በጋዛ ከተኩስ አቁም ፋታው በኋላ 200 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ

ለሰባት ቀናት የቆየውን የጋዛ የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ 200 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ15 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 6 ሺህ ህጻናት መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የጋዛ የተኩስ አቁም ፋታ እንደሚቀጥል የእስራኤል ጦር አስታወቀ

    የእስራኤል ጦር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ስድስተኛ ቀኑን የያዘው የተኩስ አቁም ፋታ እንደሚቀጥል የእስራኤል ጦር አስታውቋል።

    ሐማስ በበኩሉ የተኩስ አቁም ፋታው ለአንድ ቀን እንደተራዘመ አስታውቋል።

    ሐማስ ለሰባተኛ ቀን የተኩስ አቁም ፋታውን ለማራዘም ስምምነት ላይ መደረሱንም ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የእስራኤል ጦር የተራዘመው የተኩስ አቁም ፋታ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አልገለጸም።

    ዛሬ ይጠናቀቃል የተባለው የተኩስ አቁም ፋታ ' ተጨማሪ ታጋቾችን የማስለቀቁን ሂደትም ለማስቀጠል አሸማጋዮቹ ካደረጉት ጥረት ጋር ተያይዞም ይቀጥላል" ተብሏል።

    በስምምነቱ መሰረት ሐማስ የወሰዳቸውን ታጋቾች የሚለቅ ሲሆን በልውውጡም እስራኤል የያዘቻቸውን ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማዊ እስረኞችን ትፈታለች።

  2. ስድስተኛ ቀኑን በያዘው የተኩስ አቁም ፋታ የተከሰቱ ዋና ዋና ጉዳዮች

    ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልብ ፍልስጤማዊ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሐማስ እና እስራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል። በባለፉት ስድስት ቀናት ሐማስ ወስዷቸው የነበሩ ታጋቾች ሲለቀቁ በልውውጡ እስራኤል ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈትታለች። ለሁለተኛ ጊዜ የተራዘመው የተኩስ አቁም ፋታ ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን ለማራዘምም ንግግሮች እየተደረጉ ይገኛሉ።

    በባለፉት ሰዓታት ከተከሰቱ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል፦

    ተጨማሪ ታጋቾች ተለቀው ወደ እስራኤል ተመልሰዋል

    • ሁለት እስራኤላዊ ሩሲያውያን ታጋቾች በትናንትናው ዕለት ተለቀው ወደ እስራኤል ተመልሰዋል።
    • በኋላም ሌሎች 10 እስራኤላውያን እንዲሁም አራት የታይላንድ ዜጎች ተፈትተው በዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አማካኝነት ወደ እስራኤል ተወስደዋል።
    • እስራኤል በልውውጡ 30 ፍልስጤማውያን እስረኞች መልቀቋን አስታውቃለች። ኳታር ቀደም ሲል የሚለቀቁት እስረኞች 16 ህጻናት እንዲሁም 14 ሴቶች መሆናቸውን አስታውቃለች።

    በዌስት ባንክ ሁለት ልጆች ተገደሉ

    • እስራኤል በወረራ በያዘቻት ዌስት ባንክ ጄኒን ከተማ ሁለት ፍልስጤማውያን ህጻናት ተገድለዋል። አዳም አል ጉል የስምንት ዓመት ልጅ ሲሆን ባሴል አቡልዋፋ 14 ዓመቱ ነበር።
    • የፍልስጤም ባለስልጣናት እንደገለጹት ህጻናቱ የተገደሉት በእስራኤል ወታደሮች ነው። እስራኤል በበኩሏ ጦሯ ፈንጂ ወርውረዋል ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ እንደተኮሰና ሁለት "ከፍተኛ የሽብር አቀናባሪዎችን" ገድያለሁ ብላለች። የህጻናቱን ግድያ በተመለከተ የሰጠችው አስተያየት የለም።

