የ30 ዓመቱ የጅግጅጋ ነዋሪ የኮሮናቫይረስ ተገኘበት

በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 123 የደረሰ ሲሆን 41 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል። ለአለም ስጋት ለሆነው ኮሮና እስካሁን ድረስ የመከላከያ ክትባትም ሆነ የፈውስ መድኃኒት አልተገኘለትም። ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት በሽታውን መከላከል የሚያስችሉ ቀላል መንገዶች አሉ የእጅን ንጽህና በአግባቡ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ቀዳሚዎቹ ናቸው። ከተቻለም ከቤት አለመውጣትና በርካታ ሰው ከሚገኝባቸው ቦታዎች እራስን ማራቅ በተደጋጋሚ እየተመከረ ነው። ቢቢሲ አማርኛም ስለወረርሽኙ ዜናና መረጃዎችን እዚህ ገጽ ላይ የቀጥታ ዘገባዎችን ያቀርባል፤ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኮሮናቫይረስን የሚፈውስ መድኃኒት ለማግኘት ምን ያህል ተቃርበናል?

    ምርምር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ህመም አልቀዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ለቫይረሱ ተጋልጠው ይገኛሉ። እስካሁን ግን ከቫይረሱ እንደሚፈውስ የተረጋገጠለት መድኃኒት አልተገኘም።

    ግን ግን ከኮቪድ-19 ጨርሶ የሚፈውስ መድኃኒት ለማግኘት ምን ያህል ተቃርበናል?

    ከቫይረሱ የሚፈውስ መድኃኒት ለማግኘት ምን ተከናወነ?

    በመላው ዓለም የሚገኙ ተመራማሪዎች ከ150 በላይ የሆኑ የተለያዩ መድኃኒቶች ላይ እየተመራመሩ ሙከራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። ምርምር እና ሙከራ እየተደረገባቸው የሚገኙት አብዛኞቹ መድኃኒቶች በገበያ ላይ ያሉ ወይም ከዚህ ቀደም የሚታወቁ ናቸው።

    • የዓለም ጤና ድርጅት 'ሶሊዳሪቲ ትሪያል' የተሰኘ ለኮቪድ-19 ፍቱን የመሆን ተስፋ ያለውን መድኃኒት ለማግኘት ምርምር ላይ ይገኛል።
    • ዩናይትድ ኪንግደም በበኩሏ ከ5 ሺህ በላይ ታማሚዎች የሚሳተፉበት የዓለማችን በመጠኑ ሰፊ የሆነ የምርምር ሥራ እያከናወንኩ ነው ብላለች።
    • በርካታ የምርመር ማዕከላት ደግሞ ከበሽታው የዳኑ ሰዎችን ደም በመጠቀም ኮቨድ-19ን ለማከም ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ። ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ ኮሮናቫይረስን ለመፈወስ ተስፋ ያለው መድኃኒት የቱ ነው?
  2. መንትዮቹ ነርሶች በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው አለፈ

    መንትዮቹ

    የፎቶው ባለመብት, ZOE DAVIS

    መንትዮቹ እህትማማቾች በኮሮናቫይረስ ከተያዙ በኋላ በሦስት ቀናት ልዩነት በበሽታው ምክንያት መሞታቸው ተነገረ።

    መንትዮቹ ሁለቱም ነርሶች የነበሩ ሲሆን ዕድሚያቸውም 37 ነበር። ኬቲ ዴቪስ ብሪታኒያ ውስጥ በሳውዝሃምፕተን ሆስፒታል ማክሰኞ ዕለት ህይወቷ ሲያልፍ መንትያ እህቷ ኤማም በዚሁ ሆስፒታል ውስጥ ትናንት [አርብ] አርፋለች።

    የመንትዮቹ እህት የሆነችው ዞዊ ከህልፈታቸው በኋላ፤ “ሁለቱ ሁል ጊዜ ወደ ዓለም የመጣነው አብረን እንደሆነው ሁሉ የምንሄደውም አንድ ላይ ነው በማለት ይናገሩ ነበር” ብላለች።

    ጨምራም መንትያ እህቶቿ አብረው ይኖሩ እንደነበርና ሌላ የጤና ችግር እንደነበረባቸው ገልጻ፤ ለተወሰነ ጊዜ ህመም ላይ እንደቆዩ ተናግራለች።

    "እህቶቼ ምን ያህል ልዩ እንደነበሩ ለመግለጽ ቃላቶች ያጥሩኛል” ስትልም ሃዘኗን ገልጻለች።

  3. ኮሮናቫይረስንና የፀሐይ ብርሃንን ምን አገናኛቸው?

