በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 21 ሺህ ተጠጋ

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የማህበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 21 ሺህ ተጠግቷል። ይህንንም ተከትሎ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር "ማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ" በትናንትናው ዕለት የብሄራዊ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በይፋ አስጀምረዋል።ዘመቻው አገር አቀፍ ንቅናቄ በማድረግ ማህበረሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በሃላፊነትና በንቃት እንዲተገብር የሚያስችል እና ሰፊ ምርመራ በማድረግ የወረርሽኙን ሁኔታ ይበልጥ በማወቅ ቀጣይ ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል። "ማንም" የሚል ስያሜ የተስጠው ዘመቻ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን በነሃሴ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት 200 ሺህ ሰዎችን የመመርመር ዕቅድ ተይዟል። አገሪቷ እስካሁን ድረስ 444 ሺህ 226 የላብራቶሪ ምርመራዎችን አከናውናለች።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሜክሲኮ ከፍተኛ የሞት ቁጥር በማስመዝገብ ሦስተኛዋ አገር ሆነች

    ሜክሲኮ

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    ሜክሲኮ በዓለማችን ላይ ከአሜሪካ እና ብራዚል በመቀጠል በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከፍተኛ ሞት በማስመዝገብ ሦስተኛዋ አገር ሆነች።

    እስካሁን በአጠቃላይ 46 ሺህ 688 ሰዎች በቫይረሱ የሞቱ ሲሆን፤ 424 ሺህ 637 ደግሞ በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ከዚህ ቀደም ዩናይትድ ኪንግደም ነበረች ሦስተኛውን ቦታ ይዛ የነበረው። እስከ አርብ ድረስ የነበረው ቁጥርም 46 ሺህ 204 ነው።

    የሜክሲኮ ባለስልጣናት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ከተዘገበውም በላይ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።

    ፕሬዝደንት አንድሬስ ማኑዌል ሎፔዝ ደግሞ እየተዳከመ የመጣውን ምጣኔ ሀብት እንዲያንሰራራ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ ይፈልጋሉ።

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ በዓለማችን ላይ እስካሁን 17.5 ሚሊየን ሰዎች በኮሮረናቫይረስ የተያዙ ሲሆን፤ 679 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    አሜሪካ እስካሁን 153 ሺህ 415 ሞት ስታስመዘግብ ብራዚል ደግሞ 92 ሺህ 475 ሞት ማስተናገዷን አስታውቃለች።

    የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የወረርሽኙ ጉዳት እስከ መጪዎቹ ዓሥርት ዓመታት ድረስ የሚስተዋል ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቋል።

  2. የአውሮፓ አገሮች ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ድቀት ገጥሟቸዋል

    አውሮፓ

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    የአውሮፓ አገራት በኮቪድ-19 ሳቢያ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ድቀት ገጥሟቸዋል።

    ስፔን በዘመናዊ ታሪክ ያልታየ የምጣኔ ሀብት ውስጥ ገብታለች። የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ድረስ 18.5 በመቶ ቀንሷል። ይህም በዓመቱ መባቻ ከቀነሰው 5.2 በመቶ በተጨማሪ ነው።

    ከዩሮዞን አገራት በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳችው ስፔን ስትሆን፤ የፈረንሳይ ምጣኔ ሀብትም ከፍተኛ ጫና ደርሶበታል። በሁለተኛው መንፈቀ ዓመት ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በ13.8 በመቶ አሽቆልቁሏል።

    በፈረንሳይ የስታትስቲክስ ተቋም መረጃ መሠረት ደግሞ፤ ሚያዝያ ላይ ከፍተኛ ውድቀት ገጥሞ ነበር። ግንቦት እና ሰኔ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ሲላላ ግን መሻሻል ታይቷል።

    ከአውሮፓ አገሮች በግንባር ቀደምነት በወረርሽኙ የተጎዳችው ጣልረያን፤ ምጣኔ ሀብቷ በ12.4 ቀንሷል።

    በመላው አውሮፓ የአገራት ምጣኔ ሀብት በ11.9 ቀንሷል። ይህም ከጎርጎሮሳውያኑ 1995 ወዲህ ከፍተኛው ነው።

  3. በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 21 ሺህ ተጠጋ

  4. የቢቢሲ አማርኛ የዕለተ ቅዳሜ ሐምሌ 25/2012 ዓ.ም የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    ቢቢሲ አማርኛ

    እንደምን አደራችሁ?

