በኢትዮጵያ 150 ሰዎች ኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው የአንድ ሰው ህይወት አለፈ

በኢትዮጵያ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁትር ከዕለት ዕለት በፍጥነት እየጨመረ ነው። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለው የቫይረሱ መስፋፋት በጣም ከፍተኛ እንደሆነ በየዕለቱ የሚወጣው መረጃ ያመለክታል። በዚህም በአገሪቱ እስካሁን ከተመዘገበው 1637 የህሙማን ቁጥር ውስጥ ከአንድ ሺህ የሚበልጡት ከአዲስ አበባ የተገኙ ናቸው። አሁንም የቫይረሱ ስርጭት ባለበት እንዲቆም እጅን በሚገባ መታጠብ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በባለሙያዎችና በመንግሥት የሚመከሩ መከላከያዎች ናቸው። ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ የቀጥታ ዘገባዎቻችንን እዚህ ገጽ ላይ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኢትዮጵያ ተጨማሪ 142 ሰዎች በኮቪድ-19 ሲያዙ 3 ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል

    የጤና ጥበቃና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዛሬ ባወጡት ዕለታዊ ሪፖርት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ምርመራ ከተደረገላቸው 4120 ሰዎች ውስጥ 142ቱ ኮቪድ-19 እንዳለባቸው ተራጋግጧል።

    ዛሬ ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች 84ቱ ወንዶች 57ቱ ደግሞ ሴቶች ሲሆኑ እድሜያቸውም ከ7 ዓመት አስከ 78 ባለው ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

    140ዎቹ ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ አንድ ሰው ከፖርቹጋል፤ አንድ ሰው ደግሞ ከጅቡቲ መሆናቸው ታውቋል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጠ 142 ሰዎች መካከል 126 ከመዲናዋ አዲስ አበባ ናቸው።

    ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ሦስት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉም ተሰምቷል። አጠቃላይ የሟቾች ቁጥርም 17 ደርሷል።

    እስከ ዛሬ በተደረገው ከ120 ሺህ 429 የኮሮናቫይረስ ምርመራ 1486 ሰዎች ላይ የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቷል።

    አሃዝ
  2. በካሜሮን ትምህርት ቤቶች መከፈታቸውን ተከትሎ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጥር ጨመረ

    ተማሪ በክፍል ውስጥ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ካሜሮን ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ትምህርት ቤቶችን መክፈቷን ተከትሎ በቫይረሱ የተያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥርም መጨመሩ ተነግሯል።

    አገሪቱ ሰኞ እለት ብቻ 254 በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ማግኘቷን የገለፀች ሲሆን ማክሰኞ ደግሞ ተጨማሪ 188 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አስታውቃለች።

    መንግሥት ተማሪዎች በኮሮናቫይረስ እንዳይያዙ የመከላከያ እርምጃዎችን እየወሰድኩ ነው ያለ ሲሆን፣ ይህም መማሪያ ክፍሎቻቸውን በአግባቡ ማጽዳት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማከፋፈል እንዲሁም ሳኒታይዘር እንዲጠቀሙ ማድረግ መሆኑን ገልጿል።

    በካሜሮን ሰኞ እለት ትምህርታቸውን የጀመሩት የሁለተኛ ደረጃ የሚያጠናቅቁ እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው።

    ተማሪዎች በክፍላቸው ውስጥ አንድ ሜትር ተራርቀው እንደሚቀመጡም ተገልጿል።

    የትምህርት ኃላፊዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽን በትምህርት ቤቶች ሊስፋፋ ይችላል በሚል ስጋታቸውን የገለፁ መምህራንን ማስፈራራታቸው ተዘግቧል።

    በካሜሮን እስካሁን ድረስ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ካደረጉ ሰዎች መካከል 6,585 በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ ሁለት መቶ ደግሞ ሞተዋል።

  3. በዩክሬን የአንድ እግር ኳስ ቡድን 25 አባላት በኮሮናቫይረስ በመያዛቸው ለይቶ ማቆያ ገቡ

    በዩክሬን ጭምብል ያጠለቁ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዩክሬን የአንድ እግር ኳስ ቡድን አባላት የሆኑ ተጫዋቾች ለሁለት ሳምንት ለይቶ ማቆያ ገቡ።

