በኢትዮጵያ የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ከ62 ሺህ በላይ ሆነ

በኢትዮጵያ በባለፉት ሃያ አራት ሰአታት 3271 የላብራቶሪ ምርመራ መደረጉን ተከትሎ፣ በአጠቃላይ በሃገሪቷ የተደረገውን ምርመራ 62 ሺህ 300 አድርሶታል። ሃገሪቷ የመመርመር አቅሟንም በመጨመር በቀን ውስጥ 10ሺህ ሰዎችንም የመመርመር እቅድ እንዳላትም የጤና ሚኒስትሯ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው። በሃገሪቷም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 365 የደረሰ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል 238ቱ በህክምና ላይ ይገኛሉ፤120ዎቹም አገግመዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሃገሪቷ በኮሮናቫይረስ አምስት ዜጎቿን በሞት የተነጠቀች ሲሆን፤ ሁለቱም ወደመጡበት ሃገራት ተመልሰዋል። ስለወረርሽኙ የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት የቢቢሲ አማርኛን የቀጥታ ዘገባ ከእዚህ ገጽ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የቤተክርስቲያኑ አገልጋዩ የቃልኪዳን ስነ ስርዓት በማስፈፀሙ በቁጥጥር ስር ዋለ

    በደቡባዊ ናይጄሪያ በምትገኘው ካላባር ከተማ በአንድ ቤተክርስትያን ውስጥ የሚያገለግል ግለሰብ የወጣውን የእንቅስቃሴ ገደብ ተላልፎ በቤተእምነቱ ውስጥ ለተጋቢዎች የቃልኪዳን ስነ ስርዓት በማስፈፀሙ በቁጥጥር ስር ዋለ።

    በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል ባለስልጣናት ወደ ቤተ እምነቱ ሲገቡ እንግዶች ለቅቀው ሲወጡ ይታያል።

    የቤተ እምነቱ አገልጋይ በከተማዋ የኮቪድ-19 ግብረ ኃይል በቁጥጥር ስር የዋለው ቅዳሜ እለት ሲሆን ከቤተክርስትያኑ ውጪ በርከት ያለ መኪና በማየታቸው ተጠራጥረው መግባታቸው ተነግሯል።

    "እየተዘዋወርን የእንቅስቃሴ ገደቡ በአግባቡ ተፈፃሚ መሆን አለመሆኑን እየቃኘን ነበር። በርካታ መኪኖች ቆመው ስናይ ለምን እንደመጡ ተገርመን ነበር የገባነው" ሲሉ ለቢቢሲ ፒጅን የቅኝቱ መሪ ተናግረዋል።

    በቤተ እምነቱ ውስጥ ሲገቡ 300 ያክል ሰዎች አካለዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ተሰባስበው እንደነበር ጨምረው አስረድተዋል።

    በግዛቲቱ ከአምስት ሰው በላይ መሰብሰብ የተከለከለ ሲሆን የአፍና አፍንጫም መሸፈኛ እንዲደረግ መመሪያ ተቀምጧል።

  2. ኳታር፡ 'ጭምብል ያላጠለቁ ሶስት ዓመት ይታሠራሉ'

    ማስክ ያደረጉ ሰው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኳታር፡ ኳታርና እና ኩዌት ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) የማያደርጉ ሰዎች ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጣልባቸው አስታውቀዋል። በመሆኑም በኳታር ይህንን ሕግ የሚጥሱ ሦስት ዓመት የሚደርስ እስር ይጠብቃቸዋል ተብሏል። በኩዌት ግን ሕጉን ለሚተላለፉት ከፍተኛው ቅጣት የሦስት ወር እስር ነው።

    ሌባኖስ፡ በሌባኖስ የተጣለው የአራት ቀናት ከቤት ያለመውጣት ገደብ ቢጠናቀቅም በምሽት የተጣለው የሰዓት እላፊ ግን እንደነበረ ነው። በአገሪቷ የተወሰኑ ገደቦች መላላታቸውን ተከትሎ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደቡ እንደገና የተጣለው ባለፈው ሳምንት ነበር።

    የመን፡ በየመኗ የወደብ ከተማ ኤደን በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከመደበኛው በአምስት እጥፍ መጨመሩን ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል። በመሆኑም የጦር ቀጠና በሆነችው አገር የቫይረሱ መስፋፋት ስጋትን ፈጥሯል።

