የ30 ዓመቱ የጅግጅጋ ነዋሪ የኮሮናቫይረስ ተገኘበት

በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 123 የደረሰ ሲሆን 41 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል። ለአለም ስጋት ለሆነው ኮሮና እስካሁን ድረስ የመከላከያ ክትባትም ሆነ የፈውስ መድኃኒት አልተገኘለትም። ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት በሽታውን መከላከል የሚያስችሉ ቀላል መንገዶች አሉ የእጅን ንጽህና በአግባቡ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ቀዳሚዎቹ ናቸው። ከተቻለም ከቤት አለመውጣትና በርካታ ሰው ከሚገኝባቸው ቦታዎች እራስን ማራቅ በተደጋጋሚ እየተመከረ ነው። ቢቢሲ አማርኛም ስለወረርሽኙ ዜናና መረጃዎችን እዚህ ገጽ ላይ የቀጥታ ዘገባዎችን ያቀርባል፤ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ የሚያላሉ የአውሮፓ አገራት እየተበራከቱ ነው

    የኮቪድ-19 ምርመራ ጣቢያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቼክ ሪፐብሊክ፡ መንግሥት ጥሎ የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ከዛሬ ጀምሮ አንስቷል።

    የአገሪቱ የጤና ሚንስትር እንዳሉት እስከ 10 ሰዎች ድረስ በመሆን በቡድን መንቀሳቀስ ይቻላል።

    የውጪ አገር ጉዞም ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ይፈቀዳል ተብሏል። የአውሮፓ አባል አገራት ዜጎችን የኮቪድ-19 ምርመራ እየተደረገላቸው ከሰኞ ጀምሮ ወደ ቼክ ሪፐብሊክ መግባት እንደሚችሉ መንግሥት አስታውቋል።

    ጣሊያን፡ ከአውሮፓ ክፉኛ በኮቪድ-19 ከተጠቁ አገራት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ጣሊያን፤ ተጥሎ የሚገኘውን ገደብ ደረጃ በደረጃ እያላለች ትገኛለች።

    ከዚህ ቀደም ምግብ እና መድሃኒት የሚሸጡ አነስተኛ ሱቆችን ክፍት አድርጋ ነበር። አሁን ደግሞ የህዝብ ትራንስፖርት፣ የግንባታ እና አምራች ተቋሞቿን ከሰኞ ጀምሮ ክፍት ልታደርግ ነው።

    ቤልጂየም፡ መንግሥት የጣለውን እገዳ እንዴት መነሳት እንዳለበት የሚያጤን ኮሚቴ ተቋቁሟል። ኮሚቴው ከአንድ ሳምንት በኋላ አነስተኛ ሱቆች፣ ጸጉር ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች ሳይቀሩ ክፍት እንደሚደረጉ ይጠብቃል።

  2. በዩናይትድ ኪንግደም በሁለት ደቂቃ ውስጥ 5 ሺህ የቤት ውስጥ መመርመሪያዎች ታዘዙ

    በዩናይትድ ኪንግደም በሁለት ደቂቃ ውስጥ 5 ሺህ የቤት ውስጥ ምርመራዎች ታዘዙ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዩናይትድ ኪንግደም ትዕዛዝ ለመቀበል የሚያስችል አንድ ድረ ገጽ ከተከፈተ በኋላ በሁለት ደቂቃ ውስጥ 5 ሺህ በቤት ውስጥ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያዎች መታዘዛቸውን የአገሪቷ መንግሥት አስታወቀ፡፡

    ድረ-ገጹ ቁልፍ ሰራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው የቫይረሱ ምልክት እንዳለባቸው እና ምርመራ እንዲደረግላቸው ለመመዝገብ ያስችላቸዋል፡፡

    ሰዎች ግላዊ መረጃቸውን በኦንላይን ከሞሉ በኋላ በጽሁፍ መልዕክት ወይም በኢ ሜይል ቀጠሮ እንዲይዙ አሊያም የቤት ውስጥ መመርመሪያ እንዲጠይቁ ያዛል፡፡

