በኢትዮጵያ 150 ሰዎች ኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው የአንድ ሰው ህይወት አለፈ
በኢትዮጵያ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁትር ከዕለት ዕለት በፍጥነት እየጨመረ ነው። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለው የቫይረሱ መስፋፋት በጣም ከፍተኛ እንደሆነ በየዕለቱ የሚወጣው መረጃ ያመለክታል። በዚህም በአገሪቱ እስካሁን ከተመዘገበው 1637 የህሙማን ቁጥር ውስጥ ከአንድ ሺህ የሚበልጡት ከአዲስ አበባ የተገኙ ናቸው። አሁንም የቫይረሱ ስርጭት ባለበት እንዲቆም እጅን በሚገባ መታጠብ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በባለሙያዎችና በመንግሥት የሚመከሩ መከላከያዎች ናቸው። ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ የቀጥታ ዘገባዎቻችንን እዚህ ገጽ ላይ ይከታተሉ።
የቀጥታ ሽፋን
እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች!
በአዲስ አበባ ከተማ እስከ ትናንት ድረስ በተደረጉ የላብራቶሪ ምርመራዎች 956 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።
በመላው አገሪቱም ቢሆን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1344 ደርሷል። የሟቾች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄዶ 14 ደርሷል።
በአዲስ አበባ ካሉ አስር ክፍለ ከተሞች በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ መረጃ ያሳያል።
የቫይረሱ ስርጭት ባለበት እንዲቆም እጅን በሚገባ መታጠብ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በባለሙያዎችና በመንግሥት የሚመከሩ መከላከያዎች ናቸው። ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ የቀጥታ ዘገባዎቻችንን እዚህ ይከታተሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሞዛምቢክ ኮቪድ-19 ህሙማን የግድያ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሞዛምቢክ የኮሮናቫይረስ ህሙማን ከፍተኛ የሆነ መድልዎና መገለል እየደረሰባቸው ሲሆን አንዳንዶቹም የግድያ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው ተብሏል።
በተለይም በመዲናዋ ቤይራ የሚገኙ ህሙማን የግድያ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነም ሪፖርት ማድረጋቸውንም የጤና ባለሙያዎች ገልፀዋል።
በዚህ ምክንያት ወደ ህክምና ማዕከል የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል ተብሏል።
በተለይም እንደ ጉንፋን ምልክት ያላቸው ሰዎች ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ሁኔታ ሪፖርት ያደርጉ የነበረ ሲሆን አሁን ቁጥሩ እንደቀነሰ ተገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ የጤና ባለሙያዎች የኮሮናቫይረስ ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች ወደ ጤና ማዕከላት እንዲመጡ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
በኮሮናቫይረስ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ያለው የጥላቻ መንፈስም የጤና ሚኒስቴሩ ስለ ቫይረሱ ስለተገኘባቸው አካባቢዎችና ሌሎች መሰል የሚሰጣቸውን መረጃዎች እንዲገድብ እንዳደረገውም ተገልጿል።
የደቡብ ሱዳን ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኛ መሞታቸው ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Getty
የምስሉ መግለጫ, ጆን ሉክ ጆክ የአገሪቷን የሽግግር ሕገ መንግሥት ካረቀቁት መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ የደቡብ ሱዳን የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ጆን ሉክ ጆክ ሰኞ እለት ምሽት ባጋጠማቸው ህመም በዋና መዲናዋ ጁባ መሞታቸው ተሰምቷል፡፡
ፖለቲከኛው ማክሰኞ እለት ጠዋት በከተማዋ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሕይወታቸው እንዳለፈ ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበሩ ሲሆን፤ የአገሪቷን የሽግግር ሕገ መንግሥት ካረቀቁት መካከል አንዱ ነበሩ፡፡