    ምስል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች ሃገራት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተጣለውን የእንቅሳቃሴ ገደብ ተከትሎ ዜጎቻቸው ቫይታሚን ዲ እንዲወስዱ እየመከሩ ነው።

    ለወትሮው ብዙዎቻችን የማይከፈልበት ቫይታሚን ዲ ከፀሐይ እናገኛለን። ከፀሐይ የሚገኝው ቫይታሚን ዲ ከሌሎች የቫይታሚን ዓይነቶች ጋር ተዳምሮ ሰውነታችን እንዲነቃቃና በሽታን ወግድ እንዲል ይረዳል። የቫይታሚን ዲ ጥቅም የሚገባን ወረርሽኝ ሲመጣ ነው ይላሉ የዘርፉ ሰዎች።

    ዩናይት ኪንግደም ውስጥ ያሉ ሰዎች ቢያንስ በቀን 10 ማይክሮግራም ቫይታሚን ያለበት ኃይል ሰጭ እንዲወስዱ ይመከራሉ። በተለይ ደግሞ እያደገደገ ያለውን የክረምት ወቅት ተከትሎ ሰዎች ከቤታቸው መውጣት ካልቻሉ በሚል ነው ይህ ምክር የተለገሳቸው። ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ፡ ኮሮናቫይረስንና የፀሐይ ብርሃንን ምን አገናኛቸው?

  4. ቤልጂየም ሱቆችንና ትምህርት ቤቶችን ልትከፍት ነው

    ብስክሌት የሚነዳ ታዳጊ

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    የምስሉ መግለጫ, ቤልጂየም ከመጋቢት መጀመሪያ አንስቶ እንቅስቃሴ አግዳለች

    የቤልጂየሟ ጠቅላይ ሚኒስርት ሶፊ ዊልምስ አገራቸው በኮሮናቫይረስ ምክንያት ጥላቸው የነበሩትን እገዳዎች ቀስ በቀስ ለማንሳት የሚያስችል ዝርዝር ዕቅድ ይፋ አደረጉ።

    በዚህም መሰረት ከሁለት ሳምንት በኋላ ሁሉም ሱቆች እንዲከፈቱ የተፈቀደ ሲሆን ትምህርት ቤቶችም ተከትለው ሥራ ይጀምራሉ። ነገር ግን በአንድ ክፍል ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ውስን ይሆናል ተብሏል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጨምረው ይህ ውሳኔ ሁኔታዎችን በመመልከት ሊለወጥ የሚችል እንደሆነም አመልክተዋል።

    ቤልጂየም ውስጥ እስካሁን በተደረገ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከ44 ሺህ ሰው በላይ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋጧል።

    በተጨማሪም 11.4 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት አገር ውስጥ በበሽታው ምክንያት 6,700 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ይህም ሞት ከአውሮፓ አገራት ጋር በነፍስ ወከፍ ሲነጻጸር ከፍተኛው እንደሆነም ተነግሯል።

    ከተመዘገበው ሞት ግማሽ ያህሉ ያጋጠመው በዕድሜ የገፉ ሰዎች በሚጦሩባቸው ማዕከላት ውስጥ ነው።

  5. የኢትዮጵያ አየር መንገድ 'የቻይና በረራዬን መቀጠሌ ትክክል ነበር' አለ

  6. የአሜሪካ ሦስት ግዛቶች የጣሉትን የእንቅስቃሴ ገደቦች እያነሱ ነው

    ስፓ፣ የውበት ሳሎን፣ የንቅሳት ቤቶች - የአሜሪካ ሶስት ግዛቶች  የእንቅስቃሴ ገደባቸውን እያነሱ ነው

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    ሦስት የአሜሪካ ግዛቶች የኮሮናቫይረስን ለመግታት አውጀውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ በማንሳት የተወሰኑ ሱቆች እንዲከፈቱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

