራን ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ጥቃት አንደምትፈጽም ጠቅሶ በአገሪቱም የአስቸኳይ ጊዚ አዋጅ መታወጁን አስታውሷል።

    ይህ እስራኤል በኢራን የኒውክሌር እና ወታደራዊ ተቋማት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ተከትሎ የመጣ ነው።

    የእስራኤል የአየር ክልልም ለማንኛውም በረራ ዝግ ሆኗል።

    "ይህ በፍጥነት የሚለዋወጥ እና ከፍተኛ አደጋዎችን የሚያስከትል ሁኔታ መሆኑን እንገነዘባለን። ሁኔታው ​​በበለጠ፣ በፍጥነት እና ያለ ማስጠንቀቂያ የመባባስ አቅም አለው። አሁን ያለው ሁኔታ ከአገሪቱ ውጭ ያለውን የአየር ግንኙነት በማቋረጡ የመንገድ ትስስሮችንም ሊያስተጓጉል ይችላል።"

    ግጭቱ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚደረጉ የአየር በረራዎችን አቅጣጫ ሲያስቀይር የቴል አቪቭ አውሮፕላን ማረፊያ ዝግ ሆኗል።

    አየር መንገዶች ወደ ቴል አቪቭ የሚያደርጉትን በረራዎች የሰረዙ ሲሆን ኢራን በከተማው ደቡባዊ ክፍል በፈጸመችው ጥቃት ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር በኢራን ጥቃት የእስራኤል ሰላማዊ ዜጎች መሞታቸውን ተከትሎ ቴህራን "ከባድ ዋጋ ትከፍላለች" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

  12. ሦስተኛ ቀኑን ስለያዘው የእስራኤል እና ኢራን የአየር ጥቃት እስካሁን ምን እናውቃለን?

    የሁለቱ አገራት ግጭት ተባብሶ በእስራኤል እና ኢራን መካከል የአየር ጥቃት ልውውጡ ቀጥሏል።

    አዳዲስ ሁነቶች መከሰታቸውን ቀጥለዋል።

    ትናንት ምሽት ጥቃት ያደረሱት የኢራን ሚሳዔሎች በርካታ ጉዳት ማድረሳቸው ተሰምቷል።

    የእስራኤል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት በጥቃቱ ቢያንስ 10 ሰዎች ሲገደሉ፤100 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አሳውቋል።

    ከጥቂት ቀናት በፊት በመንግሥታቱ ድርጅት የኢራን አምባሳደር በእስራኤል ጥቃት 78 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

    ትናንትና የኢራን ብሔራዊ ቴሌቭዥን በቴህራን በአንድ የመኖሪያ አፓርትመንት ላይ በደረሰ ጥቃት 20 ሕፃናትን ጨምሮ 60 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።

    የኢራን ነዳጅ ሚኒስቴር በዋና ከተማው የሚገኘው የሳህራን ነዳጅ ማከማቻ በእስራኤል ጥቃት መመታቱን ገልጿል።

    የነዳጅ ማቀነባበሪያው በጥቃቱ የእሳት አደጋ ቢደርስበትም አሁን በስራ ላይ መሆኑ ተሰምቷል።

    በባትያም እስራኤል የሚገኘው ዘጋቢያችን ባለ 10ኛ ወለል ሕንፃ ፍርራሽ ውስጥ ሰባት ሰዎች መውጫ ማጣታቸውን ዘግቧል።

    ከዚህ አስቀድሞ የኢራን ሚሳኤል በአደጋ ዞን ውስጥ የሚገኝን ሕንፃ መምታቱን ተከትሎ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ሰምተናል።

    በኢራን የደረሰውን የጉዳት መጠን አናውቅም።

    ከእስራኤል የአየር ጥቃት በኋላ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ የሚያመላክቱ መረጃዎች አልሰማንም።

    የአየር ጥቃቶቹ በቴህራን መሰረተ ልማቶች እና የነዳጅ ማከማቻዎች ላይ ያደረሱትን ጉዳትም አናውቅም።

    በኢራን መንግሥት እግድ ምክንያት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ወደ አካባቢው መግባት አይችሉም።

