የ30 ዓመቱ የጅግጅጋ ነዋሪ የኮሮናቫይረስ ተገኘበት

በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 123 የደረሰ ሲሆን 41 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል። ለአለም ስጋት ለሆነው ኮሮና እስካሁን ድረስ የመከላከያ ክትባትም ሆነ የፈውስ መድኃኒት አልተገኘለትም። ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት በሽታውን መከላከል የሚያስችሉ ቀላል መንገዶች አሉ የእጅን ንጽህና በአግባቡ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ቀዳሚዎቹ ናቸው። ከተቻለም ከቤት አለመውጣትና በርካታ ሰው ከሚገኝባቸው ቦታዎች እራስን ማራቅ በተደጋጋሚ እየተመከረ ነው። ቢቢሲ አማርኛም ስለወረርሽኙ ዜናና መረጃዎችን እዚህ ገጽ ላይ የቀጥታ ዘገባዎችን ያቀርባል፤ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ተስፋ የተጣለበት የኮሮናቫይረስ ክትባት በሰው ላይ ሙከራው ተጀመረ

  2. የኮቪድ-19 ምጣኔ ሃብታዊ ተጽዕኖ

    ስልኩን የሚነካካ መንገደኛ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለሁሉም ሰው የሚሰማ እና የሁሉንም በር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ያንኳኳ ነው።

    በዚህ ሳምንት ብቻ የኮሮናቫይረስ ወረረርሽኝ የዓለምን ምጣኔ ሃብት ምን ያህል እንደጎዳው የተስተዋለበት ነው።

    አውሮፓውያን የወረርሽኙን መዛመት ለመቀነስ በራቸውን ዘግተው በመቀመጣቸው እና የንግድ ተቋማት ስራ በመፍታታቸው የተነሳ ትናንትና የአውሮፓውያን የንግድ እንቅስቃሴ በዚህ ሳምንት ክፉኛ መጎዳቱን የንግዱ ማህበረሰብ አባላትና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

    ይህ መረጃ ምጣኔ ሃብታቸውን ለመታደግ መነጋገር ለጀመሩት ለአውሮፓ አባል አገራት ትልቅ የማንቂያ ደወል ነው ተብሏል።

    የጃፓንም አገልግሎት ሰጪዎች ቢሆኑ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው እየተሰማ ነው። የጃፓን ፋብሪካዎችም ሞተራቸውን አጥፍተው ሰራተኞቻቸውን ወደ ቤት ሸኝተው ያለወትሯቸው ሰጥ እረጭ ብለዋል።

    በዚህም የተነሳ በሚያዚያ ወር የታየው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ደካማ ነው ተብሏል።

    በሶስተኛው ዓለም ያሉ አገራትም ቢሆኑ ዜጎቻቸውን ከወረርረሽኙ ለመታደግ እንቅሰቃሴን በማገዳቸው የተነሳ ቀድሞውንም ከእጅ ወዳፍ የሆነ ገቢ ያገኝ የነበረው ህዝባቸው ለከፋ ረሃብ፣ ኢኮኖሚያቸውም ለእርዳታ እጁን ዘርግቷል።

    በአሜሪካ በአምስት ሳምንታት ብቻ ከ30 ሚሊዮን በላይ ስራቸውን ያጡ ሰዎች ለመንግሥት ያመለከቱ ሲሆን የአለማችን ግዙፍ የሚባለው ኢኮኖሚም ወገቤን እያለ ይገኛል።

    በዚህ ማለዳም ከዩናይትድ ኪንግደም የተሰማው መረጃ የአገሪቱ የችርቻሮ ንግድ በ5.1 በመቶ ቀንሶ መታየቱን ነው። ይህም እአአ ከ1996 ወዲህ የታየ ከፍተኛ ማሽቆልቆል ነው ተብሏል።

    ለጊዜው አገራት ቤት ውስጥ የመቀመጥ ትዕዛዛቸውን ባራዘሙ ቁጥር ምጣኔ ሃብታቸው መታመሙና መጎዳቱ ይቀጥላል። ይህ ደግሞ የኮሮናቫይረስ ስርጭት በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ሊቀጥል ይችላል በሚል የሚሰጉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አሉ።

