በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሽያጩ የደራው የካሜሮኑ የኮክቴል መጠጥ

በካሜሮኗ የንግድ ማዕከል ዱዋላ የሚገኝ አንድ መጠጥ ቤት የኮክቴል መጠጦቹን በዚህ ቤት መቀመጥ አስገዳጅ በሆነበት ጊዜ እንዴት መሸጥ እንደሚችል መላ ዘይዷል።
በርካታ የንግድ እንቅስቃሴዎች መውጫው ጠፍቷቸው ቀጥ ባሉበት ወቅት ይህ ጄጄ ኩዌስት የተባለው መጠጥ ቤት (ባር) በየቤቱ የኮክቴል መጠጦቹን የማድረስ ስራን ጀምሯል።
"የመጀመሪያዎቹ ቀኖች ላይ ምን እያደረግን እንደነበር ግራ ተጋብተን ነበር" ብሏል የመጠጥ ቤቱ ስራ አስኪያጅ አሌክሳንደር ኩዌስት።
ከጥቂት ቀናት በኋላም መጠጥ የሚፈልጉ ሰዎች ይደውሉላቸው ጀመር።
ልክ በተደወላላቸው አንድ ሰአት ውስጥ ቤቱ (አፓርትመንቱ) ውስጥ ሆኖ የተለያዩ መጠጦችን አቀላቅሎ በሞተር ሳይክል ቤታቸው እንዲደርስ ያደርጋል።

አንድ ሊትር የኮክቴል መጠጥ ወደ 640 ብርም ያወጣል።
ምንም እንኳን በኮሮናቫይረስ ምከንያት ጫና ቢደርስባቸውም በአሁኑ ወቅት ካለው ሁኔታ ጋር ራሳቸውን በማላመድ መጠጣቸውንም እየሸጡ ይገኛሉ።
"በኔ አስተያየት ጥሩ ንግድ የሚባለው በየትኛውም ሁኔታ ደንበኞችን ማገልገል ሲቻል ነው። በአሁኑ ሰአት ደንበኞቻችን በአስቸጋረ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። እኛም አለንላችሁ እያልን ነው" ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ "ፍሪጃችሁ ውስጥ ምንድን ነው ያለው?" የሚል አገልግሎት ጀምሯል። ደንበኞች ፍሪጃቸው ውስጥ ያለውን የመጠጥ አይነቶች ያሳዩታል እሱም እነዚህን መጠጦች ደባልቀው ምን መስራት እንደሚችሉ ምክሩን ይለግሳል።


















