“የአገራችን እድገት እንዲስተጓጎል ምክንያት አንሁን” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛን ለማስተዋወቅ በጀመረው ዘመቻ ኢትዮጵያ “ማስክ ኢትዮጵያ” በሚል መቀላቀሏን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው አስፍረዋል።
“በዚህ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ዘመቻ የሁላችንም ተሳትፎ ጨምሮ፣ እውቀታችን አድጎ፣ ባህሪያችንም ተለውጦ፣ ወረርሽኙን በተሻለ አቅም መከላከል እንችላለን ብዬ አምናለሁ” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሁሉም ሰው ጭምብልን በትክክልበማድረግ፣ ሁልጊዜም በመጠቀም ከራሳችን አልፎ ወገኖቻችንም ከበሽታ እንጠብቅ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
“አንድም ሰው በበሽታ እንዲያዝ፣ የማይተካ ሕይወት እንዲያልፍ፣ የአገራችን እድገት እንዲስተጓጎል ምክንያት አንሁን” ብለዋልፕሬዝዳንቷ።
አክለውም “የሁላችንም ያልተቋረጠና የተባበረ ጥረት ወረርሽኙን ለማሸነፍ ይሁን”
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት ውጤታማ ከሆኑት መከላከያዎች መካከል አካላዊ ርቀት መጠበቅና ጭምብል ማጥለቅ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት በተደጋጋሚ ሲያሳስብ ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Office of the President













