በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ በተገኘ በሁለተኛው ወሩ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምርመራ ተደረገ

በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ እንዳለበት የተረጋገጠ ሰው የተገኘው መጋቢት 04/2012 ዓ.ም ነበር። የመጀመሪያው ቫይረሱ የተገኘበት ግለሰብ ጃፓናዊ ዜግነት የነበረው ሲሆን በሥራ አጋጣሚ ከበርካታ ኢትዮጵያዊን ጋር ተገናኝቶ ነበር። ባለፉት ሁለት ወራት የበሽታው መስፋፋት ቀስበቀስ እጨመረ አሁን ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ደርሷል። ነገር ግን ከሚያዝያ ወር መጨረሻ ጀምሮ በየዕለቱ እየተመዘገበ ያለው ቁጥር አሳሳቢ ሆኗል። በሽታው የሚገኝባቸው ቦታም እየሰፋ ነው። የጤና ባለሙያዎች በሽታው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚናገሩት የእጅ ንጽህናን በአግባቡና በተደጋጋሚ መጠበቅና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ከመከላከያ መንገዶቹ ዋነኞቹ ሲሆኑ፤ በተጨማሪ ደግሞ በርካታ ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ቦታ ላይ የምንገኝ ከሆነ የአፍና የአፍናጫ መሸፈኛ መጠቀምም አሁን የግድ እየሆነ ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. አንድ ሺህ የሚጠጉ አፍሪካዊያን የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘዋል ተባለ

    የአለም ጤና ድርጅት በትዊተር ገፁ እንዳሰፈረው በአፍሪካ ውስጥ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል ብሏል።

    ድርጅቱ በተጨማሪም የአፍሪካ መንግሥታት ለነርሶችና ዶክተሮች የመከላከያ ቁሳቁሶች እንዲያሟሉ ጥሪ አቅርቧል።

    ከኮሮና ህሙማን ጋር ንክኪ የሚኖራቸው የህክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን የሚከላከሉበት የህክምና ቁሳቁሶችን መሟላታቸውን መንግሥታት እርግጠኛ መሆን አንዳለባቸውም አፅንኦት ሰጥቷል።

    በተለይም ከህሙማኑ ምራቅ ናሙና ጋር ንክኪ ያላቸው የላብራቶሪ ሰራተኞችም ሆኑ ዶክተሮች ደረጃውን የጠበቀ መከላከያ ያስፈልጋቸዋልም ተብሏል። ከዚህም ውስጥ በውስጡ መተንፈሻ የተገጠመለት ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ጭምብልና ቶሎ ቶሎ መቀየር የሚችሉ ጋወኖች ይገኙበታል ።

  2. ሊባኖስ ለተከታታይ አምስት ቀን ማንም ሰው ከቤቱ እንዳይወጣ አዘዘች

    በሊባኖስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጣለ።

    የተጣለው የሰዓት እላፊ ከነገ ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን እስከ ሰኞ ማለዳ ድረስ ይቆያል ተብሏል።

    ከዚህ ቀደም የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳ በኋላ ለአንድ ወር ያህል በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

    ዜጎች " ቤታቸው መቀመጥ አለባቸው አስቸኳይ ጉዳይ ካልገጠማቸው በስተቀር ወደ የትም መሄድ የለባቸውም" ያሉት የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ማናል አብደል ሳማድ ናቸው።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን ዲያብ በበኩላቸው፣ ባለፉት አራት ቀናት ብቻ 100 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ገልፀዋል።

    መንግሥት አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ላይ ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ የማያደርጉ ሰዎችንም " ግዴለሽና ሃላፊነት የጎደላቸው" በማለት ወርፈዋቸዋል።

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ከሆነ በአገሪቱ 870 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ ከእነዚህም መካከል 26 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

    በሊባኖስ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳ በኋላ የአካላዊ ርቀት መጠበቅ ተግባራዊ እንዲሆን በማሳሰብ ሱቆችና የአምልኮ ስፍራዎች ተከፍተዋል። ይህ የሆነው ከሁለት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።

