በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 21 ሺህ ተጠጋ

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የማህበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 21 ሺህ ተጠግቷል። ይህንንም ተከትሎ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር "ማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ" በትናንትናው ዕለት የብሄራዊ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በይፋ አስጀምረዋል።ዘመቻው አገር አቀፍ ንቅናቄ በማድረግ ማህበረሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በሃላፊነትና በንቃት እንዲተገብር የሚያስችል እና ሰፊ ምርመራ በማድረግ የወረርሽኙን ሁኔታ ይበልጥ በማወቅ ቀጣይ ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል። "ማንም" የሚል ስያሜ የተስጠው ዘመቻ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን በነሃሴ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት 200 ሺህ ሰዎችን የመመርመር ዕቅድ ተይዟል። አገሪቷ እስካሁን ድረስ 444 ሺህ 226 የላብራቶሪ ምርመራዎችን አከናውናለች።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በስፋት የሚደረግ የኮቪድ-19 ምርመራ የበሽታው ምልክት የማያሳዩትንም ማካተት አለበት-ቶኒ ብሌር

    ቶኒ ብሌር

    የፎቶው ባለመብት, PA Media

    የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚነስትር ቶኒ ብሌር በጅምላ የሚደረጉ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች ምልክቱን የማያሳዩ ሰዎችንም ቢያካትት ሌላ የእንቅስቃሴ ገደብ ላለመጣል እንደሚያግዝ ተናገሩ።

    የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታይምስ ከተሰኘ የሬዲዮ ጣብያ ጋር በነበራቸው ቃለመጠይቅ " 70 በመቶ ያህል ቫይረሱ ያለባው ሰዎች ምልክት አያሳዩም የሚል ግምት አለ፤ ስለዚህ ምልክት የሚያሳዩትን ብቻ የምንመረምር ከሆነ የምርመራ ስልቱ አብዛኛውን ህዝብ ያላማከለ ነው የሚሆነው" ሲሉ ተናግረዋል።

    ቶኒ ብሌር አክለውም ክትባት ወይንም ውጤታማ የሆነ ህክምና እስኪገኝ ድረስ የቫይረሱን ስርጭት በቁጥጥር ስር ለማዋል ያለው መፍትሄ ሰፊ ምርመራ ማድረግ ነው ብለዋል።

    አክለውም በብዛት ምርመራ ማድረግ ዳግም የእንቅስቃሴ ገደብ ከመጣል እንደሚታደግና ምጣኔ ሃብቱንም ቫይረሱን እየተቆጣጠሩ ማስቀጠል ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።

    ከዚህ ቀደም ቶኒ ብሌር ቫይረሱ ጥሎን ስለማይሄድ እንዴት አብረን መኖር እንዳለብን ልንማር ይገባል ብለው ነበር።

    • ከመንግሥት መግለጫ ጀርባ ያለው የሶማሊያ ኮቪድ-19 ሟቾች ቁጥር እውነታ ሲፈተሽ

    • የተባበሩት መንግሥታት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው አለም ቀውስ ይገጥማታል ሲል አስጠነቀቀ

      ዥዋዥዌ

      የፎቶው ባለመብት, Reuters

      የተባበሩት መንግሥታት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ዓለም "አጠቃላይ ቀውስ" እንደሚገጥማት አስጠነቀቀ።

      የድርጅቱ ዋና ፀኃፊ አንቶኒዩ ጉታሬስ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት፣ ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ትምህርት ቤቶችን መክፈት መሆኑን ተናግረዋል።

      ከ160 አገራት በላይ ትምህርት ቤቶችን የዘጉ ሲሆን ይህም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎችን ጎድቷል።

      ወርርሽኙ ከመከሰቱ አስቀድሞ 250 ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደነበሩ ሮይተርስ ዘግቧል።

