ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ በተገኘ በሁለተኛው ወሩ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምርመራ ተደረገ
በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ እንዳለበት የተረጋገጠ ሰው የተገኘው መጋቢት 04/2012 ዓ.ም ነበር። የመጀመሪያው ቫይረሱ የተገኘበት ግለሰብ ጃፓናዊ ዜግነት የነበረው ሲሆን በሥራ አጋጣሚ ከበርካታ ኢትዮጵያዊን ጋር ተገናኝቶ ነበር። ባለፉት ሁለት ወራት የበሽታው መስፋፋት ቀስበቀስ እጨመረ አሁን ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ደርሷል። ነገር ግን ከሚያዝያ ወር መጨረሻ ጀምሮ በየዕለቱ እየተመዘገበ ያለው ቁጥር አሳሳቢ ሆኗል። በሽታው የሚገኝባቸው ቦታም እየሰፋ ነው። የጤና ባለሙያዎች በሽታው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚናገሩት የእጅ ንጽህናን በአግባቡና በተደጋጋሚ መጠበቅና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ከመከላከያ መንገዶቹ ዋነኞቹ ሲሆኑ፤ በተጨማሪ ደግሞ በርካታ ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ቦታ ላይ የምንገኝ ከሆነ የአፍና የአፍናጫ መሸፈኛ መጠቀምም አሁን የግድ እየሆነ ነው።
የቀጥታ ሽፋን
ታንዛንያ አራት የሕዝብ እንደራሴዎቿን አባረረች
የታንዛንያ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ቻዴማ አራት የሕዝብ እንደራሴዎችን አባረረ። እንደራሴዎቹ ፓርቲው ስብሰባ ላይ የጣለውን እገዳ በመጻረራቸው ነው የታገዱት።
ከ383 የምክር ቤት መቀመጫ 62 ያለው ፓርቲው የሕዝብ እንደራሴዎች ቢያንስ ለ14 ቀናት ራሳቸውን እንዲያገሉና ከፓርላማው ቅጥር ግቢ እንዲርቁም አዟቸው ነበር።
ፓርቲው ውሳኔውን ያስተላለፈው ሦስት እንደራሴዎች ከሞቱ በኋላ ነው። በእርግጥ እንደራሴዎቹ በምን ምክንያት እንደሞቱ አልታወቀም።
ባለው ሳምንት የዳሬ ሰላም ፖሊስ፤ ፓርላማ አንሳተፍም ያሉ ተቃዋሚ እንደራሴዎችን ለጥያቄ እፈልጋችኋለሁ ማለቱም ይታወሳል።
በታንዛንያ ለቀብር እና ለሠርግ መሰብሰብ ቢታገድም፤ ከዛ ያለፈ የእንቅስቃሴ ገደብ ግን አልታወጀም። እስካሁን 480 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 16 ደግሞ ሞተዋል።
አምሰት የኮሮናቫይረስ ጽኑ ህሙማን በእሳት አደጋ ሞቱ
በሩሲያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ላይ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የነበሩ አምስት የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች ህይወት ጠፋ።
የሩሲያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው እሳቱ የተነሳው በቬንትሌተር ውስጥ ባለ የኤሌክትሪክ መስመር ሳቢያ ነው።
የአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋዎች ሚኒስትር እንዳሉት ለአምስቱ ህሙማን ሞት ምክንያት የሆነው እሳት በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን 150 ሰዎች ከሆስፒታሉ እንዲወጡ ተደርጓል።
ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ምን ያህል ሰዎች በእሳት አደጋው ጉዳት እንደደረሰባቸው እስካሁን የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።
ሩሲያ በአሁኑ ጊዜ በኮሮናቫይረስ በተያዙ ሰዎች ብዛት ከዓለም በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ነገር ግን ሰኞ ዕለት አገሪቱ 11,656 በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ማግኘቷን ብታስታውቅም ፕሬዝዳንት ፑቲን ተጥሎ የነበረውን የእንቅስቃሴ እገዳ ለማላላት ወስነዋል።
