በጋዛ ከተኩስ አቁም ፋታው በኋላ 200 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ
ለሰባት ቀናት የቆየውን የጋዛ የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ 200 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ15 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 6 ሺህ ህጻናት መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የቀጥታ ሽፋን
የጋዛ ሰርጥ በባለፉት 24 ሰዓታት
በእስራኤል እና በሐማስ የተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታ ሊጀመር የቀረው ከአንድ ሰዓት ያነሰ ጊዜ ቢሆንም በጋዛ የአየር ጥቃቱ ቀጥሏል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ የሚፈጽመውን የአየር እና የድሮን ጥቃቶቹን እንደቀጠለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከእገታ ቀድሞ ነጻ ማን ይውጣል የሚለው በሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የምስሉ መግለጫ, የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መጂድ አል-አንሳሪ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መጂድ አል-አንሳሪ ከሐማስ እገታ ቀድሞ ነጻ የሚወጣው የሚለየው በሰብዓዊነት ላይ በመመሥረት ይሆናሉ አሉ።
ቃል አቀባዩ ይህን ያሉት እስራኤል እና ሐማስ ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ከነገ አርብ ጠዋት 1 ሰዓት ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው።
እስራኤል ከጠዋቱ 1 ሰዓት ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚዘልቅ ጦርነት የማቆም ፋታ የምትሰጥ ሲሆን፣ ሐማስ ደግሞ ከሰዓት 10 ሰዓት ላይ 13 ታጋቾችን ይለቃል ተብሎ ይጠበቃል።
እስራኤልም እንዲሁም በእስር ቤት ይዛቸው የምትገኛቸውን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ እስረኞችን ትለቃለች።
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በመግለጫቸው ቀድመን ትኩረት የምንሰጠው ሴቶች እና ሕጻናትን በተቻለ መጠን ከጉዳት መጠበቅ ነው ያሉ ሲሆን ነገ ነጻ የሚሆኑት ታጋቾች ማንነት ይፋ ባይሆንም ሁሉም ግን ሕጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሐማስ እስራኤል ላይ መስከረም 26 ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ 1200 በላይ ሰዎች ገድሎ ከ230 ያላሱ ሰዎችን አግቶ መውሰዱ ይታወሳል።
ሐማስ ከሳምንታት በፊት በእስራኤል ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ በጋዛ ተይዘው ከነበሩ ታጋቾች መካከል 50 የሚሆኑት ተገድዋል ማለቱ ይታወሳል።
ኳታር የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ፋታ አርብ ጠዋት እንደሚጀምር አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, IDO DAN
የምስሉ መግለጫ, በሐማስ ታግተው ከሚገኙት መካከል የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑት ኤሬዝ እና ሳሃር ይገኙበታል እስራኤል እና ሐማስን ስታደራድር የቆየችው ኳታር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ለቀናት የሚቆየው ጦርነት የማቆም ፋታ ነገ አርብ በጋዛ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 1 ሰዓት እንደሚጀምር አስታወቀች።
ሐማስ ደግሞ በስምምነቱ መሠረት የመጀመሪያዎቹን 13 ታጋቾች አርብ ከሰዓት በኋላ 10 ሰዓት ላይ ይለቃል ብላለች።
በሐማስ ታግተው ከነበሩት መካከል ቀድመው የሚለቀቁት ሴቶች እና ሕጻናት እንደሚሆኑ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መጂድ አል-አንሳሪ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ታጋቾቹን ነገ ከሰዓት ከሐማስ የሚረከበው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
የእስራኤል አየር ኃይል በአንድ ቀን 300 የሐማስ ዒላማዎችን መምታቱን ገለጸ
የእስራኤል አየር ኃይል በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ 300 የሐማስ ዒላማዎችን በ24 ሰዓታት ውስጥ መደብደቡን ገለጸ።
ጦሩ በኤክስ ገጹ (የቀድሞው ትዊተር) ላይ እንዳለው ከሆነ በአየር ኃይሉ የተደበደቡት የሐማስ “ማዘዣ ጣቢያዎች፣ ዋሻዎች፣ ጦር መሳሪያ ማከማቻ ሰፍራዎች፣ ጦር መሳሪያ ማምረቻዎች እና ፀረ-ታንክ ሚሳኤል መተኮሻ ቦታዎች” ናቸው።
የእስራኤል ጦር መግለጫን ተከትሎ ሐማስ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
በእስራኤል-ሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ ውጊያ መቀጠሉ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ እስራኤል እና ሊባኖስ በሚዋሰኑበት ድንበር አቅራቢያ በእስራኤል ጦር እና በሄዝቦላህ መካከል የሚደረገው ውጊያ መቀጠሉ ተገለጸ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ ጦራቸው ፀረ-ታንክ ቡድን ላይ እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ከምድር ወደ ሰማይ የሚወነጨፍ ሚሳኤል በሌባኖስ የአየር ክልል ውስጥ እየበረረ የነበረ የእስራኤል የጦር አውሮፕላን ላይ ተተኩሶ የነበረ ቢሆንም፣ የእስራኤል ፀረ-ሚሳኤል ሥርዓት ጥቃቱን ማክሸፉ ተመላክቷል።
ይህን ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ የሄዝቦላሀ ዒላማዎችን መደብደባቸው ተገልጿል።
ሄዝቦላህ በበኩሉ ተዋጊዎቹ አል-ማርጅ በተሰኘ አካባቢ በአንድ ቦታ ተሰባስበው የነበሩ የእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አስታውቋል።
የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ ዳይሬክተር በእስራኤል መከላከያ በቁጥጥር ስር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ ዳይሬክተር በእስራኤል መከላከያ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያ ተናገሩ። ዳይሬክተሩ አቡ ሳላሚያ ከሆስፒታሉ የሚወጡ ህመምተኞችን አጅበው ባሉበት ሰዓት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአልሺፋ የአጥንት ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር አድናን አል ቡርሽ ገልጸዋል።
የእስራኤል መከላከያ በጉዳዩ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።እስራኤል የሐማስ እዝ በሆስፒታሉ ስር አለ በሚል በአልሺፋ ላይ ወረራ በመፈጸም ተቆጣጥራው ትገኛለች።
ሐማስም ሆነ የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች ይህንን ክስ አይቀበሉትም። የእስራኤል ጦር ባለፈው ሳምንት ሆስፒታሉን ከተቆጣጠረ በኋላ የሐማስ ዋሻ ነው ያለውን እና 55 ሜትር እርዝማኔ አለው ያለውቪዲዮ አሳይቷል።
ህሙማንን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ሆስፒታሉን ለቀው እንዲወጡ በእስራኤል ትዕዛዝ ተሰጥቶናል በሚል በእግራቸው ሸሽተዋል። እስራኤል ትዕዛዝ አልሰጠሁም ስትል አስተባብላለች።
እስራኤል በራፋህ ያደረሰቻቸው የአየር ጥቃቶች በምስል
እስራኤል በግብጽ እና ጋዛ የድንበር ማቋረጫ ራፋህ የአየር ጥቃቶችን ፈጽማለች።
በኻን ዩኒስ አቅራቢያ የምትገኘው ራፋህ እስራኤል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ሰሜናዊ ጋዛን ለቀው እንዲሸሹባት ከተመረጡት ከተሞች አንዷ ናት።
የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ ባለፉት 24 ሰዓታት በፈጸመው ጥቃቶች 300 የሐማስ ኢላማዎችን መትቻለሁ ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጋዛ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት የዘገየው ከታጋቾች ዝርዝር ጋር በተያያዘ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዛሬ፣ ሐሙስ ረፋድ ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ሲጠበቅ የነበረው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ለመዘግየቱ ከታጋቾች ዝርዝር ጋር በተያያዘ መሆኑን የፍልስጤም ባለስልጣናት ገለጹ።
የዘገየውም በመጨረሻዋ ሰዓት መሆኑንም ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
የትኞቹ ታጋቾች ይለቀቁ? እንዴት? በሚለውም ዝርዝር ምክንያትም መራዘሙ ተነግሯል። ጊዜያዊ የተኩስ አቁሙም አርብ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችልም የእስራኤል መንግሥት ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቀረውም ጉዳይ የሎጂስቲክ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
ኳታር በበኩሏ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መቼ እንደሚጀምር በቀጣዩ ሰዓታት እንደሚገለጽ አስታውቃለች።
የኳታር መንግሥት ቃለ አቀባይ እንደተናገሩት ከእስራኤል እና ሐማስ ጋር የተደረገው ስምምነት የተያያዘው ውይይት ቀጥሏል ብለዋል። በነዚህም ውይይቶች ላይ ግብጽ እና አሜሪካ የሚሳተፉ ሲሆን “ጦርነቱ ጋብ የሚልባቸውን ቀናት ፈጠን ብሎ የማስጀመር እንዲሁም ሁለቱ ወገኖች ስምምነቱ እንዲያከብሩ የሚያስፈልጉ ጉዳዮችም ውይይቱ ቀጥሏል” ተብሏል።
እስራኤል በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ በፈጸመችው ጥቃት የአንድ ቤተሰብ 52 አባላት ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
እስራኤል ረቡዕ በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ በፈጸመችው ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አምሳ ሁለት አባላት መገደላቸውን የፍልስጤም ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ያለው የማያባራ የአየር ጥቃት ዛሬ ረፋድ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ በነበረው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ጋብ እንደሚል ተጠብቆ ነበር። ነገር ግን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ አልሆነም፤ መቼ እንደሚጀምርም ግልጽ አልሆነም።
የፍልስጤም አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሪያድ አል ማሊኪ በስደተኞቹ መጠለያ በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት 52 ሰዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውንም ገልጸዋል።
“ዛሬ ጥዋት ብቻ በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ የኳድራ ቤተሰብ 52 አባላት ለዘር እንዳይተርፉ ሆነው ተፈጅተዋል” ብለዋል።
ቢቢሲ ይህንን በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም። የፍልስጤም አስተዳደር መቀመጫውን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ያደረገ ነው።
የጋዛው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚዘገይ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጋዛው ጦርነት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ዛሬ ረፋድ ላይ ተግባራዊ እንዲደረግ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ስምምነት ላይ ቢደረስም ቢቢሲ እንደሚዘገይ ከእስራኤል መንግሥት ምንጭ መረጃ ሰምቷል።
በጋዛ የታገቱት ከአርብ በፊት እንደማይለቀቁ የእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተደረገው ስምምነት ላይ ንግግሮች መቀጠላቸውን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ብሔራዊ የጸጥታ አማካሪ ትዛኪ ዘኔግቢ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ቀደም ብሎ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የመጀመሪያዎቹ ታጋቾች ሐሙስ እንደሚለቀቁ አስታውቆ ነበር።
በስምምነቱ መሰረትም በሐማስ የተወሰዱ 50 ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን በልውውጡም እስራኤል ካሰረቻቸው ፍልስጤማውያን ውስጥ 150 ሴቶች እና ህጻናት የሚለቀቁ ይሆናል።
ሰባተኛ ሳምንቱን በያዘው የጋዛው ጦርነት ከ13 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከነዚህም በርካቶቹ ህጻናት መሆናቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከእስራኤል በኩል ደግሞ 1 ሺህ 200 ተገድለዋል።
የሆሊውዷ ተዋናይት እስራኤልን ‘በማውገዟ’ ከስክሪም ተከታታይ ፊልም ተባረረች
‘የፍልስጤማውያንን ሕጻናት ግድያን የደገፉት’ የኦባማ የቀድሞ ረዳት በቁጥጥር ስር ዋሉ
ለአራት ቀናት የሚቆየው ተኩስ አቁም ዛሬ ሐሙስ ረፋድ አራት ሰዓት ይጀምራል

የፎቶው ባለመብት, AFP
የምስሉ መግለጫ, ራፋህ ውስጥ ከተፈጸመ የአየር ጥቃት በኋላ ከፍርስራሽ ስር በሕይወት ያሉ ሰዎችን ለመፈለግ የሚጥሩ ሰዎች በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ለአራተ ቀናት የሚቆየው የተኩሰ አቁም ዛሬ ሐሙስ ረፋድ አራት ሰዓት ላይ እንደሚጀምር ሐማስ አስታወቀ።
ቢቢሲ ከምንጮቹ ማረጋገጥ እንደቻለው ከአንድ ወር በላይ እየተካሄደ ያለውን ውጊያ ለአራት ቀናት ጋብ ለማድረግ የተደረሰው ስምምነት ሐሙስ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል።
የተኩስ አቁሙ እውን ከሆነ ከሰዓታት በኋላ ደግሞ በሐማስ እጅ ከሚገኙት ታጋቾች የመጀመሪያዎቹ ከሰዓት በኋላ ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሐማስ ፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ ሙሳ አቡ ማርዙክ ለአል-ጃዚራ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ለቀናት የሚዘልቀው ውጊያ ጋብ የማድረግ ስምምነት የመጀመሪያዎቹ ታጋቾች ከመለቀቃቸው ከሰዓታት በፊት ተግባራዊ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።
የግብፅ የደኅንነት ምንጮች ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተኩስ ማቆሙ ሐሙስ ረፋድ አራት ሰዓት ላይ ተግባራዊ እንዲሆን አደራዳሪዎች መፈለጋቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም ምክንያቱ ታጋቾቹን ከመልቀቁ በፊት ሐማስ “ጥቂት ሰዓታት” እንደሚያስፈልገው በመግለጹ መሆኑነ ተናግረዋል።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ውጊያው ጋብ ማለት የሚጀምረው “ሐሙስ በሆነ ሰዓት ላይ” እንደሆነ ለሮይተርስ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የዜና ወኪሉ የአስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊ ኮኽን ምንም እንኳን ትክክለኛውን ሰዓት ከመግለጽ ቢቆጠቡም እስራኤል የመጀመሪያዎቹን ነጻ የሚወጡ ታጋቾች ሐሙስ ዕለት እንደሚቀበሉ መናገራቸውን ዘግቧል።
ይህ ጦርነት ሳይሆን ሽብርተኝነት ነው፡ ፖፕ ፍራንሲስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የምስሉ መግለጫ, ፖፕ ፍራንሲስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ የሆኑት ፖፕ ፍራንሲስ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት ጦርነት ሳይሆን “ሽብርተኝነት” ነው አሉ።
ጳጳሱ ይህንን የተናገሩት በሐማስ የታገቱ ሰዎች ቤተሰቦችን እና በጋዛ ውስጥ የሚኖሩ ዘመዶች ያሏቸውን ሰዎች በተናጠል አግኝተው ባነጋገሩበት ወቅት ነው።
ፖፕ ፍራንሲስ አስካሁን እየተካሄደ ያለው የእስራኤል-ሐማስ ግጭት ከጦርነት በላይ በመሆን “የሽብር ድርጊት” እየሆነ ነው ብለዋል።
በዚህም ሁለቱም ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን “እየተሰቃዩ ነው” ሲሉ ጦርነቱ በሕዝቡ ላይ ያስከተለውን ጉዳት በጥብቅ አውግዘዋል።
ቫቲካን ውስጥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚገኘው መኖሪያቸው በርካታ ሰዎችን በየሳምንቱ ከሚያገኙበት ሥነ ሥርዓት በኋላ ጳጳሱ ባደረጉት ንግግር “ሁለቱም ወገኖች እንደተሰቃዩ ሰምቻለሁ፣ በጣም ተሰቃይተዋል” ብለዋል።
ጨምረውም “ሰላም እንዲሰፍን ወደፊት እንጓዝ. . . ሁላችሁም ተባረኩ” ሲሉ ለሰላም ጥሪ አቅርበዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ ባልደረባቸው ከአራት ቤተሰቧ ጋር መገደሏን አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Tedros Adhanom Ghebreyesus
የምስሉ መግለጫ, ዲማ አለሃጅ ከስድስት ወር ልጇ፣ ከባለቤቷ እና ከሁለት ወንድሞቿ ጋር ትናንት ተገድላለች። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም አንድ ባልደረባቸው ከአራት የቤተሰብ አባሎቿ ጋር ጋዛ ውስጥ መገደሏን አስታወቁ።
ዲማ አልሃጅ የተባለችው የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባ ከስድስት ወር ልጇ፣ ከባለቤቷ እና ከሁለት ወንድሞቿ ጋር ትናንት ማክሰኞ መገደሏን ገልጸዋል።
“ሐዘናችንን የምገልጽበት ቃላት የለኝም” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ።
ዶ/ር ቴድሮስ ጨምረውም ከመስከረም 26 ወዲህ 108 የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች በጋዛ መገደላቸውን ገልጸዋል።
ደቡብ አፍሪካ የእስራኤል ኤምባሲ እንዲዘጋ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ እንዲቋረጥ ወሰነች
እስራኤል ከእስር የምትለቃቸውን ፍልስጤማውያንን ዝርዝር አወጣች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል እስር ቤት (ፋይል ፎቶ) እስራኤል ከሐማስ ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ከእስር የምትለቃቸውን 300 ፍልስጤማውያንን ዝርዝር ይፋ አደረገች።
በእስራኤል የፍትሕ ሚኒስቴር ገጽ ላይ የወጣው ዝርዝር የታሳሪዎችን ስም፣ እድሜ እና ለእስር ተዳርገውበታል የተባለው የሕግ ጥሰትን ዘርዝሯል።
አብዛኞቹ ታሳሪዎች ከ14 እስከ 18 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ድንጋይ መወርወር፣ ከሐማስ ጋር ግንኙነት መፍጠር ወይም የሐማስን ጥቃት ማወደስ ከሚሉ ክሶች አንስቶ ቦምብ መወርወር እንዲሁም የግድያ ሙከራ መፈጸም የሚሉ ክሶች የቀረቡባቸው ናቸው።
እስራኤል 300 ፍልስጤማውያንን እለቃለሁ ብትልም በስምምነቱ መሠረት በመጀመሪያው ዙር የሚለቀቁት እስረኞች 150 ሰዎች ናቸው።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች ከ7ሺህ ያላነሱ ፍልስጤማውያን በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ የገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 200 ሴቶች እና 60 ልጆች ይገኙባቸዋል።
የሂዩማን ራይትስ ዋች ዳይሬክተር ሳሪ ባሺ የፍልስጤማውያን ታዳጊዎች ጉዳይ በእስራኤል ወታደራዊ ሕግ እንዲታይ በመደረጉ ወላጆች ወይም ጠበቆች በሌሉበት እንዲመረመሩ እና ለተራ ጥፋቶች ለረዥም ሰዓት በእስር እንዲቆዩ ይደረጋሉ ብለዋል።
ኳታር የሐማስ እና እስራኤል የደረሱት ስምምነት መቼ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይፋ ይደረጋል አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ስምምነት እንዲደርስ ያስቻለችው ኳታር ሐማስ እና እስራኤል የደረሱት ስምምነት መቼ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይፋ አድርጋለች።
በዚህም የባሕረ ሰላጤዋ አገር “የተኩስ አቁም የሚጀምርበት ጊዜ በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ውስጥ ይፋ ይሆናል” ብላለች።
የተኩስ አቁሙ ለአራት ቀናት ይቆያል ከማለት ባለፈ “ሊራዘም ይችላል” ስትል አስታውቃለች።
ሐማስ 150 ፍልስጤማውያን ከእስራኤል እስር ነጻ ይወጣሉ አለ
ሐማስ ከእስራኤል ጋር በደረሰው ስምምነት መሠረት 150 ፍልስጤማውያን ከእስራኤል እስር ቤት ይወጣሉ አለ።
ሐማስ ከእስራኤል አግቶ ከያዛቸው መካከል 50 ሰዎችን ለመልቀቅ መስማማቱ ይታወሳል። 50ዎቹ ታጋቾች በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ ባሉ 150 ፍልስጤማውያን ሴቶች እና ህጻናት ምትክ እንደሚለቀቁ ገልጿል።
በስምምነቱ መሠረት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰብዓዊ እርዳታ፣ የህክምና ቁሳቁስ እና ነዳጅ የጫኑ የጭነት መኪናዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ያስችላል ሲል ሐማስ ገልጿል።
እስራኤል ለጦርነቱ ፋታ በምትሰጥበት ወቅት በጋዛ ማንንም እንደማታጠቃ እና እንደማታሰር መግለጿን መግለጫው አክሏል።
በአራቱ ቀናት በደቡባዊ ጋዛ የአየር ትራፊክ ሙሉ በሙሉ ይቆማል። በሰሜን ጋዛ ደግሞ ለስድስት ሰዓታት እንደሚቆም ተናግሯል።
ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካን ጨምሮ በበርካታ አገራት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ሐማስ መስከረም 26 አሰቃቂ ጥቃት ከመፈጸም ባለፈ ወደ 230 የሚጠጉ ሰዎችን አፍኖ ወስዷል።
