በጋዛ ከተኩስ አቁም ፋታው በኋላ 200 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ

ለሰባት ቀናት የቆየውን የጋዛ የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ 200 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ15 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 6 ሺህ ህጻናት መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. እስራኤል የምትለቃቸው ፍልስጤማውያን እስረኞች እነማን ናቸው? ለምንስ ታስረው ቆዩ?

  2. 39 ፍልስጤማውያን ከእስራኤል እስር ቤት ተለቀቁ

    ከእስር የወጣ ፍልስጤማዊ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት 39 ፍልስጤማውያን አርብ ምሽት ከእስራኤል እስር ቤት ተለቀቁ።

    አብዛኛዎቹ ከእስራኤል እስር ቤት የተለቀቁት በዕድሜ ወጣት የሆኑ እና ድንጋይ ከመወርወር እስከ የግድያ ሙከራ በሚሉ ክሶች የታሰሩ ነበሩ።

    24 ሴቶች እና 15 ወንዶች ከእስር ተለቀው ዌስት ባንክ ሲደርሱ በርካታ ደጋፊዎች የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማን እያውለበለቡ በደስታ ተቀብለዋቸዋል።

    አርብ ከእስር ከተለቀቁት ፍልስጤማውያን መካከል አንዷ ማራህ ባኬር ስትሆን፣ በእስራኤል ፖሊስ አባል ላይ በስለት ጥቃት ፈጽማለች በሚል ከስምንት ዓመት በፊት የ16 ዓመት ታዳጊ ሳለች ነበር የታሰረችው።

    ማራህ “መፈታቴ አስደንቆኛል” ያለች ሲሆን፣ ከእስር የወጣችው በርካታ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት የተገደሉበት ወቅት በመሆኑ ሙሉ ደስታ አይሰጠኝም ብላለች።

  3. እስራኤል 13 ዜጎቿ ነጻ መውጣታቸውን ይፋ አደረገች

    ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በሐማስ ከታገቱ ዜጎቻቸው መካከል 13ቱን መረከባቸውን ይፋ አደረጉ።

    “የመጀመሪያዎቹን ታጋቾች ተቀብለናል። ሕጻናት፣ እናቶቻቸው እና ሌሎች ሴቶችን። እያንዳንዳቸው ለእኛ ትልቅ ትርጉም አላቸው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

    “አንድ ነገር ላይ ትኩረት እንድታደርጉ - ለቤተሰብ አባላት - ለእስራኤል ዜጎች፡ ሁሉንም ታጋቾች ለመመለስ ቁርጠኞች ነን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።

    በቀጣይ አራት ቀናት 50 እስራኤላውያን ታጋቾች እና 150 ፍልስጤማውያን ከእገታ እና ከእስር ነጻ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

  4. ከሐማስ እገታ ነጻ የወጡ ሰዎች ቤተሰብ አባላት እፎይታ

    ታጋቾች

    ትናንት አርብ ሐማስ 13 እስራኤላውያን፣ 10 የታይላንድ እና 1 የፊሊፒንስ ዜጋን ከእገታ መልቀቁ ታውቋል።

    ሐማስ እና እስራኤል በደረሱት ስምምነት መሠረት ነጻ የወጡት 13 ሴቶች እና ሕጻናት እስራኤላውያን አገራቸው ደርሰዋል።

    በሌላ በኩሉ 39 ፍልስጤማውያን ከእስራኤል እስርቤት ተለቀው ወደ ዌስት ባንክ ተወስደዋል።

    ነጻ ከወጡት እስራኤላውያን መካከል አራቱ ዕድሜያቸው ሁለት፣ አራት፣ ስድስት እና 9 ሲሆን ከመካከላቸው የ85 ዓመት አዛውንት ሴትም ይገኙበታል።

    ዮኒ አሸር የተባሉት እስራኤላዊ የ34 ዓመቷ ባለቤቱ እና የ4 እና የ2 ዓመት ሴት ልጆቹ ታግተውበት ነበር።

    “ከደረሰብን ጉዳት እና አሳዛኝ መከረ ቤተሰቤን ለመታደግ ቆርጫለሁ። አሁን ላይ ደስታዬን አልገልጽም። ደስታዬን የምገልጸው ሁሉም ታጋቾች ሲለቀቁ ብቻ ነው” ብሏል።