    ቡድኑ ለይቶ ማቆያ የገባው በርካታ ተጫዋቾችና የቡድን ሠራተኞች በኮሮናቫይረስ በመያዛቸው ነው ተብሏል።

    ለቅዳሜ ተይዘው የነበሩ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎችም እንዲሁም ስልጠናዎች በሙሉ ተሰርዘዋል።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ምርመራ ከተደረገላቸው 65 ተጫዋቾችና የቡድኑ አባላት መካከል 25 ተጫዋቾች ኮሮናቫይረስ ተይዘው መገኘታቸውን ዘግበዋል

    በዩክሬን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል በሚል የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎ የነበረ ሲሆን ሁኔታዎች በመሻሻላቸው ነበር በቅርቡ ገደቡ የተነሳው።

    በአገሪቱ የሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦች ተጫዋቾቻቸውንና አሰልጣኞቻቸውን እንዲያስመረምሩ ጥሪ ቀርቧል።

  4. ቻይና ለዓለም ጤና ድርጅት መረጃ በመስጠት በኩል ዘግይታለች መባሉን አስተባበለች

    የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ቻይና ለዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 በሚመለከት መረጃ ስታጋራ ዘግይታለች የሚለውን ክስ 'ውሸት" አለች።

    የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዛሆ ሊዪን አገራቸው ኮቪድ-19 በሚመለከት ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ሪፖረት ስታደርግ " ከፍተኛ መዘግየት ተፈጥሯል" በዚህም የተነሳ በድርጅቱ ባለሙያዎች ዘንድ " ተስፋ መቁረጥ ተፈጥሮ ነበር" የሚለውን የአዣንስ ፍራንስ ዘገባ አምርረው ተቃውመዋል።

    የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ከውስጥ አዋቂ ደረሰኝ ባለው መረጃ እና በርካታ ቃለ መጠይቆችን ማድረጉን በመግለጽ ቻይና የቫይረሱን ባህርይ ይፋ ለማድረግ ለሳምንታት " ምክክር ስታደርግ" ነበር ብሏል።

    ይህ መረጃ በወቅቱ የዓለም ጤና ድርጅት ካወጣው መግለጫ ጋር የሚጣረስ ነው።

    በወቅቱ የዓለም ጤና ድርጅት ቻይና ለሰጠችው ፈጣን ምላሽ በተደጋጋሚ ያንቆለጳጰሰ ሲሆን በተለይ ደግሞ የቫይረሱን አጠቃላይ ባህርይ "በፍጥነት" በማጋራቷ አመስግኗት ነበር።

  5. በኡጋንዳ፡ በኮቪድ-19 የተያዙ 11 ኤርትራውያን ተገኙ

    የጭነት መኪና

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኡጋንዳ በመጋቢት 12 ለመጀመርያ ጊዜ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ስታገኝ አብዛኛዎቹ ሹፌሮች መሆናቸው ገልጻ ነበር።

    የጤና ሚኒስትሯ ጄን አሰንግ ባለፈው እሁድ በሰጡት መግለጫም፤ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኡጋንዳ የገቡ 50 የሚሆኑየትልልቅ መኪና አሽከርካሪዎች ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው ጠቁመዋል።

    ከእነዚህ ግንቦት ወር ላይ የተመረመሩ ሹፌሮች፤ 10 የሚጠጉት ኤርትራውያን መሆናቸው የሚኒስትሩ መግለጫ ያመለክታል።

    በዚህ መሰረት፣ በሚያዝያ 28፣ አንድ ከኬንያ በማላባ ድንበር ወደ ኡጋንዳ ሲገባ የተመረመረ ኤርትራዊ በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል። በግንቦት 6 ደግሞ፣ በተመሳሳይ ከታንዛንያ የመጣ፣ በግንቦት 8 ከደቡብ ሱዳን በኢለጉ ድንበር ሲገቡ የነበሩ አራት ኤርትራውያን በቫይረሱ መያዛቸው እንደተረጋገጠ የጤና ሚኒስቴሩ መግለጫ ያሳያል።