    በእገታ ላይ የነበረው ጨቅላ እጣ ፈንታ

    • ሐማስ በእገታ ላይ የነበረው የ10 ወር ጨቅላ እስራኤል በፈጸመችው የጋዛ የአየር ጥቃት መገደሉን አስታውቋል። ከጨቅላው በተጨማሪ ታላቅ ወንድሙ እና እናቱም ተገድለዋል ብሏል።
    • እስራኤል በበኩሏ ይህንን እያጣራሁ ነው ብላለች። ማክሰኞ ዕለት ሐማስ ሁለት ሌሎች ትንንሽ ልጆች ለሌላ "እስላማዊ አንጃ ቡድን" እንደሰጣቸው አስታውቋል።
  3. የሰሜናዊ ጋዛ አካባቢዎች ለመኖሪያነት ከማይሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡ የመንግሥታቱ ድርጅት

    የፈራረሱ ሕንጻዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ባለፉት ሳምንታት በእስራኤል ያልተቋረጠ ጥቃት ምክንያት ከባድ ውድመት በደረሰባት በጋዛ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ ያሉ ከፊል አካባቢዎች በአሁኑ ጊዜ ለመኖሪያነት እንደማይሆኑ የመንግሥታቱ ድርጅት ገለጸ።

    በጋዛ የድርጅቱ የስደተኞች ጉዳይ ዳይሬክተር የሆኑት ቶማስ ዋይት ይህንን ያሉት በሰሜናዊ የጋዛ ክፍል እና በጋዛ ከተማ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎችን ከጉብኙ በኋላ ነው።

    እስራኤል የእግረኛ ሠራዊት ዘመቻ በጋዛ ላይ በጀመረችበት ጊዜ በሰሜናዊ ጋዛ የሚገኙ ሲቪሎች ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ ካዘዘች በኋላ በምድር እና በአየር ከባድ ጥቃቶችን ስትፈጽም መቆየቷ ይታወቃል።

    ዳይሬክተሩ ለቢቢሲ ራዲዮ 4 እንደተናገሩት “በደህናው ጊዜ ሞቅ ያለ የሕዝብ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ከተማ፣ ዛሬ መንገዶቿ በፍርስራሾች ተሸፍነዋል” ብለዋል።

    ጨምረውም በከተማዋ ዳርቻዎች በሚገኙ አካባቢዎች ያሉ ሁሉም ሕንጻዎች ፈራርሰው በመንገዶች ላይም የሚንቀሳቀስ ሰው እንደማይታይ ተናግረዋል።

    ቶማስ ዋይት በጋዛ ውስጥ በተመለከቷቸው እና ውስን ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች “ጥቂት ሰዎች ከሱቆች በር ላይ እና ከቤታቸው ደጅ ተቀምጠው” በማየታቸው የሕይወት ምልክቶች ቢመለከቱም ከተማዋ “ጸጥ ረጭ” እንዳለች ገልጸዋል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት ቡድን በሰሜናዊ ጋዛ ወደሚገኘው ጃባሊያ የእርዳታ አቅርቦት ለማድረስ የተጓዘ ሲሆን፣ “በመጨረሻም አንዳች አይነት ድጋፍ በማግኘታቸው ነዋሪዎች ታላቅ እፎይታ ተሰምቷቸዋል” ብለዋል ዳይሬክተሩ።

    በሰሜናዊ ጋዛ ባደረጉት ጉብኝትም “ከፍተኛ መጠን ያለው ውድመት የደረሰባቸው” የተወሰኑ አካባቢዎች ለሰዎች መኖሪያ መሆን ከማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደደረሱ አመልክተዋል።

    በአንጻራዊነት ደግሞ በጥቃቶቹ “ያልተነኩ የሚመስሉ” ሌሎች አካባቢዎች ቢኖሩም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና ውስን የውሃ አቅርቦት ብቻ ስላላቸው ችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    በተጨማሪም “ሁሉም መደበኛ አገልግሎቶች እና እንቅስቃሴዎች…ጋዛ ውስጥ የሉም” ብለዋል የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣን።