    በዚህ ሳምንት መጨረሻ የሚከበረውን የኢድ አል ፈጥር በዓል ተከትሎ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ጥብቅ ውሳኔዎችን እያስተላለፉ ነው። ሳዑዲ አረቢያ በበዓሉ ጊዜ በአገሪቷ ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ለመጣል አቅዳለች።

    ግብፅም ለስድስት ቀናት የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለማቋረጥ ያሰበች ሲሆን የሰዓት እላፊውንም ከአራት ሰዓታት ቀደም ብላ ለማድረግ አስባለች።

  3. የዓይን እማኞች በመቀለ በፀጥታ ኃይሎች ስለተገደለው ወጣት ምን ይላሉ?

  4. የደቡብ አፍሪካ ጦር የመስክ ሆስፒታሎችን መገንባት ጀመረ

    ጦሩ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለማስፈፀም ኃይሉን አሰባስቧል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ጦሩ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለማስፈፀም ኃይሉን አሰባስቧል

    የደቡብ አፍሪካ ጦር ኮቪድ-19 በአገሪቷ ላይ እያደረሰ ላለው የጤና ቀውስ ለመዘጋጀት በመስክ ላይ አራት ሆስፒታሎችን መገንባት መጀመሩን ዘ ኢንድፔንደንት ኦንላይን ድረ ገፅ ዘገበ።

    እንደ ድረ ገፁ ዘገባ ጦሩ ከ18 ቀናት በፊት ሁሉም ሰራተኞቹ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፤ ወረርሽኙ አስከፊ ሊሆን ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያ ከተሰጠ በኋላ፤ የ2010 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የተካሄደበትን ስታዲየም ወደ ሆስፒታል የመለወጥም እቅድ አለው።

    ድረ ገፁ በጦሩ ውስጥ ያሉ ምንጮቹን “ሆስፒታሎችን የመገንባት እቅዱ ያልተለመደ አይደለም፤ ያለው የጤና ተቋማትን ለማጠናከር ያለመ ነው” ማለታቸውን ጠቅሷል።

    ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ ደቡብ አፍሪካ የጣለችውን ሙሉ በሙሉ በቤት የመቀመጥ ገደብ ስታላላ ወረርሽኙ እየጨመረ በመምጣቱ ዜጎች ለከፋው ቀውስ እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።

    ደቡብ አፍሪካ እስካሁን በአገሪቷ በአንድ ቀን ውስጥ ከተመዘገበው ከፍተኛ የተባለውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መዝግባለች።

    አገሪቷ ባለፉት 24 ሰዓታት 1ሺህ 160 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 15ሺህ 515 ደርሷል።

    ከእነዚህ መካከል 7ሺህ 76 ሰዎች ከቫይረሱ ሲያገግሙ 264 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

  5. ሰበር, በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ከፍተኛው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዘገበ

    BBC

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ 1775 የላብራቶሪ ምርመራ 35 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በዕለታዊ መግለጫቸው አስታውቀዋል።

    ይህም አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 352 አድርሶታል።

    ቫይረሱ የተገኘባቸውም 17 ወንድና 18 ሴት ሲሆኑ 24ቱ ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው፤ ስድስቱ የውጭ አገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው ቀሪዎቹ አምስቱ ደግሞ ምንም አይነት ንክኪም ሆነ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ናቸው ተብሏል።

    በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ከአዲስ አበባ ፣ ከኦሮሚያ ፣ ከሶማሌ ክልል እና ከአማራ ክልል መሆናቸው ተገልጿል።

  6. ኮሮናቫይረስን በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግ አገራት ጥያቄ ያቀርባሉ ተባለ

  7. በሩሲያ ከ8ሺህ በላይ ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ ተያዙ

    ዣንጥላ ይዛ የምትራመድ ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሩሲያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 8ሺህ 926 ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዘገበች። ይህም በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ከ290 ሺህ በላይ አድርሶታል።

    ባለፉት 24 ሰዓታትም 91 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል።

    አጠቃላይ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥርም 2ሺህ 722 ሆኗል።

  8. የቻይና ፕሬዚደንት በዓለም ጤና ድርጅት ጉባዔ ላይ ንግግር ሊያደርጉ ነው

    ዢ ጂንፒንግ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የቻይና ፕሬዚደንት ዢ ጅንፒንግ ዛሬ በሚካሄደው 73ኛው የዓለም ጤና ድርጅት ጉባዔ ላይ ንግግር ሊያደርጉ ነው።.