  3. 'ውሃ ስለተቆረጠብኝ እጄን መታጠብ አልችልም'

    'ውሃ ስለተቆረጠብኝ እጄን መታጠብ አልችልም'

    የፎቶው ባለመብት, Kenny Karpov

    በርካታ የአውሮፓ ሃገራት ውስጥ ሰዎች የውሃ ክፍያ መፈፀም አልቻሉም ብሎ መቁረጥ ሕገ-ወጥ ነው።

    አሜሪካ ደግሞ እውነታው ወዲህ ነው። የውሃ መክፈል ካልቻሉ ውሃ አያገኙም።

    በኮሮናቫይረስ ምክንያት የዕለተ'ለት ገቢያቸውን ማግኘት ያልቻሉ አሜሪካውያን የውሃ መክፈል አቅቷቸዋል። ቢሆንም መንግሥት እጃቸሁን ታጠቡ እያላቸው ነው።

    «ውሃ ማግኘት ካልቻልኩኝ አሁን ስድስት ወራት ሊሆነኝ ነው» ትላለች አሜሪካዊቷ አኪቫ ዱር።

    የሁለት ልጆች እናቶች የሆነችው አኪቫ ዲትሮይት በተሰኘችው የአሜሪካ ከተማ ውስጥ ባለ ደሳሳ ጎጆ ሥር ትኖራለች። የምትኖርበት አካባቢም አሜሪካ ውስጥ ኑሯቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች የሚኖሩበት ነው።

    የአኪቫ ኑሮ የሌሎች በርካታ አሜሪካውያንም እውነታ ነው። በዚህ ላይ ወረርሽኝ ሲጨምርበት ሕይወት ምን ያህል እንደሚከብድ መገመት አዳጋች አይደለም።

  4. በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች 117 ደረሱ

    የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ

    የፎቶው ባለመብት, ጠየና ሚኒስቴር

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከተደረገላቸው 933 ሰዎች መካከል አንድ ግለሰብ ላይ ብቻ ቫይረሱ እንደተገኘ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ሚኒስቴሩ እንዳለው በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 117 ደርሷል።

    ከእነዚህም መካከል 25 ሰዎች ሲያገግሙ ሶስት ሰዎች ደግሞ መሞታቸው ይታወቃል።

  5. የትራምፕ አስተዳደር የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የፀኃይ ብርሃን ላይ የሚደረግ ምርምርን ደገፈ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የትራምፕ አስተዳደር የፀኃይ ብርሃን የኮሮናቫይረስን ለመዋጋት ሁነኛ መሳሪያ ነው በማለት በእርሱ ላይ የሚደረጉ ጥናቶችን ደገፉ።

    የአገር ውስጥ ደህንነት የሳይንስ ክፍል ኃላፊ ቢል ብራያን፣ ቫይረሱ ለፀኃይ ብርሃን፣ ለሙቀጥና፣ ለእርጥበት አዘል አየር ሲጋለጥ በፍጥነት ይዳከማል ብለዋል።

    ጥናቱ ግን እስካሁን ድረስ ለህትመት ያልበቃ ሲሆን ተገቢውን ፍተሻም አልተደረገበትም ተብሏል።

    ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ እንዳሉት ጥናቱ በፈረንጆቹ በጋ እንደሚቀንስ ተስፋን የፈነጠቀ ነው ብለውታል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ከፍተኛ ብርሃንም ሆነ ፀረ-ባክቴሪያ በመውጋት በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን ለማከም ሊውል ይችላል ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

    የጤና ባለሙያዎች ግን አደገኛ የሆነ የስህተት መረጃ በማሰራጨት እየወነጀሏቸው ነው።

    በፈረንጆቹ በጋ ወቅት የኮሮና ቫይረስ በንኖ ይጠፋል የሚል ሃሳብ በተለያየ ጊዜ ሲነሳ ነበር።

  6. አልጄሪያ ኮቪድ-19 ስርጭት የተስፋፋባት ከተማዋ ላይ ጥላ የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ አላላች

    አልጄሪያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አልጄሪያ የኮሮናቫይረስ በሰፊው ተስፋፍቶባት የነበረው ግዛቷ ላይ ጥላ የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ በማቆም የሰዓት እላፊ ጣለች።

    ይህ ውሳኔ የተላለፈው ለረመዳን የጾም ወር መሆኑ ተገልጿል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብድላዚዝ የሰዓት እላፊው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ አንድ ሰዓት ድረስ እንደሚቆይ ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቫይረሱ ተሰራጭቶባት በነበረው ቢልዳ ግዛት ያነሱት የእንቅስቃሴ ገደብ ከረመዳን በኋላ ዳግም ይመለስ አይመለስ ያሉት ነገር የለም።

    የአልጄሪያ ሌሎች ግዛቶች፣ ዋና ከተማዋን አልጀርስን ጨምሮ፣ የሰዓት እላፊ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ ተጥሎባቸው የቆየ ቢሆንም አሁን ግን ወደ አንድ ሰዓት ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

    የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት አብድልመጂድ ቴቦኔ የእንቅስቃሴ ገደቡ እና የሰዓት እላፊው ከታወጀ በኋላ የኮቪድ-19 ስርጭት ላይ ለውጥ አለ ብለዋል።

    በቅርቡም አልጄሪያውያን ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ይመለሳሉ ማለታቸውን ዢንዋ የዜና ወኪል ዘግቧል።

  7. በደቡብ ኮሪያ ባለፉት ሃያ አራት ሰአታት ሞት አልተከሰተም

    ኮሪያ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በደቡብ ኮሪያ በባለፉት ሃያ አራት ሰአታት ውስጥ በኮሮና የሞተ ሰው አልተመዘገበም ተብሏል።

    ይህም በወር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ተገልጿል።

    የአገሪቷ የበሽታዎች ቁጥጥር ድርጅት እንዳሳወቀው ሞት ካለመመዝገብ በተጨማሪ በኮሮናቫይረሰ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነስ ያሳየ ሲሆን፤ ስድስት ሰዎች ብቻ ተመዝግቧል። ቁጥሩም በሁለት ወር ውስጥ ትንሹ ነው ተብሏል።

    ከባለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ከፍተኛ ስራ በሰራችው ደቡብ ኮሪያ፤ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች መርምራለች፤ በርካታ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ገንብታለች፤ የድንገተኛ ህክምና መስጪያ ተቋማትንም በማጠናከር ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ስራ ሰርታለች።

    ምንም እንኳን በቫይረሱ 240 ዜጎቿ ህይወታቸውን ቢያጡም ከሌሎች አገራት ጋር ሲወዳደር አሃዙ ትንሽ ነው። አገሪቷ ይህንን ሁሉ ማሳካት የቻለችው እንደ ሌሎች አገራት አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ውሳኔዎችን ሳታሳልፍ ነው። ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴም አልቆመም ነበር።

    ሆኖም የጤና ኃላፊዎቹ መዘናጋት እንደማይገባና ስራው ሊቀጥል እንደሚገባ እየተናገሩ ነው።

    በባለፉት ቀናትም ምንም እንኳን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቢቀንስም ክትባት እስካልተገኘ ድረስ ሌላ ወረርሽኝ ሊነሳ ይችላል በሚልም እያስጠነቀቁ ነው። ከማስጠንቀቅም አልፈው ወረርሽኙን መከላከል የሚያስችል የረዥም ጊዜ የጤና ስርአትም በመንደፍ ላይ ናቸው።

  8. ግብፅ በረመዳን ፆም የሰአት እላፊ አዋጇን አላላች

    በግብፅ ሰዎች ተሰብስበው ሲሰግዱ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር የረመዳንን ፆም ምክንያት በማድረግ የሰአት እላፊው እንደሚያጥር አሳውቀዋል።

    በዚህም መሰረት ከምሽቱ 2፡00 ይጀምር የነበረው የሰአት እላፊ ወደ 3፡00 እንዲገፋ መደረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊ ተናግረዋል። ይህም ከዛሬ እለት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

    ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የንግድ ቦታዎችም የሚከፈቱ ይሆናል። ሬስቶራንቶችም ምግብ በየቦታው የማድረስ አገልግሎት እንዲሰጡ ተፈቅዶላቸዋል።

    ተሰብስቦ የሚደረግ ፀሎትም ሆነ ስግደት የተከለከለ ሲሆን መስጂዶችም እንደተዘጉ ይቆያሉ።

    ግብፅ የሰአት እላፊ አዋጇን ያስተላለፈችው ከወር በፊት ሲሆን በወቅቱም በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 366 ነበር።

    በአሁኑ ወቅት 3ሺ891 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 287 ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል።

  9. የፊት ጭምብሎች በቤት እንዲሰሩ ምክንያት የሆነችው ህንዳዊቷ ሳይንቲስት

    ህንዳዊቷ ሳይንቲስት

    ህንድ ከቢሊዮን በላይ ለሚቆጠረው ህዝቧ የፊት ጭምብሎች በቤት እንዲሰሩ መንግሥትን ስትገፋፋ የነበረች ህንዳዊት ሳይንቲስት አለች።

    ሻይላጃ ቪ ጉብታ ትባላለች፣ 58 አመቷ ነው፣ በስነ ህይወትና በኬሚስትሪ የትምህርት ዘርፍ የላቀ ደረጃ ላይ ከደረሱት ህንዳዊያን መካከል አንዷ ናት።

    የህንድን መንግሥት ቴክኖሎጂን እንዴት መጠቀም እንዳለበት፣ ፖሊሲዎችንም በማርቀቅ ታማክራለች።

    "በቤት ውስጥ የሚሰሩ የፊት ጭምብሎች የቫይረሱን ሁኔታ እንዳይዛመት ይረዱታል፤ በተለይም እንዲህ እንደ ህንድ ባሉ የህዝብ ቁጥራቸው ከፍተኛ በሆነበትና በተጨናነቁ ቦታዎች" በማለት ትናገራለች።

    የፊት ጭምብሎችን ማድረግ የቫይረሱን መዛመት ይገታል የሚሉ ጉዳዮች አሁንም ቢሆን መከራከሪያ ሲሆን የአለም አቀፉ የጤና ድርጅትም ቢሆን ይህንን የሚደግፍ በርካታ መረጃዎች የሉም ይላል። ነገር ግን በርካታ የእስያ ሃገራት የፊት ጭምብልን ማድረግ አስገዳጅ አድርገውታል።

    በህንድ የፊት ጭምብሎች ቅናሽ ባልሆኑበት ሁኔታ በቤት ውስጥ የሚሰሩ የፊት ጭምብሎች ቫይረሱ ከሰው ሰው እንዳይዛመቱ ለመከላከል ጥሩ አማራጮች ናቸው ትላለች።

  10. ደቡብ አፍሪካ የጣለችውን የእንቅስቃሴ ገደብ ልታላላ ነው

    ደቡብ አፍሪካ ለአንድ ወር የቆየ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላ ነበር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የእንቅስቃሴ ገደቡን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እንደሚያላሉ አስታወቁ።

    ፕሬዝዳንቱ ለዚህ ውሳኔ ያበቃቸው ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

    ፕሬዝዳንቱ አሁንም ቢሆን በርካታ ሰዎች በቤታቸው መቀመጥ እንዳለባቸው ያስጠነቀቁ ሲሆን ሕዝባዊ ስብሰባዎች እንደታገዱ አንንደሚቆዩ የአገሪቱ ድንበሮችም ዝግ እንደሆኑ እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

    ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የተወሰኑ ሱቆች ክፍት የሚሆኑ ሲሆን ከሰራተኞቻቸው መካከል አንድ ሶስተኛው ብቻ ወደ ስራ ገበታው ይመለሳል።

    የተወሰኑ ትምህርት ቤቶችም ይከፈታሉ ያሉ ሲሆን በአንድ ክፍል ላይ የሚኖረው የተማሪ ቁጥር ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል።