    ይህም በእስራኤል ጥቃት የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ከባድ ያደርገዋል።

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን እስራኤል ላይ የሚደርሰው ጥቃት ላይ በማተኮር በእስራኤል ኢራን ላይ ስላደረሰችው ጥቃት አነስተኛ ሽፋን እየሰጡ መሆኑን የቢቢሲ ሞንተሪንግ ዘጋቢ ሳራ ጃላሊ ገልፃለች።

    ይህም ማለት ኢራን በእስራኤል እየፈፀመች ባለችው የአየር ጥቃት ተከታታይ መረጃዎችን እያገኘን ሲሆን፤ በአንፃሩ እስራኤል በኢራን ላይ በምታደርሰው ጥቃት ምን ያህል ጉዳት እየደረሰ እንደሆነ እየተገለፀ አይደለም።

  13. እስራኤል በኢስፋሃን የሚገኘውን የኢራን የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ደበደበች

    በማዕከላዊ ኢስፋሃን ግዛት የሚገኘው የኢራን የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት በእስራኤል ጥቃት እንደደረሰበት የኢራንባለስልጣን አረጋገጡ።

    የኢስፋሃን የፀጥታ ጉዳዮች ምክትል ገዥ አክባር ሳሊሂ እስካሁን በዋናው መሥሪያ ቤቱ ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተጎዳ ሰው ስለመኖሩ መረጃ አለመኖሩን ጠቅሰው የደረሰው የጉዳት መጠን እየተገመገመ ነው ብለዋል።

    ትናንት ምሽት የኢራን መገናኛ ብዙኃን እስራኤል በቴህራን ኖቦኒያድ አካባቢ በሚገኘው የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ላይ ጥቃት ማደረሷን ዘግበው ነበር።

  14. የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ የእስራኤልን ጥቃት እንድታወግዝ ጠየቁ

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰይድ አባስ አራግቺ እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ላደረሰችው ጥቃት "አሜሪካ ተባባሪ ናት" ካሉ በኋላ "ኃላፊነት መውሰድ አለባት" ብለዋል።

    ዩናይትድ ስቴትስ የእስራኤልን ጥቃት እንድታወግዝ የጠየቁት ሚኒስትሩ፣ አሜሪካ ለእስራኤል ይሁንታን እና ድጋፍ ባትሰጥ ጥቃቱ በፍፁም አይከሰትም ነበር ብለዋል።

    "አሜሪካ በዚህ ጥቃት ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላት ከተለያዩ አካላት መልእክቶች ደርሰውናል። ነገር ግን ይህንን ማስተባበያ አናምንም ከዚያ የሚቃረን ማስረጃ ነው ያለን" ሲሉ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው የሚቀጥለው ዙር የኒውክሌር ድርድር፣ ስምምነት ላይ ለመድረስ መንገድ ሊከፍት ይችል ነበር ሲሉ እስራኤል ውይይቱን አበላሽታለች ሲል ከስሰዋል።

  15. ለሦስተኛ ምሽት የቀጠለው የእስራኤል እና ኢራን የአየር ጥቃት የኒውክሌር ስምምነት ተስፋን አጨለመ

    በቴህራን የኒውክሌር መርሐ ግብር ዙሪያ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ስድስተኛ ዙር ድርድር ዛሬ ሊደረግ ነበር።

    እስራኤል ለሦስተኛ ምሽት በኢራን ላይ የአየር ጥቃት ስትፈፅም፤ ቴህራን በበኩሏ ሁለት የባላስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፋለች።

    ቴህራን በጥቃቶቹ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰባት መረጃ እያወጣች አይደለም። እስራኤል ግን በኢራን ጥቃት የተገደሉትን እና የቆሰሉትን እየቆጠረች ነው።

    የሕይወት መጥፋቱ የእስራኤል መንግሥት የኢራንን መከላከያ እና የምጣኔ ኃብት መሰረተልማቶች የበለጠ እንዲደበድብ ሊያደርግይችላል።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ኢራን ሚሳኤሎቿን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን ከቀጠለች ቴህራን “ትቃጠላለች” ያሉ ሲሆን፤ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይድ አባስ አርጋቺ በበኩላቸው ካለ ዋሽንግተን ድጋፍ እስራኤል ጥቃት አትፈፅምም ነበር ብለዋል።