      "አሁን ያልተነገረ የሰውልጅ አቅምን ያባከነ፣ ለአስርታት የተለፋበትን ሂደት መና ያስቀረ እና የነበረውን ኢ-ፍትሃዊነትን ያሰፋ አጠቃላይ ቀውስ ገጥሞናል" ብለዋል ጉታሬስ በንግግራቸው።

    • ሆን ብለው የሚስሉ ተጫዋቾች ቀይ ካርድ እንዲሰጣቸው ተወሰነ

      ቀይ ካርድ

      የፎቶው ባለመብት, Reuters

      በእግር ኳስ ጨዋታዎች ወቅት ሆን ብለው ሌሎች ተጫዎች ላይ የሚስሉ ተጫዋቾች ቀይ ካርድ እንዲሰጣቸው የእግር ኳስ ህግ አውጭዎችና ማህበሩ መወሰኑ ተገልጿል።

      የአለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ሆን ብሎ መሳል ከዚህ ቀደም ከነበሩት መሳደብ፣ የማይሆኑ ቃላትን መጠቀምና ምልክቶችን ማሳየት ከሚሉት ጥፋቶች ጋር እንደሚካተት አስታውቋል።

      ሆኖም እነዚህ ጥፋቶች እንዳሉ ሆነው የጥፋቶቹን አፈፃፀምና ዝርዝር ባህርይ በመረዳት የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያሳልፉት ዳኞች እንደሆኑም አስፍሯል።

    • አልጀሪያ መስጊዶችን ልትከፍት ነው

      መስጊድ ሲፀዳ

      የፎቶው ባለመብት, AFP

      የአልጀሪያ ፕሬዚዳንት አብደልማድጂድ ቴቡን መስጊዶች ቀስ በቀስ የሚከፈትበቱን ሁኔታ እንዲያጠኑ ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን አዘዙ።

      ከፍተኛ የፀጥታ አካካላት ስብሰባ ላይ ነው ፕሬዚዳንቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብደላዚዝ ድጀራድን ከአንድ ሺህ ሰዎች በላይ ሰዎች መያዝ የሚችሉ ትልልቅ መስጊዶች ላይ እንዲያተኩሩም ነግረዋቸዋል።

      ፕሬዚዳንቱ ትልልቅ መስጊዶችን የመረጡበት ምክንያትም ሲያስረዱ " አስፈላጊ የሚባለውን አካላዊ ርቀት መጠበቅ ስለሚያስችሉ" ነው ብለዋል።

      የፊት ጭምብል ማድረግ ግዴታ ነው ተብሏል።

      ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህር ዳርቻ መዝናኛዎች፣ ፓርኮችና ሌሎች ህዝባዊ ቦታዎች የሚከፈቱበትን ሁኔታ እየመከሩ እንደሆነም ተጠቅሷል።

      የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በሚል መስጊዶች፣ የባህር ዳርቻ መዝናኛዎችና ፓርኮች ተዘግተው ነበር።

      በአልጀሪያ እስካሁን ድረስ 30 ሺህ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል።

    • እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች!

      በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ወደ 20 ሺህ እየተጠጋ ነው። የሟቾች ቁጥር ደግሞ 336 ደርሷል። በርግጥ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥርም 7 ሺህ 931 መሆኑን ከጤና ሚኒስቴር መረጃ መረዳት ይቻላል። ትናንት ብቻ በኮቪድ-19 መያዛቸው ከተረጋገጠ 583 ሰዎች መካከል 386 ያህሉ ከአዲስ አበባ መሆናቸው ተገልጿል። እንዲሁም ሕይወታቸው ካለፈ 26 ሰዎች መካከልም 23 ግለሰቦች ከዚሁ ከዋና መዲናዋ አዲስ አበባ ነው።

      በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የምንኖር የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች የሆንን ሁሉ ራሳችንንም ሆነ ወዳጆቻችንን ለኮሮናቫይረስ ላለማጋለጥ አካላዊ ርቀታችንን መጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግና እጃችንን በውሃና በሳሙና በሚገባ መታጠብ እንዳለብን አንርሳ።

      ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ዋና ዋና መረጃዎችን በዚህ የቀጥታ ዘገባ ገፃችን ላይ እናቀርብላችኋለን።

      መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል!

