በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 30 ሺህ ተጠጋ
በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የማሕበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ሲሆን ከዚህ ቀደም በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ በመቶዎች ይገኝ የነበረው ወደ ሺህ ተሻግሯል። በትናንትናው ዕለትም ከፍተኛ የተባለው 1ሺህ 652 እንዲሁም በዛሬው ዕለት 982 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ቁጥሩ ወደ 30 ሺህ ተጠግቷል። አገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥር 528 አድርሶታል። በአጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 12 ሺህ 359 መድረሱን የጤና ሚንስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ አመላክቷል። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለ609 ሺህ 463ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ አከናውናለች። ሳይዘናጉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እራሳችንንና ሌሎችን ከበሽታው እንጠብቅ።
የቀጥታ ሽፋን
የቤይሩት ፍንዳታን ተከትሎ በርካታ የህክምና ማዕከላት ጥቅም አልባ ሆነዋል
ኒውዚላንድ 14 በከሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች አገኘች
ሁለት ጊዜ ከቡራዩ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ያመለጡት እስረኞች እየተፈለጉ ነው
አዲሱን የሩሲያ የኮቪድ-19 ክትባት ምን የተለየ ያደርገዋል?
እንደምን አደራችሁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለአለም ስጋት ሆኖ እንደቀጠለ ሲሆን በዬቀኑም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እያሻቀበ ነው።
በአለማችን ከሃያ ሚሊዮን ሰዎች በላይ በቫይረሱ ተይዘዋል። በአገራችን የወረርሽኙ የማህበረሰብ ስርጭት እየጨመረ ሲሆን 25 ሺህ 118 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
አገሪቷም በኮሮናቫይረስ ያጣቻቸውን ዜጎች ቁጥር 463 ደርሷል፤ 11 ሺህ 34 ሰዎችም አገግመዋል።
አገሪቷ የመመርመር አቅሟን እየጨመረች መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን እስካሁንም ድረስ 535 ሺህ 431 የላብራቶሪ ምርመራዎችን አከናውናለች።
የተረጋገጠ ክትባትም ሆነ መድሃኒት በሌለበት ሁኔታ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም ጭምብል ማጥለቅ እንደሆነ ባለሙያዎች ምክራቸውን ይሰጣሉ። ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ አዳዲስ መረጃዎችን በዚህ ቀጥታ ዘገባችን ታገኛላችሁ።
በዛሬው ዕለት 943 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 23 መሞታቸው ተገለፀ

በኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት ለ14 ሺህ 540 ሰዎች በተደረገ ምርመራ 943 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን 25 ሺህ 118 አድርሶታል።
የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ እንደሚያመለክተው በዛሬው ዕለት የ23 ሰዎች ህይወት አልፏል። አገሪቷ በኮሮናቫይረስ ያጣቻቸውን ዜጎች ቁጥር 463 ደርሷል።
ከዚህም በተጨማሪ በባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 338 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን ይህም አጠቃላይ ቁጥሩን 11 ሺህ 34 እንዳደረሰው መግለጫው ጠቁሟል።
አገሪቷ የመመርመር አቅሟን እየጨመረች መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን እስካሁንም ድረስ 535 ሺህ 431 የላብራቶሪ ምርመራዎችን አከናውናለች።
የፍሎሪዳው የፖሊስ ኃላፊ ጭምብል ማድረግን አገዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሌሎች አገራት አካላዊ ርቀትን መጠበቅም ሆነ ጭምብል ማጥለቅ ይህን ያህል ጥያቄ ባይሆንም በኮሮናቫይረስ ክፉኛ እየተመታችው ባለችው አሜሪካ ጭምብል አወዛጋቢ ሆኗል።
በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶችም ጭምብል ማጥለቅ አስገዳጅ ሳይሆን ምርጫም ሆኗል።
በፍሎሪዳ ማሪዮን ከተማ የሚገኙ የፖሊስ ኃላፊ ግን ሰራተኞች ጭምብል እንዳያደርጉ አዘዋል። ኃላፊው ሰራተኞቻቸውን ብቻ ሳይሆን ለስራም የሚመጡ ደንበኞችም ጭምብል ማድረግ አይችሉም ብለዋል።