    ኪታይ ከፍቅረኛዋ ዊቻኢ ካላፓት ጋር
    የምስሉ መግለጫ, ኪታይ ከፍቅረኛዋ ዊቻኢ ካላፓት ጋር

    የታይላንድ ዜጎች መለቀቅም በወዳጅ ዘመዶቻቸው በኩል የተለያየ ስሜትን ፈጥሯል። በተለይ ኪቲያ ቱኤንግሳኤንግ ከእገታው በኋላ በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ አልፋላች።

    ኪታይ የ28 ዓመቱ ፍቅረኛዋ ዊቻኢ ካላፓት መስከረም 26 ላይ ከታገተ በኋላ መገደሉ በታይላንድ መንግሥት ተነግሯት ነበር። ቀጥሎ ደግሞ በጥቃቱ ተገድለዋል ከተባሉት የታይላንድ ዜጎች ዝርዝር ውስጥ የፍቅረኛዋ ስም አልነበረም።

    ከአምስት ቀናት በፊት የፍቅረኛዋን ስም በሐማስ ታግተው ከሚገኙ ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ከተመለከተች በኋላ አርብ ነጻ ወጥቷል።

  5. "አባቴ አሁንም እገታ ላይ ነው፤ ለሌሎች ቤተሰቦች ግን ደስተኛ ነኝ"

    ማያና ከወላጅ አባቷ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, FAMILY HANDOUT

    የምስሉ መግለጫ, ማያና ከወላጅ አባቷ ጋር

    ማያና ካፕሉን ኬይዳር ምንም እንኳ እርግጠኛ ባትሆንም አባቷ አሁንም በሐማስ እገታ ስር እንዳለ ታምናለች።

    ትናንት አርብ ነጻ ከሆኑት መካከል አባቷ አንዱ እንደማይሆን ቀድማ ብትገነዘብም፤ 13 እስራኤላውያን መለቀቃቸው ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ትናገራለች።

    ሐማስ አባቷ ይኖርበት ወደ ነበረው መንደር ከገባ ከሰዓታት በኋላ ወላጅ አባቷ በሐማስ ታጣቂዎች ተይዞ ሲሄድ የሚያሳይ ምስል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መመልከቷን ታስታውሳለች።

    ሐማስ እና ታጋች

    የፎቶው ባለመብት, SM

    ማያና አባቴ ነሁንም ጻ ባይሆንም “የቤተሰብ አባላታቸውን ለሚያገኙ ሰዎች ግን ደስተኛ ነኝ” ብላለች።

    በኳታር አደራዳሪነት እስራኤል እና ሐማስ በደረሱት ስምምነት መሠረት በቀጣይ 4 ቀናት 50 እስራኤላውያን ነጻ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ማያናም ይህ ስምምነት ተፈጻሚ ሆኖ ብዙ ታጋቾችን ነጻ ማውጣት እንዲቻል ምኞቴ ነው ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

  6. በሐማስ ከተለቀቁት ታጋቾች መካከል 13ቱ እስራኤላውያን ናቸው

    Al Qahera TV

    የፎቶው ባለመብት, Al Qahera TV

    በሐማስ እና እስራኤል መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ዛሬ አርብ ነጻ ከወጡት ታጋቾች መካከል 13ቱ እስራኤላውያን መሆናቸው ተገለጸ።

    የእስራኤል አምቡላንስ አገልግሎት ኃላፊ የቀይ መስቀል ምንጮችን ጠቅሰው እንደተናገሩት 13 የአገራቸው ዜጎች ነጻ መውጣታቸን ተናግረዋል።

    ቀደም ቀይ መስቀል ዛሬ በጠቅላለው 24 ሰዎች መለቀቃቸውን አስታውቋል።

    ኳታር ዛሬ ነጻ የወጡት 13ቱ እስራኤላውያን፣ 10 የታይላንድ ዜጎች እና 1 ሰው ደግሞ የፊሊፒንስ ዜጋ መሆኑን አስታውቃለች።

  7. ታጋቾቹ የጤና መጓደል አይታይባቸውም ተባለ

    ታጋቾች

    የፎቶው ባለመብት, Al Qahera TV

    የእስራኤል ጤና ኃላፊዎች ዛሬ ከሐማስ እገታ ነጻ የወጡት ታጋቾች የጤና መጓደል አይታይባቸውም አሉ።

    የእስራኤል አምቡላንስ አገልግሎት ኃላፊ አሊ ቢን ታጋቾቹ ምንም አይነት አካላዊ የጤና መጓደል አይታይባቸውም ስለማለታቸው የእስራኤል ጦር ራዲዮ ዘግቧል።