      መልካም ቀን ከቢቢሲ አማርኛ ጋር!

      በጎድጓዳ እቃ የተቀመጡ አትክልቶች

      የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    • የጋምቢያ ሦስት ሚኒስትሮች ኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

      በጋምቢያ ሦስት ሚኒስትሮች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የአገሪቷ ፕሬዚደንት በሰጡት መግለጫ አስታወቁ።

      የገንዘብ ሚኒስተር ማምቡርህ ንጄ፣ የፔትሮሊየምና ኢነርጂ ሚኒስተር ፋፋ ሳንያንግ እና የግብርና ሚኒስተር አሜ ፋቡርህ በቫይረሱ መያዛቸውን በትዊተር ገፃቸው አጋርተዋል።

      ፕሬዚደንት አዳማ ባሮው፤ ምክትል ፕሬዚደንቱ ኢሳቶ ቶራይ በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ለይቶ ማቆያ ገብተው ነበር።

      በጋምቢያ እስካሁን 500 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ዘጠኝ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

      ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ሰው በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን አስገዳጅ ያደረገ ሲሆን መሰባሰብንም ከልክሏል።

      የ X ይዘትን ይለፉት
      ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

      ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

      ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

      የ X ይዘት መጨረሻ

    • አፍህን ሸፍን ሲባል መሳሪያ አውጥቶ የተኮሰው አሜሪካዊ

      የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ

      የፎቶው ባለመብት, Getty Images

      አንድ ፔንሳልቫንያ ውስጥ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ ሲጋራ ሊሸምት ባመራበት መገበያያ ሱቅ ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርግ ሲነገረው የሱቁን ባልደረባ ላይ መሳሪያ በመምዘዝ መተኮሱ ተገልጿል።

      አዳም ዛቦሮውስኪ የሚባለው ይህ ግለሰብ፤ ቤተልሄም በምትባል አነስተኛ ከተማ የፔንሳልቫንያ አነስተኛ ከተማ ውስጥ በምትገኝ ሲጋራ መሸጫ ሱቅ ለመግባት ሲሞክር ነው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርግ የተነገረው።

      የመደብሩ ሰራተኛ አዳምን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርግ አጥብቀው በመጠየቃቸው ሁለት ሲጋራ ሰርቆ ሊሄድ መሞከሩ ተገልጿል።

      የመደብሩ ሰራተኛ ግለሰቡን ውጪ ድረስ ተከትለው ሲጋራውን ለማስጣል ሲሞክሩ አዳም መሳሪያ በማውጣት መተኮሱ ተገልጿል።

      በሚቀጥለው ቀን ዛቦሮውስኪ ፖሊስ ላይ የተኮሰ ሲሆን፤ ከፖሊሶች ጋር በነበረው የተኩስ ልውውጥም ቆስሎ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።

      የዛቦሮውስኪ ጠበቃ ግለሰቡ በቅርቡ ስራውን ማጣቱን እንዲሁም ከባለቤቱ ጋር በነበረው የፍርድ ቤት ክርክር ባለቤቱ ልጁን እንድታሳድግ መወሰኑ እና በዚህም መጎዳቱን ጠቅሰው ተናግረዋል።