    ጆርጂያ እና ኦክላሆማ ውስጥ የውበት ሳሎኖችና ስፓዎች ተከፍተዋል። አላስካ ደግሞ ምግብ ቤቶች ሥራ እንዲጀምሩ ፈቅዳለች።

    እንቅስቃሴ በተፈቀደባቸው ሦስቱም ግዛቶች ያሉ ነዋሪዎች አሁንም ቢሆንም ማኅበራዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁና ጭምብል እንዲያደርጉ ይገደዳሉ።

    ጆርጂያ ውስጥ የቦውሊንግ መጫወቻዎች፣ ስፓ፣ የውበት ሳሎን፣ የንቅሳት ቤቶችና መሰል ሱቆች እንዲከፈቱ ተፈቅዶላቸዋል። ሰኞ ዕለት ደግሞ ምግብ ቤቶችና ሲኒማ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ክፍት ይሆናሉ።

    አሜሪካ፤ በኮቪድ-19 ምክንያት 26 ሚሊዮን ሰዎች ከሥራ ውጭ ሆነውባታል። ይህም የጠቅላላ ሕዝቧን 15 በመቶ የሚሸፍን ነው።

    ሃገሪቱ በቫይረሱ ምክንያት ከ50 ሺህ በላይ ዜጎቿን አጥታለች።

    ፕሬዝደንት ትራምፕ ትናንት [አርብ] የነበራቸውን ጋዜጣዊ መግለጫ ያለወትሯቸው አቋርጠው መውጣታቸው አይዘነጋም።

    የኮሮናቫይረስ በሽተኞች ፀረ-ተዋሕስያንን ቢወጉ ሊድኑ ይችላሉ ሲሉ የሰጡት አስተያየት መዘባበቻ አድርጓቸዋል።

    የሕክምና ባለሙያዎችና መድኃኒት አምራቾች የፕሬዝደንቱን አስተያየት አደገኛ ሲሉ ወንጅለውታል። ፀረ-ተሕዋስ ፈሳሾች ወደ ሰውነት ውስጥ ከገቡ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ መርዛማ ናቸው። ሌላው ቀርቶ የውጭ ሰውነታችን ክፍል ላይ እንኳን ካረፉ አደጋ ሊያመጡ ይችላሉ ሲሉ መክረዋል።

    ትራምፕ፤ የሰጡት ሐሳብ ሽሙጣዊ እንደሆነና ከአውድ ውጭ እንደተወሰደባቸውም ተናግረዋል።

  7. በርካታ ሰዎች ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ እየተሻገሩ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል

  8. መንፈሳዊ ጉባኤ ያካሄዱት ፓስተር በፖሊስ ተያዙ

    Covid-19

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በደቡብ ሞዛምቢክ በምትገኘው ዛቫላ ውስጥ የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመቆጣጠር መንግሥት የታለውን መሰብሰብ እገዳ የተላለፉ አንድ ፓስተር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ።

    የሐይማኖት መሪው ፓስተር ሬልቫ ጓምቤ ከረዳታቸው ጋር በፖሊስ የተያዙት የመንግሥትን ክልከላ ጥሰው ከ300 ሰዎች በላይ የተሳተፉበት ሐይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በማካሄዳቸው ነው።

    ሊቻንጋ በተባለው መንደር ውስጥ የአካባቢውን ቀደምት አያቶች ለማስታወስ በተዘጋጀው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ በሬዎች እና ዶሮዎች ታርደው እንደነበር ተገልጿል።

    የአገሪቱ አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው ሥነ ሥርዓቱ ሲካሄድ ፖሊስ እንዲያስቀመው የተጠራ ሲሆን የአካባቢው ዳኛም ሁለቱ የሐይማኖት አባቶች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ፈቃድ ሰጥተዋል።

    የሰዎችን መተንፈሻ አካላት የሚያጠቃው በኮሮናቫይረስ አማካይነት በሚቀሰቀሰው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሞዛምቢክ ውስጥ እስካሁን 46 ሰዎች መያዛቸው ተረጋግጧል።

  9. ቻይና በኮሮናቫይረስ ጅማሬ ላይ የሚደረግ ምርመራን ተቃወመች

    ቻይናዊያን

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    በኮሮናቫይረስ አመጣጥ ላይ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ መርምራ እንዲደረግ የቀረበውን ጥሪ ቻይና ተቃወመች።

    በብሪታኒያ የቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ቼን ዌን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የቀረበው ጥያቄ ቻይና ቫይረሱን ለመዋጋት ከምታደርከው ጥረት የሚያደናቅፍ ፖቲካዊ ይዘት ያለው ነው።