    ይሁን እንጅ ድረ ገጹ ከሁለት ሰዓታት በኋላ ተዘግቷል፡፡

    ከመዘጋቱ በፊት 20 ሺህ ጥያቄዎችን ያስተናገደ ሲሆን 15 ሺዎቹ ለመመርመር ቀጠሮ የጠየቁ ሲሆን 5 ሺህ የሚሆኑት የቤት ውስጥ መመርመሪያ መሳሪያ አዘዋል፡፡

    ዩናይትድ ኪንግደም እየተገባደደ ባለው ኤፕሪል ወር መጨረሻ ድረስ 100 ሺህ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ለማድረግ አልማለች፡፡

  3. "የሩዋንዳ የጸጥታ ኃይሎች ግድያ እና አስገድዶ መድፈር እየፈጸሙ ነው" ሂውማን ራይትስ ዎች

    የሩዋንዳ ፖሊስ በቅኝት ሥራ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የሩዋንዳ ፖሊስ በቅኝት ሥራ ላይ

    በሩዋንዳ የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣለች በኋላ የሩዋንዳ የጸጥታ ኃይሎች ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እንዲሁም እስር እየፈጸመ ነው ሲል ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ከሰሰ፡፡

    የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዎች እንዳለው በአገሪቷ ደቡባዊ ንያንዛ ግዛት በትንሹ ሁለት ሰዎች በፖሊስ ተገድለዋል፡፡

    በተጨማሪም የእንቅስቃሴ ገደቡን ጥሰዋል በሚል የተያዙ ሰዎችም በስታዲየሞች ታስረዋል፤ ሴቶችም የጸጥታ ኃይል መለዮ በለበሱ ሰዎች ተደፍረዋል ብሏል፡፡

    ከዚህም ባሻገር ይህንን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የዘገቡ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ታስረዋል ሲል ነው ሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የከሰሰው፡፡

    የሩዋንዳ ጦር በበኩሉ ይህንን ድርጊት የፈጸሙ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ምርመራ መጀመሩን ገልጾ፤ እስካሁን 5 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል፡፡

    በአንዳንድ አገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የተጣሉ ገደቦችን ተከትሎ የጸጥታ አካላት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸሙ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

  4. የኮሮናቫይረስ ምርመራ በደሴ ከተማ ዛሬ ይጀመራል

    የኮሮናቫይረስ ምርመራ በደሴ ከተማ ዛሬ ይጀመራል

    የፎቶው ባለመብት, AMMA

    የኮሮናቫይረስ ምርመራ በደሴ ከተማ ዛሬ እንደሚጀመር የአማራ መገናኛ ብዙኃን ዘገበ፡፡

    የምርመራ ማዕከሉ በአንድ ቀን ውስጥ 300 ናሙናዎችን የመመርመር አቅም እንዳለው ተነግሯል፡፡

    መገናኛ ብዙኃኑ የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የደሴ ከተማ ቅርንጫፍ ዳይሬክተርን አቶ አሰፋ ምሳዬን ጠቅሶ እንደዘገበው ምርመራውን የሚያካሂዱ ባለሙያዎች ሥልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡

    ማዕከሉ በደሴ ከተማ አስተዳዳር ፣ ደቡብ ወሎ ዞን እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

    በአማራ ክልል የባህርዳርና የጎንደር መመርመሪያ ማዕከላት አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በሌሎች የክልሉ ከተሞች የምርመራ ማዕከላትን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታሪኩ በላቸው ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

    በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በቫይረሱ ተያዙ ሰዎች ቁጥር 117 የደረሰ ሲሆን አምስቱ ግለሰቦች በክልሉ የተገኙ ናቸው፡፡

  5. ፖላንድ ትምህርት ቤቶችን ለተጨማሪ አንድ ወር ዘጋች

    ፖላንድ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በፖላንድ መንግሥት የመጀመሪያ ደረጃና ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ለተጨማሪ አንድ ወር ተዘግተው እንዲቆዩ መወሰኑን የፖላንድ የትምህርት ሚኒስትር ዳሪዩዝ ፒያትኮውስኪ አስታወቁ፡፡