    ይህም ኢራን በቀጠናው የአሜሪካን ዒላማዎች እንድትደበድብ በር ሊከፍት ይችላል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ይህን የምታደርግ ከሆነ የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ጠንካራ ኃይል ይወርድባታል ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል “በቀላሉ” ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

    ከሦስት ቀናት በፊት በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የኒውክሌር ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስፋ ነበር።

    አሁን ግን በእስራኤል እና ኢራን ፍንዳታዎች ሲሰሙ እና የጥንቃቄ ደወሎች ሲስተጋቡ ይህ ተስፋ ተበትኗል።

  16. ኢራን ምን ዓይነት ሚሳዔሎችን ታጥቃለች?

    በመካከለኛው ምሥራቅ እና በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ካሉ አገራት መካከል በወታደራዊ አቅሟ ኃያል የሆነችው ኢራን ወሳኝ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን በማምረት ትታወቃለች።

    ኢራን ከእስራኤል እና ከምዕራባውያን ጋር በሚወዛግባት የኒውክሌር ፕሮግራሟ በአካባቢው ስሟ በተደጋጋሚ ይነሳል።

    ከዚህ ባሻገርም ሩሲያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ጥቅም ላይ የሚውሉት አውዳሚ አጥፍቶ ጠፊ እና ከርቀት የሚታዘዘቱ ድሮኖችን የምታመርት ሲሆን፣ ረጅም ርቀት በመጓዝ ዒላማቸውን የሚመቱ ሚሳዔሎችንም በመሥራት ትታወቃለች።

    የእስራኤል ጥቃትን ተከትሎ ባለፉት ቀናትም ኢራን የተለያዩ የእስራኤል አካባቢዎችን በመምታት ውድመት ያደረሱ ሚሳዔሎችን ጥቅም ላይ አውላለች።

    ኢራን ምን ዓይነት እና ምን ያህል ርቀትን የሚያካልሉ ሚሳዔሎች አሏት?

  17. ኢራን በእስራኤል ላይ በፈጸመችው ጥቃት የወደሙ መኖርያ ቤቶችን የሚያሳዩ ምስሎች

    ኢራን በእስራኤል ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ የደረሰውን ውድመት የሚያሳዩ ምስሎች እየወጡ ነው።

    እስራኤል በኢራን ላይ ለፈፀመችው የአየር ጥቃት አፀፋ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ያስወነጨፈችው ቴህራን በአገሪቱ ሰሜናዊ እና ማዕከላዊ አካባቢዎች የሚገኙ የመኖሪያ ቤቶች መትታለች።

    የእስራኤል ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ቢያንስ 10 ሰዎች መሞታቸውንና ከ100 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል።

  18. እስራኤል ኢራናውያን ከወታደራዊ ተቋማት እንዲርቁ አሳሰበች

    የእስራኤልመከላከያ ሠራዊት ኢራናውያን ከወታደራዊ ተቋማት አካባቢ እንዲርቁ አሳሰበ።

    መከላከያ ሠራዊቱ በኤክስ ገጹ ላይ በለጠፈው ጽሑፍ “በወታደራዊ የጦር መሣሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎች ውስጥም ሆነ በአካባቢውእንዲሁም የድጋፍ ተቋሞቻቸው አካባቢ የሚገኙ ሰዎችወዲያውኑ ለቅቀው እንዲወጡ እና ተጨማሪ መግለጫ እስኪሰጥ ድረስ እንዳይመለሱ” ብሏል።

    “በእነዚህ ተቋማት አካባቢ መገኘታችሁ ሕይወታችሁን አደጋ ላይ ይጥለዋል” ይላል መግለጫው።

    ዛሬ ማለዳ የኢራን የመንግሥትመገናኛ ብዙኃን አገሪቱ በእስራኤል ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ሲዘግቡ፣ እስራኤልበኢራን ላይ ስለፈፀመችው ጥቃት ውሱን ሽፋን ሰጥቷል።

