በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 21 ሺህ ተጠጋ

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የማህበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 21 ሺህ ተጠግቷል። ይህንንም ተከትሎ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር "ማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ" በትናንትናው ዕለት የብሄራዊ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በይፋ አስጀምረዋል።ዘመቻው አገር አቀፍ ንቅናቄ በማድረግ ማህበረሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በሃላፊነትና በንቃት እንዲተገብር የሚያስችል እና ሰፊ ምርመራ በማድረግ የወረርሽኙን ሁኔታ ይበልጥ በማወቅ ቀጣይ ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል። "ማንም" የሚል ስያሜ የተስጠው ዘመቻ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን በነሃሴ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት 200 ሺህ ሰዎችን የመመርመር ዕቅድ ተይዟል። አገሪቷ እስካሁን ድረስ 444 ሺህ 226 የላብራቶሪ ምርመራዎችን አከናውናለች።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኮሮናቫይረስ ከመቼውም በላይ ለአሜሪካ ስጋት ነው ተባለ

    አሜሪካ ኮሮናቫይረስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከፕሬዝደንት ትራምፕ የጤና አማካሪዎች መካከል አንዷ በአሜሪካ የቫይረሱ ስርጭት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል ሲሉ አስጠነቀቁ።

    ዲቦራህ ብሪክ ለሲኤንኤን ሲናገሩ በሽታው “እጅግ ፈጣን በሆነ መልኩ በመላው አገሪቱ እየተስፋፋ ነው” ብለዋል።

    የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከመቼውም በላይ ለአሜሪካ ስጋት መሆኑንም የፕሬዝደንቱ አማካሪ ተናግረዋል።

    በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ የአሜሪካን ግዙፍ ከተሞች እና ገጠራማ ስፍራዎች እያጠቃ ይገኛል።

    በገጠራማ የአሜሪካ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ መክረዋል።

  2. ኢራን በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ማሳነሷን አንድ ሾልኮ የወጣ መረጃ አጋለጠ

  3. የኮሮና ምርመራ ውጤትን በ90 ደቂቃ የሚለይ መሳሪያ ወደ ሥራ ሊገባ ነው

    Covid-19 testing

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዩናትድ ኪንግደም የኮሮናቫይረስን ምርመራ ውጤትን በ90 ደቂቃዎች ውስጥ የሚያሳውቅ መመርመሪያ ቁስ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ ሥራ ሊገባ ነው።

    የዩኬ መንግሥት እንዳስታወቀው ይህ የምርመራ ዘዴ ኮቪድ-19ን ከሌሎች ወቅትን ጠብቀው ከሚመጡት ጉንፋን መሰል በሽታዎች ይለያል።

    የጤና ሚንስትሩ የምርመራ ዘዴው ውጤትን በፍጥነት ማሳወቁን በመጥቀስ የምርመራ ስርዓቱ “እጅግ ጠቃሚ ነው” ብለዋል።

    እስካሁን በበርካታ የዓለማችን ክፍል የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤቶች የሚወጡት በ24 ሰዓታት ውስጥ ነው።

  4. የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች እንዴት አደራችሁ!

    ህጻናት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአዲሱን ሳምንት ምዕራፍ የምንከፍተው በያላችሁበት ሰናይ ቀን እንዲሆንላችሁ በመመኘት ነው።

    ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ከሃገር ውስጥ እንዲሁም ከተቀረው ዓለም ያገኘናቸውን ወቅታቂ መረጃዎችን በቀጥታ ገጻችን ማድረስ ጅምረናል።

    መልካም ዕለተ ሰኞ፤ መልካም ሳምንት!

  5. በኢትዮጵያ ከፍተኛ የተባለው 28 ሰዎች ሲሞቱ 707 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጠ

    ዕለታዊ የኮሮናቫይረስ ግራፊክስ

    በዛሬው ዕለት 7ሺህ 607 የላብራቶሪ ምርመራ ተከናውኖ 707 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 18 ሺህ 706 መድረሱን የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጋራ ዕለታዊ መግለጫ አመላክቷል።

    ከዚህም በተጨማሪ አገሪቱ መዝግባው የማታውቀው 28 ሟቾችን የመዘገበች ሲሆን አገሪቷ እስካሁን በቫይረሱ ያጣቻቸውን ሰዎች ቁጥር 310 አድርሶታል።

    በባለፉት 24 ሰዓታት 406 ሰዎች ማገገማቸውን ተከትሎም በአጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 7 ሺህ 601 መሆኑንም መግለጫው አስፍሯል።

    ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 437 ሺህ 319 የላብራቶሪ ምርመራዎችን አከናውናለች።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የማህበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል።