    አሁንም በርካታ ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ ተጠይቋል።

    ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ለአንድ ወር የቆየው የእንቅስቃሴ ገደብ የቫይረሱን ስርጭት በማዘግየት ረገድ ውጤት አምጥቷል ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም ሰዎች መብላት ገቢ ማግኘት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ቫይረሱ ዳግም እንዳይቀሰቀስ ያስጠነቀቁ ሲሆን በበርካታ ከተሞች ይህ ስጋት መኖሩ ተገልጿል።

  11. ዩኬ፡ ሚሊዮኖች ለኮሮናቫይረስ ምርመራ ሊመዘገቡ ነው

    UK

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 10 ሚሊዮን ገደማ ቁልፍ በሚባሉ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሊደረግላቸው ነው።

    ነገር ግን ሠራተኞቹ ምርመራ የሚደረግላቸው የበሽታውን ምልክት ካሳዩ ብቻ ነው ተብሏል።

    የብሔራዊ ጤና አገልግሎት ሠራተኞች፣ የማሕበረሰብ ጤና ሠራተኞች፣ የፖሊስ መኮንኖች፣ አስተማሪዎችና ጋዜጠኞች ከሚመረመሩት መካከል ይገኙበታል።

    ከዚህ ቀደም የኮቨዲ-19 ምርመራ ማድረግ የሚችሉት ሥራቸው ከወረርሽኙ ጋር ግንኙነት ያላቸው ብቻ ነበሩ ተብሏል።

    ነገር ግን መንግሥት በቀን ቢያንስ 100 ሺህ ሰዎች እመረምራለሁ ቢልም አሁን 23 ሺህ ናቸው እየተመረመሩ ያሉት ተብሏል።

    የጤና ሚኒስትሩ ማት ሃንኮክ ግን አሁን ወደ 51 ሺህ ደርሰናል እያሉ ነው።

    ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በጠቅላላው በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 18 ሺህ ተሻግሯል።

  12. ቶም ሃንክስ ለኮሮና ደብዳቤ በመጻፍ ስጦታ ላከ

  13. ዶናልድ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ መከላከል ዙሪያ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ተነጋገሩ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት የአፍሪካ መሪዎች ጋር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ስለሚሰሩት ስራ በስልክ ተነጋገሩ።

    ዶናልድ ትራምፕ የደቡብ አፍሪካውን ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እና የኬንያውን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ነው ትናንት ያነጋገሩት።

    ፕሬዝዳንቱ ደቡብ አፍሪካ ወረርሽኙን ለመግታት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ አሜሪካ ከደቡብ አፍሪካ ህዝብ ጎን ትቆማለች ማለታቸው ተሰምቷል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለኬንያም ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ ገልፀው ከፕሬዝዳንት ኬንያታ ጋር በቅርበት ለመስራት ተስማምተዋል።

  14. 'ፀረ-ባክቴሪያ ብንወጋስ' ያሉት ትራምፕ ነቀፋ እያስተናገዱ ነው

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለኮቪድ-19 መከላከያ ለምን ሰዎች ፀረ-ተባይ አይወጉም ብለው የሰጡት አስተያየት መዘባበቻ እያደረጋቸው ነው።

    አነጋጋሪው ትራምፕ አክለውም የኮሮናቫይረስ በሽተኞችን ሰውነት ዩቪ በተሰኘ ሰው ሰራሽ ብርሃን ማፅዳት ቢቻል የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።

    ትናንት አንድ የጤና ባለሙያ የፀሐይ ብርሃንና ፀረ-ባክቴሪያ ቫይረሱን ለማጥፋት ወሳኝ ናቸው ማለታቸውን ተከትሎ ነው ፕሬዝደንቱ ይህን አስገራሚ አስተያየት የሰጡት።

    «እና፤ እስቲ አስቡት፤ ሰውነትን በአስገራሚ 'አልትራቫዮሌት' ወይም ሌላ በጣም ጠንካራ ብርሃን ብናፀዳው» ሲሉ ፕሬዝደንቱ ፅንሰ-ሃሳባቸውን ያሰሙት።

    «ፀረ-ባክቴሪያ ደግሞ በአንድ ደቂቃ ቫይረሱን ድራሹን የሚያጠፋው። እና ይህንን ፀረ-ባክቴሪያ ሰዎችን የምንወጋበት መላ ይጠፋል?»

