በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 965 ሰዎች ነጻ ሆነው ተገኙ

ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት የተነሳው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ስጋት መሆኑ ቀጥሎ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,501,156 ደርሷል። ኮሮናቫይረስ እስያን፣ አውሮፓን አሜሪካን አዳርሶ አሁን አፍሪካን ክፉኛ ያሰጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ምንም አንእኳ አገራት ቀድመው የተለያዩ እርምጃዎች ቢወስዱም የአፍሪካውያን አኗኗር ግን ጥግግት የበዛበትና አብዛኛውን ነገር በጋራ የመጠቀም ባህል ስር የሰደደ በመሆኑ ለቫይረሱ በቀላሉ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እዚህም እዚያም ይሰማል። እርስዎ ደህና ቤተሰብዎም ጤና እንዲሆኑ በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ሁሉ ይተግብሩ። መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል። የኮቪድ-19 የቀጥታ ዘገባችንን እዚህ ያገኛሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኮሮናቫይረስ፡ በታንዛኒያ የተቃዋሚው መሪ 'ለዜጎች የሀሰት ተስፋ መስጠት' እንዲቆም አሳሰቡ

    በታንዛኒያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, በታንዛኒያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

    በታንዛኒያ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዚቶ ካብዌ በአገሪቷ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየተዛመተ ባለበት ሰዓት መንግሥት ለዜጎች የማይሆን ተስፋ መስጠቱን ማቆም አለበት ሲሉ አሳሰቡ፡፡

    መሪው አክለውም ዜጎች የወረርሽኙ ትክክለኛ ምንነት ሊነገራቸው ይገባል ብለዋል፡፡

    በታንዛኒያ ትንናት ብቻ በቫይረሱ የተያዙትን 30 ሰዎች ጨምሮ እስካሁን 284 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ 10 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

    የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃሲም ማጃሊዋ ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት ዜጎች መንግሥትንና የጤና ባለሙያዎች የሚሉትን ማመን እንዳለባቸው ትናንት አሳስበዋል፡፡

    ሚኒስትሩ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ጥብቅ እገዳዎችን ከማሳለፍ በፊት መንግሥት በቅድሚያ ሊያጤነው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

    በታንዛኒያ እስካሁን ሃይማኖታዊ ስብሰባዎችን ማድረግ አልተከለከለም፡፡

    እንዲያውም ፕሬዚደንት ጆን ማጉፋሊ “ኮሮናቫይረስ በክርስትና ውስጥ አይኖርም በመሆኑም ቤተክርስቲያን እንሂድ፤ በርትተን እጸልይ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

  2. "ሞትን ተሻገርኳት" ከኮሮናቫይረስ ያገገመች ሴት

  3. አውስትራሊያ የዱር እንስሳት ስጋ ገበያ ይታሰብበት እያለች ነው

    የቻይና ዱር እንስሳት ስጋ ገበያ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ቻይና ከአራቱም አቅጣጫዎች ጫና እየበረታባት ይመስላል፤ በተለይ ደግሞ 'ዌት ማርኬት' በመባል የሚታወቀወን የዱር እንስሳት ስጋ መሸጫ ጣብያ እንድትዘጋ።

    የአውስትራሊያ መንግሥት ሃገሪቱ ገበያውን እንድትቆጣጠር ጫና እንዲያሳድሩ ለቡድን 20 ሃገራት አቤቱታ አሰምታለች።

    አውስትራሊያ ገበያው ሙሉ በሙሉ እንኳን ባይዘጋ ቀስ በቀስ ሊቀር ይገባል የሚል ሃሳብ ታቀርባለች።

    ዌት ማርኬት የሚባሉት ገበያዎች፣ ትኩስ የእንስሳት ስጋ፣ አሳ፣ ፍራፍሬና አትክልት የሚሸጡበት ሥፍራ ነው።

    ኮሮናቫይረስ ከቻይናዋ ዉሃን ከተማ ውስጥ ካለ አንድ መሰል ገበያ ሳይመነጭ አልቀረም የሚል ግምት አለ።

    የአወስትራሊያ ግብርና ሚኒስትር «እንደ ሲድኒ አሳ መሸጫ ያለ የስጋ ገበያ ቢሆን ጥሩ ነበር። ምክንያቱም ደህንነቱ የተጠበቀ ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።

    ነገር ግን የዱር እንስሳት፣ አንዳንዴም በሕይወት እያሉ እንዲሁም ሌሎች በቀላሉ የማይገኙ እንስሳት የሚሸጡ ከሆነ አደጋው የከፋ ነው ይላሉ ሚኒስትሩ።