    ምርመራው ያስፈልጋል የተባለው የኮቪድ-19 ቫይረስ በመጀመሪያ ላይ እንዴት እንደተሰራጨ የሚያመለክት መረጃ ቢገኝ አገራት በአሁኑ ጊዜ የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት የሚያደርጉትን ጥረት ሊያግዝ ይችላል ተብሎ ስለታሰበ ነው።

    ቫይረሱ ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ በቻይናዋ ዉሃን ከተማ ውስጥ ከሚገኝ የዱር እንስሳት ሥጋ መሸጫ ገበያ ተነስቷል ተብሎ ይታመናል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ቻይና ወረርሽኙን የያዘችበትን መንገድን ሲተቹ የቆዩ ሲሆን የአሜካዋ ግዛት ሚዙሪ ደግሞ ቻይና የቫይረሱን መስፋፋት ለማስቆም ብዙም አልጣረችም ስትል ክስ አቅርባለች።

    አንዳንዶች ይህ የኮሮናቫይረስ ቻይና ዉሃን ውስጥ በሚገኝ ቤተ ሙከራ የተሰራ ነው በማለት ጥርጣሬያቸውን ሲገልጹ ቢቆዩም፤ ሳይንቲስቶች ግን ክሱን “ውሃ የማያነሳ” ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ሕብረት ቻይናን ቫይረሱ ስላስከተለው የጤና ቀውስ የተሳሳተ መረጃን እያሰራጨች ነው ሲል ከሷል።

    የሕብረቱ የውጪ ጉዳዮች አንድ ክፍል እንዳለው ሩሲያና ቻይና ከወረርሽኙ ጋር የተያያዙ የአውሮፓ ሕብረትና ጎረቤት አገራትን ኢላማ ያደረጉ “የሴራ ትርክቶችን” እያሰራጩ ነው ሲል ከሷል።

  10. የዕለተ ቅዳሜ ሚያዝያ 17/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    እንደምን አደራችሁ?

    ይህ ቢቢሲ አማርኛ ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ ስለኮሮናቫይረስ ዜናና መረጃዎችን የሚያቀርብበት የቀጥታ ዘገባ ገጹ ነው።

    የዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 17/2012 ዓ.ም የቀጥታ ዘገባችን እዚህ ላይ ይጀምራል። የዕለተ አርብ ዘገባዎቻችንን ለመመልከት ከፈለጋችሁ ወደ ታች በመውረድ ልታገኙ ትችላላችሁ።

    መልካም ዕለት ይሁንላችሁ!

    ቢቢሲ አማርኛ
  11. እንፋሎት መታጠን ከኮሮና ያድናል?

    የፈላ ውሃ እንፋሎት መታጠን ቫይረስን እንደሚገድል የሚያረጋግጥ መረጃ የለም

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የፈላ ውሃ እንፋሎት መታጠን ቫይረስን እንደሚገድል የሚያረጋግጥ መረጃ የለም

    በአፍሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ በመሆኑም አብዛኞቹ መንግሥታት ወረርሽኙን ለመግታት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡ አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅም የማያፈናፍን ገደብ ጥለዋል፡፡

    ይሁን እንጂ የወረርሽኙን መስፋፋት ተከትሎ የተሳሳቱ መረጃዎች በአህጉሪቷ እየተሰራጩ ነው፡፡ ከእነዚህ የተሳሳቱ መረጃዎች መካከል አንዱ ደግሞ በእንፋሎት መታጠን (ስቲም) ከኮሮና ይከላከላል የሚል ነው፡፡ ይህንን ሃሳብ የታንዛኒያው ፕሬዚደንት ጆን ማጉፋሊም ተጋርተውታል፡፡

    ፕሬዚደንቱ ለባህላዊ መድሃኒቶች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ሲገልጹ፤ በእንፋሎ መታጠን በአፍንጫና በአፍ ውስጥ ያሉ ቫይረሶችን ይገድላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

    ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት ኮሮናቫይረስ ያስከተለውን ቀውስ ለመዋጋት የሚያስችሉ ዘዴዎችን በተመለከተ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