    እርምጃው በዚህ ወር መጨረሻ ላይ እንደሚያበቃ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ይህ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

    በመሆኑም ሚኒስትሩ የማጠቃለያ ፈተናዎች የሚሰጡበትን የጊዜ ሰሌዳ ከልሰዋል፡፡

    38 ሚሊየን ሕዝብ በሚኖርባት ፖላንድ፤ በአንጻራዊነት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ዝቅተኛ ነው፡፡ እስካሁን 10 ሺህ 759 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ 463 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡

    መንግሥት የጣላቸውን ገደቦች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ ሊያላላ ይችላል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

    በመጀመሪያው ዙር የገደብ ማላላት፤ ፓርኮች እና ጫካዎች ክፍት ተደርገው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሳይክል መጋለብ እንዲሁም አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግን ጨምሮ በማንኛውም ጊዜ ሱቅ እንዲሁም የእምነት ተቋማት መሄድ ተፈቅዷል፡፡

    በሁለተኛው ዙር ደግሞ መንግሥት በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ክፍት የነበሩትን ሆቴሎችን ፣ ቤተ መጽሐፍትንና ቤተ መዘክሮችን ለመክፈት አቅዷል፡፡

  6. ደቡብ አፍሪካውያን ማስክ ማድረግ በከበዳቸው ፕሬዝደንታቸው እየተሳለቁ ነው

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    ደቡብ አፍሪካውያን የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ማድረግ በከበዳቸው ፕሬዝደንታቸው ላይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየሳለቁ ነው።

    ትናንት ፕሬዝደንት ሲሪያል ራማፎሳ መንግሥታቸው ጥሎ የሚገኘውን ጥብቅ ያለመንቀሳቀስ ገደብ እንደሚያላላ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ተናግረዋል።

    ፕሬዝደንቱ ለህዝብ መልዕክት ሲያስተላልፉ ሰዎች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ማድረግ እንዳለበት ለመስታወስ ማስክ ለማጥለቅ ሙከራ ያደረጋሉ። ራማፎሳ ግን ነገሮች እንዳሰቡት አልሆነላቸውም።

    ማስኩን ለማድረግ የጭንብሉ ገመድ ወደ ጆሯቸው ሲጎትቱ በሌላኛው በኩል ያለው ገመድ ያመልጣቸዋል። እንደገና የፊት እና አፍ መሸፈኛው ዓይናቸውን ሲሸፍን ታይተዋል።ይህም ፕሬዝደንቱን መሳቂያ አድርጓቸዋል።

  7. ጸረ-ተህዋሲያን አምራቹ ምርቴ ለመድሃኒትነት አይውልም ሲል አስጠነቀቀ

    ጽረ-ተህዋሲያን የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዓለማችን ግዙፍ ጸረ-ተህዋሲያን የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች አቅራቢው ምርቶቼ ለመድሃኒትነት አይውሉም ሲል አስጠነቀቀ።

    ፕሬዝደንት ትራምፕ ከኮቪድ-19 ለመዳን ሰዎች ለምን ጸረ-ተህዋሲያን አይወጉም ሲሉ አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል።

    ይህ አስተያየት ፕሬዝደንቱን መዘባበቻ አድርጓቸዋል።

    አርቢ የተሰኘው የዲቶል እና ላይሶል አምራች እነዚህ ምርቶች በምንም አይነት መልኩ መወሰድ የለባቸውም ብሏል።

    አምራቹ ጨምሮም ጸረ-ተህዋሲያን ምርቶቹ ጥቅም ላይ መዋል ያለባቸው በማሸጊያቸው ላይ በተቀመጠው መመሪያ መሠረት ለጽዳት ብቻ ነው ብሏል።

