በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 30 ሺህ ተጠጋ

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የማሕበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ሲሆን ከዚህ ቀደም በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ በመቶዎች ይገኝ የነበረው ወደ ሺህ ተሻግሯል። በትናንትናው ዕለትም ከፍተኛ የተባለው 1ሺህ 652 እንዲሁም በዛሬው ዕለት 982 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ቁጥሩ ወደ 30 ሺህ ተጠግቷል። አገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥር 528 አድርሶታል። በአጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 12 ሺህ 359 መድረሱን የጤና ሚንስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ አመላክቷል። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለ609 ሺህ 463ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ አከናውናለች። ሳይዘናጉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እራሳችንንና ሌሎችን ከበሽታው እንጠብቅ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ግብፃውያን ወረርሽኙ ሳይገታቸው ድምጽ እየሰጡ ነው

    ግብፅ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ግብፃውያን ራሳቸውን ከኮቪድ-19 የሚከላከሉባቸው መንገዶች ተመቻችተው ለአዲስ ብሔራዊ ምክር ቤት ድምጽ እየሰጡ ይገኛሉ።

    ለመራጮች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲሁም ጓንት መዘራጀቱ ተዘግቧል። በተጨማሪም የራሳቸውን እስኪርብቶ እንዲያዘጋጁና ከሌሎች መራጮች ራቅ ብለው እንዲቆሙም ተደርጓል።

    ግብፅ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ በኮቪድ-19 በተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ናት።

    ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች በወረርሽኙ ሳቢያ ምርጫ እንዲራዘም ቢወሰንም፤ እንደ ሲሪ ላንካ እና ቤላሩስ ያሉ አገሮች ምርጫ ለማካሄድ ወስነዋል።

    ‘ኢንስቲትዮት ፎር ዴሞክራሲ አሲስታንስ’ የተባለ ድርጅት እንዳለው፤ 69 አገሮች እና ግዛቶች በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ምርጫ ሲያራዝሙ ከ50 በላይ ደግሞ ምርጫ እንዲከናወን ውሳኔ አሳልፈዋል።

    የግብፅ የምርጫ ውጤት ነሐሴ 19 ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

  2. አሜሪካ ለናይጄሪያ 200 ቬንትሌተሮች ለገሰች

    ናይጄሪያ 200 ቬንትሌተሮች ከአሜሪካ መንግሥት ተሰጥቷታል። እነዚህ በልገሳ ያገኘቻቸውን ቬንትሌተሮች ለተለያዩ ሆስፒታሎች ማከፋፈል ልትጀምር መሆኗንም አስታውቃለች።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለናይጄሪያ ቬንትሌተሮቹን ለመስጠት ቃል ገብተው የነበረው በሚያዚያ ወር ከፕሬዝዳንት ሙሀመዱ ቡሃሪ ጋር በነበራቸው የስልክ ምልልስ ወቅት ነበር።

    ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ ናይጄሪያን በዚህ ወረርሽኝ ወቅት እንደሚረዷት ተናግረው ነበር።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በግንቦት ወር ቬንትሌተሮቹን ለናይጄሪያ መላካቸውን ከተናገሩ በኋላ የናይጄሪያ ማስታወቂያ ሚኒስትር ላይ ሞሐመድ እንዳልደረሳቸው ተናግረው ነበር።

    በወቅቱ ሚኒስትሩ ሲደርሰን ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን ብለው ነበር።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  3. የማላዊ መንግሥት ኮቪድ-19ን ለመከላከል በጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የተነሳ ሊከሰስ ነው

    እጅ መታጠብ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ማላዊ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት በሚል የጣለችው አዲስ የእንቅስቃሴ ገደብ ከተለያዩ አካላት ተቃውሞ ገጥሞታል።

    የእንቅስቃሴ ገደቡ የተጣለው በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ሲሆን አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መንግሥትን ፍርድ ቤት እገትረዋለሁ ሲል ተናግሯል።

    በአዲሱ የእንቅስቃሴ ገደብ ከ10 ሰው በላይ መሰብሰብ የተከለከለ ሲሆን ቀብርም ቢሆን ከ50 ሰው በላይ መገኘት አይችልም ተብሏል።

    ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ሲሆን ይህንን ደንብ ተላልፎ የተገኘ ግለሰብ 13 ዶላር ይቀጣል ተብሏል።

    መጠጥ ቤቶችም ቢሆኑ በቀን ለስድስት ሰዓት ብቻ እንዲሠሩ ተደንግጓል። ከቀኑ ስምንት ሰዓት እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ክፍት ሆነው በቀሪዎቹ ሰዓታት እንዲዘጉ ጥብቅ መመሪያ ተላልፏል።

    የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አዲሱ የእንቅስቃሴ ገደብን መጣል ያስፈለገው እየጨመረ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመግታት በማስፈለጉ ነው ብለዋል።

    ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎ የነበረ ቢሆንም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ክስ ተመስርቶ ነበር።

    የቤተ እምነት መሪዎች በአዲሱ መሰብሰብን በሚገድበው መመሪያ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልፀዋል።

    የዲሞክራሲና ምጣኔ ሀብት ልማት ኢኒሼቲቭ ማዕከል የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መንግሥት የፍርድ ቤት እገዳን ጥሶ ገደብ በማውጣቱ በድጋሚ ክስ እመሰርታለሁ ሲል ዝቷል።

    የጤና ሚኒስትሩ ኩምቢዜ ቺፖንዳ በገደቡ ላይ የሃይማኖት አባቶችን ለማነጋገር ቃል ገብተዋል።

    እስካሁን ድረስ ከ4600 በላይ ማሊያውያን በኮቪድ-19 መያዛቸው በምርመራ ሲረጋገጥ ከእነዚህም መካከል 146 ሰዎች መሞታቸውን ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መዝግቧል።

  4. በሩስያ የኮቪድ-19 ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ አገኘ

  5. ናሚቢያ በኮሮና ምክንያት የዓሳ ማጥመድ ገበያዋን ለጨረታ አቀረበች

    የናሚቢያ ዓሳ ምርት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ናሚቢያ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የዓሳ ማጥመድ ገበያዋን ለግል ኩባንያዎች በጨረታ እንደምታቀርብ የዓሳ ማስገር ሚኒስትሩ አልበርት ካዋና አሳውቀዋል።

    ከጨረታው የሚገኘው ገንዘብ በሃገሪቱ የኮሮናቫይረስ በሽታን ለመግታት ጥቅም ላይ የሚውል ነው ተብሏል።

    ሆርስ ማኬሬል፣ ሄክ እና ሞንክ የተሰኙት የዓሳ ዝርያዎች ናቸው ለጨረታ የሚቀርቡት ብሏል መንግሥት።

    ሚኒስትሩ ከጨረታው የሚገኘውን ገቢ መድኃኒት ለመግዛት የሕክምና ዕቃዎችን ለሟሟላት ይጠቀምበታል ብለዋል።

    የዓሳ ማስገር ኢንዱስትሪ ለጨረታ ሲቀርብ በሃገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    አንድ የሃገር ውስጥ ራድዮ ስለ ጨረታው የጤና ሚኒስትሩ የሚያውቁት ነገር የለም የሚል ዘገባ ሠርቷል።

    ዓሳ ከማዕድንና ከግብርና ቀጥሎ የናሚቢያ ምጣኔ ሃብት ሶስተኛው ማገር ነው።

  6. በኮሮናቫይረስ ለመበልጸግ የሚሯሯጡት ጋናውያን የሆስፒታል ሰራተኞች

  7. ትራምፕ አሜሪካውያን ተመልሰው ወደ ሃገራቸውን እንዳይመጡ ሊከለክሉ ይችላሉ

    አሜሪካ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው መሪ ዶናልድ ትራምፕ ከሌሎች ሃገራት ወደ ቀያቸው የሚመጡ አሜሪካውያንን መግባት ሊከለክሉ ይችላሉ እየተባለ ነው።

    ፕሬዝዳንቱ ይህን ያቀዱት ተጓዦች ኮሮናቫይረስ ይዘው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ በመስጋት ነው።

    ኒውዮርክ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ ይህ ረቂቅ አዋጅ ባለሥልጣናት ማንኛውም ሰው የኮሮናቫይረስ አለበት ብለው የሚጠረጥሩ ከሆነ መግባት መከልከል መብታቸው ነው ይላል።