    ከፍተኛ ሙቀት የቫይረስ ጸር ነው ነበር ያሉት፡፡

    በዩናይትድ ኪንግደም ኖቲንግሃም ዩኒቨርሲቲ የተላላፊ በሽታዎች ስፔሻሊስት የሆኑት ኬት ኔል፤ ከፍተኛ የሆነ የሙቀት እንፋሎት ሆስፒታሎችንና ፋብሪካዎችን ለማጽዳት ብንጠቀምበትም ወደ ሰውነት ማስገባት ግን ለሰው ልጅ አካል አደገኛ ነው ይላሉ፡፡

    ባለሙያው እንዳሉት ቫይረስን ለመግደል ተብሎ ትኩስ እንፋሎት መታጠን ዳግም ሊጠገን በማይችል መልኩ ሳንባችንን ይጎዳል፡፡

    ከዚህም ባሻገር እንፋሎቱ ከውሃ ማፍያው ድስት ወጥቶ ወደ ሰውነት ሲገባ በፍጥነት ይቀዘቅዛል፤ በመሆኑም እንደሚባለው ቢሆንም እንኳን ቫይረሱን ሊገድል አይችልም በማለት አስረድተዋል፡፡

    የዓለም ጤና ድርጅትም ቫይረሱን ለመከላከል በትኩስ ውሃ ሰውነትን መታጠብ አደገኛ እንደሆነ አስጠንቅቋል፡፡

  12. ጣሊያን ከአንድ ወር ወዲህ ዝቅተኛውን የሞት መጠን መዘገበች

    ጣሊያን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ጣሊያን ከአንድ ወር ወዲህ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በ24 ሰዓታት ውስጥ አነስተኛ የሞት ቁጥር አስመዘገበች።

    በጣሊያን ባለፉት 24 ሰዓታት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 429 ነው። ይህም በአገሪቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን በጠቅላላው ወደ 25ሺህ 969 ከፍ አድርጎታል።

    ይህም ብቻ ሳይሆን በጣሊያን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም የመቀነስ ምልክት እያሳየ ነው። ባለፉት 5 ተከታታይ ቀናት አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል።

    በጣሊያን 92ሺህ 994 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

  13. ፈረንሳይ ታጥቦ በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል ማስክ ለዜጎቿ ልታቀርብ ነው

    ማስክ ያደረገች ሴት በብስክሌት ስትጓዝ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፈረንሳይ ከቀጣዩ ሳምንት በኋላ ታጥቦ በድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ለዜጎቿ በሽያጭ ልታቀርብ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

    በአሁኑ ሰዓት በአገር ውስጥ የሚገኙ እና ከአገር ውጪ ያሉ አቅራቢዎች 10 ሚሊዮን ማስክ ማምረታቸውን እና በተያዘው የፈረንጆቹ ወር መጨረሻ ላይ ከ25 ሚሊዮን በላይ ማስክ ለስርጭት ዝግጁ ይሆናል ብሏል የፈረንሳይ መንግሥት።

    ፈረንሳይ ጥላ የምትገኘው የእንቅሳሴ ገደብ ስታላላ ሰዎች ከቤታቸው ሲወጡ እና የህዝብ ትራንስፖርት ሲጠቀሙ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታቸው ይሆናል ተብሏል።

    በፈረንሳይ በመድሃኒት ቤቶች ውስጥ የህክምና ማስኮች እጥረት ካጋጠመ ከሁለት ወራት በላይ አስቆጥሯል።

    እነዚህ ከጨርቅ የተሰሩ እና በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉት የፊት እና አፍ መሸፈኛዎች ከ2 እስከ 5 ዩሮ ይከፈልባቸዋል ተብሏል።

    ፈረንሳይ በቫይረሱ የተያዙ 158ሺህ 387 ሰዎች የሚገኙባት ሲሆን 21ሺህ 856 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

  14. የ30 ዓመቱ የጅግጅጋ ነዋሪ የኮሮናቫይረስ ተገኘበት

  15. አሜሪካ ቬንትሌተሮችን ወደ ደቡብ አሜሪካ አገራት ልትልክ ነው

    Trump

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ ቬንትሌተሮች ወደ ሆንዱራስ፣ ኢኳዶር፣ ኢንዶኔዢያ እና ኤል ሳልቫዶር እንደምትልክ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታወቁ።

    ፕሬዝደንቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ "በቅርቡ ካመረትናቸው በርካታ ቬንትሌተሮች" የተወሰኑትን ወደ ኢኳዶር እንልካለን ብለዋል።