    አል ቃሄር የተባለ የግብፅ የቴሌቪዥን ጣቢያ ታጋቾች ከአምቡላንስ ሲወርዱ አሳይቷል።

    ታጋቾቹ ከሰባት ሳምንታት እገታ በኋላ ነው ዛሬ ነጻ የወጡት።

    ኃላፊው ጨምረውም ከቀይ መስቀል ተወካዮች ከተረከቧቸው ታጋቾች መካከል 13ቱ የእስራኤል ዜጎች መሆናቸውን እና 11ዱ ደግሞ የውጭ አገር ዜጎች መሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

  8. ቀይ መስቀል ዛሬ የተለቀቁት ታጋቾች 24 መሆናቸውን ገለጸ

    ቀይ መስቀል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ዛሬ አርብ ሐማስ የለቀቃቸው ታጋቾች ቁጥር 24 መሆኑን አስታወቀ።

    ቀደም ሲል 12 የታይላንድ ዜጎች ነጻ መውጣታቸውን የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ገልጸው ነበር።

    የእስራኤል ጦር ደግሞ 13 ታጋቾችን ከቀይ መስቀል መረከቡን ገልጿል።

    በጠቅላላው በዛሬው ዕለት 25 ታጋቾች ተለቀዋል የተባለ ቢሆንም፣ ቀይ መስቀል የተለቀቁት ሰዎች ቁጥር 24 ናቸች በማለቱ የቁጥር ልዩነቱ እንዴት እንደመጣ ግልጽ አይደለም።

  9. የእስራኤል ጤና ማዕከላት ለታጋቾች ሕክምና ለመስጠት እየተጠባበቀ ነው

    አምቡላንስ

    የፎቶው ባለመብት, Israeli Government Press Office

    በሐማስ ታግተው ለነበሩ ሰዎች የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ለመስጠት የተቋቋሙት ማዕከላት ታጋቾችን እየተጠባበቁ ነው።

    ቀደም ሲል የእስራኤል ጦር ሐማስ የለቀቃቸውን 13 ታጋቾች መረከቡ ተገልጿል።

    ዛሬ አርብ ሐማስ የለቀቃቸው ሴቶች እና ሕጻናት ለሰባት ሳምንታት ያህል በጦርነት ቀጠና ውስጥ ይዞ አቆይቷቸዋል።

    እስራኤል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ቤተሰብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  10. የእስራኤል ጦር 13 ታጋቾችን ከቀይ መስቀል ተረከበ

    የእስራኤል ጦር ሐማስ የለቀቃቸውን 13 ታጋቾች መረከቡ ተዘገበ።

    የፈረንሳይ ዜና ወኪል የሆነው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የእስራኤል የደኅንነት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ጦሩ ታግተው የነበሩ ሰዎችን ከቀይ መስቀል ተረክቧል።

    ቀደም ሲሉ ከሐማስ እገታ ነጻ ይወጣሉ የተባሉት 13 ታጋቾች ለቀይ መስቀል ተላልፈው መሰጠታቸው ተገልጾ ነበር።

    ታጋቾቹ በጋዛ እና ግብፅ መካከል በሚገኘው የራፋህ የድንበር በር አልፈው ወደ ግብፅ ተሻግረው ነበር።

    ይህን ሂደት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ከከፍተኛ የአገሪቱ ጦር መኮንኖች ጋር በመሆን በቅርበት ሲከታተሉት ቆይተዋል።

    በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ዛሬ ጠዋት የጀመረው እና ለቀናት የሚቆየው ጦርነት ጋብ የማድረግ አካል የሆነው የታጋቾች መለቀቅ በቀጣይ ቀናትም እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

  11. 13 ታጋቾች ለቀይ መስቀል ተላልፈው ተሰጡ

    ራፋ የድንበር በር የሰዎች እንቅስቃሴ ጨምሮ ታይቷል።

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ራፋ የድንበር በር የሰዎች እንቅስቃሴ ጨምሮ ታይቷል።

