የቶተንሃም ተጨዋቾች የኮሮና ሕግን በመጣሳቸው ይቅርታ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Instagram
የቶተንሃም እግር ኳስ ተጨዋቾች ሰርጅ ኦሪየር እና ሞሳ ሲሶኮ ኮሮናቫይረስን ተከትሎ የተጣለውን ገደብ በመጣሳቸው ይቅርታ ጠየቁ።
ተጨዋቾቹ ይቅርታ ያሉት አብረው ልምምድ ሲያደርጉ የሚያሳይ ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ከለቀቁ በኋላ ነበር።
ኦሪየር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀውና በኋላ ያጠፋው ቪዲዮ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አድርጎ ከሲሶኮ ጋር ጎን ለጎን ሲሮጡ ያሳያል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ለብቻ አሊያም አብረዋችሁ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ብቻ ይሁን ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
ተጨዋቾቹ ይቅርታቸውንም ለመግለፅ ለብሔራዊ የጤና አገልግሎት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
እንደ ጆንሆፕኪንስ መረጃ በዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን 130 ሺህ 184 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 17 ሺህ 337 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።