      “ በመልካም ጤንነት ላይ አይደለም፤ ስራውን አጥቷል፣ ልጁን አጥቷል፣ በወረርሽኙ ወቅት መከራ ተፈራርቆበታል።” ብለዋል።

    • ታንዛኒያ በኦንላይን ማንኛውንም ተቃውሞ ማስተባበርን አገደች

      የመከላከያ ልብስ የለበሰ ባለሙያ

      የፎቶው ባለመብት, Getty Images

      ታንዛኒያ በኦንላይን ማንኛውንም ዓይነት ተቃውሞ ማስተባበር የሚከለክል አዲስ ሕግ አወጣች።

      ይሁን እንጂ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች በኦንላይን የሚሰራጩ መረጃዎችን የሚወስነው አዲሱ ሕግ፤ የሰዎችን የመናገር ነፃነት ይወስናል ሲሉ ተቃውመውታል።

      በዚህ በአዲሱ ሕግ መሰረት በኦንላይን ማንኛውንም ሰልፍማስተባበር፣ ማቀድ እንዲሁም መደገፍ ሕገ ወጥ ነው። ከዚህም ባሻገር ከመንግሥት ፈቃድ ውጭ ስለ ወረርሽኙ ምንም ዓይነት መረጃ በኦንላይን ማጋራትንም ሕጉ ይከለክላል።

      በሌላ በኩል የታንዛኒያ ባለሥልጣናት ፆተኝነት እና ሥርዓተ ፆታ ላይ የተመሰረቱ የጥላቻ ንግግሮች የተመለከቱ ደንቦችን አስወግደዋል።

      አዲሱ ሕግ ሰዎች መልዕክት በሚለዋወጡባቸው እንደ ዋትስ አፕ ያሉ መድረኮችም ሰዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋል ተብሏል።

      የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቡድን በበኩላቸው ከአምስት ዓመታት በፊት ፕሬዚደንት ጆን ማጉፋሊ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የታንዛኒያ ባለሥልጣናት መንግሥትን በሚተቹ ሚዲያዎች ፣ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች፣ እና ግለሰቦች ላይ ጫና እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

    • በኢትዮጵያ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 336 ደረሰ

      የኮቪድ-19 እለታዊ መግለጫ

      የፎቶው ባለመብት, ቢቢሲ

      በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት ለ6907 ናሙናዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎ 583 ሰዎች ላይ ኮቪድ-19 መገኘቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ አመለከቱ።

      በአገሪቱ እስካሁን ድረስ ኮቪድ-19 እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥርም 19 ሺህ 289 ደርሷል።

      ባለፉት 24 ሰዓታት ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ 26 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ይህም በአጠቃላይ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥርን 336 አድርሶታል።

      በጤና ሚኒስቴር እለታዊ መግለጫ መሰረት ባለፉት 24 ሰዓታት 330 ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ማገገማቸው ሲገለፅ፣ 145 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ህክምናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

      በኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ተይዘው ሙሉ በሙሉ ያገገሙ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥርም 7931 ደርሷል።

      በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ከተገኘ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለ444 226 ናሙናዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጓል።

    • በኮቪድ-19 መነሻ ላይ ምርምር ሊጀመር መሆኑ ተገለፀ

      ማስክ ያደረገ ግለሰብ

      የፎቶው ባለመብት, Reuters

      በተለይ አሜሪካና ቻይናን አሁንም ድረስ እያወዛገበ የሚገኘው የኮሮናቫይረስ መነሻን ጉዳይ ለማጥናት የሚያስችል መሠረት መጣሉን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

      የተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት እንዳለው ለዚሁ ምርምር ሁለት ባለሙያዎች፤ ሰዎች በቫይረሱ እንዴት ሊያዙ እንደቻሉ የመጀመሪያ ደረጃ ምርምር ማድረግ እንደሆነ በመግለፅ በቻይና የሚያካሂዱትን የምርምር ወሰን ለይተው አጠናቀዋል።

      ከቻይናና ከተቀረው ዓለም የተውጣጡ ተመራማሪዎችን እና አጥኝዎችን የያዘው ይህ ዓለም አቀፍ የምርመራ ቡድን ምርምራውን እንደሚጀምር ተገልጿል።