    መንግሥት ስለጉዳዩ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ፕሬዝደንት ትራምፕ በርካታ ሕጎችን አውጥተዋል። ከነዚህም መካከል የውጭ ሃገር ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያግደው ይገኝበታል። ነገር ግን አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ሰዎች መግባት መውጣት ይችሉ ነበር።

    የትራምፕ አስተዳደር መሰል ሕጎችን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ግልፅ አይደለም ሲል ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።

    አሜሪካ እስካሁን ድረስ 5 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንደተያዙባት ይፋ አድርጋለች።

  8. ኢትዮጵያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች መርምራለች

    ዕለታዊው የኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ አሃዝ

    ዕለታዊው የኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙና ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች አሃዝ ወጥቷል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት 11,039 ናሙናዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ 773 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም አስታውቀዋል።

    ይህም ኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ወዲህ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 23,591 አድርሶታል።

    በሌላ በኩል ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ ባለፉት 24 ሰዓታት 13 ሰዎች ሞተዋል። አጠቃላይ የሟቾች ቁጥርም 420 ደርሷል።

    ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 10 ሺህ 411 ደርሷል። ባለፉት 24 ሰዓታት205 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸው ተገልጿል።

    ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከ509 ሺህ በላይ ናሙናዎች መርምራለች።

  9. ዶ/ር ቴድሮስ መሪዎች ቫይረሱ ማኅበረሰቡ ውስጥ እንዳይሰራጭ መግታት አለባቸው አሉ

    የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም

    የዓለም አገራት መሪዎች ቫይረሱ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዳይሰራጭ ማድረግ ከቻሉ ወረርሽኙ መገታቱ አይቀርም ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ዶ/ር ቴድሮስ ዕለተ ሰኞ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በዚህ ሳምንት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሊደርስ እንደሚችል ተናግረዋል።

    ክትባት እስካልተገኘ ድረስ ወረርሽኙን ማስቆም የምንችለው መሠረታዊ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ነው። እነዚህም፡ እጅን መታጠበ፣ አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣ ምርመራ ማድረግና ቫይረሱ የተገኘባቸውን ለይቶ ማቆየት ነው ሲሉ ኃላፊው ተደምጠዋል።

    ኃላፊው፤ መንግሥታት ትምህርት ቤቶችን ከመክፈታቸው በፊት በሽታው በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ሥርጭት መግታት መቻላቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል።

    «መልዕክቴ ግልጽና ግልጽ ነው። ቫይረሱ እንዳይሰራጭ መጫንና መጫን ግድ ይላል» ሲሉ ነው ኃላፊው ጄኔቫ ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤታቸው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።

  10. ኒው ዚላንድ ለ101 ቀናት አዲስ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አላገኘሁም አለች

    የኒው ዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    ላለፉት 101 ቀናት በኒው ዚላንድ አዲስ በቫይረሱ የተያዘ ሰው እንደሌለ ተገልጿል። ነገር ግን ከሌሎች አገራት መጥተው በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች አሉ።

    የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርንም የተገኘውን ውጤት ''እጅግ ወሳኝ ምዕራፍ'' በማለት አሞካሽተውታል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር በተያያዘ የወሰዷቸው በርካታ እርምጃዎች ከጅምሩ ሙገሳ እንዲያገኙ አድርጓቸው ነበር።

    በኒው ዚላንድ ውስጥ አሁን ያሉት 21 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሁሉም ከሌላ አገራት ቫይረሱን ይዘው የመጡ ሲሆን እነሱም ቢሆን በለይቶ ማቆያዎች ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው ነው።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተበት ከካቲት ወር ጀምሮ ኒው ዚላንድ ውስጥ 1219 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ጠበቅ ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ፣ ሁሉንም ድንበሮች መዝጋትና ውጤታማ የምርመራና ንክኪ የመለየት ሥራዎች ኒው ዚላንድን ውጤታማ እንዳደረጋት ይታመናል።

  11. ብራዚልና አሜሪካ አሁንም በርካቶችን በቫይረሱ ሰበብ እያጡ ነው

    መቃብር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርና በወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር በብራዚልና በአሜሪካ አሁንም በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ ነው።