    ዛሬ ከሐማስ እገታ ነጻ ይወጣሉ የተባሉት 13 ታጋቾች ለቀይ መስቀል ተላልፈው መሰጠታቸው ተዘገበ።

    ቻናል 12 የተባለ የእስራኤል ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀይ መስቀል 13ቱን ታጋቾች ከሐማስ ተረክቦ በአሁኑ ሰዓት ወደ ግብፅ እያጓጓዛቸው እንደሆነ ዘግቧል።

    ታጋቾቹ በጋዛ እና ግብፅ መካከል በሚገኘው የራፋህ የድንበር በር የሚያልፉ ሲሆን፣ በአካባቢው የሰዎች እንቅስቃሴ ጨምሮ ታይቷል።

    ቀይ መስቀል ከሐማስ የተረከባቸውን 13ቱን ታጋቾች ወደ ግብፅ አሻግሮ ለእስራኤል ጦር የሚያስረክብ ይሆናል።

    ይህን ሂደትም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እና የእስራኤል ጦር አዛዥ ከቴል አቪቭ ሆነው በቅርበት እየተከታተሉት ነው ተብሏል።

  12. በሐማስ ታግተው የነበሩ 12 የታይላንድ ዜጎች ተለቀቁ

    12 የታይላንድ ዜጎች ከሐማስ እገታ ነጻ መውጣታቸውን የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤምባሲ ኃላፊዎች "ታጋቾቹን ሊወስዱ እያመሩ ነው" ያሉ ሲሆን፣ ታጋቾቹን ከየት እና መቼ እንደሚቀበሉ ግን ያሉት ነገር የለም።

    ቀደም ሲል ግብፅ ከከፍተኛ ጥረት በኋላ 12 የታይላንድ ዜጎች እንዲለቀቁ አድርጊያለሁ ብላ ነበር።

    የታይላንድ ዜጎች መለቀቅን በተመለከተ እስካሁን በሐማስ በኩል የተባለ ነገር የለም።

    የታይላንድ ዜጎች መለቀቅ የተሰማው እስራኤል ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ 13 ታጋቾችን በቀይ መስቀል በኩል ከሐማስ እገታ ነጻ ይወጣሉ ብላ እየተጠባበቀች ባለበት ሰዓት ነው።

    ሐማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 230 ያላሱ ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ ሰርጥ መውሰዱ ይታወሳል።

  13. ታጋቾችን ከሐማስ የመረከቡ ሥራ ቀላል አይሆንም ተባለ

    ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ከሐማስ እገታ ነጻ የሚሆኑ ሰዎችን ለመረከብ ጋዛ ቀድሞ ቢገኝም ሂደቱ ግን ቀላል እንደማይሆን ተገምቷል።

    ቀይ መስቀል ታጋቾቹን ጋዛ ውስጥ የት እና ስንት ሰዓት እንደሚቀበል ይነገረዋል። ሁሉንም ታጋቾች ከአንድ ቦታ ወይም ከተለያዩ ቦታዎች ሊረከብ ይችላል።

    ቀይ መስቀል 13ቱን ታጋቾች ከሐማስ ተቀብሎ ደግሞ ወደ ግብፅ አሻግሮ ለእስራኤል ጦር ማስረከብ ይኖርበታል።

    ቀይ መስቀል ከዚህ በተጨማሪም ከእስራኤል እስር ቤቶች የሚለቀቁ ፍልስጤማውያንን ተቀብሎ ወደ መኖሪያቸው መሄድ የሚሹ ከሆነ ወደ ዌስት ባንክ ይወስዳል።

  14. የእስራኤል ጦር ነጻ የሚወጡ ታጋቾችን ለመቀበል መዘጋጀቱን ገለጸ

    መጫወቻ ሰፍራ

    የፎቶው ባለመብት, Israel Defense Forces

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል አርብ [ዛሬ] ከሰዓት በኋላ ከሐማስ እገታ ነጻ ይወጣሉ ተብለው የሚጠበቁ ሰዎችን ለመቀበል ዝግጅት መጨረሱን አስታወቀ።

    ጦሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ለታጋቾች የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ እና የሚቆዩባቸው በርካታ ቦታዎች ዝግጁ ሆነዋል ብሏል።