ምንም እንኳን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ጆን ሉክ በኮቪድ -19 ሳይሞቱ እንዳልቀረ ቢዘግቡም፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን በቅርቡ ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸው መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በአገሪቷ እስካሁን 994 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 10 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ከሁለት ሳምንታት በፊትም የአገሪቷ ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማቻር በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
ከዚህም ባሻገር ሌሎች 10 ሚኒስትሮች እና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት እየሰራ ያለ ግብረ ኃይል አባላት የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቫይረሱ መያዛቸው ተነግሯል፡፡
ደካማ የጤና አገልግሎት ሥርዓት ባላት ደቡብ ሱዳን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር አስጊ እንደሆነ የእርዳታ ድርጅቶች አስጠንቅቀዋል፡፡
በአገሪቷ ለዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት የጤና ዘርፉን እጅጉን የጎዳው ሲሆን ሁሉም የጤና ተቋማት በድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች ላይ ጥገኛ ናቸው፡፡
ደቡብ ሱዳን ለ12 ሚሊየን ሕዝብ ያላት 25 የጽኑ ህሙማን አልጋዎችና 4 ቬንትሌተሮች ብቻ ናቸው፡፡
በኒውዮርክ በትናንትናው ምሽት 700 የሚሆኑ ሰዎች መታሰራቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን ተከትሎ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ተቃውሞ እየተካሄደ ነው፡፡
በተቃውሞው ንብረቶች ወድመዋል፤ ዘረፋዎች ተፈጽመዋል፤ የተለያዩ ጉዳቶችም እንዳጋጠሙ ተነግሯል፡፡
ይህንን ተከትሎ የኒውዮርክ ፖሊስ ኮሚሽነር ደርሞት ሺያ፤ "ፖሊስ ወንጀለኞች ከተማዋን እንዳይቀጣጠሩት ያደርጋል፡፡" ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ፤ በትናንትናው ምሽት 700 የሚሆኑ ሰዎች ፖሊስ ላይ ጥቃት በመሰንዘር እንዲሁም በሌሎች ጥቃቶች እና በዘረፋ መታሰራቸውን ተናግረዋል፡፡
ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችልም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ለተቃውሞ የሚወጡ ሰዎች ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መልኩ እንዲያደርጉ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡
" ባለፉት ቀናት ምንም እስር ሳንፈጽም ደግም ጥሩም አይተናል፡፡ ዛሬ ይህ ባይሆን ደስ ይለናል፡፡" ብለዋል፡፡
አክለውም "ከተማው እንዲረበሽ አንፈልግም ፤ በከተማዋ ያሉትን ሁሉንም ዜጎች እንዲሁም ንብረታቸውን እንጠብቃለን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ሰሞኑን እየተካሄዱ ያሉ የተቃውሞ ሰልፎች የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡
ኒውዮርክ በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቁ አሜሪካ ግዛቶች ግንባር ቀደሟ ስትሆን 29 ሺህ 917 ሰዎችም በቫይረሱ ሕይወታቸውን እንዳጡ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያሳያል፡፡
ሚሊኒየም አዳራሽ የኮሮናቫይረስ ህሙማንን መቀበል ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, ENA
የምስሉ መግለጫ, የጽኑ ህሙማን ክፍል በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ የተዘጋጀው የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ሕሙማንን መቀበል መጀመሩን ኢዜአ ዘግቧል።
ይህ ግዙፍ አዳራሽ በሽታው በአገሪቱ ከተከሰተ በኋላ ለህክምና ማዕከልነት እንዲውል አስፈላጊው ቁሳቁሶች እየተሟሉለት ለሁለት ወራት መቆየቱን ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር እስማኤል ሸምሰዲን ተናግረዋል።
ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ በየዕለቱ በሽታው የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ ሥራ የጨመረው ማዕከሉ 40 የጽኑ ህሙማን አልጋዎችና ከአንድ ሺህ በላይ ሌሎች የኮሮናቫይረስ ታካሚዎች መቀበል ይችላል ተብሏል።
ማዕከሉ አስፈላጊ የሆኑት የላቦራቶሪና የመድኃኒት ቤትን ጨምሮ ለጤና ባለሙያዎችና ለህሙማኑ የሚሆኑ አገልግሎቶች መስጫ ክፍሎችና አቅርቦቶች እንዳሉት ተገልጿል።
ዛሬ ግንቦት 25፣ 2012 ዓ.ም የኮሮናቫይረስ ህሙማንን ማስተናገድ መጀመሩ የተነገረለት ይህ የሚሊኒየም አዳራሽ የኢትዮጵያ የ2000 ዓመትን ክብረ በዓል ለመቀበል የተለያዩ ዝግጅቶችን ለማስተናገድ የተገነባ ግዙፍ አዳራሽ ነው።
የሚድሮክ ኢትዮጵያ አንድ አካል በሆነው በአዲስ ፓርክ ስር ሲተዳደር የቆየው ይህ አዳራሽ ለበዓሉ አከባበርና ለአጭር ጊዜ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ባለፉት 12 ዓመታት የተለያዩ ግዙፍ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን አስተናግዷል።
ኢትዮጵያ ለህክምና ተቋማት ብቻ 131 ሚሊዮን ጭምብሎች እንደሚያስፈልጋት ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን አስገዳጅ አድርጋለች የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አገሪቷ የኮሮናቫይረስ ወረርሽንን ለመዋጋት በሚቀጥሉት አራት ወራት 131 ሚሊየን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) እንደሚያስፈልጋት መናገራቸውን ፋና ዘግቧል።
ሚኒስትሯ እንዳሉት እነዚህ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስኮች) የሚያስፈልጉት በአገሪቷ ላሉ የጤና ተቋማት ብቻ ነው፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከል ስራን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በተለይም በጤና ተቋማት ላይ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የሚሆኑ የህክምና ጭምብሎች (ሜዲካል ማስኮች) በዓለም አቀፍ ደረጃ እጥረት መኖሩን በመጥቀስ፤ እንደ አገርም በርካታ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በአገሪቷ አራት ሚሊዮን ጭምብሎች (ማስኮች) ብቻ እንደነበሩ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጅ ከዚያ በኋላ በተሰሩ ሥራዎች ከሰባት ሚሊየን በላይ ጭምብሎችን ለጤና ተቋማት ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ አክለውም እነዚህን የህክምና ግብአቶች በእርዳታ ከማግኘት ባሻገር በአገር ውስጥ ጥራቱን የጠበቀ እና መስፈርቱን ያሟላ ጭምብል እንዲመረት ለማድረግም ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ የቬንትሌተሮች እጥረት መኖሩን የገለጹት ዶ/ር ሊያ፤ ከዚህ በፊት አንደ አገር 22 ቬንትሌተሮች ብቻ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
በጥገና የተስተካከሉ፣ በእርዳታ የተገኙትን እና አዲስ የተገዙትን ጨምሮ አሁን ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ 221 ቬንትሌተሮች ዝግጁ መደረጋቸውንም ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል።
በጤና ሚኒስቴርና በህብረተሰብ ጤና ተቋም መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ እስካሁን 1344 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 14 ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ኢትዮጵያ ከቻይና የሚላኩ የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ በአህጉሪቷ በማሰራጨት ትልቅ ሚና ተወጥታለች፡፡
ኮሮናቫይረስ፡ የድረ ገፅ የዓሣ ሽያጭ ተጧጡፏል
የአምስተርዳሙ ከንቲባ የጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ በተካሄደ ተቃውሞ ተወቀሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በዳም አደባባይ ወጥተዋል የአምስተርዳም ከንቲባ የጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድን አሰቃቂ ግድያ በማውገዝ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ ትችት ተሰነዘረባቸው፡፡
ከንቲባው ትችት የተሰነዘረባቸው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ተቃዋሚዎቹ አካላዊ ርቀትን ባልጠበቁበት ሁኔታ ሰልፍ እንዲወጡ በመፍቀዳቸው ነው፡፡
ከንቲባ ፌምኬ ሃልሴማ "የመቃወም መብት ነው" ሲሉ ትችቱን የተቃወሙት ሲሆን ለደች የሕዝብ ቴሌቪዥን ኤንፒኦ "ያን ያህል ትልቅ ተቃውሞ ሰልፍ መሆኑን የሚያመላክት ምንም ነገር የለም" ብለዋል፡፡
ይሁን እንጅ በአምስተርዳም ዩኤምሲ ሆስፒታል የቫይረስ ተመራማሪ እና በደች ብሔራዊ የኮሮናቫይረስ መከላከል ቡድን አባል የሆኑት ሜኖ ድጆንግ "በፍጹም የማንፈልገው ነገር ነው የሆነው" ሲሉ ለፓሮል ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡
"ለወራት ስለ አካላዊ ርቀት ማውራታችን ምክንያት አለው፡፡ ይህ አጋጣሚ ቫይረሱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሰራጭ ትዕይንት ነው፡፡ እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የቫይረስ ተመራማሪ መሆን አያስፈልግም" ሲሉ ሁኔታውን ተችተዋል፡፡
በሌላ በኩል በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የተገኘች ኪራ ዳርጊን የተባለች አንዲት ጥቁር ሴት በበኩሏ "ይህ የሁሉም ሰው ችግር ነው፡፡ እንደ ጥቁር ሴት ወንድሞቼ ሲበደሉና ሲረገጡ ማየት ሰልችቶኛል፤ እንደ አንድ ጥቁር እናት ደግሞ ለልጄም እሰጋለሁ፤ ይህ መቆም አለበት" ስትል ለሮተርስ የዜና ወኪል ተናግራለች፡፡
በአምስተርዳም የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ በመቃወም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል፡፡
በሲድኒ ሃይድ ፓርክ የተሰባሰቡት ተቃዋሚዎች በወረርሽኙ ምክንያት ሰዎች እንዳይሰባሰቡ የሚያዘውን ሕግ ጥሰው ታይተዋል፡፡
በአዲስ አበባ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአዲስ አበባ ከሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች በተለየ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ ነው።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዛሬ ባወጡት ዕለታዊ ሪፖርት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ምርመራ ከተደረገላቸው 3932 ሰዎች ውስጥ 87ቱ ላይ ቫይረሱ ሲገኝ ከእነዚህ ውስጥ 67ቱ ከአዲስ አበባ መሆኑን አመልክቷል።
ዛሬ የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች 59ኙ ወንዶች 28ቱ ደግሞ ሴቶች ሲሆኑ እድሜያቸውም ከ10 ዓመት አስከ 70 ባለው ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 7 ከአማራ፣ 6 ከኦሮሚያ፣ 4 ከሶማሊ፣ 2 ከትግራይ እና 1 ከሐረሪ ክልሎች ናቸው።
ቀደም ሲል ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በህክምና ክትትል ላይ ከነበሩት ህሙማን መካከል 12 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን እስካሁን በአጠቃላይ 231 ሰዎች አገግመዋል።
ከዚህ ባሻገር ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው በማለፉ በወረርሽኙ ምክንያት በኢትዮጵያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 14 ከፍ ብሏል።
እስከ ዛሬ በተደረገው ከ116 ሺህ 309 የኮሮናቫይረስ ምርመራ 1344 ሰዎች ላይ የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቷል።
ወርሃዊ ገቢያችን ከ15 ሺህ ብር ወደ ዜሮ ወርዷል፡ የላሊበላ አስጎብኚ
በባንግላዲሽ የሮሂንጋ መጠለያ አንድ ሰው በቫይረሱ ሞተ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የባንግላዲሽ ባለሥልጣኖች እንደተናገሩት፤ በሮሂንጋ መጠለያ ካምፕ ውስጥ የመጀመሪያው ሞት ተመዝግቧል። ሟቹ የ71 ዓመት አዛውንት ናቸው።
ከሚያንማር ጋር የምትዋሰነው ኩቱፓሎግ ነዋሪ የነበሩት አዛውንቱ ያረፉት በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሳሉ ነበር።
እስካሁን 31 የሮሂንጋ ስደተኞች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። የሚኖሩበት መጠለያ በዓለም እጅግ የተጨናነቀው ነው።
ከሚያንማር ጥቃት የሸሹ ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ የሮሂንጋ ሙስሊሞች በባንግላዲሽ ተጠልለው ይኖራሉ።
የህወሓት አቋምና የብልጽግና መልስ
ኢንዶኔዢያ 200 000 ሙስሊሞችን በዚህ ዓመት የሃጂ ጉዞ መሄድ እንደማይችሉ ገለፀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢንዶኔዢያ የዚህ ዓመት የሃጂ ተጓዦችን በኮሮናቫይረስ ስርጭት ስጋት ምክንያት እንዳይሄዱ አገደች።
በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚገኙባት ኢንዶኔዢያ በየዓመቱ ወደ ሳዑዲ አረብያ፣ መካና መዲና የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ነበሯት።
የሳዑዲ ባለስልጣናት የሃጂና ኡምራ ጉዞ ተጨማሪ ማስታወቂያ ወደፊት እስከሚነገር ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጧል ሲሉ አስታውቀው ነበር።
ምንም እንኳ ሳዑዲ የጣለችውን እገዳ ብታነሳም ኢንዶኔዢያ ተጓዦቹን ለመመዝገብና አስፈላጊ ሰነዶችን ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ የላትም ሲሉ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።
የሃጂና ኡምራ ጉዞ ባለው የኮታ አሰራር መሰረት አንድ ሰው የሃጂ ጉዞ ላይ ለመሳተፍ በአማካይ ሃያ ዓመት መጠበቅ ይኖርበታል።
በዚህ ዓመት የኢንዶኔዢያ ኮታ 200 000 ሰው ነበር።
የኢንዶኔዢያ እስልምና ጉዳዮች ሚኒስትር በቴሌቪዥን በሰጡት ማብራሪያ "መንግሥት የሃጂ 2020 ጉዞን እንዲሰረዝ ወስኗል፤ ይህንን ውሳኔ ለመድረስ እጅግ ከባድ ነው በርካቶችንም እንደሚያበሳጭ ይገባናል" ብለዋል።
ኢንዶኔዢያ እስካሁን ድረስ 1600 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን በምርመራ አረጋግጣለች።
የዘጠኝ ዓመቱ ታዳጊ በፈጠራ ስራው አማካኝነት ተሸለመ
ኬንያዊው ታዳጊ በሰራው የእጅ መታጠቢያ ማሽን ምክንያት ከበርካታ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች መካከል አንዱ በመሆን ሽልማቱን ተቀበለ።
የዘጠኝ ዓመቱ ስቴፈን ዋሙኮታ የእጅ መታጠብያ ማሽኑን የሰራው፣ ውሃ የያዘ ጀሪካን በእንጨት ላይ እንዲንጠለጠል በማድረግ እንዲሁም ከእጅ ንክኪ ነፃ ሆኖ እጅ መታጠብ እንዲቻል ፔዳል በመግጠም ነው።
ታዳጊው በሚኖርባት ምዕራብ ኬንያ ያለው የእጅ መታጠብያ ሰዎችን ከንክኪ የማያርቅና ለኮሮናቫይረስ የሚያጋልጥ መሆኑን በማስተዋሉ ይህንን የፈጠራ ስራ መስራቱን ተናግሯል።
ይህ ታዳጊ የእጅ መታጠብያ ማሽኑን በሚሰራበት ወቅት አናጢ አባቱ አግዞታል።
ስቴፈን በኮሮና ወቅት የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት ያበረከቱ 68 ሰዎች ጋር ነው ተሸላሚ የሆነው።
የ X ይዘትን ይለፉትይዘቱን X ይፈቅዳሉ?ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
በኢትዮጵያ 150 ሰዎች ኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው የአንድ ሰው ህይወት አለፈ
በምዕራብ ኦሮሚያ ነጆ አራት የመንግሥት ሠራተኞች በታጣቂዎች ተገደሉ
ትራምፕ ሩስያ ወደ ቡድን 7 ትመለስ ቢሉም አባል አገራቱ ተቃውመዋል
"ተማር ልጄ" ለኮሮናቫይረስ ተቀየሮ ሲዘፈን
ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ "ተማር ልጄ" የተሰኘው ዜማ በድጋሚ ከሮሃ ባንድ ጋር በመሆን አቀንቅኖታል። ይህ ዜማ እንደ ቀድሞ አባት ልጁን እንዲማር አይመክርም፤ ይልቅስ አባት ለልጁ ራሱን ከኮሮናቫይረስ እንዲጠብቅ የሚያስታውስ ነው።
ከአለማየሁ እሸቴ ጋር ድምፃዊ ሞገስ መብርሃቱ እና ድምጻዊት አስቴር ከበደ ያቀነቀነች ሲሆን ግጥሙን የፃፈው ደግሞ አበረ አዳሙ ነው።
ልክ እንደሰው ታሞ ኮስምኗል ዘመኑ
በደስታችን ዙፋን ተሾሟል ሐዘኑ
ከቤትህ ተሰብሰብ በመምሸቱ አትስጋ
ነገም ብርሃን አለ ጨለማው ሲነጋ. . . ይላል ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ።
ዜማውን እድምጣችሁ የተሰማችሁን ንገሩን
የ YouTube ይዘትን ይለፉትይዘቱን Google YouTube ይፈቅዳሉ?ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም። YouTube] ማስታወቂያ ሊኖረው ይችላል።ይህ ጽሑፍ በGoogle YouTube. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የGoogle YouTube ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ YouTube ይዘት መጨረሻ
ዙም መሰብሰቢያ ብቻ ሳይሆን ከሥራ ማባረሪያም ሆኗል