    ሁለቱም አገራት ስርጭቱን በመቆታጠር ረገድ አመርቂ የሚባል ሥራ መስራት አልቻሉም።

    ብራዚል እስካሁን ድረስ ከሦስት ሚሊየን በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ መያዛቸውን ያስታወቀች ሲሆን 100 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

    ይህ ደግሞ ከአሜሪካ ቀጥሎ በዓለማችን ላይ ከፍተኛውን ቁጥር ያስመዘገበች አገር ያደርጋታል።

    አሜሪካ ደግሞ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙባት 162 ሺህ ሰዎች ደግሞ መሞታቸው ታውቋል።

    የሁለቱም አገራት መሪዎች የብራዚሉ ጃዬር ቦልሶናሮ እና የአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ የቫይረሱን የስርጭት መጠንና የሚያስከትለው ጉዳት አስከዚህም ነው እያሉ ሲያጣጥሉ ነበር።

  12. የኮሮናቫይረስ አጫጭር ዜናዎች ከአፍሪካ

    አፍሪካ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    **ማላዊ ባለስልጣናት በኮሮናቫይረስ መስፋፋት ምክንያት አብያተክርስቲያናትና መዝናኛ ስፍራዎች ዝግ እንዲሆኑ አዘዋለው። መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ባለፈው ወር በአገሪቱ ያለው በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን ተከትሎ ሲሆን በዚህም መጠጥ ቤቶችና ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች እንዲዘጉ ነው የታዘዘው።

    የማላዊ መንግሥት የበሽታውን መዛመት ለመቆጣጠር በሚል ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ ልዩ የደንብ ማስከበር መኮንኖች መሰማራታቸው ተገልጿል።

    የአገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ሕዝቡ የወጡትን አዳዲስ መመሪያዎች እንዲያከብር ለማድረግ ልዩ ደንብ አስከባሪዎች ተቀጥረዋል።

    **ኬንያ ውስጥ እየጨመረ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በማድረግ የአሜሪካ መንግሥት ወደ አገሪቱ ለሚጓዙ ዜጎቹ የጉዞ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

    የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ባወጣው በኬንያ ያለው የበሽታው የስጋት ደረጃ ከፍተኛ እንደሆነ በመግለጽ ሦስተኛ ደረጃ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

    **ደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በኮቪድ ወረርሽን ምክንያት የተዳከመውን የአገሪቱን የግብይት ሥርዓት ለማገዝ በነደፉት ዕቅድ መሰረት በሴቶች ለሚተዳደሩ ተቋማት ትኩረት መስጠታቸው ተግለጿል።

    በዚህም መሰረት መንግሥት ከሚፈጽማቸው ግዢዎች ውስጥ 40 በመቶው የሚሆነው በሴቶች ባለቤትነት ስር ካሉ የንግድ ተቋማት እንዲሆኑ እንዲሆኑ አዘዋል።

    የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ሴቶች በሥራቸው አስፈላጊውን የገንዘብ ኃይል እንዲያገኙ ማድረግ ወሳኝ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

  13. አውስትራሊያ በአንድ ቀን ከፍተኛውን ሞት አስመዘገበች

    አውስትራሊያ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    በሜልቦርን የቫይረሱ ስርጭት እንደገና ማገርሸቱን ተከትሎ አውስትራሊያ በአንድ ቀን ከፍተኛ የተባለውን የሟቾች ቁጥር አስመዝግባለች።

    የቪክቶሪያ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ሜልቦርን ሰኞ ዕለት ብቻ 19 ሟቾች መመዝገባቸው ተገልጿል።

    ቪክቶሪያ እስካሁን በአውስትራሊያ ከተመዘገቡት አጠቃላይ 314 ሞቶች እና 21 ሺ 400 አጠቃላይ ቫእረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል ሁለት ሶስተኛውን ይዛለች።

    ነገር ግን በየቀኑ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመቶዎች ቢሆንም ከዚህ በፊት ከነበረው አንጻር እየቀነሰ መምጣቱ ተዘጋቧል። ይህም ምናልባት የእንቅስቃሴ ገደቡ ለውጥ እያመጣ ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል።

    የሜልቦርን ሁለተኛ ዙር የቫይረሱ ስርጭት ከአንድ ወር በፊት ቢሆንም የጀመረው ነዋሪዎች ላይ የሰአት እላፊና ጠበቅ ያሉ ገደቦች የተጣሉት ከሳምንት በፊት ነው።