    «[ትራምፕ በአመልካች ጣታቸው ወደ ጭንቅላታቸው እየጠቆሙ] እኔ ዶክተር አይደለሁም። ነገር ግን ያው እንደምታውቁት ያለሁ ሰው ነኝ።»

    የአሜሪካ ዶክተሮች የፕሬዝደንቱ ፅንሰ-ሐሳብ የሰውን ልጅ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ሲሉ እያስጠነቀቁ ነው።

    'ኃላፊነት የጎደለውና አደገኛ' ሲሉም የትራምፕን ሐሳብ ነቅፈዋል - ሰዎች በጭራሽ ፀረ-ባክቴሪያ ወደ ሰውነታቸው እንዳያስጠጉ በመምከር።

  15. በሆንግ ኮንግ ተማሪዎች ለፈተና ሊቀመጡ ነው

    በሆንግ ኮንግ ተማሪዎች ለፈተና ሊቀመጡ ነው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በሆንግ ኮንግ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲ ለመግባት የሚያስችላቸውን ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ በዛሬው እለት ሊቀመጡ ነው።

    ተማሪዎቹ ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ የታቀደው ባለፈው ወር ሲሆን በወረርሽኙ ምክንያት መራዘሙም ተገልጿል።

    ምንም እንኳን ተማሪዎቹ ፈተና ቢፈቀድላቸውም ጥብቅ የሆኑ ትእዛዛትም ተደንግገዋል። ከነዚህም መካከል የፊት ጭምብል ማጥለቅ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ ለፈተና ከመቀመጣቸው በፊትም ሙቀታቸው ይለካል።

    በሆንግ ኮንግ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1035 ነው።

    በሆንግ ኮንግ ተማሪዎች ለፈተና ሊቀመጡ ነው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  16. በሙስሊሞች ዘንድ ቅዱስ ተብለው የሚጠሩ ስፍራዎች ወና ሆነዋል

    በእየሩሳሌም የሚገኘው የአልአቅሳ መስጂድ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በእየሩሳሌም የሚገኘው የአልአቅሳ መስጂድ

    የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ተብለው የሚጠሩ ስፍራዎች ወና ከሆኑ ሰነባብተዋል። በረመዳን ፆምም ባዶ ሆነው ይቀጥላሉ ተብሏል።

    ከዚህ ቀደም ከተለያዩ አገራት የሚመጡ የእስልምና እምነት ተከታዮች የረመዳን ፆም ወርን በአምልኮዎችና ፀሎቶች ተሰባስበው የሚያሳልፉባቸው ሥፍራዎች ነበሩ።

    ከነዚህም ውስጥ በሳዑዲ የሚገኘው መካ እንዲሁም በእየሩሳሌም ያለው የአል አቅሳ መስጂዶች ይገኙበታል።

    "በእስልምና ታሪክ ውስጥ አሳዛኙ ወቅት ነው" በማለት በእየሩሳሌም የሚገኘው የአልአቅሳ መስጂድ ኢማምና ኃላፊ ሼክ ኦማር አል ኪስዋሚ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    በሳዑዲ የሚገኘው መካ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በሳዑዲ የሚገኘው መካ
  17. የጃፓኗ ኦሳካ ተከማ ከንቲባ፡ «ለግብይት መውጣት ያለባቸው ወንዶች ብቻ ናቸው»

    የጃፓኗ ኦሳካ ተከማ ከንቲባ፡ «ለግብይት መውጣት ያለባቸው ወንዶች ብቻ ናቸው»

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኦሳካ የተሰኘችው የጃፓኗ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ኢቺሮ ማትሱዊ 'ሴቶች ግብይት ከወጡ ቶሎ ስለማይመለሱ ወንዶች ናቸው መገበያየት ያለባቸው' ሲሉ የሰጡት አስተያየት አነጋጋሪ ሆኗል።