    የእስራኤል ጦር በቀይ መስቀል በኩል ታጋቾቹን ከሐማስ ከተቀበለ በኋላ የመጀመሪያ የሕክምና እርዳታ ሰጥቶ ታጋቾች ከቤተሰብ አባላት ጋር በመላው እስራኤል በሚገኙ ሆስፒታሎች እንዲቀላቀሉ አደርጋለሁ ብሏል።

    ሄሊኮፍተር

    የፎቶው ባለመብት, Israel Defense Forces

    ጦሩ ታጋቾቹን ለመቀበል ያደረገውን ዝግጅት የሚያሳይ ምስል ያወጣ ሲሆን፣ በምስሎቹ ላይ የሕጻናት መጫወቻ እና ማረፊያ ቦታ እንዲሁም ታጋቾች ይጓጓዙበታል የተባለ የጦር ሄሊኮፕተር ይታያሉ።

    እስራኤል እና ሐማስን ስታደራድር የቆየችው ኳታር የመጀመሪያዎቹን 13 ታጋቾች አርብ ከሰዓት በኋላ 10 ሰዓት ላይ እንደሚለቀቁ ማስታወቋ ይታወሳል።

    ዛሬ ከሰዓት ነጻ የሚወጡት ታጋቾች በሙሉ ሴቶች እና ሕጻናትን ናቸው።

  15. ወደ ጋዛ የሚገባው የሰብዓዊ እርዳታ መጠን ጨመረ

    እርዳታ የጫኑ መኪኖች ጋዛ ሲገቡ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, እርዳታ የጫኑ መኪኖች ጋዛ ሲገቡ

    እስራኤል እና ሐማስ ለሚካሄደው ጦርነት ፋታ ለመስጠት እና ታጋቾችን ለመልቀቅ ከስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ ወደ ጋዛ የሚገባው የሰብዓዊ እርዳታ መጠን ጨመረ።

    ስምምነቱ ተፈጻሚ ከሆነበት ከዛሬ አርብ ሰዓት አንስቶ ቢያንስ 60 መኪኖች ከግብፅ ተነስተው ወደ ጋዛ መግባታቸው ተገልጿል።

    ግብፅ በየቀኑ 130 ሺህ ሊትር ነዳጅ ወደ ጋዛ ይገባል ብላለች። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ደግሞ 100 መኪኖች እርዳታ ለማድረስ ዝግጁ ናቸው ብሏል።

    ይሁን እንጂ ከጋዛ ሕዝብ ቁጥር አንጻር አሁንም ወደ ጋዛ ሰርጥ የሚላከው ምግብ እና ነዳጅ መጠን በቂ አይደለም እየተባለ ነው።

    የኦክስፋም ባልደረባ የሆኑት ላይላ ባርሁም ለቢቢሲ ሲናገሩ ወደ 200 የሚጠጉ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች በቀጣይ አራት ቀናት ጋዛ እንደሚደርሱ ቢገለጽም፣ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ እርዳታ ጠባቂ ለሆነባት ጋዛ አቅርቦቱ በቂ አይደለም ብለዋል።

  16. ታጋቾች በግብፅ በኩል ወደ እስራኤል እንደሚወሰዱ ተገለጸ

    ታጋቾች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በእስራኤል እና በሐማስ መከካል የተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታ ከተጀመረ ሰዓታትን አስቆጥሯል።

    ለአራት ቀናት የሚቆየውንም የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ እርዳታ ወደ ጋዛ ሰርጥ መግባት መጀመሩ ተገልጿል።

    በስምምነቱ መሠረት ዛሬ ከሰዓት በኋላ 13 ታጋቾች ለዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት ይሰጣሉ። በግብፅ ራፋህ የድንበር ማቋረጫ በኩልም የሚወጡ ይሆናል።

    በግብፅ ድንበር በኩልም የእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች ተቀብለው አስፈላጊውን የማንነት ማረጋገጫ ያደርጋሉ።

    በመቀጠልም የሕክምና ምርመራዎችን ለማድረግ ወደ ሆስፒታሎች ከተወሰዱም በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙ ይሆናል።

    ከሰዓታት በኋላም እስራኤል በእስር ከያዘቻቸው ውስጥ በሺዎች ከሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንም የተወሰኑት የሚለቀቁ ይሆናል።

  17. ኳታር ደመኞቹን እስራኤልን እና ሐማስን እንዴት ከስምምነት እንዲደርሱ አስቻለች?