    በመሆኑም ወረርሽኙን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር "ማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ" በትናንትናው ዕለት የብሄራዊ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በይፋ አስጀምረዋል።

    ዘመቻው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በማድረግ ማህበረሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በኃላፊነትና በንቃት እንዲተገብር የሚያስችል እና ሰፊ ምርመራ በማድረግ የወረርሽኙን ሁኔታ ይበልጥ በማወቅ ቀጣይ ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

    "ማንም" የሚል ስያሜ የተስጠው ዘመቻ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን በነሃሴ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት 200 ሺህ ሰዎችን የመመርመር ዕቅድ ተይዟል።

  6. አውሮፕላኖች እንዴት ነው በፀረ- ተህዋሲያን የሚፀዱት?

  7. የናይጄሪያዋ ሌጎስ የአምልኮ ሥፍራዎችን ልትከፍት ነው

    አምልኮ ላይ ያሉ ሴት

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የናይጄሪያ የንግድ ማዕከል የሆነችውና የአፍሪካ ትልቋ ከተማ ሌጎስ በመጭው ሳምንት የአምልኮ ቦታዎችን ልትከፍት መሆኗን አስታወቀች።

    የግዛቷ አስተዳዳሪ ባባጂደ ሳንዎ ኦሉ፤ አማኞች ከመጪው አርብ ጀምሮ ወደ መስጊድ፤ ከእሁድ ጀምሮ ደግሞ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ሲባል ከመጋቢት ወር ጀምሮ ዝግ ሆነው የቆዩት የእምነት ተቋማት እንደገና መከፈት መቻላቸው አገሪቷ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ባደረገችው ትግል ያለውን ለውጥ አመላካች መሆኑን አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

    ይሁን እንጂ አሁንም መስጊዶችና ቤተክርስቲያናት ክፍት የሚሆኑት በሳምንት አንድ ቀን ሲሆን፤ ማስተናገድ ከሚችሉት የሰው ብዛትም በግማሽ ቀንሰው አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሏል።

    በናይጀሪያ እስካሁን ከ43 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 900 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሕይወታቸው አልፏል።

  8. በህንድ የምትተዳደረው ካሽሚር ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ አዲስ መላ ዘየደች

    ተማሪዎች በመስክ ላይ ሲማሩ

    የፎቶው ባለመብት, Abid Bhat

    በርካታ አገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ሥርጭት ለመግታት ትምህርት ቤቶችን የዘጉት ቀደም ብለው ነበር።

    ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀው ቤት ውስጥ እንዲያሳልፉ ተገደዋል።

    ተማሪዎች እንዳይቦዝኑ በበይነ መረብ አማካኝነት ትምህርት የሚሰጡ አገራት ቢኖሩም አቅሙ ለሌላቸው አገራት ግን ይህን ማድረግ ፈታኝ ሆኗል። ከእነዚህ አገራት መካከልም ሕንድ አንዷ ናት።

    ታዲያ ይህ ያሳሰባት ህንድና ፓኪስታን በሚወዛገቡባትና በሕንድ ሥር በምትተዳደረው ካሽሚር ግዛት የምትገኝ ዶድፓትሪ የተባለች ከተማ ለዚህ መፍትሄ ይሆናል ያለችውን መላ ዘይዳለች።

    በዚህም በከተማዋ የሚገኙ ተማሪዎች ከመማሪያ ክፍል ውጭ በገላጣ ሥፍራ ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል። ይህም ለተማሪዎችና ወላጆች እፎይታን ሰጥቷል።

    “ልጆቻችን ቤት ውስጥ ተዘግተው፤ ከትምህርት ርቀው በስጋት ከሚውሉ ይህ በጣም የተሻለ ነው” ሲሉ ሙሽታቅ አሕመድ የተባሉ የአንድ ተማሪ ወላጅ ተናግረዋል።

    ባለሥልጣናትም የመስክ ትምህርት ቤቶቹ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግንና አካላዊ ርቀትን መጠበቅን ጨምሮ የኮቪድ-19 የጥንቃቄ መመሪያዎችን እየተከተሉ እንደሆነም ተናግረዋል።

    መምህራኑ በበኩላቸው የከተማዋ ባለሥልጣናት በየጊዜው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ገልፀው፤ “ዝናብ መዝነብ ሲጀምር ተማሪዎቹ መጠለያ ፍለጋ ይበታተናሉ” በማለት የመስክ ትምህርት ቤቶቹ ተግዳሮት መጠለያ አለመኖሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