    ሌሎች 3 ኤርትራውያን ግንቦት 12 ላይ፣ ግንቦት 19 ደግሞ ሌላ አንድ ኤርትራዊ ሹፌር በቫይረሱ ተይዘው ሲገኙ፤ በትናንትናው እለትም አንድ ሰው መገኘቱ ተገልጿል።

    ለ30 አመታት በሹፍርና የሰራውና ላለፉት ሰባት አመታት ከኬንያ ወደ ጁባና ኡጋንዳ ደረቅ ወደቦች ጭነት በማመላለስ የሰራው ኤርትራዊ፤ “ከዚህ በፊት ከሞምባሳ ወደ ጁባ አምስት ቀን ይፈጅብኝ ነበር። አሁን ግን ከጁባ ወደ ናይሮቢ ለመግባት እንኳ አንድ ወር ወስዶብኛል” ይላል።

    በዚህ ምክንያት፤ እኔ መቅደም አለብኝ በሚል ግፊያ በሹፌሮች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች እንዳሉ ተናግሯል። ኢብራሂም ዑመር የተባለ ሌላ ሹፌርም “ያለንበት ቦታ በረሃ ስለሆነ ምግብ እንኳ ማግኘት አይቻልም። እንጀራ ሆኖብን ነው እንጂ ጉዞው በሙሉ በስጋት የተሞላ ነው” ብሏል።

  6. ደቡብ ሱዳን በግዛቷ ግብጽ የጦር ሰፈር እንድታቋቁም ፈቅዳለች?

  7. ህንዳዊው ኮሮናቫይረስን ለመከላከል አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የሚያስችል ሞተር ሳይክል ሠራ

  8. አሜሪካ በታንዛንያ አሁንም በኮሮናቫይረስ የመያዝ እድል ሰፊ ነው አለች

    ታንዛንያ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በታንዛንያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ አገሪቱ ለመጓዝ ለሚወስኑ አሜሪካውያን አዲስ የጉዞ መረጃ አወጣ።

    በታንዛንያ ባለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ምክንያት በንግድ ከተማዋ ዳሬሰላም በኮሮናቫይረስ የመያዝ እድል አሁንም ሰፊ ነው ሲል አስጠንቅቋል ኤምባሲው በመግለጫው። ነገር ግን ይህንን ያለበትን ምክንያት በማስረጃ አላስደገፈም።

    አክሎም ዜጎቹ ከቤታቸው እንዳይወጡ እና ከሌሎች ሰዎች ጋርም ማህበራዊ ተራክቦ እንዳያደርጉ መክሯል።

    "በታንዛንያ የሚገኙ የጤና ተቋማት በፍጥነት በኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ሊጥለቀለቁ ይችላሉ" ብሏል ኤምባሲው በመግለጫው።

    ይሀ የኤምባሲው መግለጫ የወጣው የታንዛንያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ አምባሳደርን ኢንሚ ፓተርሰንን ባለፈው ወር ኤምባሲው ያወጣውን ተመሳሳይ መግለጫ በመቃወም ካነጋገሩ በኋላ ነው።

    የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የኤምባሲው መግለጫ ሐሰተኛ መረጃ የያዘ ነው ካለ በኋላ ታንዛንያውያንና ጎብኚዎችን እንዲሸበሩ ያደርጋል ብሎ ነበር።

    የአሜሪካ ኤምባሲ ቢቢሲ ለጠየቀው ጥያቄ በኢሜል በሰጠው ምላሽ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ባለው ላይ ምንም ምላሽ እንደማይሰጥ አስታውቋል።

    ሰኞ ዕለት የታንዛንያ ጤና ሚኒስትር ኡሚ ምዋሊሙ በዳሬ ሰላም ሆስፒታሎች ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ አራት ሰዎች ብቻ መኖራቸውን ተናግረው ነበር።

    በዛው እለትም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች የተከፈቱ ሲሆን የተለያዩ ስፖርታዊ መርሃ ግብሮችም እንዲካሄዱ ተፈቅዷል።