በዚህም መሰረት በመላው ሩሲያ የሚገኙ የግንባታ፣ የግብርናና የፋብሪካ ሠራተኞች ወደየ ሥራ መስካቸው በመመለስ ላይ ይገኛሉ።
በአሁኑ ጊዜ በዋና ከተማዋ ሞስኮ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች የሕዝብ ትራንስፖርት ሲጠቀሙና ወደ መደብሮች ሲሄዱ የፊት ጭምብልና ጓንት እንዲያደርጉ ይገደዳሉ።
በጀርመን 1,000 የሚደርሱ አዲስ የኮቪድ-19 ታማሚዎች ተገኙ
በጀርመን 933 አዲስ የኮቪድ-19 ታማሚዎች የተገኙ ሲሆን፤ አጠቃላይ ቁጥሩ 170,508 ደርሷል።
ከዚህ ቀደም በአንድ ቀን በበሽታው የተያዙ ሰዎች 357 ነበሩ። አገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደብ ማንሳት ከጀመረች ወዲህ ለሁለተኛ ዙር በቫይረሱ እንዳትጠቃ ሲባል፤ በየቀኑ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥርን በአንክሮ እየተከታተለች ነው።
ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሪፖርት ባለመደረጉ ምክንያት፤ ትላንት ድምር አሃዙ ሲገለጽ ከፍ ብሎ ሊሆን ይችላል የሚል መላ ምትም አለ።
በአንድ ቀን የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 116 ከፍ ያለ ሲሆን፤ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 7,533 ደርሷል።
ምስጢራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እየረዳ ነው
ሴኔጋል ቤተ እምነቶችን መክፈት ጀመረች
ሴኔጋል ከዛሬ ጀምሮ ጥላው የነበረውን የመሰብሰብና የእንቅስቃሴ ገደብ ማላለት ጀመራለች። በዚሁም መስጂዶችና አብያተ ክርስቲያናት ክፍት ይሆናሉ ማለት ነው።
በአገሪቱ የሚገኙ መስጂዶች በተቀደሰው የረመዳን ወቅት ለጸሎት ክፍት እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን አብያተ ክርስቲያናትም ቢሆኑ አማኞችን መቀበል ይችላሉ።
በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት በሳምንት ለጥቂት ቀናት ብቻ ይከፈቱ የነበሩ የገበያ ቦታዎችና ሱቆች በሳምንት አንድ ጊዜ ለሚደረገው ጽዳት ካልሆነ በስተቀር ሳምንቱን ሙሉ ክፍት ይሆናሉ።
ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል በአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ወጥተው ባስተላለፉት መልእክት ‘’ሴኔጋላውያን በግልና እንደ ማኅበረሰብ ጥንቃቄ በማድረግ ኑሯቸውን መግፋት መጀመር አለባቸው’’ ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት ሰኞ ዕለት ብቻ 177 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከተገኙ በኋላ መሆኑ ደግሞ ውሳኔው ላይ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል።
በሴኔጋል እስካሁን 1886 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 19 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።
የኮሮናቫይረስ ክራሞት በኢትዮጵያ፡ ከመጋቢት እስከ ግንቦት
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ምርጫው ሊራዘም እንደሚችል ጠቆሙ
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ባለበት በዚህ ወጥቅ አጠቃላይ ምርጫ ማከሄድ ‘እብደት’ ነው ብለዋል።
ኤንቢኤስ ከተባለው ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወረርሽኙ እስከ መጪው ሰኔ በቁጥጥር ስር የማይውል ከሆነ በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ምርጫ እንደገና መታየት አለበት ብለዋል።