  18. የእስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ፋታ ምንን ይዟል?

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ውጊያ ማቆም፦ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው ውጊያ የማቆም ስምምነት ጊዜያዊ ሲሆን ለአራት ቀናት እንደሚቆይም ተገልጿል። በደቡብ እስራኤል የምትገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ የእስራኤል ጦር የተኩስ አቁም ፋታ እስከተጀመረበት የመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ በጥቃቱ እንደቀጠለ ታዝባለች።

    የታጋቾች እና እስረኞች መለቀቅ፦ በሐማስ የተወሰዱ 13 ህጻናት እና ሴቶች ዛሬ ከሰዓት የሚለቀቁ ሲሆን በአራቱ ቀናትም 50 ታጋቾች ይለቀቃሉ። በልውውጡም እስራኤል በተለያዩ እስር ቤቶቿ ከሳረቻቸው በሺዎች ከሚቆጠሩ ውስጥ 150 ፍልስጤማውያን የሚለቀቁ ይሆናል።

    የተኩስ አቁም ፋታ የመራዘም ሁኔታ፦ ከሚለቀቁት ታጋቾች በተጨማሪ በየ10 ታጋቾች አንድ ቀን የውጊያ ፋታ ሊኖር እንደሚችልም ተጠቁሟል።

    እርዳታ እና ነዳጅ፦ 200 እርዳታ የጫኑ መኪናዎች፣ አራት ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እና እንዲሁም አራት የምግብ ማብሰያ የጫኑ መኪናዎች በግብጽ የድንበር ማቋረጫ በኩል ወደ ጋዛ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል። ግብጽ በየቀኑ 13 ሺህ ሊትር ናፍጣ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንደሚፈቀድም አስታውቃለች።

  19. የእስራኤል መከላከያ 'ጦርነቱ አላከተመም' ሲል አስጠነቀቀ

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ለአራት ቀናት የሚቆየው የተኩስ አቁም ፋታ ከመጀመሩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ባወጣው መግለጫ የእስራኤል መከላከያ "ጦርነቱ አላበቃም " ሲል በጋዛ ለሚኖሩ ፍልስጤማውያን አስጠንቅቋል።

    "የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ፋታው ጊዜያዊ" ነው ሲሉም የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃለ አቀባይ አቪቻይ አድራይ በአረብኛ ቋንቋ ተናግረዋል።

    "ሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ አደገኛ የጦር ቀጠና ነው እናም ወደ ሰሜናዊ ጋዛ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው። ለደህንነታቸው ስትሉ በደቡባዊ ጋዛ ባለው የሰብዓዊ ዞን ውስጥ መቆየት አለባችሁ" ሲሉ ለጋዛውያን ተናግረዋል።

    እስራኤል ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ያለችው ደቡባዊ ጋዛንም የማያባራ የአየር ጥቃት ስትፈጽምበት መቆየቱ ይታወሳል።

  20. በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የእስራኤል- ሐማስ የተኩስ አቁም ፋታ ጀመረ

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የእስራኤል ሐማስ የተኩስ አቁም ፋታ ጀመረ።

    ለአራት ቀናት የሚዘልቀው የውጊያ ፋታ ከአንድ ሰዓት በፊት የጀመረ ሲሆን ለ15 ደቂቃ ያህል አልፎ አልፎ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።

    የተኩስ አቁም ፋታው ከመጀመሩ በፊት ባሉት 20 እና 30 ደቂቃዎችም የመጨረሻዎቹ የአየር ጥቃቶችም ተፈጽመዋል።

    ለሰባት ሳምንታት ያህል የማያባራ ጥቃት በጋዛ ላይ የፈጸመው የእስራኤል መከላከያም ፋታው እስኪጀመር እስከ መጨረሻዋ ሰዓትም ድረስ ጥቃቱን አላቆመም ነበር።

    ቢቢሲ የድሮኖች ድምጽ የሰማ ቢሆንም በባለፉት 20 ደቂቃዎች የአየር ጥቃቶች፣ የካበድ መሳሪያ ድምጾች ወይክ ከፍተኛ ፍንዳታዎች አልተሰሙም።

    በስምምነቱ መሰረት ሐማስ 50 ታጋቾችን እንዲሁም እስራኤል 150 የፍልስጤም እስረኞችን በአራት ቀናት የሚለቁ ይሆናል።