      ምርምሩ የሚጀመረውም በባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘባት በቻይናዋ ውሃን ከተማ ነው ተብሏል።

      ኮቪድ-19 በውሃን በሚገኝ የእንስሳት ገበያ እንደጀመረና ወደ ሰዎች እንደተላለፈ ይታመናል።

    • በኖርዌይ የአንዲት መርከብ ተሳፋሪዎችና ሠራተኞች በቫይረሱ ተያዙ

    • ራማፎሳ ለኮቪድ-19 የተመደበ በጀትን የሚመዘብሩ ግለሰቦችን አስጠነቀቁ

      ሲሪል ራማፎሳ

      የፎቶው ባለመብት, Reuters

      የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለኮሮናቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር የተመደበን የሕዝብ ሃብት በሚበዘብዙና “ጅቦች” ሲሉ የጠሯቸው ግለሰቦች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ።

      ይህ የፕሬዝዳንቱ ማስጠንቀቂያ ትኩረቱን ያደረገው የመንግሥት ኃብትን በሚመዘብሩ ባለስልጣናት፣ በኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎችና፣ የእርዳታ ምግብን በድብቅ የሚያከማቹ የአካባቢ አስተዳዳሪዎች ላይ ነው።

      “ በየእለቱ የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ ካለው ቀውስ ለማትረፍ መጣር የጥንብ አንሳ ባህሪ ነው። ልክ የተጎዳውን ሰለባውን እንደሚከብ ጅብ መሆን ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንት ራማፎሳ።

      “ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ያለምንም ርህራሄ በዘረፋ መሰማራታቸውን አስተውለናል” ሲሉም አክለዋል።

      ባለፈው ሳምንት የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ የሆኑት ግለሰብ የትዳር አጋራቸው ለጉዋቴንግ ግዛት ጤና ቢሮ የታቀደ ግዢ ላይ ምዝበራ በመፈፀም በመጠርጠራቸው ፈቃድ እንዲወስዱ ተደርጓል። ጥንዶቹ ምንም የሰራነው ጥፋት የለም ሲሉ አስተባብለዋል።

      ፕሬዝዳንቱ የኮቪድ-19 ፈንዶችን ያለ አግባብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው የሚረጋገጥ ግለሰቦች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

      “ ራሳቸውን ለማክበር በሚል ሕግ ተላልፈው የሚገኙ፣ ማንም ይሁኑ ከማንም ጋር ግንኙነት ይኑራቸው፣ ጥፋታቸው በዝምታ አይታለፍም" ብለዋል ፕሬዚደንቱ።

      ደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት መካከል ስትሆን ባለፈው ሳምንት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሆኗል።.

    • ኬንያዊቷ ነርስ ልጇን ከተገላገለች በኋላ በቫይረሱ ሕይወቷ አለፈ

      ነርስ ማሪያን አዎር አዱምቦ

      የፎቶው ባለመብት, @DrMercyKorir

      ኬንያዊቷ ነርስ የመጀመሪያ ልጇን ከተገላገለች በኋላ በኮቪድ-19 ሕይወቷ ማለፉ ተገለፀ።

      ነርሷ በቫይረሱ ተይዛ በሆስፒታል የሕክምና ክትትል እያደረገች ነበር።

      የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ማሪያን አዎር አዱምቦ የተባለችው ነርስ፤ ባጋጠማት ህመም ሳቢያ በምዕራብ ናይሮቢ በሚገኝ ሆስፒታል ገብታ የነበረ ሲሆን መጀመሪያ ላይ ስትመረመር ከቫይረሱ ነፃ እንደነበረች ተረጋግጧል።

      ከዚያም የጤና ሁኔታዋ ተባብሶ ወደ ሌላ ሆስፒታል ስትወሰድ፣ በቫይረሱ መያዟ ተረጋግጧል።

      ነፍሰጡሯ ነርስ ሕክምናዋን እየተከታተለች የመጀመሪያ ልጇን ከተገላገለች በኋላ ነበር ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የገባችው። ይሁን እንጂ ሕይወቷ ሊተርፍ አልቻለም።