    የዞኑ የትምህርት ኃላፊ ሞሃመድ ራምዛንም መጀመሪያ መስኩ የተዘጋጀው የጥንቃቄ እርምጃዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆኑን አስታውሰው፤ ባልተጠበቀ አየር ጠባይ ሳቢያም ትምህርቱ እንዳይስተጓጎል ድንኳን ለማዘጋጀት መሞከራቸውን ገልፀዋል።

    በግዛቷ እስካሁን ከ19 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 365 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

    ተማሪዎች በመስክ ላይ በተዘጋጀላቸው መማሪያ ቦታ

    የፎቶው ባለመብት, Abid Bhat

    መምህራን በመስክ ላይ በተዘጋጀው መማሪያ ቦታ ሲያስተምሩ

    የፎቶው ባለመብት, Abid Bhat

  9. የአውስትራሊያዋ ግዛት ወረርሽኙ በመስፋፋቱ የአስቸኳይ ጊዜ አወጣች

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያደረጉ ፖሊሶች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአውስትራሊያዋ ግዛት ቪክቶሪያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋቱን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጣች ሲሆን አዲስ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሏ ተገለፀ።

    የቪክቶሪያ ግዛት አስተዳዳሪ ዳንኤል አንድሪው እንዳሉት የተጣሉት ገደቦች ከእሁድ ምሽት 2 ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናሉ።

    በዚህ አዲስ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብም የግዛቷ ዋና ከተማ ሜልቦርን ነዋሪዎች በምሽት መንቀሳቀስ አይችሉም ተብሏል።

    ከዚህም ባሻገር ነዋሪዎች ቤት ውስጥ መቆየት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ ነገር ግን በተወሰነ መልኩ ከቤታቸው እንዲወጡ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል።

    በመሆኑም ነዋሪዎች ከቤታቸው ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው መጓዝ የማይፈቀድላቸው ሲሆን አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችሉትም በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ይሆናል።

    ለዕለት ተዕለት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለመግዛትም በአንድ ጊዜ ወደ ገበያ ማዕከላት የሚሄደውም ከአንድ ቤት አንድ ሰው ነው ተብሏል።

    አውስትራሊያ ቀደም ብላ በወሰደችው እርምጃ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር በቫይረሱ የተያዙባት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው።

    እስካሁን በአገሪቷ 17 ሺህ ገደማ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 200 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    ይሁን አንጂ በቪክቶሪያ ግዛት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአገሪቷ የተመዘገቡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም በዚሁ ግዛት የተገኙ ናቸው።

    በመሆኑም ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ተጥለው የነበሩ የእንቅስቃሴ ገደቦች በድጋሚ ተጠናክረው እንዲመለሱ ሆኗል።

    እሁድ ዕለት በግዛቷ 671 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ሰባት ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

    ይህም በአጠቃላይ በግዛቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 11 ሺህ 557 ያደረሰው ሲሆን የሟቾቹ ቁጥርም 123 ሆኗል።

    አስተዳዳሪው "በርካታ ሕዝብ በሚኖርባት ቪክቶሪያ ግዛት የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ውጤታማ የነበረ ቢሆንም ውጤቱ ግን ዘገምተኛ ነው" በማለት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

    አዲስ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብም ከአንድ ወር በላይ ለሆነ ጊዜ እንደሚቆይ አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

  10. ሪፐብሊካኖች በሚያደርጉት እጩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሚዲያዎች እንዳይሳተፉ ተወሰነ

  11. በደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከግማሽ ሚሊዮን አለፈ

  12. ኮሮናቫይረስ ሳይታወቅ ለዓመታት በሌሊት ወፎች ውስጥ ነበር

  13. የሐምሌ 26/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ያደረገ ልብስ ሰፊ

    እንደምን አደራችሁ የተከበራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ተከታታዮች?

    ቢቢሲ አማርኛ ኮሮናቫይረስን የተመለከቱ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ መረጃዎችን ወደ እናንተ ማድረሱን ቀጥሏል።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የማህበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 18 ሺህ ተጠግቷል።ይህንንም ተከትሎ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር "ማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ" በትናንትናው ዕለት የብሄራዊ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በይፋ ማስጀመራቸው ተገልጿል።ዘመቻው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በማድረግ ማህበረሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በኃላፊነትና በንቃት እንዲተገብር የሚያስችል እና ሰፊ ምርመራ በማድረግ የወረርሽኙን ሁኔታ ይበልጥ በማወቅ ቀጣይ ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

    "ማንም" የሚል ስያሜ የተስጠው ዘመቻ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን በነሃሴ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት 200 ሺህ ሰዎችን የመመርመር ዕቅድ ተይዟል።

    እጃችንን በመታጠብ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ፣ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ባለመሄድ እንዲሁም ከጤና ባለሙያዎች የሚነገሩ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበር ራሳችንን ከበሽታው እንጠብቅ እንላለን።

    ሃሳብና አስተያየት ካላችሁ በፌስቡክ አድራሻችን ብትልኩልን በአክብሮት እናስተናግዳለን።

    መልካም ቀን ይሁንላችሁ!