"በኔ ስር ያሉ ሰራተኞችም ሆነ ቢሮውን የወከሉ ሰራተኞች ጭምብል ማድረግ አይችሉም፤ ይህ የኔ ትዕዛዝ ነው" በማለት የፖሊስ ኃላፊው ቢሊ ውድስ በኢሜይል ትዕዛዝ መስጠታቸውን ኤቢሲ በዘገባው አስነብቧል።
በፍሎሪዳዋ ኦካላ ከተማም እንዲሁ ፖሊሶች ጭምብል እንዳያጠልቁ የተባሉ ሲሆን ይህም ከነዋሪው ጋር ያላቸውን ንግግር ቀለል እንዲያደርግ ነውም ተብሏል።
ፍሎሪዳ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ ግዛቶች አንዷ ስትሆን ከግማሽ ሚሊዮን ሰዎች በላይም በቫይረሱ ተይዘዋል።
አንድ የባርሴሎና እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች በኮቪድ-19 ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባርሴሎና እግር ኳስ ክለብ አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ የቡድኑ አባል የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎለት በቫይረሱ መያዙ መረጋገጡን አስታወቀ።
ባርሴሎና እንዳስታወቀው ተጫዋቹ ለቀጣዩ ዓመት ዝግጅት ከሚያደርገው ቡድን ጋር ልምምድ ሲያደርግ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰአት በቤቱ ውስጥ እራሱን ለይቶ ይገኛል።
ተጫዋቹ ምንም አይነት ምልክት እንዳልንበረውም ቡድኑ ገልጿል። አክሎም ለአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ልምምድ ለማድረግ ሐሙስ ዕለት ወደ ሊዝበን ከሚጓዘው ቡድን ጋር ምንም አይነት ንክኪ እንዳልነበረው ቡድኑ ገልጿል።
በስፔን ሊግ ከሚሳተፉ ቡድኖች መካከል እስካሁን ቫሌንሺያ በያዝነው ሳምንት አንድ ተጫዋች በቫይረሱ እንደተያዘበት ያስታወቀ ሲሆን አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ ሁለት ተጫዋቾቹ ስለመያዛቸው ገልጿል።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ማቋመሪያ መንደር ከወራት በኋላ ስራ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
በርካታ ማቋመሪያ ቤቶች የሚገኙባት ማካው በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የቁማር ገበያ ወደቀደመው ለመመለስ በማሰብ ለጎብኚዎች ቪዛ መስጠት ጀምራለች።
የእስያ የቁማር ማዕከል እንደሆነች የሚነገርላት ማካው ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ጎብኚዎቿ ጠፍተው የሙታን መንደር መስላ ነበር ተብሏል።
የማካው ባላስልጣናት እንደሚሉት ቀስ በቀስ ከረቡዕ ጀምሮ ለቱሪስቶች ቪዛ በመስጠት ነገሮችን ወደነበሩበት ለመመለስ እቅድ ተይዟል። ዘርፉ ባለሙያዎች እንደገመቱት ከሆነ የቁማር ቤት ባለቤቶች በየቀኑ እስከ 15 ሚሊየን ዶላር ድረስ ወጪ ያወጣሉ።
በግልና በቡድን የሚመጡ ቻይናውያን በሂደት ቪዛቸውን እንዲያገኙ ይደረጋል ተብሏል። ማካው ልክ እንደ ሆንግ ኮንግ ሁሉ በቻይና ስር ልዩ ራስ ገዝ አስተዳደር ነች።
ነገር ግን ባለስልጣናቱ ከቻይና ውጪ ለሚመጡ ቱሪስቶች ቪዛ ይሰጥ አይሰጥ አልያም መቼ መሰጠት እንደሚጀመር ምንም ያሉት ነገር እንደሌለ ተገልጿል።
የማካው ኢኮኖሚ በቱሪዝምና በቁማር ላይ በእጅጉ የተመሰረት ሲሆን ከወረርሽኙ በኋላ ግን ኢኮኖሚው 49 በመቶ ቀንሷል። ከዚህ በተጨማሪም ለጉብኝት ይመጡ የነበሩ ሰዎች ቁጥር 84 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
የሩስያ ክትባት ትችት በዝቶበታል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በርካቶች ሩስያ ለኮቪድ-19 ክትባት ፍቃድ የመስጠቷ ጉዳይ አልተዋጠላቸውም። ክትባቱ ጥቅም ላይ መዋል ይችላል የተባለበት ፍጥነት ክትባቱን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸው የጤና ባለሙያዎችም አሉ።
የሩስያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን እነዚህ አስተያየቶች ችላ ብለው፤ ክትባቱ ላለፉት ሁለት ወራት ሲሞከር እንደነበረና ፍቃድ እንዳገኘ አስታውቀዋል።
ፑቲን ክትባቱ ከዓለም ግንባር ቀደሙ ነው ቢሉም፤ የአሜሪካው የጤና ተቋም ጸሀፊ አሌክስ አዛር አልተቀበሉትም። “ክትባት መሥራት ውድድር አይደለም። ከፍጥነት ይልቅ ውጤታማና አስተማኝ ክትባት መሥራት ነው ቁም ነገሩ” ብለዋል።
የአሜሪካ የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያው ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ፤ የሩስያ ክትባት ጉዳይ “በጣም ያጠራጥረኛል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
አያይዘውም “ሩስያውያኑ ክትባቱ ውጤታማና አስተማማኝ መሆኑን አረጋግጠዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
የአሜሪካው ምርምር በቀጣዩ ዓመት አጋማሽ 300 ሚሊዮን ክትባቶች የማምረት እቅድ ይዟል።