    ፕሬዚደንቱ ወረርሽኙን ተከትሎ በተጣለው ዓለም አቀፍ የእንቅስቃሴ ገደብ ሳቢያ በጉባዔው ላይ በአካል ባይገኙም፤ በቪዲዮ የመክፈቻ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ቻይና ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ ስለ በሽታው ለዓለም ጤና ድርጅትና ለተቀሩት አገራት በአፋጣኝ አላሳወቀችም በሚል በአንዳንድ አገራት ወቀሳ ይቀርብባታል።

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ ምርመራ ለማድረግ ጊዜው አሁን አይደለም ሲል ሰኞ ዕለት በድጋሜ አስታውቋል።

    ጉባኤው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ በጉባዔው ላይ ከተያዙ መርሃ ግብሮች መካከልም የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተሰጠ ምላሽን የተመለከተ ገለፃ እና የምርጫ ጉዳይ ይገኙበታል።

  9. አፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግሥታት የብሩንዲ ምርጫ እንዳሳሰባቸው ገለፁ

    የምርጫ ቅስቀሳው ትናንት ተጠናቋል

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, የምርጫ ቅስቀሳው ትናንት ተጠናቋል

    የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት በብሩንዲ በመጪው ረቡዕ የሚካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በሚካሄዱ ዘመቻዎች በተቃዋሚ እና በገዥ ፓርቲ ደጋፊዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች እንዳሳሰባቸው ገለፁ።

    በመሆኑም ሁለቱንም ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የፀጥታ ኃይሎችም ፍትሃዊ የሆነ ምርጫ እንዲካሄድ እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል።

    የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች በበኩላቸው ከሦስት ሳምንታት በፊት የተጀመረውን የብሩንዲ የምርጫ ቅስቀሳ ተከትሎ 150 የሚጠጉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መታሰራቸውን ተናግረዋል።

    ፕሬዚደንት ንክሩንዚዛ በድጋሜ በምርጫ የማይወዳደሩ ቢሆንም፤ መንግሥት ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ 'ፓራማውንት ሊደር' [ዋና መሪ] የሚል ኃላፊነት እንዲሰጣቸው የሚያደርገውን ሕግ ካፀደቀ በኋላ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

    ብሩንዲ የተባበሩት መንግሥታትንም ሆነ የሲቪል ማህበረሰቡን የምርጫ ታዛቢዎች እንደማትፈልግ ማስታወቋ ይታወሳል።

    በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ መሠረት በብሩንዲ እስካሁን 42 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል።

  10. አውስራሊያዊያን የእረፍት ቀናቸውን በነጻነት ማሳለፍ ጀመሩ

    Australia

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በሜልበርን ከተማ ዳግም በተከፈተው መናፈሻ ውስጥ ነዋሪዎች ከዘመድ ወዳጆቻቸው ጋር ቅዳሜ እና እሁዳቸውን በጋራ ሲያሳልፉ

    በአውስትራሊያ ተጥሎ የነበረው ገደብ መቅለል መጀመሩን ተከትሎ ዜጎች የእረፍት ጊዜያቸውን በነጻነት ማሳለፍ ጀምረዋል።

    አብዛኛዎቹ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ሲመለከቱ ይህ ከ10 ሳምንታት በኋላ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው።

    በሜልበርን ከተማ ዳግም በተከፈተው መናፈሻ ውስጥ ነዋሪዎች ከዘመድ ወዳጆቻቸው ጋር ቅዳሜ እና እሁዳቸውን በጋራ ሲያሳልፉ ታይተዋል።

    ቪክቶሪያ የምትሰኘው ግዛትም 10 ሰዎች በአንድ ላይ መሰብሰብ ይችላሉ ስትል ፍቃድ ሰጥታለች።

    አውስራሊያ 7ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን እና 99 ሞት መመዝገቧን አስታውቃለች።

    Australia

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  11. ሕንድ በአንድ ቀን ከፍተኛ የተባለውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መዘገበች