  8. ኮሮናን ለመከላከል በረመዳን ወቅት ምን ማድረግ ይኖርብናል? የሚኒስትሯ መልዕክት

    ዶ/ር ሊያ ታደሰ

    የፎቶው ባለመብት, ENA

    የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ሊያ ታደሰ

    ረመዳን ሙስሊሙ ማህበረሰብ የተለያዩ የተቀደሱ ተግባራትን የሚያከናውንበት እና ትልቅ ክብር ያለው ታላቅ የጾም ወር ነው፡፡

    በዚህ ወቅትም በጋራ መስገድ፣ በጋራ መሰባሰብ፣ ሰደቃ ማድረግ እንዲሁም ሌሎች ተግባራት ይከናወኑበታል፡፡

    ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተከሰተበት በመሆኑ፤ በዚህ ወርም ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ አሳስበዋል።

    ሚኒስትሯ እየተከናወኑ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎች በዚህ ወርም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ዶ/ር ሊያ በዚህ ወቅት ሊወሰዱ የሚገቡ ጥንቃቄዎችን ጠቅሰዋል፡፡

    • በህብረት (በጀመዓ) መስገድ፡ በዚህ ወቅት ይህንን ማድረግ ስለማይቻል ሁሉም የእምነቱ ተከታዮች በየቤታቸው መስገድ ይኖርባቸዋል፡፡ በቤት ውስጥ በሚሰገድበት ወቅትም ርቀትን መጠበቅ፤ እንዲሁም ለመስገድ የሚጠቀሙባቸውን ቦታዎችና መስገጃዎች ማጽዳት አስፈላጊ ነው፡፡

    ·ሃይማኖታዊ ስርዓቶች፡ ጾሙን ተከትሎ ከሚካሄዱ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በፊትና በኋላ አዘውትሮ እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ ያስፈልጋል፡፡

    ·የእንቅስቃሴ ገደብ ፡ ሰው በሚበዛባቸው የግብይት ቦታዎች እንቅስቃሴን መገደብ፤ የግድ መንቀሳቀስ ካስፈለገ አፍና አፍንጫን በማስክ አሊያም በጨርቅ የተሰሩ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎችን መሸፈን ይገባል፡፡ እጅ መታጠብ በማይቻልባቸው ቦታዎች አልኮል ያላቸው የእጅ ማጽጃ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡

    ·አረጋዊያን፡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እድሜ ባይለይም እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አረጋውያን እና የልብ፣ የስኳር እንዲሁም ተጓዳኝ በሽታዎች ያለባቸው ለበሽታው የመያዝና ወደ ከፍተኛ ደረጃ የመሻገር እድሉ ከፍ ስለሚል ለእነዚህ አረጋውያን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም አረጋውያኑ ርቀታቸውን ጠብቀው በቤት ውስጥ መቆየትና እንቅስቃሴያቸውን መገደብ ይኖርባቸዋል፡፡

    ·አመጋገብ ፡ በዚህ የጾም ወቅትም የሚያስፈልገውን ያህል ምግብ ማግኘትና ጤናን መጠበቅም ያስፈልጋል፡፡

    ·ህመሞች፡ ማንኛውም ትኩሳት፣ ደረቅ ሳል የመተንፈስ ችግር እንዲሁም ከኮሮና በሽታ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ምልክቶች ያላቸው ግለሰቦች ከሌላ ሰው ጋር መስገድ የለባቸውም፡፡ በቤት ውስጥም ቢሆን ርቀትን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ አስፈላጊ የሆነ የህክምና እርዳታ መጠየቅም አስፈላጊ ነው፡፡

    በመጨረሻም ሚኒስትሯ “እርዳታ የሚሹ ወገኖችን የምንረዳበትና የምንተጋገዝበት ይሁን” ሲሉ ጥሪያቸውን በማቅረብ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

  9. በስፔን ከአንድ ወር ወዲህ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ቀነሰ

    የስፔን የጤና ባለሙያዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    መልካም ዜና ከወደ ስፔን ተሰምቷል።

    ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በቀን የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ የሆነው ከአንድ ወር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመዝግቧል።