      ልጇን የማቀፍ እድል እንኳን ሳታገኝ ይህችን ዓለም ተሰናበተች።

      የነርሷን ሕልፈት ተከትሎም ዶክተሮችና ነርሶች የተሰማቸውን ሃዘን በትዊተር ገፃቸው ገልፀዋል።

    • አየር ማውጫ ያላቸው ጭምብሎች ለምን ይከለከላሉ?

      Covid-19

      የፎቶው ባለመብት, Getty Images

      አንዳንድ የዓለማችን ሃገራት አየር ማውጫ ቀዳዳ ያላቸው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እያገዱ ነው።

      ኢትዮጵያም በቅርቡ ይህን ጭምብል መጠቀም አይመከርም ብላለች።

      በአውስትራሊያዋ የቪክቶሪያ ግዛት ተመሳሳይ ውሳኔ ወስናለች። የግዛቲቱ ጤና ሚኒስትር እኚህ ጭምብሎች ቫይረሱን ወደ ውጭ ሊያስወጡ ይችላሉ ብለዋል።

      ባለሙያዎች መተንፈሻ ቀዳዳ ያላቸው ጭምብሎች ለተጠቃሚው በቀላሉ መተንፈስ ያስችሉ እንጂ ቫይረሱን ጭምር ወደ አየር ሊለቁ ይችላሉ ይላሉ።

      ፕሮፌሰር ብሬት ሱቶን 'ማስኮቹ ተጠቃሚውን ይከላከሉ እንጂ በዙሪያ ያሉ ሰዎችን አይከላከሉም' ባይ ናቸው።

      መተንፈሻ ቀዳዳ ያላቸው ጭምብሎች ዲዛይን የተደረጉት በፋብሪካዎችና በማዕድን ማውጫዎች ለሚሰሩ ሰዎች እንዲሆኑ ታስቦ ነበር።

    • ጀርመን ገቢ መንገደኞችን ልትመረምር ነው

      ጀርመን

      የፎቶው ባለመብት, EPA

      የጀርመን ጤና ሚንስቴር የኮሮናቫይረስ ከፍተኛ ስርጭት ካለባቸው አከባቢዎች ወደ ጀመርን የሚገቡ መንገደኞች አስገዳጅ የኮቪድ-19 ምርመራ እንደሚደረግባቸው አስታወቀ።

      የጤና ሚንስትሩ ጄንስ ሳፓሃን የጀርመን ፌደራል መንግሥት ከ16 የጀርመን ግዛቶች ጋር በመቀናጀት ገቢ መንገደኞችን በአየር ማረፊያዎች እና ባቡር ጣቢያዎች ለመመርመር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

      ጀርመን እንደተጋላጭነቷ ከተቀረው የአውሮፓ አገራት አንጻር በቫይረሱ ብዙ ጉዳት አልደረሰባትም። ነገር ግን የቫይረሱ ስርጭት ዳግመኛ እያገረሸ ይገኛል።

      ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ509 በላይ መሆኑም ተነግሯል።

    • የዩኬ ዜጎች ከወትሮው በግማሽ ባነሰ ዋጋ ምግብ ሊቀርብላቸው ነው

      ዩናይትድ ኪንግደም

      የፎቶው ባለመብት, PA Media

      ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ያሉ የምግብ ቤት ተጠቃሚዎች ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ከወትሮው ዋጋ ሃምስ በመቶ ቅናሽ ይደረግላቸዋል።

      ግማሹን ወጭ መንግሥት የሚሸፍን ሲሆን ዓላማውም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ አቅማቸው የተዳከመ ምግብ ቤቶችን መደገፍ ነው።