    ርቀታቸውን ጠብቀው የተቀመጡ ሴቶች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በሕንድ መንግሥት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የጣላቸውን ገደቦች ማላላት ቢጀምርም፤ ባለፉት 24 ሰዓታት ተጨማሪ 5 ሺህ 242 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ይህም በአገሪቷ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር ነው ተብሏል።

    ይህም በአገሪቷ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 96 ሺህ 169 አድርሶታል።

    አገሪቷ ከቤት ያለመውጣት ገደቡን በዚህ በተያዘው የፈረንጆቹ ወር መጨረሻ ለማጠናቀቅ በማቀዷ ትችት ቢሰነዘርባትም፤ አንዳንድ ወሳኝ የሆኑ ሱቆችና የንግድ ተቋማት መከፈት ጀምረዋል። አውቶብሶችም በከተማ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ እንዲሁም ፈቃድ ካላቸውም የግዛት ድንበሮችን መሻገር እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋል።

    የእንቅስቃሴ ገደቡን ማላላት በኢኮኖሚ የተጎዳችዋን ሕንድ እንድታገግም ይረዳታል በሚል በአንዳንዶች ዘንድ እንደወሳኝ እርምጃም ተወስዷል።

    በሕንድ ወረርሽኙን ተከትሎ ከ120 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሥራቸውን አጥተዋል።

    በአገሪቷ ከፍተኛው የሥራ አጦች ቁጥር የተመዘገበ ሲሆን 27.1 በመቶዎቹ ሥራ አጥ ሆነዋል። ይህ አሃዝ አሜሪካ በታሪኳ ካጋጠማት ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር በአራት እጥፍ ይበልጣል ተብሏል።

  12. የአሜሪካ ኢኮኖሚ በኮሮናቫይረስ ሰበብ በ30 በመቶ ያሽቆለቁላል ተባለ

  13. ካምቦዲያ ከኮሮናቫይረስ 'ነፃ ነኝ' አለች

    ማስክ ያደረጉ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    እስያዊቷ አገር ካምቦዲያ ከኮሮናቫይረስ ነፃ መሆኗን አስታወቀች።

    ካምቦዲያ ሆስፒታል ውስጥ የነበረች አንድ የመጨረሻ ታማሚ ከኮቪድ -19 አገግማ ከሆስፒታል መውጣቷን አስታውቃለች። በመሆኑም አሁን ላይ አዲስ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ባለመኖሩ ከቫይረሱ ‘ነፃ ነኝ’ ብላለች።

    የ36 ዓመቷ ሴት በዋና መዲናዋ ከሚገኘው ሆስፒታል ሲትወጣ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል ቅዳሜ እለት በካምቦዲያ ቴሌቪዥን በቀጥታ ታይቷል።

    ካምቦዲያ 122 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ቢሆንም በቫይረሱ አንድም ሰው አልሞተም።

    ይሁን እንጅ የጤና ባለሥልጣናት ትምህርት ቤቶችን እንዲሁም በድንበር አካባቢ ምርመራ እና ለይቶ ማቆያዎችን በተመለከተ የተላለፉ ውሳኔዎችን እንደማያላሉ አሳስበዋል።

    የጤና ሚኒስትሩ ማም ቡንሄንግ “አብዛኛው በቫይረሱ የተያዘ ሰው ከሌላ ቦታ የገባ ነው፤ በመሆኑም በድንበር አካባቢ፣ በአየር ማረፊያዎች እና በተለያዩ የምርመራ ጣቢያዎች የሚደረጉ ምርመራዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል” ሲሉ ተናግረዋል።

  14. በመቀለ 'ርቀት ለማስጠበቅ' በተወሰደ እርምጃ አንድ ሰው ተገደለ

    Mekele City

    በመቀለ ከተማ 05 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፤ ተሰብስበው የነበሩ ወጣቶችን ለመበተን በተደረገው ጥረት ግጭት ተከስቶ አንድ ወጣት በፖሊስ አባል መደገሉን የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ለቢቢሲ ገለጸ።

    ፖሊስ እንዳለው ከሆነ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መጠጥ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ተከትሎ ወጣቶች 05 ቀበሌ በአንድ ላይ ተሰባሰበው እየጠጡ ነው የሚል መረጃ እንደደረሰው አስታውቋል።