    በቫይረሱ የተያዙ አዳዲስ ሰዎች የተገኙት በአብዛኛው ከአገር ውጪ የነበሩ ሊባኖሳውያን በመመለሳቸው መሆኑ ተገልጿል።

    ከአምስት ቀናት በፊት ከናይጄሪያ፣ ሌጎስ የመጡ ሁሉም ተሳፋሪዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር አስታውቆ ነበር።

    የእንቅስቃሴ ገደቡ ከተነሳ በኋላ ዜጎች በመገበያያ ስፍራዎች አካላዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ሲገበያዩ የታዩ ሲሆን፣ በአውራ ጎዳናዎችም ላይ ከተጠበቀው በላይ በርካታ ሰዎች ወጥተዋል።

    በሊባኖስ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ እየወደቀ የነበረው የአገሪቱ ምጣኔ ሃብትን ይበልጥ አባብሶታል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

  3. በምስራቅ አፍሪካ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እንቅስቃሴያቸውን የሚከታተል መሳሪያ ለመጠቀም ተስማሙ

    የምስራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎች በቀጠናው ያለውን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የከባድ ጭነት መኪና አሽከርካሪዎች የእንቅስቃሴ መከታተያን ለመጠቀም ተስማሙ።

    ውሳኔ ላይ የተደረሰው በአገራቱ ድንበር አካባቢ በተደረገው የኮቪድ-19 ምርመራ ድንበር ተሻጋሪ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች በከፍተኛ ቁጥር በኮሮናቫይረስ ተይዘው መገኘታቸውን ተከትሎ ነው።

    መሪዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ " በአገራቱ መካከል መረጃ መለዋወጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመግታት ረገድ ያለውን ቁልፍ ሚና ተረድተናል" ይላል።

    እስካሁን ድረስ የአገራቱን ድንበር የሚያቋርጡ የከባድ ጭነት መኪኖች እንቅስቃሴ ያልተከለከለ ሲሆን በአገራቱ መካከል እነዚህ መጓጓዣዎች ቁሳቁስ፣ ምግብና መድሃኒቶችን በማመላለስ ረገድ ቁልፍ ሚና አላቸው ተብሏል።

    ባለፈው ወር የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የከባድ መኪና ሹፌሮች ወደ አገራቸው እንዳይገቡ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገውት ነበር።

    " ጭነቶቹን፤፤ ቁሳቁሶቹን እንፈልጋቸዋለን። ነገር ግን በዚህ ሰዓት በሽታውን አንፈልግም. . . ስለዚህ ሹፌሮቹን አትንኳቸው፤ ሹፌሮቹም ሊነኳችሁ አይገባም" ብለው ነበር።

    የሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ እና ኡጋንዳ አገራት መሪዎች ስብሰባቸውን በቪዲዮ ያካሄዱ ሲሆን የታንዛንያ እና የብሩንዲ አቻዎቻቸው ሳይካፈሉ ቀርተዋል።

    የታንዛንያ መንግሥት ቢያስተባብልም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን በመከላከል ረገድ ጠንካራ የመከላከል ርምጃ አልወሰደም በሚል ይተቻል።

    • መጀመሪያ የተሰጠውን ምክር ቸል ያሉ አገራት አሁን እየተጎዱ ነው- የዓለም ጤና ድርጅት

      አንዳንድ የዓለም አገራት ከሌሎቹ በከፋ ሁኔታ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጎድተዋል። ይህም የሆነው በቅድሚያ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ቸል በማለታቸው መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት እየገለፀ ነው።

      አሜሪካ በድርጅቱ ላይ የምታቀርበውን ትችትና በአገሯ ቫይረሱ ያለበትን ደረጃ በመመልከት ድርጅቱ በታህሳስ ወር አጋማሽ ላይ ለሁሉም አባል አገራቱ ማስጠንቀቁን አስታውሷል፤ አክሎም በዚያው ወር መጨረሻ ላይ ዓለም አቀፍ የጤና አስቸኳይ ጊዜ ማወጁን አስታውሷል።

      በየካቲት ወርም አገራት ምርመራ እንዲያደርጉ እንዲሁም ለይቶ ማቆያ ማስገባት እንዲጀምሩ መናገሩን ገልጿል።

      የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ በአሜሪካ እና በብራዚል ስላለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወረርሽኝ ተጠይቀው በወቅቱ የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች ቸል ተብለዋል ማለታቸው ተገልጿል።