  4. ትራምፕ ‘ግሪን ካርድ’ እንዳይሰጥ ፊርማቸውን አኖሩ

    ፕሬዝድንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዶናልድ ትራምፕ ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ ወይም ‘ግሪን ካርድ’ እንዳይሰጥ ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዛቸው ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአሜሪካ ለቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ ለማግኘት የሚያመለክቱ የውጭ አገር ዜጎችን መቀበል እንደሚያቆሙ ተናግረው ነበር።

    ፕሬዝደንቱ ይህ ውሳኔያቸው የአሜሪካውያንን ሥራ ይታደጋል ብለዋል።

    የትራምፕ ተቺዎች ግን ዶናልድ ትራምፕ የቫይረሱን ወረርሽኝ ምላሽ የሰጡበት መንገድ ስላስተቻቸው ትኩረት ለመስረቅ ያደረጉት ነው እያሉ ነው።

    ይህ የትራምፕ ውሳኔ ለቀጣይ 60 ቀናት እንደሚዘልቅ ተነግሯል።

    የፕሬዝደንቱ ክልከላ ወደ አሜሪካ በየዓመቱ 50 ሺህ ሰዎችን ያጓጉዝ የነበረው ዲቪ ሎተሪን ያጠቃልላል።

    ከ20 ሺህ ያላነሱ ሰዎች በየወሩ የቋሚ መኖሪያ ፍቃድ ያገኙ ነበር ተብሏል።

    ግሪን ካርድ ለሌላ አገር ዜጎች በአሜሪካ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ይሰጣል። ከዚያም የአሜሪካ ዜግነትን ለማግኘት ማመልከት እንዲችሉ ያስችላቸዋል። በየዓመቱ በአሜሪካ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ግሪን ካርድ ይሰጣል።

  5. ከኮሮና በኋላ የቻይና ምግብ ቤቶች ከ'ፌክ' ስጋ ጋር ተመልሰዋል

    ቻይና

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቻይና 'ሬስቶራንቶቿን' እየከፈተች ነው። የስጋ ስምና ምስል ያላቸው ከእፅዋት የሚሠሩ ምግቦች ተወዳጅነታቸው እየጨመረ ነው።

    'ፌክ' ስጋ ይሏቸዋል እነሱ። ኬኤፍሲን የመሳሰሉ ትኩስ ምግብ አቅራቢ ድርጅቶች የእፅዋት ተዋፅዖ የሆኑ ምግቦችን ማዘጋጀት ይዘዋል።

    ከኮሮናቫይረስ ያገገመችው ቻይና ዓይኗን ወደ ቅጠል መልሳለች።

    ኬኤፍሲ ለመጀመሪያ ጊዜ ቻይና ውስጥ ከእፅዋት የተሠራ የዶሮ ሥጋ ለሸማቾች አቅርቧል። የሰዎችን ፍላጎት የተመለከቱ ሌሎች 'ሬስቶራንቶችም' ይህን ፈለግ እየተከተሉ ነው።

    ለነገሩ ቻይና ከ2018 ወዲህ የስጋ እጥረት አጋጥሟታል። በተለይ ደግሞ የአሳማ ስጋ። ይህ የሆነው አፍሪካን ስዋይን የተባለው በሽታ አሳማዎችን ማጥቃቱን ተከትሎ ነው። አሁን ደግሞ በኮሮና ምክንያት በርካታ የዓለማችን ቄራዎች በመዘጋታቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል።

    ነገር ግን ቻይናውያንን 'ፌክ' ስጋ ብሉ ብሎ ማሳመን በጣም ከባድ እንደሆነ ምግብ ቤቶች ይናገራሉ። ቢሆንም ቀስ በቀስ ይለመዳል የሚል ተስፋ አላቸው።

  6. ኮሮናቫይረስን የሚፈውስ መድኃኒት መቼ ይገኛል?

  7. ኮሮናቫይረስ፡ የመጀመሪያው ሟች ጉዳይ ለምን አጨቃጫቂ ሆነ?

    ሕንድ

    የሙሐመድ ሁሴን ሲዲኪ ቤተቦች ሞሐመድ በኮቪድ-19 ሞቷል ብለው አያምኑም። ሙሉ ጤና ነበረው ሲሉ ይከራከራሉ። አንድ ወር ያክል ከልጁ ጋር ሳዑዲ አራቢያ ውስጥ ሳለ ምንም ዓይነት እክል አላሳየምና።

    ነገር ግን ከሳዑዲ ከተመለሰ 10 ቀናት በኋላ ሕይወቱ አለፈ - የሕንድ የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ሰለባ ሆኖም ተመዘገበ።

    ታሞ ሳለ ቤተሰቦቹ በሁለት ከተማዎች በሚገኙ አራት ሆስፒታሎች ተዘዋውረው ሊያሳክሙት ሞክረዋል። ሁሉም ሆስፒታሎች በሽታውን ሊያገኙለት ባለመቻላቸው ነው ወደ አምስተኛው በመሄድ ላይ ሳሉ ሕይወቱ ያለፈው።

