በእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት የምግብ እጥረት በማጋጠሙ ቺሊያውያን ከፖሊስ ጋር ተጋጩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእንቅስቃሴ ገደቡ ተጥሎ ባለበት ወቅት የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ቺሊያዊያን በመዲናዋ ሳንቲያጎ ከፖሊስ ጋር ተጋጩ።
የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ፖሊስ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ዜጎችን በአስለቃሽ ጪስ ሲበትን አሳይተዋል።
በቡድን ሆነው ለተቃውሞ የወጡት ዜጎች ድንጋይ ሲወርውሩ እና እሳት ሲያቀጣጥሉ ታይተዋል።
የአካባቢው ባለስልጣናት "በረሃብ እና በሥራ አጥነት" ምክንያት ውስብስብ ችግር ውስጥ ነን እያሉ ነው።
ከተቃውሞ ሰልፉ በኋላ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ሴባስቲያን ፒኔራ፤ በቴሌቪዥን ለህዝቡ ባደረሱት መልዕክት የምግብ አቅርቦ ለቸገራቸው ዜጎች ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውዋል።
ፕሬዝደንቱ ይህን ይበሉ እንጂ ተቃውሞ የተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ባለስልጣናት መንግሥት የዜጎችን ፍላጎት የሟሟላት አቅም እንዳለው ይጠራጠራሉ።
ቺሊ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ከ46ሺህ በላይ ሰዎችን ያሉባት ሲሆን 478 ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።
