      አፈ ጉባኤዋ አክለውም አንዱ ምክንያት በአውሮፓና በአሜሪካ ያሉ አገራት አዲሱ ወረርሽኝ የሚያደርሰው ጥፋትን አያስታውሱም ብለዋል።

      በአፍሪካ አስቀድሞ መከላከል የሚኖረውን ውጤት ይረዳሉ፤ ለዚያም ይሆናል በአፍሪካ አገራት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡት ብለዋል።

    • በእንግሊዝ በኮሮናቫይረስ እየሞቱ ያሉት የትኛው የእድሜ ጎራ ያሉ ናቸው?

      በእንግሊዝ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በሆስፒታል ውስጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 23 ሺህ 709 ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 12ሺህ 451 ወይም 53 በመቶ ከ80 አመት እድሜ በላይ ናቸው።

      ከዚህም በተጨማሪ 9ሺህ 184ቱ ወይም 39 በመቶ ከ60-79 እድሜ ጎራ ላይ ያሉ መሆኑን የሃገሪቱ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት አስታውቋል።

      አጠቃላይ መረጃውም ሲታይ በኮቪድ19 የሚሞቱት 91 በመቶው ከስልሳ አመት በላይ እድሜ ላይ ያሉ ናቸው ተብሏል።

      ሌሎቹን አሃዝ የሚይዘው 8 በመቶ ከ40-59፣ 1 በመቶ ከ20- 39 እድሜና 0.05 በመቶ ደግሞ ከ0-19 እድሜ ላይ ያሉ ናቸው።

      በአገሪቷ ውስጥ በአጠቃላይ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 32 ሺህ 692 ደርሷል።

    • በናይጄሪያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጤና ተቋማቶቿን በሙሉ ለለይቶ ማቆያና ማገገሚያነት ሰጠች

      የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባዔ በአገሪቱ የሚገኙ ጤና ተቋማቶቹን በሙሉ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ለለይቶ ማቆያነትና ማከሚያነት እንዲውሉ ሰጠ።

      በናይጄሪያ የካቶሊክ የጤና ሴክረተሪያት ለቢቢሲ እንደገለፁት ቤተክርስቲያኒቱ በመላ አገሪቱ ከ440 በላይ የጤና ተቋማት ያላት ሲሆን እነዚህ ተቋማት የኮሮናቫይረስን ለመመርመር፣ ለለይቶ ማቆያና ማከሚያነት እንዲውሉ መፍቀዳቸውን አስታውቀዋል።

      ናይጄሪያ በለይቶ ማቆያ ስፍራዎች ጥበትና እጥረት እየተቸገረች ሲሆን መንግሥትም ከድርጅቶችና ከግለሰቦች ድጋፍ ጠይቆ ነበር።

      ናይጄሪያ እስከ አሁን ድረስ 4ሺህ 641 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን በምርመራ ያረጋገጠች ቢሆንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ቢመረመር ከዚህ በላይ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች እንደሚገኙ የሚናገሩ አካላት አሉ።

    • የአሜሪካ የኮሮናቫይረስ መከላከል ቁልፍ ሰው የአገራቸው ጥድፊያ አደጋ አለው ሲሉ አስጠነቀቁ

      የአሜሪካ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ቁልፍ ሰው፣ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ፣ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት በፍጥነት ወደ ስራ ማስገባት "አላስፈላጊ ስቃይና ሞት" እንደሚያስከትል ለሴናተሮች ሊያስጠነቅቁ መሆኑ ተገለፀ።

      የተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት እኚህ ግለሰብ የመንግሥት መመሪያዎችን በጣሰ መልኩ በጥድፊያ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ አገሪቱ ከወረርሽኙ የምታደርገውን የማገገም ጥረት ወደኋላ የሚቀለብስ ነው ብለዋል።

      ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ በኢሜል ለኒውዮርክ ታይምስ እንዳስታወቁት ይህንን የመከራከሪያ ሃሳባቸውን ዛሬ ለሚሰበሰበው የሴኔት ኮሚቴ ያቀርባሉ።