በኡጋንዳ እስካሁን 122 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። የሞተ ሰው ግን የለም።
በመላው አገሪቱ ከፖለቲካ ጋር የተያያዙም ሆነ ማንኛውም ህዝባዊ ስብሰባ ማድረግ የተከለከለ ቢሆንም እየተወሰደ ያለው እርምጃ ግን ቫይረሱን ለመቆጣጠር በቂ አይደለም እየተባለ ይተቻል።
በአጠቃላይ ምርጫው ፕሬዝደንቱን ለመፎካከር 24 እጩዎች ተመዝግበዋል። የ 38 ዓመቱ ሙዘቀኛና የፓርላማ አባል ቦቢ ዋይን ደግሞ ዋነኛ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ኢንዶኔዥያ ከ45 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ፈቀደች
ኢንዶኔዥያ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ስትል ከ45 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ፈቅዳለች።
“ከ45 ዓመት በታች የሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ጤናማ ናቸው፣ በፍጥነት መንቀሳቀስም ይችላሉ” ተብሏል።
ሆኖም ግን ወጣቶች በሽታውን በእድሜ ለገፉ ቤተሰቦቻቸው እንዳያስተላልፉ ምን አይነት እርምጃ እንደሚወሰድ ግልጽ አይደለም። እስያ ውስጥ ደግሞ በርካታ የቤተሰብ አባላት በጋራ ይኖራሉ።
ጃካርታ ፖስት እንደዘገበው፤ ቢያንስ 2.8 ሚሊዮን ሰዎች ሥራ አጥ ሆነዋል።
እስካሁን 14,625 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ፤ 991 ደግሞ ሞተዋል።
በኒው ዚላንድ በበሽታው ከተያዙ 90 በመቶው አገግመዋል
ኒው ዚላንድ አንድም አዲስ በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው አላገችም። በበሽታው ከተያዙ 1,497 ሰዎች ዘጠና በመቶው ደግሞ አገግመዋል።
በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥር እስካሁን ከ21 አልዘለለም። ሁለት ሰዎች አሁንም ሆስፒታል ቢሆኑም፤ የፅኑ ህሙማን ማቆያ ክፍል ግን አልገቡም።
ጠቅላይ ሚንስትር ጃሲንዳ አርደን እንቅስቃሴ ላይ ተጥሎ የነበረውን ገደብ ማንሳቱን ቀጥለውበታል። መደብሮች፣ ሲኒማ ቤቶች የልጆች መጫወቻዎችና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥሪያዎችም ተከፍተዋል።
አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አሁንም ግዴታ ሲሆን፤ በቀጣይ ትምህርት ቤቶች ከዛም መጠጥ ቤቶች ይከፈታሉ።
በደቡብ ኮርያ አዳዲስ የኮሮናቫይረስ ህሙማን እየተመዘዘገቡ ነው
በደቡብ ኮርያ መዲና የምሽት ክለቦች በሚበዙበት ሰፈር ወደ 94 የሚጠጉ አዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው ተዘገበ።
መንግሥት አካላዊ መራራቅ እንዲጠበቅ አውጥቶ የነበረውን ደንብ ካላላ ጀምሮ ነው በሽታው እያገረሸ የመጣው። ሕይወትን ወደ ቀድሞ ገፅታው መመለስ ከባድ እንደሆነ ማሳያ ነውም ተብሏል።
ባለሥልጣናት ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ወስነው የነበረ ቢሆንም እንዲዘገይ ተደርጓል።
ደቡብ ኮርያ በብሔራዊ ደረጃ እንቅስቃሴ ባትገታም፤ በርካቶችን በመመርመር እንዲሁም በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን በመከታተል የወረርሽኙን ሥርጭት መቀነስ ችላ ነበር።
በሽታው ከተገኘባቸው የምሽት ክለቦች ጥቂቱ ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች የሚያዘወትሯቸው ናቸው። ከማኅበረሰቡ በሚደርስባቸው መገለል ምክንያት ወደ ክለቦቹ ሲገቡ ሐሰተኛ ስም ተጠቅመው ነው።
በመሆኑም አሁን እንደ አዲስ በሽታው ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ለመከታተል ከባድ እንደሚሆን ተገልጿል።