  14. ሕንድ ውስጥ ሳኒታይዘር የጠጡ ቢያንስ 10 ሰዎች ህይወታቸው አለፈ

  15. በኢትዮጵያ የ10 ተጨማሪ ሰዎች ሕይወት በወረርሽኙ አለፈ

    ባለፉት 24 ሰዓታት በኢትዮጵያ ውስጥ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ዓሥር ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

    የጤና ሚኒስትር እና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ባወጡት ዕለታዊ የወረርሽኙ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው፤ ምርመራ ከተደረገላቸው 7,358 መካከል 469 ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል።

    እስካሁን ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የሞቱ ሰዎች ብዛት 274 ደርሷል።

    እስካሁን 429,712 ናሙና ላይ ምርመራ የተደረግ ሲሆን፤ ከመካከላቸውም 17,999 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል።

    በተጨማሪም ከበሽታው 245 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን፤ እስካሁን በአጠቃላይ 7 ሺህ 195 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

    ከዚህ ቀደም በሽታው እንዳለባቸው ተረጋግጦ የሕክምና ድጋፍ ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከልም 68ቱ በጽኑ ታመው እንዳሉም ተገልጿል።

    አሃዝ
  16. ቦልሶናሮ፡ “ሁላችሁም ኮቪድ-19 ሊይዛችሁ እንደሚችል እመኑ”

    ቦልሶናሮ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የብራዚሉ ፕሬዘዳንት ዣቪር ቦልሶናሮ፤ ሁሉም ሰው በኮሮናቫይረስ የሚያዝበት እድል አለ ብለዋል።

    ቦልሶናሮ ሐምሌ መባቻ ላይ በኮቪድ-19 መያዛቸው ይታወሳል። ባለፈው ሳምንት አርብ ለሳንባ ኢንፌክሽን የሚረዳ መድኃኒት እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።

    “የሆነ ቀን ኮሮናቫይረስ እንደሚይዘኝ አውቅ ነበር። እዚ ያለው ሰው ባጠቃላይ በበሽታው የሚያዝበት እድል እንዳለም አስባለሁ” ብለዋል።

    ፕሬዘዳንቱ “ምንድን ነው የሚያስፈራችሁ? ተጋፈጡት” ሲሉም ተደምጠዋል። አያይዘውም “የሚሞተው ሰው ያሳዝነኛል። ቢሆንም በየቀኑ ሰው በተለያየ ምክንያት ይሞታል” ብለዋል።

    ቦልሶናሮ ኮቪድ-19 “ቀላል” ጉንፋን ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል። የአገራቸው ምጣኔ ሀብት እንዳይጎዳ ሲሉም፤ የእንቅስቃሴ ገደብ ላለመጣል ወስነዋል።

    ብራዚል ከአሜሪካ ቀጥሎ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎችና በሟቾች ቁጥር ከዓለም ሁለተኛ ናት።

  17. ሕንድ በቀን 57 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ገለጸች

    ሕንድ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    የሕንድ ባላስልጣናት አገሪቱ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 57 ሺህ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን እንዳገኙ አስታውቀዋል። በአንድ ቀን ከተመዘገበው ይህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

    ሕንድ ከ50 ሺህ ሰው በላይ በቀን ስታስመዝብ ይህ ለሦስተኛ ተከታታይ ቀን ሲሆን የቫይረሱ ስርጭት በእጅጉ እየጨመረ እንደሆነ ማሳያ ነው ተብሏል።

    በሕንዷ የንግድ ከተማ ሙምባይ የምትገኘው ማሃራሽትራ በእጅጉ በኮሮናቫይረስ ተጠቅታለች።

    ነገር ግን በሌሎች ከተሞችም ቢሆን ቫይረሱ በሚያስፈራ ሁኔታ እየተሰራጨ ሲሆን፤ እንደ አንድራ ፕራዴሽ፣ ቴላንጋና እና አሳም ያሉ ግዛቶችም በርካቶች በቫይረሱ እየተያዙባቸው ነው።

    ሕንድ የኮሮናቫይረስን ለመመመርመር የምትጠቀምባቸውን ማዕከላት ቁጥር በእጅጉ ጨምራለች። ነገር ግን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በትክክል እየተዘገበና ምርመራ እየተካሄ አይደለም የሚሉም አልጠፉም።