      " በመመሪያው ላይ የተቀመጡትን መፈተሻ ነጥቦች አሜሪካን ወደ ስራ ለማስገባት በሚል የምንዘላቸው ከሆነ በርካታ ወረርሽኞች እንዲከሰቱ በማድረግ አገሪቱን አደጋ ላይ እንጥላለን" ማለታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

      እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ በአሜሪካ ብቻ 1.3 ሚሊዮን ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛች የተረጋገጠ ሲሆን፣ ይህም ቁጥር ከሌሎች አገራት ስድስት እጥፍ የላቀ ነው ተብሏል።

      በአሜሪካ ብቻ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

    • በለንደን የባቡር ሰራተኛ አፍሪካዊት የኮሮና ህመምተኛ ከተፋባት በኋላ በቫይረሱ ተይዛ ሞተች

      በለንደን የባቡር ጣብያ በቲኬት ቆራጭነት የምትሰራ አፍሪካዊት ኮቪድ-19 አለብኝ ያለ ግለሠብ ከተፋባት በኋላ በቫይረሱ ተይዛ መሞቷ ተገለፀ።

      ግለሰቧ የኮንጎ ዜግነት ያላት ስትሆን የ47 ዓመት ጎልማሳ ነበረች ተብሏል። ቤሊ ሙጂንጋ የምትባለው ይህች ሴት ከዚህ ቀደም የመተንፈሻ አካል ችግር ነበረባት ተብሏል።

      ጥቃቱ የደረሰባት በቪክቶሪያ ባቡር ጣብያ ስትሰራ ከሴት የሥራ ባልደረባዋ ጋር መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ከጥቃቱ በኋላ ሁለቱም ሴቶች መታመማቸው ተገልጿል።

      የብሪታንያ ትራንስፖርት ፖሊስ ሠራተኞቹ ላይ የተፋውን ግለሰብ ለማግኘት ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።

      ቤሊ ሙጂንጋ ሕመሟ ፀንቶ ወደ ሆስፒታል በገባች በሶስተኛው ቀን ሕይወቷ ማለፉ ተገልጿል።

    • የፕሬዚዳንት ፑቲን ቃለአቀባይ በኮሮናቫይረስ ተያዙ

      የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የአገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።

      ዲሚትሪ ፔስኮቭ ወደ ሞስኮ ሆስፒታልም መወሰዳቸውንም ቃለ አቀባዩን ዋቢ አድርገው ሚዲያዎቹ ዘግበዋል።

      "አዎ ታምሜያለሁ! ህክምናም እየተደረገልኝ ነው" ማለታቸውን የሩሲያው ኢንተርፋክስ ኒውስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

      የ52 አመቱ ቃል አቀባይ ህመማቸው የጠና ይሁን አይሁን ከመናገር ተቆጥበዋል።

      ከዚህ በተጨማሪ ቃል አቀባዩ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ለመጨረሻ ጊዜ መቼ እንደተገናኙም የተገለፀ ነገር የለም።

      ቃል አቀባዩ ከዚህ ቀደም በሞስኮ ሆስፒታል ተገኝተው ህሙማንን ከጎበኙና ዋናው ዶክተር ጋር መገናኘታውን ተከትሎ በተደረገላቸው ምርመራ ነው በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀው።

      በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረባት ሩሲያ አሜሪካን ተከትላ በአለም ሁለተኛዋ ሆናለች።

      በዛሬው ዕለትም በባለፉት ሃያ አራት ሰአታት ውስጥ 10 ሺህ 899 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ፤ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 232 ሺህ ደርሷል።

      መዲናዋ ሞስኮ በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቃች ሲሆን በባለፉት ሃያ አራት ሰአታትም በቫይረሱ የተያዙ 5ሺህ ሰዎችን መዝግባለች።

    • ከጎረቤት አገራት ጋር የሚዋሰኑ ክልሎችና የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት

    • "ምዕራባውያን ለአፍሪካ ሃገር በቀል መድኃኒቶች ንቀት አለባቸው" ሲሉ የማዳጋስካሩ ፕሬዚዳንት ተቹ

    • ዉሃን ለ11 ሚሊዮን ነዋሪዎቿ የኮቪድ-19 ምርመራ ልታደርግ ነው

    • የ "መ" ህጎች ኮቪድ-19ን ለመከላከል

      ከዚህ ቀደም የኤችአይቪ ወረርሽኝ ለመከላከል በሚል ከተቀመጡ መከላከያ መንገዶች መካከል ሶስቱ የ"መ"ህጎች ይገኙበት ነበር። እነዚህ የመ ህጎች መታቀብ፣ መወሰን እንዲሁም መጠቀም ነበሩ።

      አሁን ደግሞ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል አራት የ"መ" ሕጎችን የጤና ሚኒስቴር እያስተዋወቀ ነው።

      ሚኒስቴሩ በኮሮናቫይረስ በሽታ መያዛችን ዕለት-ተዕለት በምናደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሚወሰን መሆኑን በማስታወስ አራቱን የ’’መ’’ ህጎች ተግባራዊ እናድርግ የሚል መልዕክት በማስተላለፍ ዜጎች ህጎቹን ተግባራዊ በማድረግ ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ ምክር በማስተላለፍ ላይ ነው።

      እነዚህ የ"መ" ህጎች መራራቅ፣ መቆየት፣ መታጠብ እና መሸፈን መሆናቸውም ተገልጿል።

    • የለንደን የህዝብ ትራንስፖርት በወረርሽኙ ምክንያት 4.9 ቢሊዮን ዶላር ይከስራል ተባለ

      በኮሮናቫይረስ ሟቾች ቁጥር በአውሮፓ ቀዳሚ በሆነችው ዩናይትድ ኪንግደም እየደረሰባት ያለውም ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ ነው ተብሏል።

      የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመግታት የተለያዩ ርምጃዎች መውሰዷንም ተከትሎ የህዝብ ትራንስፖርት ዘርፉ ክፉኛ እየተጎዱ ካሉት መካከል አንዱ እንደሆነም ተገልጿል።

      በለንደን ብቻ 4.9 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራም እንደሚደርስ የከተማዋ የህዝብ ትራንስፖርት ኔትወርክ አሳውቋል።

      አጠቃላይ በዩኬ አስገዳጅ የቤት መቀመጥ መመሪያንም ተከትሎ የህዝብ ትራንስፖርት 90 በመቶ የሚሆነውን ገቢውን አጥቷል።

      ምንም እንኳን ዩኬ የዜጎቿን እንቅስቃሴ ብትገድብም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ቁልፍ ለሚባሉ የስራ ዘርፎች አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ መመሪያ አውጥታለች። ሆኖም የህዝብ ትራንስፖርት የሚጠቀመው ቁጥር በጣም የተመናመነ ነው ተብሏል።

      ችግሩንም ለመቅረፍ የድርጅቱ የገንዘብ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባዎችን ለማድረግም በዝግጅት ላይ ነው።

    • “በአፍሪካ በኤችአይቪ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በግማሽ ሚሊዮን ሊጨምር ይችላል”

    • በኬንያ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ለሚሄዱ በሙሉ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሊደረግ ነው

      የኬንያ ጤና ባለስልጣናት ሁሉም ለህክምና ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አስታውቀዋል።

      የጤና ባለሙያዎችን በማንኛውም ሁኔታ ከቫይረሱ ለመጠበቅና በሌላ በኩል ስርጭቱን ለመቀነስ ነው ይህ ሀሳብ የቀረበው ብለዋል የጤና ጉዳዮች ዳይሬክተሩ ፓትሪክ አሞት።

      "ለህክምና ወደ ሆስፒታሎች የሚሄዱ ሰዎች በሙሉ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲደረግላቸው መመሪያዎቻችንን እየከለስናቸው እንገኛለን።‘’

      ዳይሬክተሩ አክለውም ምርመራው ከሰዎቹና ከጤና ባለሙያዎቹ በተጨማሪ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኙ የመከላከል አቅማቸው የደከመ ታካሚዎችን ከቫይረሱ ለመከላከል ይረዳል ብለዋል።

      በኬንያ 700 የተረጋጋጡ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ሲኖሩ ከነዚህ መካከል 33 ሞተዋል፤ 251 ደግሞ አገግመዋል።

