በኢትዮጵያ የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ከ62 ሺህ በላይ ሆነ

በኢትዮጵያ በባለፉት ሃያ አራት ሰአታት 3271 የላብራቶሪ ምርመራ መደረጉን ተከትሎ፣ በአጠቃላይ በሃገሪቷ የተደረገውን ምርመራ 62 ሺህ 300 አድርሶታል። ሃገሪቷ የመመርመር አቅሟንም በመጨመር በቀን ውስጥ 10ሺህ ሰዎችንም የመመርመር እቅድ እንዳላትም የጤና ሚኒስትሯ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው። በሃገሪቷም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 365 የደረሰ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል 238ቱ በህክምና ላይ ይገኛሉ፤120ዎቹም አገግመዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሃገሪቷ በኮሮናቫይረስ አምስት ዜጎቿን በሞት የተነጠቀች ሲሆን፤ ሁለቱም ወደመጡበት ሃገራት ተመልሰዋል። ስለወረርሽኙ የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት የቢቢሲ አማርኛን የቀጥታ ዘገባ ከእዚህ ገጽ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ህንድ ለሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች በነፃ ምግብ ልታከፋፍል ነው

    የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመግታት የጣለችውን የቤት ውስጥ መቀመጥ ውሳኔን ተከትሎ ከፍተኛ ጫና ለሚደርስባቸው ማህበረሰብ አካላት ድጎማ እያደረገች ያለችው ህንድ፤ ለሁለት ወራትም ያህል በአገር ውስጥ ላሉ ተፈናቃዮች በነፃ ምግብ ልትሰጥ መሆኑን አስታውቃለች።

    የገንዘብ ሚኒስትሩ ኒርማላ ሲታራማን ከሰሞኑ እንደገለፁት 463 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጥራጥሬና እህል አቅርቦት ለ80 ሚሊዮን የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ይረዳል ብለዋል።

    አገሪቷ እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ መገደቧን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ትውልድ ቦታቸው ለመመለስ በእግራቸው ረዥም ርቀትን እየተጓዙም ይገኛሉ።

    አብዛኛዎቹ ኢ-መደበኛ የሆነው የኢኮኖሚው ዘርፍ የተሰማሩና የከተሞቹም ምጣኔ ኃብት የጀርባ አጥንት የሚባሉ ናቸው። በዚህ አስገዳጅ ቤት መቀመጥ ውስጥም ተርበን እንሞታለን በሚልም ነው ረዥም ርቀትን እየተጓዙ የሚገኙት።

    በርካታዎችም ለቀናት ያህል ያለ በቂ ምግብና ውሃ ረዥም ርቀት መጓዛቸው በአገሪቱ ውስጥ ንዴትን ፈጥሯል።

    አገሪቷ በአጠቃለይ በኮቪድ-19 እንቅስቃሴን መገደብ የሚያስከትለውን ጫና ለመቋቋም 266 ቢሊዮን ዶላር መድባለች።

  2. ቬትናም የብሪታንያ አውሮፕላን አብራሪን ህይወት ለማዳን እየጣረች ነው

    ቱሪስቶች የሚያዘወትሩት የቬትናም ከተማ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቬትናም በኮቪድ-19 የተያዘና በጽኑ የታመመን ብሪታንያዊ አውሮፕላን አብራሪ ህይወት ለመታደግ እየታገለች ነው።

    ግለሰቡ ለቬትናም አየር መንገድ የሚሰራ ነበር ተብሏል።

    የ43 ዓመቱ ግለሰብ ታካሚ-91 ተብሎ የተሰየመ ሲሆን ሳንባው 10 በመቶ ብቻ እንደሚሰራ እንዲሁም ላለፉት 30 ቀናት በመተንፈሻ መሳሪያ እየታገዘ እንደሚተነፍስ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    ግለሰቡ በቫይረሱ የተያዘው በ ሆ ቼ ሚኒ ከተማ በሚገኝ ቡና ቤት ውስጥ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ መሆኑ ይታመናል።

    ህይወቱን ለማዳን ያለው አማራጭ የሳንባ ንቅለ ተከላ ማካሄድ መሆኑን የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ተናግረዋል።