በሕንድ ባቡር ሥራ መጀመሩን ተከትሎ ትኬቶች ተሽጠው አለቁ
ሕንድ ውስጥ ወደሚገኙ ከተሞች ጉዞ የሚያደርጉ ባቡሮች ስራ መጀመራቸውን ተከትሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቲኬቶች ተሽጠው ማለቃቸው ተዘግቧል።
ለሁለት ወራት ተዘግቶ የነበረው የባቡር አገልግሎት መከፈት ብዙዎችን ያስደሰተ ሲሆን በሶስት ሰአት ውስጥ 30 ሺ ቲኬቶች ተሽጠው አልቀዋል።
ከዛሬ ጀምሮም ባቡሮች ከዋና ከተማዋ ኒው ደልሂ ወደ 15 የተለያዩ ከተሞች ይጓዛሉ። ተጓዦችም ባቡር ውስጥ በሚገቡበት ወቅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ ግዴታቸው ነው።
በተጨማሪም አካላዊ ርቀት መጠበቅ ያለባቸው ሲሆን የኮሮናቫይረስ ማንኛውም አይነት ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች ደግሞ ከነጭራሹ መግባት አይችሉም ተብሏል።
የዋይት ሐውስ ሠራተኞች ጭምብል እንዲያደርጉ ታዘዙ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መቀመጫ በሆነው ነጩ ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች በሙሉ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ የታዘዙ።
ይህ ትዕዛዝ የወጣው ሁለት የፕሬዝዳንቱ ረዳቶች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን ተከትከሎ ሲሆን ከዚህ በኋላም የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ወደሚገኝበት የዋይት ሐውስ ምዕራባዊ ክፍል የሚገቡ ሠራተኞች በሙሉ ጭምብል ያደርጋሉ ተብሏል።
የቤተ መንግሥቱ ሠራተኞች አስተዳደር ባወጣው ትዕዛዝ ላይ እንዳለው ሁሉም አባል ከባልደረቦቻቸው ጋር በማይገናኙበት ሁኔታ በቢሯቸው ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በየትኛው ቦታና ሰዓት ላይ ጭምብል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ይህ ትዕዛዝ የወጣው የምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ረዳትና የፕሬዝዳንት ትራምፕ የግል አልባሽ በወረርሽኙ በመታመማቸው ነው።
በጽህፈት ቤታቸው ያሉ ሰራተኞች ጭምብል እንዲደረግ ያዘዙት እራሳቸው መሆናቸውን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የዕለተ ማክሰኞ የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ
እንዴት አደራችሁ ውድ የቢቢሲ አማርኛ ተከታታዮች።
የዕለተ ማክሰኞ የግንቦት 4/2012 ዓ.ም ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ የአገር ውስጥና የውጭ ዜናናና መረጃዎችን የምናቀርብበት የቀጥታ ዘገባችን ተጀመረ።
አብራችሁን ቆዩ።
ነፍሰ ጡሮች ለከፋ የኮሮናቫይረስ በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ጠባብ ነው
427 ነፍሰ ጡሮችን አሳትፎ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የተሠራ አንድ ጥናት እርጉዝ ሴቶች ለከፋ የኮሮናቫይረስ በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ጠባብ መሆኑን ጠቁሟል።
ቢሆንም ከአናሳ ጎሳዎች የሆኑ ሴቶች፣ ዕድሜያቸው የገፋ ነፍሰ ጡሮችና ከመጠን ያለፈ ክብደት ያላቸው በሳንባ በሽታ ምክንያት ወደ ሆስፒታል ሊያቀኑ ይችላሉ ይላል ጥናቱ።
ከጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል አብዛኛዎቹ የስድስት ወራት እርጉዞች ናቸው። ስድስት ወራትና ከዚያ በላይ የሆናቸው እርጉዝ ሴቶች ማሕበራዊ ርቀት እንዲጠብቁ እጅጉን ይመከራሉ።