    ሰራተኞች ከቤታቸው ለመውጣት ልዩ ፈቃድ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ወሳኝ ያልሆኑ ሁሉም የንግድ ተቋማት ዝግ እንዲሆኑ ተወስኗል። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክም ቢሆን አስገዳጅ ተደርጓል።

    በቪክቶሪያ ብቻ ሰኞ ዕለት 322 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተዘግቧል። ነገር ግን ከአምስት ቀናት በፊት ከተመዘገበው ከፍተኛው 725 አንጻር ቁጥሩ መቀነስ እያሳየ ነው።

    ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ በቪክቶሪያ ከ100 በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

  14. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች

    በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ የተያዘው የመጀመሪያው ሰው ካገኘች ዛሬ አምስት ወር ይሞላታል። በእነዚህ አምስት ወራት ውስጥ አምስት መቶ ሺህ ለሚጠጉ ናሙናዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎ፣ 22 818 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በዚህ አምስት ወር ውስጥ 407 ሰዎች ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አጥተዋል። በቫይረሱ ከተያዙት ግማሽ ያህሉም፣ 10 206፣ አገግመዋል።

    ባለፈው ሳምንትም 200 000 ሰዎችን ለመመርመር ያለመ ዘመቻ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ይፋ ተደርጎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል።

    በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከ40 በላይ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያዎች በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች እንደሚገኙ በአንድ ወቅት የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። እኚህ ባለስልጣን አክለውም በአሁኑ ሰዓት የአገሪቱ የመመርመር አቅም በቀን 10 ሺህ መሆኑን ገልፀው፣ 15 000 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው ነበር።

    እንደ የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል መረጃ ከሆነ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ከሚገኙ አገራት፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮና ግብጽ በመቀጠል ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የኮቪድ-19 ምርመራ አድርጋለች።

    በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ቁጥር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የሚገኙት በአዲስ አበባ ሲሆን፣ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እየሄደ ነው።

    በየቀኑ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር በጨመረ ቁጥር መያዛቸው የሚረጋገጥ ሰዎች ቁጥርም ማደጉ አይቀርም።

    በአብዛኛው ግለሰቦች ለቫይረሱ የሚጋለጡት የሚነገሩ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ቸል በማለት መሆኑን በተደጋጋሚ ጤና ባለሙያዎች ሲነገር እደመጣል። አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ሁሌም ልንተገብራቸው የሚገቡ የጥንቃቄ ተግባራት መሆናቸውን ያስታውሳሉ።

    የቢቢሲ አማርኛ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ የቀጥታ ዘገባዎችን ከአሁን ሰዓት ጀምሮ እናቀርባለን።

    መልካም ቀን!

    የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ያደረጉ እናቶች

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

  15. በዛሬው ዕለት 565 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 17 ህይወታቸው አለፈ

    እለታዊ ግራፊክስ

    በዛሬው ዕለት ለ9 ሺህ 35 ሰዎች በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ 565 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 22 ሺህ 818 እንዳደረሰው የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዕለታዊ መግለጫ አመላክቷል።

    በባለፉት ሃያ አራት ሰዓታት 17 ሰዎች መሞታው የተገለፀ ሲሆን አገሪቷ በኮሮናቫይረስ ያጣቻቸውን ዜጎች 407 አድርሶታል።

    በአገሪቷ ውስጥ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዛሬው ዕለትም 499 ሰዎች አገግመዋል። በአጠቃላይ ያገገሙ ዜጎች ቁጥርም 10 ሺህ 206 መሆኑንም ከመግለጫው መረዳት ይቻላል።

    አገሪቷ እስካሁን ድረስ 497 ሺህ 971 የላብራቶሪ ምርመራዎችን አከናውናለች።

  16. በብራዚል በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ አለፈ

    የመቃብር ሥፍራ

    የፎቶው ባለመብት, ANADOLU AGENCY/GETTY

    ብራዚል ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ከ100 ሺህ በላይ ሞት የመዘገበች ሲሆን ይህም በዓለማችን ካሉ አገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል።

