በሊባኖስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጣለ።
የተጣለው የሰዓት እላፊ ከነገ ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን እስከ ሰኞ ማለዳ ድረስ ይቆያል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳ በኋላ ለአንድ ወር ያህል በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
ዜጎች " ቤታቸው መቀመጥ አለባቸው አስቸኳይ ጉዳይ ካልገጠማቸው በስተቀር ወደ የትም መሄድ የለባቸውም" ያሉት የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ማናል አብደል ሳማድ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን ዲያብ በበኩላቸው፣ ባለፉት አራት ቀናት ብቻ 100 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ገልፀዋል።
መንግሥት አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ላይ ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ የማያደርጉ ሰዎችንም " ግዴለሽና ሃላፊነት የጎደላቸው" በማለት ወርፈዋቸዋል።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ከሆነ በአገሪቱ 870 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ ከእነዚህም መካከል 26 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።
በሊባኖስ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳ በኋላ የአካላዊ ርቀት መጠበቅ ተግባራዊ እንዲሆን በማሳሰብ ሱቆችና የአምልኮ ስፍራዎች ተከፍተዋል። ይህ የሆነው ከሁለት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።
በቫይረሱ የተያዙ አዳዲስ ሰዎች የተገኙት በአብዛኛው ከአገር ውጪ የነበሩ ሊባኖሳውያን በመመለሳቸው መሆኑ ተገልጿል።
ከአምስት ቀናት በፊት ከናይጄሪያ፣ ሌጎስ የመጡ ሁሉም ተሳፋሪዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር አስታውቆ ነበር።
የእንቅስቃሴ ገደቡ ከተነሳ በኋላ ዜጎች በመገበያያ ስፍራዎች አካላዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ሲገበያዩ የታዩ ሲሆን፣ በአውራ ጎዳናዎችም ላይ ከተጠበቀው በላይ በርካታ ሰዎች ወጥተዋል።
በሊባኖስ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ እየወደቀ የነበረው የአገሪቱ ምጣኔ ሃብትን ይበልጥ አባብሶታል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።