አንዳንድ አገሮች ታዳጊዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው
እንዲመለሱ ውሳኔ አስተላልፈዋል። ከነዚህ አንዷ ኢንግላንድ ናት። ሆኖም ግን በሚቀጥለው ወር ትምህርት እንዲጀመር መወሰኑን አገር
አቀፉ የትምህርት ተቋም “ግዴለሽነት ነው” ብሏል።
የዩኬ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን እንደሚሉት፤
የኮሮናቫይረስ ሥርጭት ከቀነሰ፤ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ደረጃ በደረጃ ትምህርት ይጀመራል።
ውሳኔው በሳይንሳዊ ማስረጃዎች የተደገፈ መሆን
አለበት። በእርግጥ ስለቫይረሱ ብዙ ያልታወቁ ነገሮች መኖራቸው እሙን ነው።
ልጆች እምብዛም በቫይረሱ ሲያዙ አይስተዋልም።
ይህም ተስፋ ሰጪ ነው። ሆኖም ምን ያህል በሽታውን እንደሚሸከሙ እና ወደሌሎች እንደሚያስተላልፉ እስካሁን አልታወቀም።
ታዳጊዎች እንደ ጉንፋን ያሉ በሽታዎችን በስፋት
ያስተላልፋሉ። ኮሮናቫይረስ ልክ እንደ ጉንፋን የሚተላለፈው በሳል፣ በማስነጠስ፣ በቫይረሱ የተያዘ ሰዎች የነኩትን እቃ በመንካትም
ነው።
ስለዚህም ከሰዎች ሁለት ሜትር መራቅ፣ እጅ ሳይታጠቡ
ፊት አለመንካት ይመከራል።
እነዚህን የመከላከያ መንገዶች እንኳን ታዳጊዎች
አዋቂዎችም ለመከተል ይቸገራሉ።
የአምስትና የስድስት ዓመት ልጆች በአንድ ክፍል
ተሰብስው ይህን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስቻል ደግሞ ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።
ለመከታተል አስቸጋሪ የሆኑ ልጆችን መቆጣጠር ከተቻለ
በኋላ በእድሜ ከፍ ያሉ ታዳጊዎች መስከረም ላይ ትምህርት እንዲጀምሩ ለማደረግ ታስቦም ይሆናል።
አሁን ላይ ባለው ሁኔታ ትምህርት ቤቶችን ዘግቶ መቆየት እንዲሁም መክፈትም የየራሳቸው
የሆነ አደጋ አላቸው።