    ቅዳሜ ሐምሌ 25/2012 ዓ.ም

    ለመከላከል ከሚረዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ውጪ ክትባትም ሆነ መድኃኒት ባልተገኘለት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያዙት ሰዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው።

    ከቢቢሲ አማርኛ በየዕለቱ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ በየደቂቃው የሚወጡ ዜናና መረጃዎችን በተለይ በዚህ ገጽ ላይ በቀጥታ ታገኛላችሁ።

    ስለወረርሽኙ ጠቃሚና ትኩስ መረጃዎችን ለማግኘት በአመቻችሁ አጋጣሚ ሁሉ ይህንን የቀጥታ ዘገባ ገጽ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

    በባለሙያዎች የሚመከሩ የበሽታውን የመከላከያ መንገዶች ተግባራዊ በማድረግ እራሳችሁንና ሌሎችን ከወረርሽኙ እንድትጠብቁ እያስታወስን መልካም ዕለት እንዲሆንላችሁ እንመኛለን።

  5. በአማራ ክልል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ አስገዳጅ ሆነ

    ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ

    የፎቶው ባለመብት, AMMA

    በአማራ ክልል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ከዛሬ ጀምሮ አስገዳጅ መሆኑን የክልሉ የኮሮናቫይረስ መከላከልና መቆጣጠሪያ ግብረ ኃይል ማስታወቁን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

    ውሳኔው የተላለፈው ወረርሽኙ በክልሉም ሆነ በአገሪቷ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመምጣቱና በሕብረተሰቡም በአስጊ ሁኔታ መዘናጋት በመታየቱ እንደሆነ ተገልጿል።

    የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተከለከሉ መመሪያዎችም እየተጣሱ መሆናቸውን የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ተናግረዋል።

    በባህርዳር ከተማ አስተዳደር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መልበስ አስገዳጅ መሆኑን ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፤ ከዛሬ ሐምሌ 24/2012 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ መሆኑን አስታውቀዋል።

    ይህንን በማያደርጉ ግለሰቦች ላይም እርምጃ እንደሚወሰድ በመግለፅ፤ የእምነት ተቋማት፣ መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ማህበረሰቡ ይህንንና ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አሳስበዋል።

    በክልሉ ስምንት የመመርመሪያ ማዕከላት መኖራቸውንና ሦስት ማዕከላትን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑንም ዶ/ር ሙሉነሽ ጠቅሶ መገናኛ ብዙኃኑ ዘግቧል።

  6. ኬንያ ለይቶ ማቆያ የማይገቡ ተጓዦች አገራትን ዝርዝር አወጣች

    አውሮፕላን ማረፊያ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, ኬንያ የአገር ውስጥ በረራ የጀመረችው ከ15 ቀናት በፊት ነበር

    አገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽንን ለመቆጣጠር ሲባል አቋርጠውት የነበረውን በረራ እንደገና እየመለሱ ነው።

    የኬንያ መንግሥትም ለአራት ወራት አቋርጦት የነበረውን ዓለም አቀፍ በረራ ነገ፣ ሐምሌ 25፣ 2012 ዓ.ም እንደሚጀምር አስታውቋል።

    ይህንንም ተከትሎ ወደ ለይቶ ማቆያ የማይገቡ ተጓዦች አገራትን ዝርዝር አውጥታለች።

    ይሁን አንጂ ማንኛውም መንገደኛ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የሙቀት ልኬት የሚደረግለት ሲሆን ከመጓዛቸው ከአራት ቀናት በፊት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረጋቸውን ማሳየት አለባቸው ተብሏል።

    በዝርዝሩ ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ኡጋንዳና ሩዋንዳን ጨምሮ ከ18 አገራት የሚመጡ መንገደኞች ለይቶ ማቆያ መግባት ከማይጠበቅባቸው አገራት ዝርዝር ተካተዋል።

    አሜሪካም በዝርዝሩ ውስጥ የተካተተች ቢሆንም ከካሊፎርኒያ፣ ፍሎሪዳ እና ቴክሳስ የሚገቡ መንገደኞችን ግን እንደማይመለከት ተገልጿል።

    በወረርሽኙ ሳቢያ በተጣሉ ገደቦች ሳቢያ ክፉኛ ተመትቶ ለነበረው የኬንያ ቱሪዝምም ይህ መልካም ዜና ሆኗል።

  7. በዛሬው ዕለት ከፍተኛ የተባለው 915 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተያዙ

    ግራፊክስ

    በኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት በተደረገው 8 ሺህ 957 የላብራቶሪ ምርመራ አገሪቱ መዝግባው የማታውቀው 915 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን አረጋግጣለች።

    ከእነዚህ መካከል 40 ከትግራይ ፣ 127 ከኦሮሚያ ፣ 7 ከሲዳማ ፣37 ከደቡብ ፣ 20 ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣5 ከአፋር ፣ 23 ከጋምቤላ ፣ 22 ከአማራ ፣ 1 ከድሬዳዋ ፣ 6 ከሃረሪ እና 627 ከአዲስ አበባ የተገኙ ናቸው።

    በዚህም መሰረት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 17 ሺህ 530 ሰዎች መድረሱን የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚያወጡት የጋራ እለታዊ መግለጫ አመላክቷል።

    በዛሬው ዕለት የ11 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ በአጠቃላይ አገሪቷ 274 ዜጎቿን በኮሮናቫይረስ አጥታለች።

    ከዚህም በተጨማሪ በዛሬው ዕለት 187 ሰዎች ማገማቸውን ተከትሎ፤ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 6 ሺ 950 መድረሱን መግለጫው ጠቁሟል።

    አገሪቱ እስካሁን ያከናወነችው የላብራቶሪ ምርመራ 422 ሺህ 354 ነው።

  8. በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ በረራዎች እየተጀመሩ ነው

  9. የአለም አቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት በዳርፉር ያለውን የጤና ተቋማት ዘጋ

    እቃ የተሸከሙ ሕፃናት

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የአለም አቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት ፤ በሱዳን ዳርፉር እየተባባሰ በመጣው የብሔር ጥቃት ሳቢያ በአካባቢው ያሉ ሁለት የጤና ተቋማትንና የመስክ ቢሮውን ለመዝጋት መገደዱን አስታወቀ።

    ይህም 14 ሺህ ሕፃናት የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ አድርጓል ብሏል።

    እነዚህ ተቋማት በአካባቢው ለሕፃናት የምግብ እና ጤና እንክብካቤ የሚሰጡ ብቸኛ ተቋማት ነበሩ።

    ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በምዕራብ ዳርፉር በርካታ ጥቃቶች ተፈፅመዋል። ባለፈው ሳምንት 500 ታጣቂዎች ማስተሬ በተባለው አካባቢ በፈፀሙት ጥቃት ከ60 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

    መንግሥትም ለሰዎች ሕይወት መጥፋትና ለሺዎች መፈናቀል ምክንያት የሆነውን ጥቃት ለማስቆም ተጨማሪ ወታደሮችን በአካባቢው እያሰማራ ነው።

  10. ሆንግ ኮንግ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ምርጫዋን ለአንድ ዓመት አራዘመች

  11. ቬትናም የመጀመሪያውን የኮቪድ-19 ሞት መዘገበች

  12. ሶማሊያ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ልትጀምር ነው

    በሞቃዲሾ የኤደን አየር ማረፊያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሶማሊያ መጋቢት ወር ላይ በቫይረሱ የተያዘ ሰው መገኘቱን ተከትሎ በዓለም አቀፍ በረራ ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ ማንሳቷ ተገለፀ።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን አሊ ኸይሬ ከሥልጣን ከተነሱ በኋላ ሐሙስ ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደ የካቢኔ ስብሰባ ዓለም አቀፍ በረራ ከሦስት ቀናት በኋላ እንዲጀመር ተወስኗል።

    የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ሞሃመድ ማሬይም “ ለረዥም ጊዜ በጉዳዩ ላይ ክርክር ከተደረገ በኋላ ሚኒስትሮቹ በሶማሊያ ተጥለው የነበሩ የኮሮናቫይረስ መመሪያዎችን ለማላላት ወስነዋል። ከሦስት ቀናት በኋላም ዓለም አቀፍ በረራዎች እንዲጀመር ተስማምተዋል።” ሲሉ ውሳኔውን አሳውቀዋል።

    ሚኒስትሮቹም ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ከ15 ቀናት በኋላ ሊከፈቱ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

    ሐሙስ እለት የተካሄደው ይህ ስብሰባ በተወካይ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሀዲ ሞሃመድ ጉሌድ የተመራ ነበር።

  13. በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተቀዛቀዘው የዘንድሮው የአረፋ በዓል

    ምግብ እየሰፈሩ ያሉ ግለሰቦች

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ለቀድሞው ሞቅ ደመቅ ብሎ ይከበር የነበረው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በዚህ አመት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ቀዝቀዝ ብሏል።

    በተለይም አገራቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ብለው በጣሏቸው መመሪያዎች ምክንያት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሰብሰብ ብለው ማክበር ሳይችሉ ቀርተዋል።

    ከዚህ ቀደም በአረፋ በዓል ሙስሊሞች ከቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ ጋር ተሰባስበው ማዕድ መቋደስ፣ አብረው መፀለይ እና የተለያዩ ሃይማኖታዊ ተግባራትን ማከናወን ቢሆንም ወረርሽኙ እነዚህን እስላማዊ ባህሎችና አብሮነትን ቀጥ አድርገውታል።

    የኬንያዋ መዲና ናይሮቢ እንደ ቀድሞው ሳይሆን ጎዳናዎች ፀጥ ረጭ እንዳሉ ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቧል።

    "ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሴቶችና ልጆች ተሰባስበው በየጎዳናዎቹ አይታይም። ለበዓሉ የሚደረጉ ዝግጅቶች ለምሳሌ ልብስና የተለያዩ ቁሳቁሶችን መግዛት አልታዩም" በማለት ጋዜጣው አስነብቧል።

    አገሪቱ ወረርሽኙን ለመግታት በጣለችው መመሪያ ምክንያት መስጊዶች አሁንም እንደተዘጉ ነው፤ በዚችም ቅድስት ብለው በሚጠሯት እለት ሙስሊሞች በመስጊዶች መፀለይ አልቻሉም።

    ከሰሐራ በታች ባሉ አገራት ከፍተኛ የእስልምና እምነት ተከታዮች ባሏት ናይጄሪያም ፖሊስ ህዝቡ ተሰባስቦ እንዳያከብር በፅኑ ሲያስጠነቅቅ ነበር።

    የአረፋ በዓል ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ዒስማኤል ለመስዋዕት ሲያዘጋጁ በምትኩ በግ ለመስዋዕትነት የቀረበበት መሆኑን ድርሳናት ያመላክታሉ፡፡ ይህ ቀን የእርድ በዓል በመሆኑም በግ፣ ፍየል፣በሬ የመሳሰሉትን እንዳቅማቸው በርካቶች ያርዳሉ።

    የአለም ጤና ድርጅት በአረፋ በዓል የሚደረጉ መሰባሰቦች እንዳይከናወኑም ለአፍሪካ መንግሥታት አሳስቧል።

    በአረፋ በዓል ዋነኛ ሃይማኖታዊ ተግባራት ከሚባሉት መካከል ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመሄድ የሐጅ ስርዓት ማከናወን ቢሆንም በሁለት ሚሊዮን የሚቆጠሩ አማኞች ይገኙ በነበረበት በዚህ ስርዓት በ10 ሺህ ብቻ እንዲወሰን ተደርጓል።

  14. የዚምባብዌ ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ ሕይወታቸው አለፈ

    ሚኒስትር ፔሬንስ ሺሪ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዚምባብዌ የግብርና ሚኒስትር ፔሬንስ ሺሪ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ገልፀዋል።

    ሚኒስትሩ በኮሮናቫይረስ መሞታቸው የተረጋገጠው በምርመራ መሆኑንም የአገሪቱ መንግሥታዊ ጋዜጣ ሄራልድ ፕሬዚዳንቱን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

    ሚኒስትሩ የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት በሚያዘው በኮሮናቫይረስ ለሞቱ ሰዎች የሚደረገው የቀብር ስነ ስርዓት መመሪያ መሰረት በነገው እለት እንደሚቀበሩም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

    የ65 አመቱ ሚኒስትር በመዲናዋ ሃራሬ በሚገኝ የግል ሆስፒታል ረቡዕ እለት ሕይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል።

  15. ዛምብያ በአገር ውስጥ የሚካሄዱ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በድጋሚ አቋረጠች

    እግርኳስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዛምብያ እግርኳስ ማህበር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተጫዋቾቹና በቡድን አባላቱ መካከል በመስፋፋቱ ምከንያት በአገር ውስጥ የሚካሄዱ ጨዋታዎችን ሰረዘ።

    የማህበሩ የበላይ ኃላፊ አድሪያን ካሻላ እንዳሉት የሊጉ ጨዋታዎች የሚቀጥለው ሳምንት ሲጠናቀቅ ሁሉም የሊጉ ተሳታፊ ቡድኖች 27 ዙር ጨዋታዎችን አድርገው ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸው ነበር ተብሏል።

    የሊጉ ጨዋታዎች በመጋቢት ወር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ዳግም የተጀመረው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር።

    በዛምቢያ እግርኳስ ቡድን ተጨዋቾች መካከል ያለው የቫይረሱ ስርጭት መጨመሩ የተገለፀ ሲሆን ፎረስት ሬንጀርስ በተባለው ቡድን፣ 28 አባላቱ እንዲሁም ናብሳ ስታርስ ደግሞ 19 አባላቱ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገልጿል።

    የእግርኳስ ቡድኖቹ አባላት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ቢያደርጉም ውጤታቸው ሳይታወቅ ረዥም ጊዜ በመቆየቱ የተነሳ ጨዋታዎች በወቅቱ ማካሄድ አለመቻሉን ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።

    የእግር ኳስ ጨዋታው ተቋርጦ ቆይቶ በጥቅምት ወር አጋማሽ አካባቢ ዳግም እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

    ዛምብያ 5 ሺህ 555 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን በምርመራ ስታረጋግጥ ከእነዚህም መካከል 41 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

  16. የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ባለቤት በኮቪድ-19 መያዛቸው ተነገረ

    ቦልሶናሮና ባለቤታቸው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ከኮሮናቫይረስ ማገገማቸው ከተገለፀ በኋላ በሽታው ባስከተለባቸው ጉዳት የተነሳ አንቲ ባዮቲክስ እየወሰዱ መሆኑን ተናገሩ።

    “ደሜን ተመርምሬያለሁ፤ ትናንት ትንሽ ድካም ይሰማኝ ነበር። ኢንፌክሽን ስለተከሰተ አንቲባዮቲክስ እየወሰድኩ ነው” ብለዋል በቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት ባስተላለፉት መልዕክት።

    ቦልሶናሮ በቤተመንግሥታቸው ውስጥ ለአንድ ወር ያህል ራሳቸውን ለይተው ካቆዩ በኋላ “ሳምባቸው ላይ አነስተኛ ህመም” መኖሩን ጠቁመዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የታወቀው ሐምሌ መጀመሪያ ሳምንት የነበረ ሲሆን አሁን ሙሉ በሙሉ ማገገማቸው ተገልጿል።

    የቦልሶናሮ ባለቤት ሚቼል ቦልሶናሮ ደግሞ ሐሙስ ዕለት በቫይረሱ መያዛቸውን ከቤተመንግሥቱ የወጣ መረጃ ይፋ አድርጓል።

    ቦልሶናሮ ከዚህ በፊት ኮሮናቫይረስን “ቀላል ጉንፋን” በማለት ሲያቃልሉ የነበረ ሲሆን፣ የአገሪቱ ክልሎች የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት የጣሉትንም የእንቅስቃሴ ገደብ ምጣኔ ሃብቱን ይጎዳል በሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል።

  17. በቬትናም በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተከሰተ የመጀመሪያው ሞት ተመዘገበ

    ቬትናም

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ቬትናም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለም ላይ ከተከሰተ ወዲህ የመጀመሪያውን ሞት ዛሬ አስመዘገበች።

    የቬትናም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን እንደገለጹት ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ አንድም ሰው በቫይረሱ ምክንያት ያልሞተ ሲሆን አሁን ግን ዳግም በተቀሰቀሰው ወረርሽኝ ምክንያት አንድ ግለሰብ መሞቱን ዘግበዋል።

    ቬትናም ዛሬ በመዝናኛ ከተማዋ ዳናንግ 45 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የገለፀች ሲሆን ይህም ወረርሽኙ በአገሪቱ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል።

    በዳናንግ የተመዘገበው ይህ ቁጥር በአገሪቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 509 አድርሶታል።

    በአገሪቱ ከሦስት ወር በኋላ በዚህች በቱሪስቶች በምትዘወተር ከተማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዳግም ተቀስቅሷል።

    የቬትናም ባለስልጣናት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እየጣሩ ሲሆን ከ100 በላይ የህክምና ባለሙያዎች ወደ ዳናንግ ድጋፍ ለመስጠት ተልከዋል።

    በዋና ከተማዋ ሃኖይ የኮቪድ-19 ምርመራ በስፋት እየተደረገ ሲሆን መሰባሰብም ተከልክሏል።

    ቬትናም የኮሮናቫይረስን ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ለማዋል ከፍተኛ ምርመራ እና ንክኪ የመለየት በመስራቷ ስትንቆለጳጰስ ነበር።

  18. በህንድ በአንድ ቀን ብቻ በኮቪድ-19 ምክንያት 800 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

    ሕንድ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በሕንድ ሐሙስ ዕለት ብቻ በኮሮናቫይረስ የተያዙ 800 ሰዎች መሞታቸው የተገለፀ ሲሆን ይህም በአገሪቱ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 35,500 አድርሶታል።

    በአሁኑ ሰዓት ሕንድ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጣልያን በመቅደም አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

    በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ 54,000 ሰዎች የተገኙ ሲሆን ይህም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ወደ 1.6 ሚሊዮን ከፍ እንዲል አድረጓል።

    በዚህም የተነሳ ሕንድ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ በኮቪድ-19 በተያዙ ሰዎች ቁጥር ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

    በሕንድ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል በሚል መጋቢት ወር ላይ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ሰኔ ወር ላይ መላላት ጀመሯል።

    ረቡዕ ዕለት የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አዲስ የእንቅስቃሴ ገደቡን የሚያላላ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና ሆቴሎች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እንደሚከፈቱ አስታውቀዋል።

  19. የአውሮፓ ህብረት አልጄሪያን ወደ አውሮፓ መጓዝ ከሚችሉ አገራት ዝርዝር ሰረዘ

    በአልጄሪያሲያን መድሃኒት ሲረጭ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአውሮፓ ህብረት ከአልጄሪያ የሚመጡ ዜጎችን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ወደ አውሮፓ አገራት መግባት ከሚችሉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ሰረዘ።

    በአልጄሪያ በቅርቡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዳግም የተከሰተ ሲሆን እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ በአጠቃላይ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 29,229 ደርሷል።

    የአውሮፓ ህብረት ወደ አባል አገራቱ መግባት የሚችሉ አገራትን ዝርዝር ሲያስቀምጥ መስፈርቱ በአገራቱ ያለው የስርጭት መጠን እና ወረርሽኙን የመቆጣጠር አቅም ነው።

    አሁን በተሻሻለው ዝርዝር ውስጥ የሚገኙ አገራት አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ጆርጂያ፣ ጃፓን፣ ሞሮኮ፣ ኒው ዚላንድ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ኮርያ፣ታይላንድ፣ቱኒዚያ እና ኡራጋይ ናቸው።

    ይህ ዝርዝር የአውሮፓ አገራት ቱሪስቶችን መቀበል ከፈለጉ እንደ መመሪያ እንዲያገለግል ተብሎ የተሰናዳ ነው።

  20. ቦትስዋና በዋና ከተማዋ ዳግም እንቅስቃሴ ገደብ ጣለች

    ቦትስዋና በአገሪቱ ዋና መዲና ጋቦሮኔ ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የእንቅስቃሴ ገደብ አስቀመጠች።

    በከተማዋ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደቡ ሙሉ በሙሉ ሲሆን ወደ ከተማዋ ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ታግደዋል።

    ገደቡ የተጣለው አዲስ በቫይረሱ የተያዙ 30 ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ ነው።

    የእንቅስቃሴ ገደቡ ከትናንት እኩለ ለሊት ጀምሮ ተፈጻሚ መሆን ጀምሯል።

    "አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶች 25 በመቶ አቅማቸው ብቻ ይሰራሉ፤ በታሏቋ ጋቦሮኔ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አይፈቀድም። ከጋቦሮኔ መውጣትም ሆነ ወደ ከተማዋ መግባት ከአሁን ጀምሮ ተከልክሏል" ያሉት የአገሪቱ ኮቪድ-19 መከላከል ግብረ ኃይል አስተባባሪ ኬሬንግ ማሱፑ ናቸው።

    ቦትስዋና እስከ አሁን ድረስ 170 ሰዎች ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው፣ ሁለት ሰዎች ደግሞ ከዚሁ ጋር በተያያዘ መሞታቸውን በምርመራ አረጋግጣለች።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