    እስካሁን ድረስ አስር ሰዎች፣ የ70 ዓመት የቀድሞ ወታደርን ጨምሮ፣ ሳንባቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን ቢናገሩም ይኹንታን ግን አላገኙም።

    በቬትናም ህግ መሰረት በህይወት ያለ ሰው ሳንባውን መለገስ አይፈቀድለትም።

    እስካሁን ድረስ በቬትናም በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች መካከል አንድም ሰው ያልሞተ ሲሆን አሁንም ይህ እንዲቀየር የምትፈልግ አይመስልም።

    አገሪቱ እስካሁን ድረስ የአብራሪውን ህይወት ለመታደግ አሉኝ የምትላቸውን ምርጥ የሕክምና ባለሙያዎች በመመደብ ወደ 200 000 ዶላር ያወጣች መሆኑንም የቬትናም የዜና ኤጀንሲ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይን ጠቅሶ ዘግቧል።

  3. ሩሲያ 25ሺህ ቶን ስንዴ ለሰሜን ኮሪያ ላከች

    የርዳታው ስንዴ ከመርከብ ላይ ሲወርድ

    የፎቶው ባለመብት, Russian embassy, Pyongyang

    ሩሲያ 25ሺህ ቶን ስንዴ ለሰብዓዊ ርዳታ ወደ ሰሜን ኮሪያ መላኳን በፒዮንግያንግ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል።

    ኤምባሲው ጨምሮ እንዳስታወቀው የመርከቧ ሠራተኞች ራሳቸውን ለይተው የተቀመጡ ሲሆን ስንዴውም በወደቡ ላይ በተለየ ስፍራ መራገፉን አስታውቋል።

    "የሰሜን ኮሪያ የወደብ ሰራተኞችንና የባቡር ሠራተኞችን የጥምረት ሥራ ከርቀት መመልከት ችለናል" ኤምባሲው ማለቱን ታስ የተሰኘው የዜና ወኪል ገልጿል።

    አክሎም " አንዲት ቅንጣት እንኳ ስንዴ እንዳትወድቅ እንደሚጠነቀቁ እያየን ነው" ብለዋል።

    ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት 10 ሚሊየን ሰሜን ኮሪያውያን ለከፋ የምግብ እጥረት ይጋለጣሉ ሲል አስጠንቅቆ ነበር።

    አሁን ሩሲያ የላከችው የምግብ እርዳታ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለተጎዱ ይሁን ወይም በድርቅ ለተጠቁ የታወቀ ነገር የለም።

    ሰሜን ኮሪያ እስካሁ ድረስ አንድም ሰው በቫይረሱ መያዙን አላሳወቀችም።

  4. የማሽተትና የመቅመስ ስሜቷን ያጣችው ሼፍ

  5. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ወዳጆች!

    የዓለም ካርታ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ከሰሞኑ እንደገለፁት በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረስ የተያዙት 272 ሰዎች የእድሜ ስብጥር ሲታይ ከህፃናት እስከ አረጋዊያን፣ በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው።እድሜያቸው ከ15-24 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች 99 ሲሆኑ፤ ከዛ የሚቀጥለው ከ25-34 የእድሜ ክልል ውስጥ (75 ሰዎች)፣ ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ቁጥርም 19 ናቸው። በህፃናት ላይ አነስተኛ ቁጥር ቢሆኑም በሽታው እንደሚይዛቸው መረጃዎች ጠቁመዋል።

    ኮቪድ-19 የማያጠቃው የእድሜ ክልል የለም። በተለይ በኢትዮጵያ ያለው ስርጭት ትልቁ ቁጥር በወጣቶች ላይ ታይቷል። ስለዚህ እያንዳንዱ ግለሰብ የሚወስደው የግል ጥንቃቄ የኮሮና ወረርሽኝን ስርጭት መከላከል እጅግ አስፈላጊ ነው።ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን ምን ያህል ይጨምራል የሚለውን የሚወሰነው በየዕለቱ በሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ይሆናል። ስለዚህ አንዘናጋ!