    በጥቆማው መሠረት ፖሊስ ወደተባለበት ስፍራ ተሰማርቶ ወጣቶቹ እንዲበተኑ ለማድረግ ሲጥር፤ በተፈጠረ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት አልፏል ብሏል። ሆኖም ይህ በወጣቶቹ በኩል ማረጋገጥ አልተቻለም።

    ከዚህ በተጨማሪም በሁለት ወጣቶች ላይ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።

    በጠፋው ህይወት የተጠረጠረው ፖሊስም በቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማው ፖሊስ አስታውቋል።

  15. 'የቫይረሱ ምንጭ ይጣራ' የሚለው ሞሽን ከ100 በላይ አገራት ድጋፍ አገኘ

    WHO

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አውስትራሊያ ያስጀመረችው የቫይረሱ ምንጭ በገለልተኛ አካል ይጣራ የሚለው የውሳኔ ሃሳብ ከ100 በላይ አገራት ድጋፍ አግኝቷል።

    በበርካታ አገራት የተደገፈው ይህ የውሳኔ ሃሳብ፤ ዛሬ ከሰዓት የዓለም ጤና ድርጅት አባል አገራት ጤና ሚንስትሮች በሚያደርጉት ቴሌ ኮንፍረንስ ላይ ለውሳኔ ሃሳቡ ድጋፍ በመስጠት፤ ሃሳቡ ውሳኔ እንዲያገኝ ይሆናል ሲል የአውስትራሊያው ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ዘግቧል።

    ይህ የውሳኔ ሃሳብ ቫይረሱ ከየትኛው አካባቢ ጀመረ የሚለው ሳይሆን የቫይረሱ ምንጭ ምንድነው የሚለው በገለልተኛ አካል እንዲጣራ የሚጠይቅ ነው።

    የማጣራት ሂደቱ ቻይናን የሚያገል እንደሆነ ተገምቷል። ከዚህ ቀደም አውስትራሊያ የቫይረሱ ምንጭ ይጣራል የሚል ሃሳብ ባቀረበችበት ወቅት ቻይና ይህ "ፖለቲካዊ አካሄድ ነው" ስትል ተቃውማ ነበር።

    • የወባ መድኃኒት ምን ያህል ኮሮናቫይረስን ለማከም ይችላል?

    • ናይጄሪያ የኮሮናቫይረስ ክልከላን ተላልፏል ያለችውን የእንግሊዝ አውሮፕላን ያዘች

      የአዚዬሽን ሚንስትሩ ሃዲ ሲሪካ

      የፎቶው ባለመብት, Getty Images

      የምስሉ መግለጫ, የአዚዬሽን ሚንስትሩ ሃዲ ሲሪካ

      ናይጄሪያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ተጥሎ የሚገኘውን ክልከላ ተላልፏል ያለችውን የእንግሊዝ አየር መንግድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን ያዘች።

      የአቪዬሽን ሚንስትሩ ሃዲ ሲሪካ እንዳሉት፤ ፍሌርጄት የተባለው የብሪታኒያ አየር መንገድ የእርዳታ ቁሳቁሶችን እንዲያጓጉዝ የተሰጠውን ፍቃድ በመጠቀም መንገደኞችን ሲያጓጉዝ ነበር ብለዋል።

      ናይጄሪያ የበሽታውን ስርጭት ለቆጣጠር በማሰብ ተመላሽ ዜጎቿን ከመቀበል ውጪ ድንበሮቿን ለመንገደኞች የአውሮፕላን ጉዞ ዝግ ማድረጓ ይታወሳል።

      የፍሌርጄት ተግባር ከፍተኛ ችልተኝነት የታየበት ነው ያሉት የአቪዬሽን ሚንስትሩ፤ የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ጠንከር ያለ ምርመራ ይደረግባቸዋል፤ ቅጣትም ይጠብቃቸዋል ብለዋል።

      ኩባንያው ስለተያዘው ንብረቱ ያለው ነገር የለም።

      የናይጄሪያ የበረራ እግድ ለመጪዎቹ 15 ቀናት ይቆያል።

    • በአውሮፓ አገራት በቫይረሱ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነስ ነው

      ስፔን

      የፎቶው ባለመብት, Getty Images

      ሌላ አዲስ ተስፋ ከወደ አውሮፓ ተሰምቷል። በበርካታ የአውሮፓ አገራት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከረዥም ጊዜ በኋላ ቀንሶ ታይቷል።