አብዛኛዎቹ በሰላም ሲገላገሉ የተቀሩት ደግሞ ሆስፒታል ውስጥ ናቸው። ከ10 አንድ ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል ተወስደዋል። አምስት ሴቶች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።
የኮሮናቫይረስ ካለባቸው እናቶች የተወለዱ ሕፃናት አብዛኛዎቹ ጤናማ ቢሆኑም ከአምስት አንዱ ያለጊዜያቸው በመወለዳቸው ምክንያት የሕክምና እርዳታ እያገኙ ነው።
ኮሮናቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ዕድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው። በቁጥር ሲሰላ ከሃያ ሕፃናት አንድ ሆኖ ተገኝቷል።
“የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳት ያለበት በዝግታና በጥንቃቄ ነው” ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም
ከኮሮናቫይረስ ጋር የሚደረገውን ትግል ለማሸነፍ የእንቅስቃሴ ገደቦች በዝግታና በጥንቃቄ መነሳት እንዳለባቸው የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ተናገሩ።
በርካታ አገሮች የእንቅስቃሴ ገደብ እያላሉ ይገኛሉ። ሆኖም ደቡብ ኮርያ እና ጀርመን ገደቡን ካላሉ በኋላ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዳግመኛ ጨምሯል።
ዶ/ር ቴድሮስ፤ የእንቅስቃሴ ገደብን ማንሳት “ውስብስብና ከባድ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ደቡብ ኮርያ፣ ጀርመን እና ቻይና እንደ አዲስ ያገረሸውን የበሽታውን ሥርጭት መቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት እንዳላቸው ኃላፊው ተናግረዋል።
አገራት ገደብ ከማላላታቸው በፊት በሽታው በቁጥጥር ሥር መዋሉን፣ የጤና ሥርዓታቸው ጠንካራ መሆኑን እንዲሁም ህሙማንን ለይቶ የማከም አቅም እንዳላቸው እርግጠኛ መሆን አለባቸው ሲሉም መክረዋል።
ትምህርት ቤቶች አካላዊ ርቀትን እንዲያስጠብቁ፣ ቀጣሪዎች ሠራተኞቻቸው ለበሽታው እንዳይጋለጡ እርምጃ እንዲወስዱም አሳስበዋል።
ዓለም ‘ከኅዳር በሽታ’ በኋላ ምን መሰለች? ከወረርሽኙስ ምን እንማራለን?
‘የኅዳር በሽታ’ ከዚያ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ነበር ጉዳት ያስከተለው። በብዛት የሞቱት ከ20 ዓመት እስከ 40 ያሉ ናቸው።
ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የተመለሱ ወታደሮች ይኖሩበት በነበረ ማቆያ ውስጥ እንደተቀሰቀሰ የሚታመነው ይህ ወረርሽኝ፤ በዋነኛነት ያጠቃው ወንዶችን ነበር።
ድሃ አገሮችም በግንባር ቀደምነት ተጎድተዋል። ዘንድሮ በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የተሠራ ጥናት፤ በስፓኒሽ ፍሉ 550 ሺህ አሜሪካውያን (ከአጠቃላይ ሕዝቡ 0.5 በመቶው) እንዲሁም 17 ሚሊዮን የህንድ ዜጎች (ከአጠቃላይ ሕዝቡ 5.2 በመቶው) መሞታቸውን ያሳያል።
የጥናቱ መሪ ሮበርት ባሮ፤ በሽታው ምጣኔ ሀብትን አሽመድምዶት ነበር ይላሉ። አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ስድስት በመቶ ያሽቆለቀለበት ዘመን መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
“የመጀመሪያው የዓለም ጦርነትና ወረርሽኙ ተደማምረው የዓለምን ምጣኔ ሀብት እንዳልነበረ አድርገውታል” ሲሉም ያስረዳሉ።
የቤተሰቦቻቸውን ንግድ የሚረከቡ፣ የሚያርሱ፣ ባቡር የሚነዱ፣ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ወጣት ወንዶች በብዙ አገራት አልቀዋል። “በወቅቱ የወንዶች ቁጥር መቀነሱ ሴቶች የትዳር አጋር እንዳያገኙ አድርጓል” ይላሉ ሮበርት። ተጨማሪ ከዚህ ያንብቡ የ‘ኅዳር በሽታ’ እና ኮሮናቫይረስን ምን ያመሳስላቸዋል?