    ትራምፕ ጨምረውም የሆንዱራስ ፕሬዝደንት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት አሜሪካ ቬንትሌተር እና የኮቪድ-19 መመርመሪያ ቁሶችን ወደ ሆንዱራስ ትልካለች ብለዋል።

    በኤል ሳልቫዶር የሚገኙ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ለመርዳትም ቬንትሌተሮች እንደሚልኩ ትራምፕ ተናግረዋል።

    ትራምፕ የደቡብ አሜሪካ አገራት ለኢሚግሬሽን ሕጎቻቸው ድጋፍ መስጠታቸውን አወድሰዋል።

  16. የኬንያ መንግሥት እንቅስቃሴቸው ተገድቦ በቻይና ያሉ ዜጎቹን ሊያስወጣ ነው

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በቻይና እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ የሚገኙ ኬንያውያንን ለማስወጣት በረራ መሰናዳቱ ተገለጸ፡፡

    ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ኬንያዊያንም የመመለሻ ትኬት ወጪያቸውን (750 ዶላር) ሊሸፍኑ ይገባል ተብሏል፡፡

    የኬንያ አየር መንገድ በረራ ከስድስት ቀናት በኋላ የአፍሪካዊያን ማዕከል ከሆነችው ጉዋንዡ ይነሳል፡፡

    በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በግዛቷ የሚገኙ የማህበረሰብ መሪዎች፤ በርካታ አፍሪካዊያን በግድ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ወይም ጎዳና ላይ እንዲተኙ ተጽዕኖ እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል፡፡

    አብዛኞቹም በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል በሚል አድሎና መገለልን ተጋፍጠዋል፡፡

    ይህም በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ፈጥሮ ነበር፡፡

    "መንግሥት ዐይኑ ሥር እንዲህ ዓይነት በደል በዜጎቹ ላይ ሲፈጸም እያየ እንዴት ዝም ይላል?" ሲሉ በቻይና የኬንያን አምባሳደር ወቅሰዋል፡፡

    በቻይና የኬንያ አምባሳደር ሳራህ ሰረምም ለደረሰባቸው ትችት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

    አምባሳደሯ እንዳሉት ኬንያዊያን በጉዋንዡ እየደረሰባቸው ያለውን ችግር ኤምባሲው ችላ አላለም፡፡ እርዳታ ለሚሹ ዜጎችም ሌሎች አማራጮች ተዘጋጅተው ነበር ብለዋል፡፡

  17. በአሜሪካ የሟቾች ቁጥር ከ50 ሺህ አለፈ

    በአሜሪካ የሟቾች ቁጥር ከ50 ሺህ ማለፉ ተገለጸ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ የሟቾች ቁጥር ከ50 ሺህ ማለፉ ተገለጸ፡፡

    እንደ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ፤ በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ በልጧል፡፡

    ከ3ሺህ በላይ ሚሆኑት የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው ደግሞ ባለፉት 24 ሰዓታት ነው።

    አሜሪካ በዓለም ካሉ አገራት ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበባት አገር ሆናለች፡፡

    ይሁን እንጂ የአሜሪካ የጤና ባለስልጣናት በስፔን እና ጣሊያን የተመዘገቡ የሟች ቁጥሮችን ከግምት በማስገባት በአሜሪካ በቫይረሱ የተዙ ሰዎች ቁጥር ጋር ሲወዳደር የሞቱ አሜሪካውያን ቁጥር አነስተኛ ነው ይላሉ።

    በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 869 ሺህን ተሻግሯል፡፡

    በአሜሪካ 330 ሚሊየን የሚጠጋ ሕዝብ ተብሎ ይገመታል፡፡

  18. ኒኮቲን ሰዎች በኮቪድ-19 እንዳይያዙ ማድረግ ይችል ይሆን?