      የመንግሥት ድጎማ ተግባራዊ የሚሆንባቸው ከ72 ሺህ በላይ ምግብ ቤቶች ሲሆኑ ድጎማው ለአንድ ወር የሚቆይ ነው።

      ድጎማው በሰው እስከ 10 ፓውንድ ድረስ ሲሆን የአልኮል መጠጦች ላይ ምንም ዓይነት ቅናሽ አይደረግም ተብሏል።

      ተቺዎች ከልክ ላለፈ ውፍረት የሚያጋልጡ ምግቦች በድጎማው ውስጥ መካተት የለባቸውም ሲሉ መንግሥትን ይነቅፋሉ።

      አብዛኛዎቹ ምግብና መጠጥ ቤቶች ከየካቲት ወር ጀምሮ ከሥራ ውጭ ናቸው።

    • ቻይና ዜጎቿን ለኮሮናቫይረስ የባሕል መድኃኒት እንዲወስዱ ለምን ታበረታታለች?

    • በታላቋ ማንቸስተር የክተት አዋጅ ታውጇል

      ኮሮናቫይረስ በእንግሊዝ

      የፎቶው ባለመብት, REUTERS

      የእንግሊዟ ታላቋ ማንቸስተር ከተማ ባለሥልጣናት በፍጥነት እየጨመረ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት ተከትሎ የክተት አዋጅ አውጀዋል።

      የከተማዋ ፖሊስ አዋጁን ማወጅ ያስፈለገው ቫይረሱን ባለን ኃይል በቁጥጥር ሥር ለማዋል ስላስፈለገ ነው ብለዋል።

      ፖሊስ ይህ የተለመደ አሰራር ስለሆነ ሰዎች በአዋጁ እንዳይደናገጡ አሳስቧል።

      ታላቋ ማንቸስተር ከተማ በአዲስ መልክ ያገረሸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደብ ሊጥሉ ይችላሉ ከተባሉ ከተማዎች መካከል ናት።

      ከወዲሁ የአንዳንድ አከባቢዎች ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ታዘዋል።

      አልፎም መዝናኛ ሥፍራዎች ክፍት ይሁኑ እንጂ ከቤተሰብ ውጭ ምግብ ቤቶች ሌሎች የመዝናኛ ሥፍራዎች መሰባሰብ አይቻልም።

    • ሲንጋፖር ወደ ለይቶ ማቆያ የሚገቡትን በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ልትከታተል ነው

      ሲንጋፖር

      የፎቶው ባለመብት, Getty Images

      ሲንጋፖር ከመጪው ሐሙስ ጀምሮ ወደ ለይቶ ማቆያ የሚገቡትን በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ልትከታተል መሆኑ ተነገረ።

      በመኖሪያ ቤታቸው እራሳቸውን ለ14 ቀናት ለይተው እንዲቆዩ የሚታዘዙ ሰዎችን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ መጠቀም እንደሚጀምር የሲንጋፖር መንግሥት አስታውቋል።

      እራሳቸውን በመኖሪያ ቤታቸው ለይተው እንዲያቆዩ የሚታዘዙት ሰዎች ሁልጊዜም መሳሪያውን ይዘው እንዲንቀሳቀሱ ይገደዳሉ።

      ከዚህ ቀደም የጤና ባለስልጣናት ወደለይቶ ማቆያ የገቡ ሰዎችን እንቅስቃሴ የሚከታተሉት በስልክ ጥሪዎች ነበር። ከቀናት በኋላ ግን ያሉበትን ቦታ እና እንቅስቃሴያቸውን የሚጠቁም መሳሪያ ያደርጋሉ።

      ሲንጋፖር የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ያስተላለፈችውን ሕግ የሚጥሱ ሰዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ትወስዳለች።

      የለይቶ ማቆያ ሕግጋትን የሚጥሱ ሰዎች ከፍተኛ የገንዘብ መቀጮ አልያም የስድስት ወር እርስ ይተላለፍባቸዋል።