  4. ሳምንታትን በፍርሃት፣ በእንግልት እና በረሃብ ያሳለፉት የሐማስ ታጋቾች ታሪክ

  5. የጊዜያዊ ተኩስ አቁም ስምምነቱ የሚራዘምበት ዕድል ሰፊ ነው

    ለሁለት ቀናት የተራዘመው የተኩስ አቁም ፋታ ማክሰኞ ጀምሯል።

    በሁለቱ ወገኖች ስምምነት ሌላ የ48 ሰዓታት የተኩስ አቁም ፋታ የመራዘም ጥሩ ዕድል እንዳለ እየተነገረ ነው።

    አነሰም በዛም በዕቅዱ መሠረት እየተጓዘ የሚገኘውን ስምምነት ሁለቱም ወገኖች የሚፈልጉት እንደሆነ ግልጽ ነው።

    የሚካሄዱት ድርድሮች የደረሱበትን ሁኔታ ማወቅ ባይቻልም ድርድሩ እየተካሄደ ይገኛል። ስምምነቱ እንዲቀጥል የሚደረገው ጥረት ጠንካራ ሆኗል።

    ይህ ሂደት ሲጠናቀቅ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወታደሮቻቸው በጋዛ ውስጥ “ሙሉ ኃይል” እንዲጠቀሙ ማቀዳቸውን ስለመናገራቸው መዘንጋት የለብንም።

    በእስራኤል ጋዛ ድንበር የሚገኝ ታንክ ላይ የሚራመድ የእስራኤል ወታደር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  6. ከእስራኤል እስር ነጻ የወጣት ታዳጊ “ድብደባ ተፈጽሞብኛል” አለ

    ከእስራኤል እስር ቤቶች ነጻ ከወጣቱ መካከል አንዱ የሆነው የ14 ዓመት ታዳጊ፤ በእስር ላይ ሳለ ድብደባ ይፈጸምበት እንደነበረ ተናገረ።

    አሕመድ ናዋፍ ሳላኢማ የተባለው ታዳጊ ለአል ጃዚራ ሲናገር “በመጀመሪያው ቀን ጦርነት ብዙ ድብደባዎች ነበሩ፤ ሴት ታሳሪዎች ሲደበደቡ ነበር” ብሏል።

    ታዳጊው ከእስር ከተለቀቀ በኋላ በቤቱ እንዲቀመጠ እና ነጻ መውጣቱን በማስመልከት ደስታውን በአደባባይ እንዳይገልጽ ማስጠንቀቂያ ጭምር እንደተሰጠው ተናግሯል።

    “ደስታ መግለጽ እንደማይቻል ተነግሮኛል፤ ከቤት መውጣት አልችልም። ይህን ሕግ ከጣስኩ ተመልሼ እታሰራለሁ” ብሏል።

    ቢቢሲ የዚህን ሪፖርት ትክክለኛነት ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም። እስራኤል የታሳሪዎችን መብት እጠብቃለሁ ትላለች።

  7. ሐማስ ከእስራኤል አፍንጫ ስር ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ እንዴት ኃይሉን መገንባት ቻለ?

  8. በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት ከ14ሺህ በላይ መሆኑ ተገለጸ

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በሐማስ የሚተዳደረው ጤና ሚንስቴር በእስራኤል የአየር፣ የምድር እና የባሕር ጥቃቶች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ14ሺህ 500 በላይ መሆኑን አስታወቁ።

    የጋዛ ባለስልጣናት መሞታቸው ከተረጋገጡ ሰዎች በተጨማሪ እስካሁን ድረስ 1ሺህ 500 የሚሆኑ ሰዎች አድራሻ መጥፋቱን አስታውቀዋል።

    መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ማለዳ ላይ ሐማስ ወደ እስራኤል ድንበር ተሻግሮ ድንገተኛ ጥቃት ከከፈተ በኋላ እስራኤል ጠንካራ የአጸፋ እርምጃ መውሰድ መጀመሯ ይታወሳል።

    ሐማስ እስራኤላ ላይ ባደረሰው ጥቃት ከ1ሺህ 200 ሰዎች በላይ ገድሎ ወደ 240 የሚጠጉ ሰዎችን አግቶ ወስዶ ነበር።

  9. በሐማስ ታግተው የነበሩ 12 ሰዎች ሲለቀቁ 30 ፍልስጤማውያን ከእስር ነጻ ወጡ

    ከእገታ የተለቀቁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል በመስከረም 26ቱ ጥቃት ታግተው ከነበሩት ሰዎች መካከል 12 ሰዎች ነጻ መውጣታቸውን አስታወቀች።

    10 እስራኤላውያን እና 2 የታይላንድ ዜጎች ከሐማስ እገታ ነጻ ወጥተው እስራኤል ድንበር መግባታቸውን የአገሪቱ ጦር አስታውቋል።

    እስካሁን በጋዛ ታግተው የነበሩ እና ነጻ የወጡ ሰዎች ቁጥር 81 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 61 እስራኤላውያን ናቸው።