    በስፔን ባለፉት 24 ሰዓታት በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር 367 ነው።

    አሁን ላይ በአገሪቱ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 22 ሺህ 524 ደርሷል። ይህ አሃዝ ስፔን በዓለማችን ከፍተኛ የሟቾች ቁጥርን ያስመዘገበች ሦስተኛዋ አገር ያደርጋታል።

    ስፔን 219 ሺህ 764 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ይገኙባታል።

  10. የአገር አቋራጭ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ለኡጋንዳ የኮቪድ-9 ስርጭት ስጋት ሆነዋል

    የከባድ መኪኖች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኡጋንዳ ድንበር ተሻግረው የሚሰሩ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የኮሮናቫይረስ ስርጭት እንዳያስፋፉ ለማድረግ እየሰራች ነው።

    ይህ የተሰማው በአገሪቱ በቅርብ ጊዚያት ውስጥ የተመዘገቡት አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በአጠቃላይ ድንበር ተሻጋሪ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች መሆናቸውን ተከትሎ ነው።

    ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ሹፌሮች እንዳይነካኩ መክረዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት 11 የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎች በቫይረሱ መያዛቸው መመዝገቡን ተከትሎ ነው።

    ኡጋንዳ እስካሁን ድረስ 74 በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች መዝግባለች።

    ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ የኡጋንዳ ጤና ሚኒስትር ከታንዛንያና ከኬንያ አቻዎቻቸው ጋር በአገራቱ ላይ ስለተደቀነው ችግርና ምን ማድረግ እንዳለባቸው እየተወያዩ መሆኑን ገልፀዋል።

    ከውይይቱ መካከል ሹፌሮች ተመርምረው ውጤታቸው እስኪታወቅ ድረስ ጉዞ እንዳይጀምሩ የሚል ይገኝበታል ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ አክለውም በውይይቱ ከሚነሱት ጉዳዮች መካከል የቅብብሎሽ ጉዞ፣ ወይንም የአንድ አገር ሹፌር ድንበሩ ድረስ ካደረሰ በኋላ ለቀጣዩ አገር ሹፌር ማስረከብ የሚሉ ሃሳቦችም ተነስተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ አክለውም ኡጋንዳ ወደብ አልባ በመሆኗ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎቹ እንዳይገቡ ማገድ እንደማይቻል አስረድተዋል።

  11. ደቡብ አፍሪካውያን ትምባሆ እንዲያጨሱ ተፈቀደላቸው

    SA

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ደቡብ አፍሪካ ኮሮናቫይረስን ለመግታት በሚል የጣለችውን ገደብ ቀስ በቀስ እያላላች ነው።

    ሀገሪቱ ገደቡን ማላላት ያስፈለገኝ ምጣኔ ሃብቴ ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ብላለች።

    ቢሆንም ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ዜጎች አሁንም ቢሆንም ከቤታቸው እንዳይወጡ አሳስበዋል። ሃገራቸው ገደቡን ማላላት ትጀምር እንጂ አሁንም ሰዎች በጋራ የሚያደርጓቸው ነገሮች አይፈቀዱም። አልፎም የደቡብ አፍሪካ ድንበር እንደተዘጋ ይቆያል።

    ከሚቀጥለው ወር መባቻ ጀምሮ ሱቆች መከፈት ይጀምራሉ። አንድ ሶስተኛ የሃገሪቱ ሠራተኞችም ወደ ሥራ ይመለሳሉ ተብሏል።

    ደቡብ አፍሪካ የአልኮም መጠጥና ትምባሆ አይሸጡም በማለት ከሌሎች ሃገራት ለየት ያለ ሕግ አውጥታ ነበር። አሁን ግን ሰዎች ትምባሆ መሸመት ይችላሉ፤ መጠጡ ግን ክልክል ነው ተብሏል።