በዩክሬን የእለት ከእለት እንቅስቃሴ እያንሰራራ ነው
የዩክሬን መዲና ኪየቭ ወደ ቀደመ ገፅታዋ እየተመለሰች ነው። ጎዳናዎችና መናፈሻዎች በሰዎች እየተሞሉም ይገኛሉ።
እንቅስቃሴ ላይ የተጣለው ገደብ መላላቱን ተከትሎ፤ መደብሮች፣ የውበት ሳሎኖች፣ መናፈሻዎች እየተከፈቱ ነው።
ምግብ ቤቶች ወንበሮቻቸውን አራርቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ተፈቅዷል።
ወቅቱ ሞቃት በመሆኑ ብዙዎች ወደ መናፈሻ ለመግባት ሰለፍ ይዘው ነበር የዋሉት።
ዩክሬን አምብዛም በኮቪድ-19 አልተጠቃችም። ይህ ለምን እንደሆነ ባይታወቅም፤ ባለሥልጣኖች ጥብቅ እርምጃ በመውሰዳቸው መሆኑ ይገመታል።
የአገሪቱ የጤና ሥርዓት ብዙም አስተማማኝ ስላልሆነና አብዛኛው ዜጋ በእድሜ በመግፋቱ ምክንያት፤ ዩክሬን እንቅስቃሴ የገታችው ገና ጥቂቶች በቫይረሱ ሲያዙ ነበር።
በሳምንታት ውስጥ በበሽታው የተያዙና የሞቱ ሰዎች ቁጥር ቢጨምርም ከቁጥጥር አልወጣም። አሁን ባለው መረጃ መሠረት በየቀኑ 15 ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ይሞታሉ።
የተጫዋቾች ዝውውር በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዘመን
ምንም እንኳ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አውሮፓን ሰቅዞ ቢይዛትም የእግር ኳስ ሊጎች ቀስ በቀስ ሊመለሱ ይችላሉ እየተባለ ነው። ይህን ተከትሎም የዝውውር ወሬዎች ደርተዋል። እነሆ ጥቂቱን . . .
አትሌቲኮ ማድሪድ በአርሰናል የሚፈለገው ጋናዊው ቶማስ ፓርቴይን በሊቨርፑሉ አሌክስ ኦክስሌድ ቻምበርሌይን መቀየር እንደሚፈልግ ሰን የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል።
ጋዜጣው አክሎ የ30 ዓመቱ ጋቦናዊ የአርሰናል አጥቂ ፒዬር-ኤሜሪክ ኦባሜያንግ ለንስሐ አባቱ "ለሪያል ማድሪድ መጫወት እፈልጋለሁ" ማለቱን ሰምቻለሁ ብሎ ዘግቧል።
የቻይናው ክለብ ሻንግሃይ ሼንሁዋ ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦዲያን ኢጋሎ በውሰት ከሚገኝበት ማንቸስተር ዩናይትድ ተመልሶ እንዲመጣ ይፈልጋል ሲል የዘገበው ደግሞ ስካይ ስፖርትስ ነው።
የቻይና ሱፐር ሊግ ወርሃ ሐምሌ ላይ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ዩናይትዶች የኢንተር ሚላኑ ላቱሮ ማርቲኔዝን ለማስፈረም ፍላጎት እንዳላቸው እየተነገረ ነው።
ተቀናቃኞቹ አርሰናል እና ቶተንሃም የቼለሲውን ብራዚላዊ ተጫዋች ዊሊያንን ለማስፈረም እየተፎካከሩ ነው ሲል ፉትቦል ለንደን አስነብቧል። ተጨዋቹ ከቼልሲ ጋር የነበረው ውል እየተገባደደ ነው።
በተያያዘ ቼልሲዎች ዴክለን ራይስን ገዝተው ንጎሎ ካንቴን ለማድሪድ ሊሸጡ አስበዋል በማለት ሚረር ገፁ ላይ አስፍሯል።
በሀዋይ ቱሪስቶች ታሰሩ
ሀዋይ አስገዳጅ የ14 ቀናት ለይቶ ማቆያን የጣሱ ጎብኚዎችን አሰረች።
አሶሽየትድ ፕረስ አንደዘገበው፤ እስካሁን ወደ 20 ሰዎች የታሰሩ ሲሆን፤ ከቱሪስቶቹ መካከል ምግብ ለመግዛት የወጡ ጥንዶች ይገኙበታል።
ጎብኚዎች ከክፍላቸው ከወጡ በኋላ እንዳይመለሱ፤ ሆቴሎች አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ቁልፍ እንዲያዘጋጁ ትዕዛዝ ተላልፏል። ፖሊሶች ሰዎችን በስልካቸው የሚከታተል መሣሪያ የመጠቀም እቅድም ነበራቸው
ሀዋይ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ መጣሏ ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ ቀንሶታል። የጽዳት ሠራተኞችና አብሳዮችን ጨምሮ 34 በመቶ የሚሆኑ ነዋሪዎች ሥራ አጥ ሆነዋል።
እስካሁን 700 ሰዎች በበሽታው ሲያዙ 17 ሞተዋል።