    • በኢራን መስጊዶች በጊዜያዊነት ተከፍተዋል

      በኢራን ዛሬ መስጊዶች በጊዜያዊነት ተከፍተው ሌሎችም እንቅስቃሴ ላይ የተጣሉ ገደቦች እየተነሱ እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።

      መስጊዶች በተቀደሰው የረመዳን ወር ለሦስት ቀናት ክፍት ይሆናሉ። አማኞች ጤናቸውን ለመጠበቅ ጥብቅ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

      መስጊዶቹ ለምን ያህል ጊዜ ክፍት ሆነው እንደሚቆዩ አልታወቀም።

      የኢራኑ መሪ አያቶላ ካሚኒ በዚህ የጾም ወቅት ሕዝበ ሙስሊሙ መጸለይ እንዳለበት ባለሥልጣኖች ከግምት ማስገባት አለባቸው ብለዋል።

      ባለፈው ሳምንት በ160 ከተሞች፣ እምብዛም ለበሽታው ተጋላጭ ባልሆኑ አካባቢዎች መስጊዶች መከፈታቸው ይታወሳል። መስጊዶቹ ለሁለት ወራት ዝግ ነበሩ።

      በአገሪቱ 109,286 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 6,685 ሞተዋል።

    • ሰበር, ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የኮሮናቫይረስ ናሙና መርምራ 11 ሰዎች ላይ በሽታው ተገኘ

      ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ ከጀመረችበት ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ናሙና መርምራ 11 ሰዎች ላይ ቫይረሱን አገኘች።

      ባለፉት 24 ሰዓታት በ2424 ናሙናዎች ላይ በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አስራ አንድ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጠ።

      የጤና ጥበቃ ሚንስትር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሰጡት የጋራ መግለጫ፤ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 261 መድረሱ ተገልጿል።

      ቫይረሱ የተገኘባቸው ሁሉም ወንድ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ ስምንቱ በአፋር ለይቶ ማቆያ እንደነበሩ ተገልጿል። የተቀሩት ከትግራይ፣ ከሶማሌ እና ከአማራ ክልል ለይቶ ማቆያዎች እንደተገኙም ተጠቁሟል።

      ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ባጠቃላይ የጉዞ ታሪክ አላቸው። እስካሁን በኢትዮጵያ 39048 የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጓል። 148 ህሙማን በለይቶ ሕክምና የሚገኙ ሲሆን፤ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች 106 ደርሰዋል። አምስት ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።

    • ማላዊያውያን ያለመሰባሰብ ሕግን ችላ እያሉት ይመስላል

      የማላዊ ዋነኛ ፖለቲካዊ ጥምረት አባላት የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት የተቀመጠውን ያለመሰባሰብ ህግ ችላ በማለት በመጪው ሐምሌ ለሚካሄደው ምርጭ ቅስቀሳ ማድረግ ጀምረዋል።

      ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አገሪቱ የቫይረሱ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ በአንድ ቀን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መያዛቸውን ካስታወቀች በኋላ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው መታየታቸው ግርምትን ፈጥሯል።

      በተጨማሪም የምረጡኝ ቅስቀሳውን ለመታደም የሄዱት አብዛኛዎቹ ሰዎች አፍና አፍንጫ መሸፈኛ 'ማስክ' አላደረጉም ነበር ተብሏል።

      አገሪቱ ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ምርጭ አካሂዳ ፕሬዝደንት ፒተር ሙታሪካ በድጋሚ ተመርጠው የነበረ ቢሆንም የምርጫው ውጤት በአገሪቱ ሕገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት ውድቅ ሆኗል።

      የማላዊ ምርጫ ኮሚሽን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ለማድረግ ህዝብ መሰብሰብ እንዲያቆሙና ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ አሳስቦ ነበር።

      የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴርም ፓርቲዎቹ የጠሩትን ስብሰባ የሚያስቆጭና የቫይረሱን ስርጭት የሚያባብስ ነው ብሎታል።

    • ከኮሮናቫይረስ የትኞቹ ድርጅቶች አተረፉ? እነማንስ ከሰሩ?