    አንዳንድ ት/ቤቶች እንደሚከፈቱ ቢነገርም አንድ ክፍል ውስጥ መማር የሚችሉ ተማሪዎች ቁጥር ይቀነሳል።

    ደቡብ አፍሪካ ጠንከር ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ ብትጥልም የፀጥታ ኃይሎች ማስከበር አልቻሉም የሚል ወቀሳ ገጥሟቸዋል።

  12. "የአንደኛው ደህና መሆን ለሌላኛውም ደኅንነት ነው" ድምጻዊት ሐመልማል አባተ

  13. የረመዳንን ጾም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ውስጥ ሆኖ በጥንቃቄ መጾም

    ሙስሊሞች ሲመገቡ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    በዚህ ዓመት በመላው ዓለም የሚገኙ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች “ቅዱስ ወር” እያሉ የሚጠሩትን ረመዳን የጀመሩት በእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ሆነው ነው።

    በየአመቱ ሙስሊሞች ወሩን ከማለዳው እስከ ምሽት ድረስ ይጾማሉ። ይህ ያለ ምግብና ውሃ መቆየት ለሚችሉ አዋቂ ሙስሊሞች ግዴታ ነው።

    ነገር ግን በእንዲህ ያለ ወረርሽኝ ወቅት መጾም ላይ ከግንዛቤ የሚገቡ ጉዳዮች አሉ።

    የተለያዩ 'ኢንፌክሽኖችን' መከላከል ከፍተኛ አቅም ይጠይቃል ያሉት የዩኒቨርስቲ ኦፍ ሰሴክስ ተመራማሪው ዶ/ር ጄና ማኮኢቺ ናቸው።

    አክለውም ለረዥም ጊዜ ያለምግብና ውሃ መቆየት የበሽታ መከላከል አቅምን ያዳክማል ብለዋል።

    ስለዚህ ጿሚዎች ከጾም በኋላ ምግብ በሚበላበት ወቅት በቂ ካሎሪ፣ ካርቦሃይድሬት፣ ፕሮቲንና ስብ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ።

    በተጨማሪም ቫይታሚን ሲ እና አይረን በምግባችን ውስጥ መካተታቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል።

    በምንበላቸው ነገሮች ውስጥም የተለያዩ አይነት ምግቦች ቢካተቱ መልካም መሆኑን ይጠቅሳሉ።

    አትክልት ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬዎች መኖራቸው ለጿሚዎች በዚህ በኮሮናቫይረስ ወቅት ወሳኝ ነው።

    ነገር ግን ከመጠን ያለፈ መመገብም ሆነ ከመጠን በታች መብላት የመከላከል አቅምን እንደሚጎዳው ዶ/ር ማኮኦቺ ተናግረዋል።

    በጾም ወቅት በሰውነት ውስጥ የውሃ እጥረት ሊፈጠር ይችላል የሚሉት ዶ/ሩ ይህም የአየር መተላለፊያ ቧንቧዎች ላይ እንደመከላከያነት በመሆን የሚያገለግሉ ሙከሶች እንዳይኖሩ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ።

    ነገር ግን ሌሎች አማራጮችን በመውሰድ፣ እንደ በቂ እንቅልፍ ማግኘት፣ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ እና ጭንቀትን ማስወገድ የመከላከል አቅምን ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ይመክራሉ።

    ከሁሉም የተሻለው አማራጭ ራስን ከቫይረሱ መጠበቅ ነው፤ በማለትም እጅን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ መታጠብ እና የሚችሉ ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ የሚለውን የዓለም ጤና ድርጅት ምክር ያስታውሳሉ።

    የኮቪድ-19 ያለባቸው ወይንም በሌላ የጤና ችግር የታመሙ ሰዎች፣ እንደ ስኳር ያሉ ከሌላ ተያያዥ የሆነ የጤና ችግሮች ጋር የሚያማቸውም ሰዎች በተመሳሳዩ እንዲጾሙ አይገደዱም።

  14. የአሜሪካ መከላከያ ኃይል በጅቡቲ ባሉት የጦር ሰፈሮቹ የአስቸኳይ ጊዜ አወጀ

    የአሜሪካ ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ መከላከያ ኃይል በጅቡቲ የኮሮናቫይረስ ስርጭት በፍጥነት መጨመሩን ተከትሎ ባሉት ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አወጀ።