  9. የጥቁር አሜሪካዊያን ተቃውሞ ወደ ፈረንሳይ ተዛመተ

  10. የኮንግረንስ አባሏ ኢልሃን ኦማር ዘረኝነትን ለመዋጋት አስቸኳይ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተናገረች

  11. የፎርሙላ ዋን መኪና ተወዳዳሪዎች በኮሮናቫይረስ ቢታመሙም አይሰረዝም ተባለ

    የፎርሙላ ዋን ኃላፊ ቼዝ ኬሪ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፎርሙላ ዋን መኪና እሽቅድምድም ተወዳዳሪዎች በኮሮናቫይረስ ቢታመሙ መጪው ውድድሮች እንደማይሰረዙ ስራ አስፈፃሚው ቼዝ ኬሪ አስታውቀዋል።

    የፎርሙላ ዋን የመጀመሪያዎቹ ስምንት ውድድሮች በሚቀጥለው ወር እንዲካሄዱ እቅድ መያዙን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ነው ስራ አስፈፃሚው ከዚህ ውሳኔ ላይ መደረሱን ያስረዱት

    "የተወዳዳሪዎች በቫይረሱ መያዝ ውድድሮቻችንን እንዳያሰርዘን ቀድመን መንገዶች አበጅተናል" በማለት ቼዝ ኬሪ ተናግረዋል።

    ከተወዳዳሪዎች መካከል አንደኛው በህመሙ ቢጠቃ ተጠባባቂ አባላት ስላሏቸው በነሱ መተካት ይችላሉ ብለዋል።

    መጋቢት ወር ላይ የአውስትራሊያው ግራንድ ፕሪክስ ውድድር ይጀመራል ተብሎ ቢጠበቅም ማክላለን የተባለው ተወዳዳሪ በኮሮናቫይረስ በመታመሙ እንዲራዘም ተደርጓል።

    ሆኖም ስራ አስፈፃሚው ለፎርሙላ ዋን ድረገፅ እንደተናገሩት "ምን ይሆናል በሚሉ መላ ምቶች ውድድሮችን አናራዝም። ተወዳዳሪዎችም መወዳደር ባለመቻላቸውም እንዲሁ ውድድሮችን አንሰርዝም" ብለዋል

  12. "በጣም እርግጠኛ ሆነን ያወጣነው ሪፖርት ነው" አምነስቲ ኢንተርናሽናል

  13. አይቦፕሮፊን ለኮሮናቫይረስ ህክምና እንዲውል ሙከራ እየተደረገ ነው

    የአይቦፕሮፊን እንክብሎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሳይንቲስቶች አይቦፕሮፊን የተሰኘውን የህመም ማስታገሻ በሆስፒታል ውስጥ ለሚገኙ የኮሮናቫይረስ ህሙማንን ህክምና መዋል ይችላል የሚለው ላይ ምርመራ እያደረጉ ነው።

    ለንደን መቀመጫቸውን ያደረጉት ሴይንት ቶማስና ኪንግስ ኮሌጅ የተውጣጣ ቡድን ለህመም ማስታገሻነት የሚውለው አይቦፕሮፊን መተንፈስ ለሚያዳግታቸውም እፎይታን ይሰጣል እያሉ ነው።

    መድኃኒቱ ዋጋው ተመጣጣኝ ከመሆኑ አንፃርም በውድ ዋጋ ከሚሸጠው ቬንትሌተር ፈንታ ህሙማንን ሊታደግ ይችላል እያሉ ነው።

    ሊበሬት የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚህ ሙከራ ህሙማን ከሚደረግላቸው እንክብካቤ በተጨማሪ ግማሾቹ አይቦፕሮፊን ሰውነታቸው ላይ የሚያመጣው ለውጥ የሚገመገም ይሆናል።

    በሙከራው ገበያው ላይ ያለው አይቦፕሮፊን አይነት ሳይሆን በተለየ የአቀማመር ሁኔታ የተቀመሙ አይቦፕሮፊን ተግባራዊ ይደረጋሉ። እነዚህን ለየት ያሉ የአይቦፕሮፊን አይነቶች በመገጣጠሚያ ህመሞች የሚሰቃዩ ሰዎች ይወስዷቸዋል።

    በእንስሶች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የመተንፈሻ እክሎችን እንደሚፈውስ ነው ይህም ከኮሮናቫይረስ ችግሮች አንዱ ሲሆን፤ በሰውም ላይ ውጤታማ መሆን ከቻለ ፈውስ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው።

  14. በደቡብ አፍሪካ የተጣሉ አንዳንድ እገዳዎች ኢ-ህገመንግሥታዊ ናቸው ተባለ

    በደቡብ አፍሪካ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ መካከል ሲጋራ ማጨስ ታግዷል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የወጡ አንዳንድ መመሪያዎች " ኢ ሕገመንግስታዊ እና እርባና ቢስ" ናቸው አለ።

    ጉዳዩ ለፍርድ ቤቱ የቀረበው "ሊበርቲ ፋይተርስ ኔት ወርክ" በተሰኘ የአገር በቀል ድርጅት ሲሆን ተቋሙ በፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ በመቃወም ክሱን አቅርቧል።

    በዋና ከተማዋ ፕሪቶሪያ፣ የሚገኘው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ማክሰኞ እለት እንደወሰነው " የወጡት መመሪያዎች የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለማስቆም ወይንም ለመቀነስ ከሚለው ዓለማ ጋር የማይጣጣሙ ናቸው" ብሏል።

    ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ለ14 ቀን እንዲዘገይ በማድረግ በእነዚህ ቀናትም መንግሥት መመሪያዎቹን ለማሻሻል ወይንም ለመቀየር እንደሚችል ተናግሯል።

    የሚኒስትሮች ምክርቤት መመሪያዎቹን "በመከለስና በማሻሻል ዳግም እናወጣቸዋለን" በማለት እገዳዎቹ ግን ለአሁኑ ባሉበት እንደሚቆዩ ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል።

    በደቡብ አፍሪካ ተጥሎ የነበረው ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ከግንቦት የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ በተወሰነ መልኩ የተሻሻለ ሲሆን ከሰኔ ጀምሮም ለሁለት ወር ያህል ተጥሎ የነበረው የመጠጥ ሽያጭ ክልከላ ተነስቷል።

    አሁንም ግን በደቡብ አፍሪካ ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላው መንቀሳቀስም ሆነ ዜጎቻቸውን ለማውጣት ከሚደረጉ በረራዎች በስተቀር ሌሎች ዓለም አቀፍ በረራዎች ታግደዋል።

    ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች ከፍተኛው ቁጥር (30,000) የሚገኝባት ስትሆን 700 ሰዎችም በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል።

  15. ቢል ጌትስ በክትባት ስም ክንዳችን ውስጥ ሊቀብሩት ያሰቡት ነገር አለ?

  16. በምዕራብ ትግራይ በመሬት ካሳ ጉዳይ ለተቃውሞ የወጡ '45 ሰዎች ታሰሩ'

  17. የፕሪሚየር ሊጉ ቡድኖች የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያደርጉ ተፈቀደላቸው

    ሰኞ እለት በአንፊልድ ስታዲያም ሊቨርፑል ልምምድ ሲያደርግ

    የፎቶው ባለመብት, LFC

    የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለቡድኖቹ የወዳጅነት ግጥሚያዎችን ማካሄድ እንዲችሉ ፈቃድ ሰጠ። ፕሪሚየር ሊጉ ሰኔ አስር ከመጀመሩ በፊት ጥብቅ የሆነ መመሪያዎችን በማስቀመጥ ቡድኖች፣ የወዳጅነት ጨዋታዎችን እንዲያካሂዱ ፈቃድ ሰጥቷል።

    ቴሌግራፍ ጋዜጣ እንደዘገበው በደረጃ ሰንጠረዡ ከላይ ያሉት ቡድኖች ለሊጉ ውድድር ለመዘጋጀት እንዲረዳቸው የወዳጅነት ግጥሚያ እንዲያደርጉ ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል።

    የወዳጅነት ጨዋታዎች በልምምድ ሜዳዎች አልያም በስታዲየሞች ሊካሄዱ ይችላሉ ተብሏል።

    ፕሪሚየር ሊጉን የሚያስተዳድረው አካል በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በጨዋታው ላይ የሚሳተፉ ተጫዋቾች ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት እንዲያቀርቡ የሚለው ይገኝበታል።

  18. ፓኪስታን ባደረገችው ጥናት 670 ሺህ ያህል የሚገመቱ ምልክት የማያሳዩ ህሙማን ሊኖሩ እንደሚችሉ አስታወቀች

    በፖኪስታን ፀሎት የሚያደርጉ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የጤና ባለሙያዎች የፓኪስታኗ ፑንጃብ ግዛት ለ30 ቀን ያህል በእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ እንድትቆይ ምክረ ሃሳብ አቀረቡ።

    እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በግዛቲቱ መንግሥት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት 670 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ቢገመትም ምንም ምልክት አያሳዩም ተብሏል። ምልክት የማያሳዩ ህሙማን ግን ወደ ሌሎች እንደሚያስተላልፉም እንደተረጋገጠም ተገልጿል

    ይህ የሆነው በፑንጃብ ግዛት ዋና ከተማ ላሆር መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

    ላሆር 12 ሚሊየን ነዋሪዎች ሲኖሯት እስካሁን ድረስ 27 ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል።

    ይህ የዳሰሳ ጥናት አክሎ እንዳስታወቀው የትኛውም የመኖሪያ አካባቢም ሆነ የሥራ ቦታ ከቫይረሱ ነፃ አይደለም።

    በከተማዋ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት እድሜያቸው 50ና ከዚያ በላይ የሆኑ አዛውንቶች ናቸው ተብሏል።

    ከዚህ ሳምንት ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት እየወደቀ በመሆኑ “ፓኪስታን ከቫይረሱ ጋር መኖር አለባት” በሚል የእንቅስቃሴ ገደቡ እንዲነሳ ተከራክረዋል።

    በፓኪስታን በአጠቃላይ 76 ሺህ ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ሲረጋገጥ 1621 ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ያሳያል።

  19. ጣልያን ለቱሪስቶች ድንበሮቿን ከፈተች

    ሮም

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በአውሮፓ የሚገኙ ሃገራት ያሳለፏቸውን ቤት ውስጥ የመቀመጥም ሆነ የእንቅስቃሴ ገደቦች እያላሉ ሲሆን በኮሮና ክፉኛ የተጠቃችው ጣልያንም ድንበሮቿን ለጎረቤት ሃገራት ቱሪስቶች ክፍት አድርጋለች።

    ከዚህም በተጨማሪ በሃገሪቱ የነበረው የጉዞ እገዳ የሚነሳ ሲሆን ህዝቡም በተለያዩ ግዛቶች እንደፈለገ መንቀሳቀስ ይችላል ተብሏል።

    "በአሁኑ ወቅት ህጎቻችንን ስናላላ ወረርሽኙ ሊነሳ እንደሚችል ከስጋት ጋር ነው። ነገር ግን ሁኔታዎችን ባሉበት ተቀብለን እንቅስቃሴዎችን መፍቀድ አለብን ያለበለዚያ መቼም ቢሆን ሊከፈቱ አይችሉም "በማለት የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሰፔ ኮንቴ ተናግረዋል።

    የሃገሪቱ የምጣኔ ኃብት መሰረት ቱሪዝም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ጫናም ደርሶበታል። በአሁኑ ወቅት ግን የቱሪዝሙ ዘርፍ እንዲያንሰራራም በሮም የሚገኙ ቦታዎች በባለፉት ቀናት ለጎብኝዎች ክፍት ሆነዋል።

    በጣልያን በኮሮናቫይረስ 230 ሺህ ሰዎች ሲጠቁ፤ 33 ሺህ 500 ዜጎቿንም አጥታለች።

  20. አሜሪካ ሕግን በመጠቀም ጥቁር ዜጎቿ ላይ ግፍ ትፈፅማለች?