  18. በአሜሪካ ሥራ አጦች ይሰጣቸው የነበረው ድጎማ ተቋረጠ

    ተቃውሞ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኮሮናቫይረስ በዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደሩ፤ የንግድ ተቋሞች ድጋፍ አስፈልጓቸዋል።

    በአሜሪካም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሚሰጣቸው ድጎማ በወረርሽኙ ወቅት ሕይወታቸውን ለመግፋት አግዟቸዋል።

    ሆኖም ትላንት ምሽት ለሥራ አጦች የሚሰጠውን ጥቅማ ጥቅም በተመለከተ ምክር ቤቱ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻለም።

    ይህ ማለት ደግሞ በየወሩ ለሚሊዮኖች የሚሰጠው 600 ዶላር ይቋረጣል ማለት ነው።

    ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነት ላይ መድረስ ያልተቻለው በዴሞክራቶች ምክንያት ነው ብለው ወቅሰዋል።

    ዴሞክራቶች በበኩላቸው ለሰባት ቀናት ክፍያውን ለመቀጠል ከዋይት ኃውስ የቀረበው ሐሳብ ትርጉም የለሽ ነው ብለዋል።

    ሪፐብሊካኖች፤ በዴሞክራቶች የሚመራው ምክር ቤት ካቀረበው የገንዘብ መጠን ያነሰ እንዲከፈል ይፈልጋሉ።

  19. በሙከራ ላይ ያሉት ክትባቶች ከምን ደርሰው ይሆን?

    ክትባት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ከፍተኛ የተመራማሪዎች ቡድን ለኮቪድ-19 የሚሆን ክትባት በያዝነው ዓመት ለመስራት ተስፋ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

    ነገር ግን ክትባት የመስራት ሂደቱ ምን ያህል ሊፈጅ ይችላል?

    ቢቢሲ በሰበሰበው መረጃ መሰረት እስካሁን ድረስ 140 የክትባት መድሀኒቶችን ለማምረት ጥረት እየተደረገ ሲሆን ወደ 20 የሚጠጉት ደግሞ በሰዎች ላይ ሙከራ እየተደረገባቸው ነው።

    ከሙከራዎቹ መካከል፡

    • በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እየተሰራ የሚገኘው የሙከራ ክትባት የሰው ልጆችን በሽታ የመከላከል አቅም ማነቃቃት እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፤ አስትራዜኔካ የሚባለው የመድሀኒት አምራች ለዩኬ ብቻ 100 ሚሊየን ክትባቶችን እንዲያመርት ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
    • አሜሪካ ውስጥ ግንቦት ላይ በሰዎች የተሞከሩት ክትባቶች ቫይረሱን የመግደል አቅም እንደላቸው አሳይቷል።
    • አንድ ቻይና ውስጥ የሚገኝ ቡድን ደግሞ ክትባቱ ደህንቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል። የቻይና ወታደሮችም እንዲጠቀሙት እየተደረገ ነው።
  20. በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች 17.5 ሚሊዮን ደረሱ

    ጭምብል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዓለም በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 17.5 ሚሊዮን መድረሱን እና፤ 697 ሺህ ሰዎች መሞታቸውን ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ያወጣው መረጃ ያሳያል።

    ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ዘገባዎችን እንመልከት፡-

    . አሜሪካ- የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያው ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ፤ በዚህ ዓመት መጨረሻ “ውጤታማና አስተማማኝ” ክትባት እንደሚገኝ ተስፋ እንደሚያደርጉ ለምክር ቤት ተናግረዋል።

    . ሜክሲኮ- የሟቾች ቁጥር ከ46,000 አልፏል። ይህም በሟቾች ቁጥር ሦስተኛ ከሆነችው ዩናይትድ ኪንግደም በላይ ነው።

    . ደቡብ ኮሪያ - አንድ የአገሪቱ ተገንጣይ ኮቪድ-19ን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለማስተጓጎል ሞክሯል በሚል ታስረዋል።

    . ቬትናም - ወረርሽኙ መሰራጨት ሲጀምር በቁጥጥር ስር አውላው በነረበረው ቬትናም፤ ሁለተኛ ሰው በቫይረሱ ሳቢያ ሞቷል።

    . ብራዚል - ፕሬዘዳንት ዣቪር ቦልሶናሮ፤ ትላንት “ሁላችሁም በኮሮናቫይረስ ትያዛላችሁ” ሲሉ ንግግራቸውን ለማዳመጥ ለተሰበሰቡ ሰዎች ተናግረዋል።