    ጅቡቲ እስካሁን ድረስ 986 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ስታረጋግጥ ከእነዚህም መካከል ሁለቱ መሞታቸውን አሳውቃለች።

    የአሜሪካ ጦር በዚህች ከአንድ ሚሊዮን በታች ህዝብ ያላት አገር ቫይረሱ የበለጠ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረበት ታውቋል።

    በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ጦር አዛዥ የሆኑት ግለሰብ በሰጡት መግለጫ የሚወሰዱት የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሰጣቸውና የአሜሪካንና የጅቡቲ ኃይሎችን ደህንነትና ጤና ለመጠበቅ ይረዳናል ብለዋል።

    ይህ መመሪያ በጅቡቲ የሚንቀሳቀሱ ሁሉንም የአሜሪካ ወታደሮችና ሰራተኞች የሚመለከት እንደሆነ ተገልጿል።

    ይሀ የአስቿኳይ ጊዜ አዋጅ ለቀጣዮቹ 30 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በጅቡቲ ወደብ የሚሰሩ አሜሪካውያንም በዚህ መመሪያ ይገዛሉ ተብሏል።

    ጅቡቲ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ የጨመረው በአንድ ሳምንት ውስጥ ሲሆን እስካሁን ከተያዙት ሰዎች ውስጥ የአሜሪካውያን ስለመኖራቸው የተባለ ነገር የለም።

    በአፍሪካ የሚገኘው የአሜሪካ ጦር የፀረሽብር እንቅስቃሴዎች ላይ የሚሳተፍ ሲሆን በተለይ በሶማሊያ የአል ሸባብ ታጣቂዎችን ለማጥቃት በርካታ የአየር ላይ ጥቃቶች ያካሄዳል።

    በተጨማሪም በአህጉሪቱ በጥምረት ለሚሰሩ ወታደሮች ስልጠናም ይሰጣል።

  15. ቢዮንሴ 6 ሚሊዮን ዶላር ልትለግስ ነው

    Beyonce

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፖፕ ሙዚቃ ንግሥቷ ቢዮንሴ ለኮሮናቫይረስ መከላከል 6 ሚሊዮን ዶላር ልትለግስ ነው።

    ቢጉድ የተሰኘው የቢዮንሴ እርዳታ ድርጅት እንዳስታወቀው ገንዘቡ በአሜሪካ ግዛቶች በማሕበረሰብ ደረጃ ለሚሠሩ ድርጅቶች ይከፋፈላል ተብሏል።

    አድናቂዎቿ 'ክዊን ቢ' እያሉ የሚጠሯት ቢዮንሴ ቫይረሱ ጥቁር አሜሪካዊያን ላይ እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ እንደሚያሳስባት አልሸሸገችም።

    «አብዛኛዎቹ ጥቁር አሜሪካውያን ከቤታቸው ሆነው የመሥራት አቅም የላቸውም። በዚያ ላይ አፍሪካ አሜሪካዊ ማሕበረሰቦች በቫይረሱ እጅጉን ተጎድተዋል» ስትል ነው በኢንስታግራም ገጿ መልዕክት ያስተላለፈችው።

    «ቫይረሱ ጥቁሮችን በሚያሳስብ ሁኔታ እየጎዳ ነው። እባካችሁ ተጠንቀቁ። አንድ ቤተሰብ ነን። ታስፈልጉናላችሁ።»

  16. "በኮሮናቫይረስ ተይዣለሁ ብዬ በመዋሸቴ ለእስር ተዳረግኩ"

  17. በታንዛንያ ኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል ርምጃዎች በፍጥነት ባለመወሰዳቸው በርካታ ሰውን ለቫይረሱ አጋልጧል ተባለ

    በታንዛንያ ሕእወት እንደቀድሞው ቀጥሏል

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ታንዛንያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት ለመግታት ጠበቅ ያለ እርምጃ ባለመውሰዷ በአገሪቷ ከፍተኛ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

    የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ማትስሺዲሶ ሞየቲ እንዳሉት ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በምስራቅ አፍሪካ አገራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ሊጨምሩ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።

    "በታንዛንያ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አለመቻሉ፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎች አለመከልከላቸውና ጠበቅ ያለ ርምጃ ለመውሰድ በመዘግየቱ በአገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው ይችላል ብለን እናምናለን" ብለዋል በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ።

    የታንዛንያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት ጠበቅ ያሉ እርምጃዎችን ከመውሰድ ይልቅ ሕዝባቸው በእምነት ተቋማት እንዲሰባሰብ በመፍቀዳቸው በሰፊው ይተቻሉ።

    ታንዛንያ በኮሮናቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያውን ሰው ያገኘችው ከአንድ ወር በፊት ሲሆን እስከ ትናንት ድረስ 284 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

    በታንዛንያ ትምህርት ቤቶች ለአንደ ወር ተዘግተው የነበሩ ሲሆን ይህም ለአንድ ሳምንት ተራዝሟል።

  18. በኮቪድ-19 ተይዘው የነበሩት ቦሪስ ጆንሰን መቼ ወደ ስራ እንደሚመለሱ አይታወቅም

    ቦሪስ ጆንሰን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ የተሰኘው ጋዜጣ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ ከኮሮናቫይረስ ሙሉ በሙሉ አገግመው ሰኞ እለት በስራ ገበታቸው ላይ ይገኛሉ ሲል አስነብቧል።

    ጽህፈት ቤታቸው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው የሚመለሱበት ጊዜ አይታወቅም ሲል መልሷል።

    ቦሪስ ጆንሰን ጤንነታቸው ተሻሽሎ ወደ ስራ እየተመለሱ መሆኑን እያየን ነው ነገር ግን መቼ ሙ በሙሉ ኃላፊነታቸውን ተረክበው በቢሯቸው እንደሚገኙ ጥርት ያለ የጊዜ ሰሌዳ አልተቀመጠም ተብሏል።

    የጽህፈት ቤቱ አፈ ጉባኤ ምንም እንኳ እርሳቸውን ተክሎ እየሰሩ ያሉትን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶምኒክ ራብ ጋር ቢነጋገሩም የመንግሥት ስራ እየሰሩ አይደለም ብለዋል።

    ቦሪስ ጆንሰን ከኮቪድ-19 ካገገሙ በኋላ ንግስቲቱንና ዶናልድ ትራምፕን በስልክ አነጋግረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከጆንሰን ጋር በስልክ ካወሩ በኋላ "በጣም ደህና ነው፤ በፊት የማውቀው ባለሙሉ ኃይልና ተነሳሽነት ያለው ቦሪስ" ነበር ብለዋል።

  19. ለዩናይትድ ኪንግደም ጭንብል የለገሱት ሁለት ሕጻናት

    ሁለት ቪዬትናማውያን ሕፃናት ለዩናይት ኪንግደም ሐገራት 20 ሺህ የአፍና አፍንጫ ጭምብሎች ለግሰዋል።

    በዋና መዲናዋ ሃኖይ የሚኖሩት ናን እና ኮይ የተሰኙት እኒህ ሕፃናት ጭምብሎቹን የገዙት ለጥቂት ዓመታት ባጠራቀሙት ገንዘብ ነው።

    በቪዬትናም የብሪታኒያ አምባሳደር ጋሬት ዋርድ ለሕፃናቱ የምስጋና ደብዳቤ ፅፈዋል። በደብዳቤያቸውም ሕፃናቱ ላደረጉት እርዳታ ያላቸውን ክብር ገልፀዋል።

    ጭምብሎቹ ባለፈው ሳምንት 100 ብሪታኒያውያንን ይዞ ወደ እንግሊዝ በገባው የመንገደኞች አውሮፕላን መላኩንም አሳውቀዋል።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  20. ረመዳን ጾምና ሌሎች በዓላት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት