በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ በተገኘ በሁለተኛው ወሩ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምርመራ ተደረገ

በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ እንዳለበት የተረጋገጠ ሰው የተገኘው መጋቢት 04/2012 ዓ.ም ነበር። የመጀመሪያው ቫይረሱ የተገኘበት ግለሰብ ጃፓናዊ ዜግነት የነበረው ሲሆን በሥራ አጋጣሚ ከበርካታ ኢትዮጵያዊን ጋር ተገናኝቶ ነበር። ባለፉት ሁለት ወራት የበሽታው መስፋፋት ቀስበቀስ እጨመረ አሁን ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ደርሷል። ነገር ግን ከሚያዝያ ወር መጨረሻ ጀምሮ በየዕለቱ እየተመዘገበ ያለው ቁጥር አሳሳቢ ሆኗል። በሽታው የሚገኝባቸው ቦታም እየሰፋ ነው። የጤና ባለሙያዎች በሽታው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚናገሩት የእጅ ንጽህናን በአግባቡና በተደጋጋሚ መጠበቅና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ከመከላከያ መንገዶቹ ዋነኞቹ ሲሆኑ፤ በተጨማሪ ደግሞ በርካታ ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ቦታ ላይ የምንገኝ ከሆነ የአፍና የአፍናጫ መሸፈኛ መጠቀምም አሁን የግድ እየሆነ ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የአውሮፓ አገራት ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ እያላሉ ነው

    በመላው አውሮፓ አገራት ቫይረሱ ዳግም ተመልሶ እንደማይከሰት ተስፋ በማድረግ ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ እያላሉ ነው።

    ፈረንሳይ ከዛሬ ጀምሮ ትምህርት ቤቶች አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች በመቀበል ትምህርት ይጀምራሉ። የልብስና የመጽሀፍ መሸጫ፣ የቤተ ውበቶች የሚከፈቱ ሲሆን ምግብ ቤቶች እና ሲኒማ ቤቶች ዝግ ሆነው ይቆያሉ ተብሏል።

    ቤልጂየም አብዛኛዎቹ ንግድ ቤቶች ዛሬ የሚከፈቱ ሲሆን ምግብ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች እና ካፌዎች ዝግ እንደሆኑ ይቆያሉ ተብሏል። የሚከፈቱት ንግድ ቤቶችም ቢሆኑ ማህበራዊ ርቀት መጠበቁን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።

    ኔዘርላንድስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በከፊል ክፍት ይሆናሉ የተባለ ሲሆን በተጨማሪም ቤተ መጽሀፍቶች፣ ፊዚዮቴራፒ መስጫዎች፣ የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤቶች እና ቤተ ውበቶችም አገልግሎት መሥጠት ይጀምራሉ ተብሏል።

    ስዊዘርላንድ የመጀመሪያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቢከፈቱም አንድ ክፍል የሚይዘው የተማሪ ቁጥር ግን ይቀነሳል ተብሏል። ምግብ ቤቶች፣ የመጽሀፍት መደብሮች፣ የአካላዊ ርቀትን ጠብቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ተፈቅዷል።

    ስፔን አንዳንድ ከተሞች እስከ አስር ሰው ድረስ መሰብሰብ ተፈቅዷል። ከቤት ውጪ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ምግብ ቤቶችም ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ ተብሏል።

    ዩናይትድ ኪንግደም በእንግሊዝ በዚህ ሳምንት የእንቅስቃሴ ገደቡ የሚላላ ሲሆን በሌሎች የስፍራዎች ግን ባለበት ይቆያል ተብሏል።

    ዴንማርክ፣ ሱቆች እንዲሁም በፖላንድ ምግብ ቤቶች፣ ይከፈታሉ።

    ጀርመን፣ ኦስትሪያ እና ጣሊያን ደግሞ ቀደም ብለው የእንቅስቃሴ ገደቡን ማላላት ጀምረዋል።

  2. በአውሮፓ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1.5 ሚሊዮን አለፈ

    በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ 1.3 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘውባት በወረርሽኙ ክፉኛ ከተመቱ አገራት ቀዳሚዋ ሆናለች። ይህንን ቁጥር ግን በአህጉር ደረጃ አውሮፓ በልጣለች።

    ከአውሮፓ አገራት ዩናይትድ ኪንግደም በቫይረሱ ምክንያት በሞቱ ሰዎች ከፍተኛውን ስታስመዘግብ ስፔን ደግሞ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር የአውሮፓን አገራት ትመራለች።

    ስፔን (224,350 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 26,621 ደግሞ ሞተዋል)

    ዩናይትድ ኪንግደም (220,449 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 31,930 ደግሞ ሞተዋል)

    ጣልያን (219,070 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 30,560 ደግሞ ሞተዋል)

    ሩሲያ (209,688 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣1,915 ደግሞ ሞተዋል)

    ፈረንሳይ (177,094 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 26,383 ደግሞ ሞተዋል)

    ጀርመን (171,879 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 7,569 ደግሞ ሞተዋል)

    ቤልጂየም (53,081 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 8,656 ደግሞ ሞተዋል)

    ኔዘርላንድስ (42,826 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 5,459 ደግሞ ሞተዋል)

  3. በዛምቢያ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ከመንግሥት ምስጋና ቀረበላቸው

    በዛምቢያ የሚገኙ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን መለየት ላይ በመሳተፋቸው መንግሥት ምስጋና አቀረበላቸው።

    እነዚህ ሴቶች በድንበር ከተማዋ ናኮንዴ የቫይረሱ ስርጭት መስፋፋቱን ተከትሎ ኮሮናቫይረስ የተያዙ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶችንና ሹፌሮችን መለየት ችለዋል ተብሏል።

    በዚህች የድንበር ከተማ ከ76 እስከ 85 የሚሆኑ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ በወሲብ ንግድ የተሰማሩና ሹፌሮች ናቸው።

    የድንበር ከተማዋ ናኮንዴ ወደ ታንዛኒያ የሚሄዱና ከታንዛንያ የሚመጡ ከባድ የጭነት መኪኖች የሚርመሰመሱባት ከተማ ናት።

    የዛምቢያ የጤና ሚንስትር ቺሉፊያ " ሴቶቹ ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች በመለየት ረገድ በጣም ረድተውናል። ልናገላቸውና መድልኦ ልናደርስባቸው አይገባም" ያሉ ሲሆን አክለውም በቫይረሱ የተያዙ ሴቶች የደንበኞቻቸውን ስልክ በመስጠትና ከማን ጋር የቅርብ ንክኪ እንደነበራቸው በመለየት መተባበራቸውን ገልፀዋል።

    ዛምቢያ እስካሁን ድረስ 267 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የገለጸች ሲሆን ሰባት ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

  4. ሳኡዲ አረቢያ ተጨማሪ እሴት ታክስ በሶስት እጥፍ ከፍ አደረገች

    ሳኡዲ አረቢያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የደቀቀውን ኢኮኖሚዋን ለመደገፍ የተጨማሪ እሴት ታክስ ላይ ሶስት አጥፍ ጭማሪ ልታደርግ መሆኑን ገልጻለች።

    መቀመጫውን ሪያድ ያደረገው መንግሥት በተጨማሪም ለዜጎቹ ይሰጠው የነበረውን የኑሮ መደጎሚያ ገንዘብ እንደሚያቋርጥ አስታውቋል።

    የኮሮናቫይረስ ባስከተለው ዓለም አቀፍ ቀውስ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ በነዳጅ ሀብት የበለጸገችው ሳኡዲ አረቢያ የገቢ መጠኗ በእጅጉ ቀንሶባታል።

    ሳኡዲ አረቢያ ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር ኦኮኖሚው በነዳጅ ላይ ብቻ እንዳይንጠለጠል በሚል ተጨማሪ እሴት ታክስን ያስተዋወቀችው።

    የሳኡዲ አረቢያ ዜና ተቋም እንደዘገበው ተጨማሪ እሴት ታክሱ ከፈረንጆቹ ሰኔ ወር ጀምሮ 5% ወደ 15% ከፍ ይላል።

  5. ቻይና በኮሮናቫይረስ ወረርሽን መስፋፋት ምክንያት ሹላን የተሰኘች ከተማዋን ዘጋች

    በቻይናዋ ጂሊን ግዛት ሹላን ከተማ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስፋፋትን ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጣለ። ከተማዋ ከፍተኛ ስጋት ያለባት በሚል መለየቷም ተገልጿል።

    ባለፉት ቀናት በግዛቲቱ 11 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ሲገለጽ፤ በቫይረሱ መጀመሪያ የተያዘችው በልብስ ንጽህና መስጫ ውስጥ የምትሰራ ሴት ነበረች ተብሏል።

    ይህች 45 ዓመት ሴት በቅድሚያ ባለቤቷን ከዚያም እህቶቿንና ሌሎች የቤተሰብ አባሎቿን በቫይረሱማስያዝዋ የተገለፀ ሲሆን ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ የላትም ተብሏል።

    በከተማዋ የሚገኙ የሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች የተዘጉ ሲሆን፤ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎትም እንዲቋረጡ ተደርገው ነዋሪዎች በቤታቸው እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል።

    ሹላን በጂላን ግዛት ውስጥ የምትገኝ ከተማ ስትሆን እስካሁን ድረስ ምንም በቫይረሱ የተያዘ ሰው ካላስመዘገበችው ሰሜን ኮሪያ ጋር አጠገብ የምትገን ከተማ ነች።

  6. በጀርመን እየጨመረ የነበረው የህሙማን ቁጥር መቀነስ አሳየ

    በጀርመን ሰሞኑን እየታየ የነበረው በበሽታው አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ357 ከፍ ብሎ በአጠቃላይ በአገሪቱ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሰዎች 169,575 እንዳደረሰው ዛሬ መንግሥት ያወጣው መረጃ አመለከተ።

    ከዚህ በተጨማሪም በወረርሽኙ ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች አሃዝ በ22 ጨምሮ 7,417 ደርሷል።

    አሁን የወጣው የአሃዝ መረጃ እንደሚጠቁመው በቅርቡ እየታየ የነበረው የመጨመር አዝማሚያ እየተገታ መሆኑን አመልካች ነው ተብሏል።

    ጀርመን የወረርሽኙን መስፋፋት ለመቆጣጠር ተቃርባለች በተባለበት ጊዜ የታየው የቁጥር መጨመር አገሪቱ በእንቅስቃሴ ገደቦች ላይ የማላላት እርምጃ መውሰድ መጀመሯን ተከትሎ መሆኑ በሽታው ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሮ ነበር።

    አንዳንዶች ግን ይህ የአሃዝ መቀነስ የተፈጠረው በሽታውን የሚመለከቱ ሪፖርቶች በመዘግየታቸው ሊሆን ስለሚችል የወረርሽኙ መስፋፋት ቀንሷል ከመባሉ በፊት ተጨማሪ ጥቂት ቀናትን መታገስ ሳያስፈልግ አይቀርም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

  7. የ‘ኅዳር በሽታ’ እና ኮሮናቫይረስን ምን ያመሳስላቸዋል?

  8. በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 80 ሺህ ተጠጋ

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ከሆነ በአሜሪካ ባለፉት 24 ሰዓታት በኮቪድ-19 ምክንያት 776 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ በአጠቃላይ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 79,526 ደርሷል።

    ከዚህ ቀደም በቫይረሱ ምክንያት በየዕለቱ ሲሞቱ የነበሩ ሰዎች ቁጥር ትንሹ 1000 ትልቁ ደግሞ 2500 የነበረ ሲሆን ይህ ዝቅተኛው ነው ተብሏል።

    በዓለማችን ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በከፍተኛ ቁጥር የሚገኙባት አሜሪካ ናት። ይህ ሊሆን የቻለው ከአገሪቱ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥርና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰዎች መመርመርከመቻል ጋር ተያይዞ ነው ተብሏል።

    በአሜሪካ አሁን 1,329,260 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ ይህም ቁጥር በዓለማችን በቫይረሱ ከተጠቁ አገራት ሁለተኛ ከሆነችው ስፔን በአምስት እጥፍ ይበልጣል።

  9. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች!

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ላይ የሚያተኩረው የቀጥታ ዘገባችንን ለማንበብ እንኳን ወደ ገፃችን በሰላም መጡ! ከዚህ ሰዓት ጀምሮ በዓለማችን ከሚከሰቱ ዜናዎች መካከል አበይቶቹን እየመራረጥን እናደርሳችኋለን።

    እናንተም ራሳችሁንና ቤተሰባችሁን ከቫይረሱ ስርጭት እየጠበቃችሁ ከእኛ ጋር እንድትሆኑ እንጋብዛለን ።

    መልካም ቀን!