      ጣሊያን በ24 ሰዓታት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 145 ነው ስትል ትናንት አስታውቃለች።

      ስፔን በበኩሏ የሟቾች ቁጥር 85 ብቻ ነው ብላላች። ይህም የእንቅስቃሴ ገደቦችን ከጣለች ወዲህ ይህ ዝቅተኛው በ24 ሰዓታት ውስጥ የተመዘገበ የሞት መጠን ነው።

      ተመሳሳይ መልካም ዜናም ከወደ ዩናይትድ ኪንግደምም ተሰምቷል። የአገሪቱ መንግሥት የሟቾች ቁጥር 170 መሆኑን አስታውቋል። ይህም ከሁለት ወራት በኋላ በ24 ሰዓታት ውስጥ የተመዘገበው አስተኛው የኮቪድ-19 የሞት መጠን መሆኑ ነው።

    • በብራዚል የሳኦ ፖሎ ሆስፒታሎች በኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ተጨናንቀዋል

      ሆስፒታል

      የፎቶው ባለመብት, AFP/GETTY IMAGES

      የምስሉ መግለጫ, በመጭዎቹ ሁለት ሳምንታት በሳኦ ፖሎ የሚገኙ የሕዝብ ሆስፒታሎች ቦታ እንደማይኖራቸው የከተማዋ ከንቲባ አስጠንቅቀዋል

      የኮሮናቫይረስ ወረርሽኘን ተከትሎ የድንገተኛ ክፍል አልጋዎች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ የአገሪቷ የጤና አገልግሎት ሥርዓትን ሊያፈራርሰው እንደሚችል የብራዚል ትልቋ ከተማ ሳኦ ፖሎ ከንቲባ አስታወቁ፡፡

      ከንቲባ ብሩኖ ኮቫስ እንዳሉት በከተማዋ የሚገኙ ሆስፒታሎች 90 በመቶ በታማሚዎች የተያዙ ሲሆን በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ቦታ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

      በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተጠቃችው ሳኦ ፖሎ እስካሁን በቫይረሱ 3ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ሞት ተመዝግቦባታል፡፡

      ብራዚል ቅዳሜ ዕለት በሟቾች ቁጥር ስፔን እና ጣሊያንን በመብለጥ በዓለማችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

      ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ያሉባቸው አገራት አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው፡፡

      የአገሪቷ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ባለፉት 24ሰዓታት 7 ሺህ 938 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን ይህም በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 241 ሺህ አድርሶታል፡፡

      በላቲን አሜሪካ ባለፉት 24 ሰዓታት 485 ሰዎች በቫይረሱ የሞቱ ሲሆን በአጠቃላይ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 16 ሺህ 118 ደርሷል፡፡ ይህም የአለማችን ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር ሆኖ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተመዝግቧል፡፡

      በብራዚል የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው በቂ ምርመራ እየተደረገ ባለመሆኑ በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በይፋ ከተመዘገበው በላይ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

      የብራዚል ፕሬዚደንት ጀር ቦለሶናሮ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በቂ እርምጃ አለመውሰዳቸውን ተከትሎ በአገር ውስጥም በውጭም ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡

      ይባስ ብሎ ባለፈው እሁድ በዋና ከተማዋ ብራዚሊያ፤ከደጋፊዎቻቸው እና ህጻናት ጋር ሆነው ፎቶ በመነሳት ከዓለም የጤና ምክሮች አንዱ የሆነውን አካለዊ ርቀትን ጥሰው ታይተዋል፡፡

    • እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ተከታታዮች?

      Addis Ababa

      የፎቶው ባለመብት, Getty Images

      ቢቢሲ አማርኛ የተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፍ ዘገባዎችን በቀጥታ ወደ እናንተ ማድረሱን ቀጥሏል፡፡

      እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እስካሁን በዓለማችን 4 ሚሊየን 713 ሺህ 769 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋጋጠ ሲሆን፤ 1.7 ሚሊዮን በላይ ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል፡፡

      ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ ምክሮችን በመተግበር ራሳችንን እና ማህበረሰባችንን ከኮሮናቫይረስ እንከላከል መልዕክታችን ነው፡፡

      ያማረ ቀን ይሁንላችሁ!