    በአገሪቷ ቫይረሱ በሦስት ወራት ውስጥ 50 ሺህ ሰዎችን የገደለ ሲሆን ይህ ቁጥር በ50 ቀናት ውስጥ እጥፍ ሆኖ ተመዝግቧል።

    ከ3 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎችም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። የወረርሽኙ ሥርጭት እስካሁን ጣሪያው ላይ ባይደርስም ሱቆችና ምግብ ቤቶች ግን እንደገና ተከፍተዋል።

    የአገሪቷ ፕሬዚደንት ቦልሶናሮ ቫይረሱ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ አቃለው ያዩት ሲሆን በሽታውን ለመቆጣጠር የተወሰዱ እርምጃዎችንም ኢኮኖሚውን ይጎዳል በማለት ተቃውመውታል።

    ራሳቸው በቫይረሱ ተይዘው ያገገሙት ፕሬዚደንቱ፤ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በግዛት አስተዳዳሪዎች የተጣሉ ገደቦች ላይም አልተስማሙም ነበር።

    በተደጋጋሚም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ደጋፊዎቻቸው በተሰበሰቡበት ተገኝተዋል።

    ባለሙያዎች ባለሥልጣናት የወረርሽኙን ሥርጭት ሊጨምረው በሚችለው ኢኮኖሚውን ማስጀመር ላይ ትኩረት በማድረጋቸው "የቦልሶናሮ መንግሥት የተቀናጀ እቅድ የለውም" ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

    የፌደራል መንግሥት ለወረርሽኙ የሚሰጠው ምላሽ የሚመራውም ምንም የሕብረተሰብ ጤና ልምድ በሌላቸው የጦር ጀነራል ነው።

    ከዚህ ቀደም ሁለት የጤና ሚኒስትሮች አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ እና በሽታውን ለማከም ውጤታማ እንዳልሆነ በጥናት የተገለፀውን ሃይድሮክሲክሎሮኪን መድሃኒት በመጠቀም ረገድ ከፕሬዚደንቱ ጋር ባለመስማማታቸው ሥራቸውን ለቀዋል።

    ፕሬዚደንቱ ‘ቀላል ጉንፋን’ ብለው ከሚጠሩት ኮቪድ -19 በፀረ ወባ መድሃኒት ማገገማቸውን መግለፃቸውን ተከትሎ ከአገር ውስጥም ከውጭም ትችት ተሰንዝሮባቸዋል።

  17. በሕንድ በኮቪድ ጊዜያዊ ሆስፒታል ባጋጠመ የእሳት አደጋ ቢያንስ አስር ህሙማን ሞቱ

  18. በድሬዳዋ ከሃያ በላይ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች በኮቪድ-19 ተያዙ

  19. የነሐሴ 3/2012 ዓ.ም. የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ

    ጫማ የሚጠርግና የሚያስጠርግ ግለሰቦች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አድርገው

    እንደምን አደራችሁ የተከበራችሁ ተከታታዮቻችን?

    ቢቢሲ አማርኛ ኮሮናቫይረስን የተመለከቱ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ መረጃዎችን ወደ እናንተ ማድረሱን ቀጥሏል።

    የቫይረሱ ሥርጭት በተለይ በአንዳንድ አገራት በአስጊ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው። በአፍሪካም እስካሁን 1 ሚሊየን 35 ሺህ 929 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 22 ሺህ 922 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

    በአህጉሪቷ ካሉ አገራትም ደቡብ አፍሪካና ግብፅ ክፉኛ በቫይረሱ ተጠቅተዋል።

    በአገራችንም በቫይረሱ የሚያዙና ሕይወታቸው የሚያልፉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋትም የበሽታውን ሥርጭት ወደ ከፋ ደረጃ ያደርሰዋል የሚል ከፍተኛ ስጋት አለ።

    በመሆኑም ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ የጤና መመሪያዎችን በመተግበር ራሳችንንና ማህበረሰባችንን ከበሽታው እንጠብቅ እንላለን።

    መልካም ቀን ይሁንላችሁ!

  20. ባለፉት 24 ሰዓታት 801 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተነገረ

    COVID-19

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት 801 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ሲረጋገጥ 10 ሰዎች ደግሞ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ህይወታቸው አልፏል። 801 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው ከ10ሺህ919 ሰዎች ናሙና ተወስዶ ነው። ኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ሪፖርት ከተደረገ ወዲህ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 22ሺህ 253 ደርሷል።