    በፈረንሳይ የሚገኙ ተመራማሪዎች ኒኮቲን ሰዎች በኮቪድ-19 የመያዝ እድላቸውን ስለመቀነሱ ምርምር ለማድረግ እቅድ ላይ ይገኛሉ።

    ምርምሩ የሚጀምረው ከጤና ባለስልጣናት ይሁንታ ከተገኘ ነው።

    ተመራማሪዎች ኒኮቲን በራሱ ለጤና ጠንቅ መሆኑን አሳስበዋል።

    ከዚህ ቀደም ከአንድ የፈረንሳይ ሆስፒታል የተገኘ መረጃ እንዳመላከተው ከ343 የኮቪድ-19 ታማሚዎች 4.4 በመቶ የሚሆኑት ብቻ አጫሾች ናቸው።

    ከሁለት ዓመታት በፊት በፈረንሳይ የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው ከጠቅላለው ህዝብ 25 በመቶ የሚሆኑት አጫሽ የሚባሉ ናቸው።

    በቻይና የተካሄደ አንድ ጥናት ደግሞ አጫሽ ሰዎች ከባድ የሚባል የኮቪድ-19 ምልክቶች ታይቶባቸዋል።

    የዓለም ጤና ድርጅትም ሲጋራ ማጨስ የሳምባ ጤንነትን ስለሚጎዳ የኮቪድ-19 ምልክቶች እንዲባባሱ እድሉን ያሰፋል።

  19. "የትራምፕ ንግግር ከተናገሩበት አውድ ውጭ ተወስዷል" ዋይት ሃውስ

    ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ዋይት ሃውስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የኮቪድ -19 ህክምና አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ከአውድ ውጭ ተወስዷል አለ፡፡

    ፕሬዚደንቱ ሐሙስ ዕለት በነበራቸው መግለጫ ላይ ጸረ- ተህዋስ ኬሚካል በመውጋት ወይም የጸሀይ ጨረር በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ለማከም ሊውል ይችላል ሲሉ መላ ምት ሰጥተዋል፡፡

    ይህ አስተያየታቸውም በበርካታ ዶክተሮች ትችት ገጥሞታል፡፡ ጸረ - ተህዋስ ኬሚካል ወደ ሰውነት ከገባ መመረዝን ያስከትላል፡፡

    ይህንን ተከትሎ የዓለማችን ግዙፉ ጸረ ተህዋስ እና የንጽህና መጠበቂያ አምራቹ ድርጅትም ምርቶቼ ለመድሃኒትነት አይውሉም ሲል ማስጠንቀቁ ይታወቃል፡፡

    የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ካይሌህ ማክኢናንይ፤ "ፕሬዚደንት ትራምፕ በተደጋጋሚ የኮሮናቫይረስ ህክምናን በተመለከተ አሜሪካ የህክምና ባለሙያዎችን ማማከር እንደሚገባ ተናግረዋል፤ ይህ ንግግራቸውንም በሌላ መግለጫቸው ላይም ደግመውታል" ብለዋል፡፡

    አክለውም "ነገሩን የፕሬዚደንቱን ንግግር ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ከአውድ ውጭ ለወሰዱና በአሉታዊ አርዕስት ላሰራጩ ሚዲያዎች ተውት" ብለዋል፡፡

  20. የዓለም ጤና ድርጅት የቫይረሱን ክትባት ለማፋጠን የሚያስችል እቅድ አስተዋወቀ

    ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን የቪዲዮ ስብሰባ ሲካፈሉ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዓለም መሪዎች በዓለም ጤና ድርጅት ተነሳሽነት የተዘጋጀውንና በቫይረሱ ላይ የሚደረጉ ምርምሮችን፣ ሂደቶችን፣ መድሃኒት እና ሙከራዎቹን ለማፋጠን የሚያስችል እቅድ አስተዋወቁ፡፡

    በቪዲዮ በተካሄደው በዚህ ፕሮግራም ላይ "የምንጋራው ኃላፊነት ሁሉም ሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለማሸነፍ የሚያስችለውን መሳሪያ እንዲያገኝ ማረጋገጥ ነው" ሲሉ የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል፡፡

    የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮንም "ክትባቱ ዝግጁ ሲሆን በዓለም ላይ ላለ ለማንኛውም ሰው መቅረብ አለበት" ብለዋል፡፡

    የጀርመኗን ቻንስለር አንጌላ መርክልን ጨምሮ ሌሎች የዓለም መሪዎች እና የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን፤ "የኮቪድ -19 ክትባት ዓለም አቀፋዊ የህዝብ ጥቅም ነው" በማለት ተመሳሳይ ሃሳብ አስተጋብተዋል፡፡

    ይሁን እንጅ አሜሪካ በዚህ ተነሳሽነት ላይ እንደማትሳተፍ አስታውቃለች፡፡

    በቅርቡ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም ጤና ድርጅት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያቆሙ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