    እስራኤል በበኩሏ 30 ፍልስጤማውያንን ከእስር የለቀቀች ሲሆን ይህም አጠቃላይ ቁጥሩን ወደ 180 ከፍ አድርጎታል።

    እስካሁን ድረስ ከእስራኤል እስር ቤቶች ነጻ የወጣቱ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ወንዶች ናቸው።

  10. እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ተጥሶ ጥቃት እንደተፈጸመባት አስታወቀች

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተጥሶ አባላቱ አቅራቢያ ሦስት ፍንዳታዎች ማጋጠማቸውን አስታወቀ።

    ጦሩ ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ላይ በሰሜን ጋዛ ባጋጠመው ፍንዳታ በርካታ የሠራዊቱ አባላት ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።

    ሐማስ በበኩሉ ፍንዳታው ያጋጠው የእስራኤል ጦር የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣሱ ነው ብሏል።

    የሐማስ የጦር ክንፍ አል-ቃስም ብርጌድ ቃል አቀባይ፣ ሐማስ ለስምምነቱ ተገዢ መሆኑን ጠቅሰው አደራዳሪዎች ግን እስራኤል በምድር እና በአየር ተኩስ እንድታቆም ጫና ማሳደር አለባቸው ብለዋል።

    ዛሬ ረፋድ ላይ በሰሜን ጋዛ ሰማይ ላይ ትልቅ ጭስ ታይቶ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ጭስም በምን ምክንያት እንደተፈጠረ እስካሁን ድረስ ግልጽ አይለም።

    ቀደም ስል ሲወጡ የነበሩ ሪፖርቶች የተኩስ አቁም ስምምነቱ መራዘሙን ያላወቁ ፍልስጤማውያን ቡድኖች በእስራኤል ወታደሮች ላይ ተኩስ ከፍተዋል ብለው ነበር።

  11. የሞሳድ እና የሲአይኤ ኃላፊዎች ኳታር ይገኛሉ

    የእስራኤል እና የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ኃላፊዎች በቀጣይ ሊደረግ ስለሚችል የተኩስ አቁም ስምምነት ለመወያየት ኳታር ይእንደሚገኙ ተነገረ።

    ሮይተርስ እና የፈረንሳይ የዜና ወኪል፣ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገቡት የእስራኤሉ ሞሳድ እና የአሜሪካ ሲአይኤ የስለላ ተቋማት ኃላፊዎች ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ይገናኛሉ።

    በኳታር አደራዳሪነት ሐማስ እና እስራኤል ለአራት ቀናት ተኩስ ለማቆም የደረሱት ስምምነት ሰኞ ዕለት ለሁለት ተጨማሪ ቀናት ተራዝሟል።

    በዚህ አዎንታዊ ለውጥ ላይ ለተጨማሪ ቀናት ለጦርነቱ ፋታ ለመስጠት ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

    በዚህ ውይይት ላይ የግብፅ ባለሥልጣናትም ተሳታፊ ስለመሆናቸው ተመላክቷል።

  12. በጋዛ ከቦምብ ይልቅ ሕክምና ሳያገኙ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊበልጥ ይችላል ተባለ

    በጋዛ ያሉ ሕጻናት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በጋዛ ያሉ ሕጻናት

    የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ በጥቃቶች ከሚገደሉ ሰዎች በላይ ሕክምና ሳያገኙ ሕይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል አለ።

    ድርጅቱ ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጠው በጋዛ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች በልጆች እና ጨቅላዎች ላይ የተቅማጥ በሽታ እና የመተንፈኛ ኢንፌክሽን መበራከቱን ተከትሎ ነው።

    በእነዚህ በሽታዎች እየተጠቁ ላሉት ምንም አይነት የሕክምና እርዳታ እየተሰጠ አለመሆኑን ድርጅቱ ገልጾ የካንሰር፣ የልብ ወይም የስኳር ህመምተኞችም ምንም አይነት የጤና ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑንን ገልጿል።

    የተመድ የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) በበኩሉ በጦርነቱ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ የቆሰሉ ሕጻናት በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች እና ሜዳዎች ላይ ወድቀው ይገኛሉ ብሏል።

    ሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ጦርነቱን ዳግም መጀመር ጨርሶ መታሰብ የለበትም የሚሉ ሲሆን፣ ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት በሁለቱ ተዋጊዎች መካከል እንዲደረግም ጠይቀዋል።

  13. ለጦርነት ፋታ ለመስጠት ስምምነት ቢኖርም በጋዛ ሰማይ ላይ ጭስ ታየ

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, AFP TV

    ሐማስ እና እስራኤል ለጦርነቱ ፋታ ለመስጠት የደረሱትን ስምምነት ቢያራዝሙም በጋዛ ሰማይ ላይ ትልቅ ጭስ ታይቷል።

    አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መራዘሙን ያላወቁ ፍልስጤማውያን ቡድኖች በእስራኤል ወታደሮች ላይ ተኩስ ሳይከፍቱ አልቀሩም።

    በኳታር አደራዳሪነት ሐማስ እና እስራኤል ለአራት ቀናት ተኩስ ለማቆም የደረሱት ስምምነት ሰኞ ዕለት ለሁለት ተጫማሪ ቀናት መራዘሙ ይታወሳል።

    ለተጨማሪ 48 ሰዓታት ተኩስ ለማቆም በተደረሰው ስምምነት ወቅት ሦስት ፍልስጤማውያን በአንድ እስራኤላዊ ለመለወጥ ሐማስ እና እስራኤል ተስማምተዋል።

  14. ሐማስ ሁሉም ታጋቾች በቁጥጥሩ ስር እንደማይገኙ አስታወቀ

    በቅርቡ ከእገታ ነጻ የወጣ ታዳጊ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በቅርቡ ከእገታ ነጻ የወጣ ታዳጊ

    ሐማስ በመስከረም 26ቱ ጥቃት የታገቱት ሰዎች በሙሉ በቁጥጥሩ ስር እንደማይገኙ አስታወቀ።

    በኳታር የሚገኙ አንድ ከፍተኛ የሐማስ መሪ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ታጋቾች በሌሎች ሚሊሻ ቡድኖች እጅ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

    ለምሳሌ በመስከረም 26ቱ ጥቃት ተሳታፊ ከነበሩት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ 20 ታጋቾችን ይዞ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል አስሩ ዛሬ የሚለቀቁ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ነገ ረቡዕ ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    በመስከረም 26ቱ ጥቃት ተሳታፊ ከሆኑ ቡድኖች መካከል አንዱ የፍልስጤም እላማዊ ጂሃድ ነው
    የምስሉ መግለጫ, በመስከረም 26ቱ ጥቃት ተሳታፊ ከሆኑ ቡድኖች መካከል አንዱ የፍልስጤም እላማዊ ጂሃድ ነው

    ሐማስ ታጋቾችን እየለቀቀ ለጦርነቱ ፋታ የሚሰጥበት ቀን እንዲራዘም ፍላጎት ቢኖረውም፣ እስራኤል ግን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ዕለታዊ ግምገማ እየተካሄደበት በየዕለቱ እንዲራዘም ፍላጎት አላት።

    ሐማስ መረጃ ለመሰብሰብ እና የታጋቾች መገኛ ቦታን ለማወቅ ረዘም ያለ ጊዜ ያስፈልገኛል እያለ ነው።

    በጋዛ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች መውደማቸው እና የነዳጅ አቅርቦት ውስንነት ይህን የፍለጋ ተግባር ከባድ እንደሚያደርገው ይገመታል።

  15. ከ6 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን እስረኞች በእስራኤል ሲገኙ ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑት ክስ አልተመሰረተባቸውም

    ፍልስጤማውያን እስረኞች ሲፈቱ የነበረው ደስታ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የተኩስ አቁም ፋታውን ተከትሎ በእስራኤል እስር ቤት የሚገኙ 150 የሚሆኑ ታዳጊዎች እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞች ተለቀዋል።

    በአራተኛው ዙር 30 ህጻናትን ጨምሮ 33 ፍልስጤማውያን እስረኞች ተፈትተዋል። በእስራኤል እስር ቤቶች 6 ሺህ 704 ፍልስጤማውያን ታስረው እንደሚገኙ የመብት ተቋማት ያስታወቁ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 2 ሺህ ሰባ የሚሆኑት ፍርድ ቤት አልቀረቡም ወይም ክስ አልተመሰረተባቸውም።

    አስተዳደራዊ እስራት ተብሎ በሚጠራውም ሁኔታ በእስራኤል እስር ቤቶች እንደሚገኙ ሃሞኬድ የተባለው የእስራኤል የመብት ድርጅት አስታውቋል።

    የሐማስ እና የእስራኤል የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎም በአራት ዙሮች 150 ፍልስጤማውያን ተፈትተዋል።

    በትናንትናውም ዕለት 33 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞች ሲፈቱም በርካቶች ደስታቸውን ሲገልጹም ታይተዋል።

    እስራኤል በወረራ በያዘቻት ዌስት ባንክ አቅራቢያ በሚገኘው ራማላህ የፍተሻ ኬላም ሲደርሱም ፍልስጤማውያን ተቀብለዋቸዋል።

    እስረኞቹ ድንጋይ መወርወርን ጨምሮ በግድያ ሙከራ እንደተጠረጠሩ ቢገለጽም በርካቶቹም ክስም ሳይመስረትባቸው በእስር ቤቶች ቆይተዋል።

    በዌስት ባንክ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች ቢያንስ አንድ የቤተሰብ አባላቸው በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ይታሰባል።

    ፍልስጤማውያኑ በእስራኤል ውስጥ በመታሰራቸውም ዘመዶቻቸው ወደ እስራኤል ሄደው መጎብኘት አይችሉም።

    መስከረም መጨረሻ የደረሰውንም ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል እስር ቤቶች ያለ ፍርድ የታሰሩ ፍልስጤማውያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አስታውቀዋል።

    ፍልስጤማውያን እስረኞች ሲፈቱ የነበረው ደስታ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፍልስጤማውያን እስረኞች ሲፈቱ የነበረው ደስታ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፍልስጤማውያን እስረኞች ሲፈቱ የነበረው ደስታ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  16. የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የተለቀቁ ታይላንዳውያን ታጋቾችን ለመውሰድ ወደ እስራኤል አቀኑ

    የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርንፕሬይ ባሂድድሃ ኑካራ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርንፕሬይ ባሂድድሃ ኑካራ የተኩስ አቁም ፋታውን ተከትሎ የተለቀቁ 17 ታይላንዳውያን ታጋቾችን ወደ አገራቸው ለመውሰድ ወደ እስራኤል አቀኑ።

    ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፓርንፐሬይ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እስራኤል ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ከተለቀቁትም መካከል ሐማስ መስከረም መጨረሻ ባደረሰው ጥቃት የተጎዱ ሶስት የታይላንድ ዜጎችም በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይጎበኟቸዋል ተብሏል።

    ባለስልጣኑ በእስራኤል ውስጥ ተቀጥረው ከሚገኙ የታይላንድ ሰራተኞችም ጋር እንደሚገናኙ የታይላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    የተለቀቁት ታጋቾችም ሐሙስ እለት ወደ ባንኮክ እንደሚመለሱም ይጠበቃል። ተጨማሪ 15 የታይላንድ ዜጎች በሐማስ ታግተው እንደሚገኙም የታይላንድ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

  17. ከተለቀቁት ታጋቾች መካከል የሶስት ዓመት መንትያ እህትማማቾች እና እናታቸው ተካተውበታል

    የሶስት ዓመት መንትያ እህትማማቾች እና እናታቸው

    የፎቶው ባለመብት, Handout

    በአራተኛ ዙር ከተለቀቁት ታጋቾች መካከል የሶስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው መንትያ እህትማማቾች እና እናታቸው እንደተካተቱበት ተገለጸ።

    ሻሮን አሎን ኩኒያ እና መንትያ ልጆቿ ኤማ እና ዩሊ ቢለቀቁም ባለቤቷ እና ወንድሙ አሁንም ታግተው እንዳሉ ይታመናል።

    ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ ጥቃት በከፈተበት ወቅት ቤሰተቡ በአንድ ቤት ውስጥ ተጠልለው ነበር ተብሏል። ሐማስ ቤቱን በእሳት ሲያቀጥለው እና ቤተሰቡ ሊያመልጥ ሲሞክርም ተይዘው መታገታቸውም ተነሯል።

    የሻሮን እህት ዳንኤል አሎኒ እና ልጇም ታግተው የነበሩ ሲሆን ሁለቱም አርብ እለት ከእገታ ተለቀዋል። የታገቾች እና የጠፉ ቤተሰቦች ኮሚቴም መንትያዎቹ እህትማማቾን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

    ኤማ "በጣም አስደናቂ እና በፍቅር የተሞላች ህጻን ናት። ከአሻንጉሊት ይልቅ የጭነት መኪናዎችን የምትመርጥ እውነተኛ የኪቡዝ ተወላጅ ናት። እህቷ ዩሊ ዓይናፋር ስትሆም ከመታገቷ በነበሩት ሳምንታት የበለጠ ተጫዋች እየሆነች ነበር" የሚል መግለጫም አውጥቷል።

    ሻሮን እና ባለቤቷ ዴቪድ የተገናኙት እሱ በሚተውንበት ፊልም ላይ የህዝብ ግንኙነት ትሰራ በነበረበት ወቅት መሆኑም ተገልጿል።

  18. የአሜሪካ ባሕር ኃይል የእስራኤላዊያንን መርከብ አግተው የነበሩ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ

  19. ሐማስ 11 ተጨማሪ ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል 30 ህጻናትን ጨምሮ 33 እስረኞችን ፈታች

    ከእስር የተፈታ ፍልስጤማዊ ህጻን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በተኩስ አቁም ፋታው አራተኛ ቀን ሐማስ 11 ተጨማሪ እስራኤላውያን ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል 30 ህጻናትን ጨምሮ 33 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።

    ሐማስ ከለቀቃቸው ታጋቾች መካከል የሶስት ዓመት መንትያ ህጻናት እንደሚገኙበትም ተገልጿል።

    በኳታር አሸማጋይነት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ፋታን ተከትሎ እስካሁን ድረስ 69 ታጋቾችን በሶስት ዙሮች ለቋል። እስራኤል በበኩሏ 150 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።

    ለአራት ቀናት ይቆያል ተብሎ የነበረው የተኩስ አቁም ፋታ ለተጨማሪ ሁለት ቀናት የተራዘመ ሲሆን በዚህም ጊዜ ተጨማሪ ህጻናት እና ሴቶች በአብዛኛው የተካተቱበት የታጋቾች እና የእስረኞች ልውውጥ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

  20. እስራኤል እና ሐማስ ጊዜያዊ ተኩስ አቁሙን ማራዘማቸውን ኳታር አስታወቀች

    ተኩስ አቁምን በመጠቀም ፍልስጤማውያን ከሰሜናዊ ጋዛ እየወጡ ነው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ተኩስ አቁምን በመጠቀም ፍልስጤማውያን ከሰሜናዊ ጋዛ እየወጡ ነው

    በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው እና ለአራት ቀናት የቆየው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ለተጨማሪ ሁለት ቀናት እንዲራዘም ከስምምነት መደረሱን ኳታር አስታወቀች።

    ባለፈው አርብ ጀምሮ እስከ ዛሬ ሰኞ ሌሊት ድረስ ታጋቾችን እና እስረኞችን ለመልቀቅ እንዲሁም ሰብዓዊ እርዳታዎች ወደ ጋዛ እንዲደርሱ ለማስቻል የተደረሰው ጦርነት የመግታት ስምምነት ሰኞ ሌሊት ያበቃል ተብሎ ነበር።

    ባለፉት አራት ቀናት ሐማስ ከእስራኤል ታጋቾች የተወሰኑትን የለቀቀ ሲሆን፣ እስራኤል ደግሞ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለቃለች።

    በተጨማሪም በችግር ላይ ለሚገኙት የጋዛ ነዋሪዎች ምግብ፣ ውሃ፣ መድኃኒት እና ነዳጅ እንዲገባ ተደርጓል።

    በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ግጭቱን በጊዜያዊነት እንዲያቆሙ ለማስቻል ኳታር ቁልፍ ሚና የተጫወተች ሲሆን፣ ግብፅ፣ አሜሪካ እና ሌሎች ወገኖች ተሳታፊ ናቸው።