    «ሴቶች ይህንን ያንን ሲሉ ሰዓት ስለሚወስዱ ገበያ መውጣት የለባቸውም» ሲሉ ነው አስተያየት የሰጡት።

    ወንዶች ግን ይላሉ ከንቲባው፤ «ወንዶቻ የተባሉትን ነገር ብድግ ብድግ አድርገው ስለሚመጡ እኔ ወንዶች ብቻ ግብይት ይውጡ ባይ ነኝ፤ የሰዎች ንክኪንም ይቀንሳል።»

    ከንቲባው በዚህ አስተያየታቸው ከየአቅጣጫው ትችት እየዘነበባቸው ነው። ፍርደ-ገምድልና ክብር የለሽ አስተያየት ነው ከንቲባው የሰጡት ያሉ ሰዎች በማሕበራዊ ሚድያዎች ነቀፋቸውን አሰምተዋል።

    ይህንን አስተያየታቸውን ተከትሎ እንዴት እንዲህ ያለ አስተያየት ይሰጣሉ ተብለው የተጠየቁት ከንቲባው «ምናልባት አስተያየት ሌላ ትርጉም ያለው ሊመስል ይችላል፤ ነገረ ግን እኔና ቤተሰቤ ይህንን የምናደርገው» ብለዋል።

    ሴቶች የቤት ውስጥ ሥራና ልጅ የመንከባከብ ኃላፊነት እንዲወስዱ በሚጠበቅባት ጃፓን ፆታን መሠረት ያደረጉ የሥራ ክፍፍሎች ጎልተው ይታያሉ።

  18. በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 50 ሺ ደረሰ

    ሻማ የምታበራ ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኮሮና ክፉኛ እየተመታች ባለችው አሜሪካ የሟቾች ቁጥር 49 ሺ 759 ደርሷል።

    አገሪቷ በአለም ላይ በኮሮና በሞቱ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚም ሆናለች። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 866 ሺ የደረሰ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ እያገገሙ ያሉት 10 ከመቶ በታች ናቸው።

    በአብዛኛው የአሜሪካ ግዛቶች አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ውሳኔ ቢተላለፍም የተለያዩ ግዛቶች የንግድ ቦታዎችን ቀስ በቀስ እየከፈቱ ይገኛሉ። ይህንንም ሁኔታ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተችተውታል። ፕሬዚዳንቱ ይህንን ይበሉ እንጂ ግዛቶች እንቅስቃሴን እንዲፈቅዱ እንዲሁም ቤት የመቀመጥ ውሳኔን ተቃውመው ሰልፍ የወጡ ሰዎችን በመደገፍ ከሰሞኑ በትዊተር ገፃቸው መልእክት ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው።

    አሜሪካ በኮሮና ለተጎዱ ጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ኢንተርፕራይዞችና ቫይረሱን ለመመርመር 484 ቢሊዮን ዶላር መድባለች። በአገሪቷ ውስጥ በኮሮና ምክንያት 26.4 ሚሊዮን አሜሪካውያን ስራቸውን አጥተዋል፤ ይህም አሃዝ 15 በመቶ የሚሆነው የሰራተኛ ሃይል ነው ተብሏል።

  19. በረመዳን ጾም ወር ክልከላ የተደረገባቸው ቁልፍ የሙስሊም አገራት

    በኮሮናወረርሽኝ ምክንያት መካን የሚሳለሙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል

    የፎቶው ባለመብት, ABDEL GHANI BASHIR

    የሳዑዲ አረቢያ ንጉሥ ሠልማን በመካና መዲና በኃይማኖት አባቶችና በመስጂዱ ሰራተኞች አጠር ያለ የታራዊህ ፀሎት እንዲደረግ ደንግጓል።

    በታላቁ የመካ መስጂድና በመዲና የነብዩ መስጂድ ይህ እንዲከናወን መታዘዙ ተሰምቷል። ማንኛውም ሙስሊም ወደ እነዚህ መስጂዶች እንዲገባ አልተፈቀደም። ሁሉም በቤቱ ፀሎት እንዲያደርግ ታዟል።