    በመንግሥት ቴሌቪዥን የቀረቡት የማለዳ ዜናዎች “የአይረን ዶምን ማውደም” ስለተባለው ጥቃት ሰፊ ሽፋንየሰጡ ቢሆንም፣ እስራኤል ኢራን ላይ ያደረሰችውን ጥቃት በጥቂቱ ጠቅሰው ስለደረሰው ጉዳት ምንም ሳይሉ አልፈዋል።

    ኢራን ውስጥ የሚዲያ ነፃነት ዝቅተኛ ሲሆን፣ መንግሥት እስራኤል በጥቃቱ ያደረሰችውን ጉዳት መጠን አሳንሶ ማቅረብ ይፈልጋል።

  19. "ኢራን እና እስራኤል በቀላሉ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ እንችላለን" -ትራምፕ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል እና በኢራን መካከል በተፈጠረው ግጭት አሜሪካ አለመግባቷን ተናግረዋል።

    ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ "ዩናይትድ ስቴትስ ዛሬ ምሽት በኢራን ላይ ከደረሰው ጥቃት ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራትም" ሲሉ ለጥፈዋል።

    ኢራን አሜሪካ እና አጋሮቿ የቴህራንን የአጸፋ ጥቃት እንድታከሽፍ እስራኤል እንዳይረዱ አስጠንቅቃለች።

    ትራምፕ አክለውም “በማንኛውም መንገድ፣ሁኔታ ወይም መጠን በኢራን ጥቃት ከደረሰብን የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይሎች አይታችሁት በማታውቁት ኃይል እና ጥንካሬ ምላሽ ይሰጣል” ብለዋል።

    “ሆኖም ኢራን እና እስራኤል በቀላሉ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ እና ይህን ደም አፋሳሽ ግጭት ማቆም እንችላለን” ብለዋል።

  20. ቅዳሜ ምሽት እስራኤል እና ኢራን አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል

    ቅዳሜ አመሻሹ ላይ እስራኤል እና ኢራን አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ የሚሳዔል ጥቃት ሰንዝረዋል።

    • የኢራን የነዳጅ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የእስራኤል ጥቃት በቴህራን የሚገኘው ሻህራን የነዳጅ ማምረቻ እና ማከማቻ ላይ ያነጣጠረ ነበር።ሚኒስቴሩ አክሎም በሁለቱም ቦታዎች ሁኔታው ​​በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጿል።
    • በደቡባዊ ቡሻህር ግዛት ሁለት ዋና ዋና የነዳጅ ማምረቻዎች በእስራኤል ጥቃት እንደ ደረሰባቸው ሚኒስቴሩ ገልጿል።
    • ኢራን በእስራኤል ላይ አዲስ ጥቃት በመሰንዘር ማዕከላዊ እና የአገሪቱን ሰሜናዊ ክፍል መትታለች።
    • የእስራኤል የዜና አውታሮች እንደዘገቡት በአገሪቱ ሰሜናዊሀይፋ አቅራቢያ በሚገኝ የመኖሪያ ሰፈር ላይ በደረሰ የሚሳዔል ጥቃት ቢያንስ አራት ሰዎች ተገድለዋል።
    • የእስራኤልየድንገተኛ አደጋ አገልግሎት በማዕከላዊ እስራኤል በደረሰው ጥቃት አራት ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጧል።
    • የእስራኤል ጥቃት በቴህራን በሚገኘው የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ አንደኛውን የቢሮ ሕንፃዎች እንዲሁም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የፈጠራ እና ምርምር ድርጅት በጥቂቱ ጎድቷል ሲል የኢራን ብሐየራዊ መገናኛ ብዙኃን እና የእስራኤል መከላከያ ገልጸዋል። እነዚህ ቦታዎች ዒላማ የተደረጉት ከኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮጀክት ጋር በመገናኘታቸው ነው ሲል የእስራኤል መከላከያ ማብራርያ ሰጥቷል።
    • ቅዳሜ ምሽት፣ የእስራኤል መከላከያ በምዕራብ ኢራን የሚገኘውን ከመሬት በታች ያለ ስፍራን ዒላማ በማድረግ "ምድር ለምድር የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን እና የክሩዝ ሚሳኤሎችን ለማከማቸት እና ለማስወንጨፍ ያገለግላል” ያላቸውን ስፍራዎች ደብድቧል።