የሩስያ ክትባት የተተቸው በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ አገራት ጭምርም ነው።
የጀርመን ጤና ሚንስትር ጀንስ ሳፊን “ክትባቱ በአግባቡ ካልተመረመረ፤ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ክትባቱን መስጠት አደገኛ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
ኬንያ ስለ ክትባት ከሩስያ ጋር እነጋገራለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኬንያ የጤና ጥበቃ ባለሥልጣኖች በክትባት ዙርያ ከሩስያ ጋር በቅርበት እንደሚሠሩ አስታወቁ።
ካፒታል ኤፍኤም ራድዮ እንደዘገበው፤ የተቋሙ ከፍተኛ ጸሐፊ ሜርሲ ሙዋንጋጊ “ክትባቱን ከመጠቀማችን በፊት አስተማማኝነቱን ለማረጋገጥ ከሩስያ ጋር አንሠራለን” ብለዋል።
ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ፤ የኬንያ መንግሥት ከሩስያ ጋር የሚያደርገውን ንግግር በተመለከተ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አሠራርን እንደሚከተል ተናግረዋል።
የሩስያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ለኮቪድ-19 የሚሆን ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ መሰጠቱን መግለጻቸው ይታወሳል።
ክትባት በማስመዝገብ ረገድ ሩስያ የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች። ሆኖም ግን ሩስያ ክትባቱን ያዘጋጀችበት ፍጥነት ላይ ብዙ ባለሙያዎች ጥያቄ እያነሱ ነው።
የሩስያ ተመራማሪዎች የዘለሉት ደረጃ ይኖራል ያሉ ባለሙያዎችም አሉ።
በኬንያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 27,425 ደርሷል።
በኮቪድ-19 ሳቢያ የሞቱ ሰዎች 741 ሺህ ደርሰዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨረስቲ መረጃ መሠረት በመለው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 20.2 ሚሊዮን ሲደርስ፤ 741 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ከተለያዩ አገሮች የተሰባሰቡ ዘገባዎችን እንቃኝ፦
ዩናይትድ ኪንግደም፡ ባለፉት 11 ዓመታት ባልታየ ሁኔታ የምጣኔ ሀብት ድቀት ገጥሟታል። ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በ20.4 በመቶ አሽቆልቁሏል።
የተለያዩ የአውሮፓ አገራት፡ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ሌሎችም የአውሮፓ አገሮች ውስጥ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየጨመረ ነው። ባለሥልጣኖችም ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ነው።
አውስትራሊያ፡ በአገሪቱ በአንድ ቀን በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ከፍተኛው ቁጥር ተመዝግቧል። ቪክቶሪያ ግዛት ውስጥ 21 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ሩስያ፡ ለኮቪድ-19 ክትባት ፍቃድ የመሰጠቱ ጉዳይ ከአሜሪካ የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ አጭሯል።
ኒው ዚላንድ፡ ባለፉት 102 ቀናት በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ያልመዘገበችው ኒው ዚላንድ ውስጥ አራት ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን ተከትሎ በኦክላንድ ግዛት የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል።
በኒው ዚላንድ ከ102 ቀናት በኋላ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ላለፉት 102 ቀናት በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ያላገኘችው ኒው ዚላንድ፤ አውክላንድ በተባለ ግዛቷ አራት ቫይረሱ ያለባቸው ግለሰቦች አግኝታለች።
በከተማዋ ዳግመኛ የሦስት ቀን የእንቅስቃሴ ገደብም ተጥሏል።
በበሽታው የተያዙት አራት ግለሰቦች የአንድ ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ፤ የቅርብ ጊዜ የጉዞ ታሪክ የላቸውም።
ከግለሰቦቹ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች ለመለየት እየተሞከረ ይገኛል።
የኦክላንድ ነዋሪዎች ከቤት እንዳይወጡ፣ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ የንግድ ዘርፎች ውጪ ያሉት እንዲዘጉ እንዲሁም ሰዎች በብዛት እንዳይሰበሰቡም ውሳኔ ተላልፏል።
በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ100 በላይ ሠራተኞች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተነገረ
እንደምን አደራችሁ?
የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ? የቀጥታ ዘገባ ገጻችን ተጀምሯል። ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ዘገባዎችን ወደ እናንተ እናደርሳለን።
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ24 ሺህ አልፏል። ራሳችሁንና ቤተሰባችሁን ከወረርሽኙ ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አትዘንጉ።
መልካም ቀን!

የፎቶው ባለመብት, Metema wereda communication affairs office
ከመቶ በላይ ክትባቶች ላይ ምርምር እየተደረገ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሩስያ ላለፉት ሁለት ወራት በሰዎች ላይ ሙከራ የተደረገበት ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል መፈቀዱን አስታውቃለች።
የምዕራቡ ዓለም ተመራማሪዎች ግን ክትባቱ ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው።
ከሩስያው በተጨማሪ ከ100 የሚበልጡ ክትባቶች ላይ ምርምር እየተደረገ ሲሆን፤ ከ20 በላዮቹ በሰው ላይ እየተሞከሩ ነው።
አሜሪካ ስድስት ክትባቶች ላይ ምርምር እያደረገች ሲሆን፤ የተላላፊ በሽታዎች ሙያተኛው ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ እንደሚሉት፤ በዚህ አመት መጨረሻ “አስተማማኝና ውጤታማ” ክትባት ይገኛል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አራት ክትባቶችን ለማምረት ስምምነት ተፈራርሟል። ይህም በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲና በአስትራዜንካ ተቋም ጥምረት የሚሠራውን 100 ሚሊዮን ክትባት ማምረትን ያካትታል።
ከዚህ በተጨማሪ ኢንዶኔዥያ እና ሜክሲኮም የክትባት ምርምር የመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ በአንድ ቀን 20 ሰዎች በኮቪድ-19 ሕይወታቸው አለፈ

በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በ11 ሺህ 881 ናሙናዎች ላይ በተደረገ ምርመራ፤ 584 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋገጠ።
የጤና ሚንስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም በጋራ በሰጡት መግለጫ መሠረት፤ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 24 ሺህ 175 ደርሷል።
ተጨማሪ 20 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ የሟቾች ቁጥር 440 ደርሷል።
190 ሰዎች በጽኑ እንደታመሙና፤ 285 ተጨማሪ ሰዎች ከበሽታው እንዳገገሙ ተገልጿል። ይህም ከበሽታው ያገገሙ ሰዎችን ቁጥር 10 ሺህ 696 አድርሶታል።
ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ባጠቃላይ 520 ሺህ 891 ናሙና ላይ ምርመራ ተካሂዷል።
በአማራ ክልል 23 የሕክምና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Metema wereda communication affairs office
በአማራ ክልል ባለፉት ወራት በተደረገ የኮሮናቫይረስ ምርመራ 83 አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተገለጸ።
በአማራ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፤ የሕብረተሰብ ጤና ኢመርጀንሲ ማኔጅመንት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ አሌ አያል እንደገለፁት፤ በክልሉ በተለይ ተጋላጭ ናቸው በሚል የተለዩ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው ላይ በተደረገ ምርመራ ነው ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቀው።
እስካሁን በአማራ ክልል በሚገኙ 48 ወረዳዎች ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች በምርመራ ተገኝተዋል።
ቫይረሱ በብዛት የተገኘው በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ አካባቢ መሆኑን የገለፁት አቶ አሌ፤ አካባቢው ከሱዳን ጋር አዋሳኝ መሆኑን እና የሰዎች እንቅስቃሴ ከፍተኛ መሆኑን በምክንያትነት አስቀምጠዋል።
በክልሉ በስፋት ከተጠቁት የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል የቀን ሠራተኞች እንደሚገኙበት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በሥራቸው፣ በአኗኗር ዘይቤያቸው እና ባላቸው ሰፊ ግንኙነት ምክንያት 259 የሚሆኑ የቀን ሠራተኞች የኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው በምርመራ ለማወቅ ተችሏል ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ተጋላጭ ናቸው የሚባሉት የሕክምና ባለሙያዎች በክልሉ በተለየ ሁኔታ ተጠቅተዋል ባይባልም፤ አሁን ቁጥሩ እየጨመረ 23 ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ገልጸዋል።
እስካሁን ድረስ በአማራ ክልል ከ42 ሺህ 752 በላይ ናሙናዎች ላይ የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጓል።