    የሙስሊሞች ሶስተኛዋ ቅዱስ ስፍራ በሆነችው እየሩሳሌም የሚገኙት ዶም ኦፍ ዘ ሮክ እና አላቅሳ መስጆዶችም በረመዳን ወቅት ለህዝበ ሙስሊሙ ዝግ ሆነው ይቆያሉ።

    “እንዲህ አይነት ውሳኔ ከ 1ሺህ 400 ዓመት ወዲህ የመጀመሪያው ነው፤ ከባድ ነው፤ ልባችንን ይሰብረዋል” ብለዋል የአላቅሳ ዳይሬክተር ሼክ ኦማር አል ኪስዋኒ።

    የኃይማኖት አባቶችና ጥበቃዎች በመስጂዱ የሚደረግን የጣራዊህ ፀሎት እንዲካፈሉ የተፈቀደ ሲሆን ይኸው ፀሎት በኦንላየን ለሌሎች ሙስሊሞች የሚተላለፍ ይሆናል።

    የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በረመዳን ወር መስጂዶች እንዲዘጉና ሰዓት እላፊው እንዲቀጥል መደረጉን አስታውቀው ይህም “የሕዝብን ደህንንት ለመጠበቅ ሲባል ነው” ብለዋል።

    ይህ ገደብ ከተጣሰ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተባባሰ “ከዚህ ጠበቅ ያለ” ገደብ ሊጣል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በአገሪቱ በወረርሽኙ ምክንያት ለተጠቁ 10 ሚሊዮን ምግብ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

    “በረመዳን ለሁሉም ምግብ ማቅረብ ወረርሽኙን ስንከላከል የምንወጣው ማህበራዊ ግዴታችን ነው” ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሼክ መሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቶም በትዊተር ገፃቸው ላይ።

    የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስም ጥላ የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ በመጠኑ አላልታለች።

  20. ጉምቱው የጤና ባለሙያ 'የዓለም ጤና ድርጅት ቻይናን ከልክ በላይ አምኗታል' ይላሉ

    ጉምቱው የጤና ባለሙያ 'የዓለም ጤና ድርጅት ቻይና ከልክ በላይ አምኗታል' ይላሉ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የካናዳ ወረርሽኝ ተከላካይ ቡድን አባል የሆኑ አንድ ጉምቱ የጤና ባለሙያ የዓለም ጤና ድርጅት ለወረርሽኙ የሰጠው ምላሽ የቻይና ባለሥልጣናት መረጃ ላይ የተመረኮዘ ነበር ይላሉ።

    ባለሙያው በዚህ ምክንያት ዓለም ለወረርሽኙ ምላሽ መስጠት ከነበረባት ጊዜ ቢያንስ በሶስት ሳምንታት ዘግይታለች ባይ ናቸው።

    ዶ/ር ዴቪድ ኔይለ ሲቢሲ ለተሰኘው ጣብያ ድምፃቸውን ሲሰጡ ነው፤ ድርጅቱ ቻይና ቀድሞውንም ቢሆን የተሟላ መረጃ ሰጥታ እንደማታውቅ እያወቀ እምነት መጣል አልነበረበትም ያሉት።

    «እኔ እንደማስበው ቢያንስ 2 ወይም 3 ሳምንታት ዘግይተናል። ይህ ደግሞ የሚቆጭ ነው። ነገሮች ሲረጋጉ ይህ የሚገለጥ ይሆናል።»

    ቢሆንም ይላሉ ባለሙያው «ቢሆንም የዓለም ጤና ድርጅት ቀድሞ አውቆ ቢሆን ኖሮ የሚወስደው እርምጃ ሁኔታዎችን ይቀይራል ማለት አይደለም።»

    ዶክተሩ፤ የዶ/ር ቴድሮስ መሥሪያ ቤት የማያቋርጥ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ያስረግጣሉ።

    የዓለም ጤና ድርጅት ለኮሮናቫይረስ ምላሽ ዳተኝነት አሳይቷል በሚል ከተለያዩ አቅጣጫዎች ትችት እየገጠመው ነው። ምሬታቸውን በማሰማት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን የሚቀድማቸው አልተገኘም።