    ሞሐመድ ሕይወቱ ባለፈች ቀን የሕንድ ባለሥልጣናት ግለሰቡ ኮቪድ-19 ነበረበት ሲሉ ተናገሩ።

    «እኔ መንግሥት የሚለውን አላምንም። የሞት ማስረጃ እንኳን አልተሰጠንም» ይላል የሞሐመድ ልጅ።

    ሞሐመድ፤ መጀመሪያ የታከመበት ሐኪም ቤት ያሉ ዶክተሮች የኒሞኒያ ምልክት እንደታየበት ነገር ግን ኮቪድ-19 እንዳለሆነ የሚገልፅ ማስረጃ ለቤተሰቦቹ ቢሰጡም መንግሥት ግን ኮሮናቫይረስ ነው ይላል።

    ይህ ጉዳይ ነው እንግዲህ ቤተሰቦቹንም ሆነ በርካታ ሕንዳውያንን ሊያሳምን ያልቻለው።

  8. አሜሪካ ውስጥ ሁለት የቤት እንስሳት ኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

    ድመት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካዋ ኒው ዮርክ ግዛት ሁለት ድመቶች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው ተዘግቧል።

    ቢሆንም በሽታው ከቤት እንስሳት ወደ ሰው እንደሚተላለፍ የሚጠቁም ምንም ዓይነት መረጃ ስለሌ ስጋት አይግባዎ ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

    ድመቶቹ ቫይረሱ ካለበት ሰው እንደተላለፈባቸው ነው የታመነው ይላሉ አሜሪካዊው ጉምቱ የጤና ባለሙያ አንቶኒ ፋውቺ።

    የአሜሪካ ጤና መከላከል ማዕከል ሲዲሲ ድመቶቹ መጠነኛ የሆነ የአተነፋፈስ ችግር አሳይተዋል ብሏል።

    እስካሁን ድረስ ሶስት ነብሮች፣ አምስት አንበሶችና ሁለት ውሾች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው ተዘግቧል።

  9. በቻይና የኮቪድ-19 ሞት ከተመዘገበ 7 ቀናት አለፉ

    በቻይና የኮቪድ-19 ሞት ከተመዘገበ 7 ቀናት አለፉ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቻይና በኮቪድ-19 የሞተ ሰው ከመዘገብኩ 8 ቀናት አልፎኛል አለች።

    ዛሬ (ሐሙስ) በቫይረሱ የተያዙ 10 ሰዎችን እንዳገኘች ይፋ ያደረገችው ቻይና፤ በአገሪቱ በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ4,632 ፈቀቅ ሳይል ከስምንት ቀናት በላይ ዘልቋል።

    ቻይና የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ስለወሰደችው ተግባር እና በቫይረሱ የተያዙ እና የሞቱ ሰዎችን በሚመለከት ሪፖርት ያደረገቻቸው አሃዞች ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው አንዳንድ መሪዎች መናገራቸው ይታወሳል። ከእነዚህም መካከል የአሜሪካ እና የፈረንሳይ ፕሬዝደንቶች ዶናልድ ትራምፕ እና ኢማኑኤል ማክሮን ተጠቃሽ ናቸው።

    ትናንት ደግሞ የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ ቻይና የቫይረሱን አደገኛነት እና ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ሳታሳውቅ ለረዥም ጊዜ ቆይታለች ሲሉ በቻይና ላይ ክስ መስርተዋል።

    ቻይና ግን በውጪ ጉዳይ ቃል አቀባይዋ በኩል የመሪዎቹን ክስ ስታጣጥል ቆይታለች።

  10. የአንድ ወር ጨቅላ ከኮሮናቫይረስ አገገመ

    ህጻን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በታይላንድ የአንድ ወር ጨቅላ ከኮሮናቫይረስ መዳኑ ተገለጸ። ህጻኑ በአገሪቷ በእድሜ ትንሹ የኮሮናቫይረስ ታማሚ ነበር።

    ዶክተሮች ጨቅላ ህጻኑን ለማዳን አራት ጸረ ቫይረስ መድሃኒቶችን መጠቀማቸውን የህጻኑን ሐኪም ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ ዘግቧል።

    "ይህንን ህጻን ለማዳን የተጠቀምነው ዘዴ ለ10 ተከታታይ ቀናት መድሃኒቱን መስጠት ነበር። በየቀኑም ክትትል እናደርግለት ነበር። ከዚያም ከሦስት እስከ አምስት ካሉት ቀናት በኋላ የተነሳው የራጅ ውጤት ጤናው መሻሻል እያሳየ እንደሆነ አመለከተ" ሲል በባንኮግ ባምራስናራዱራ የተላላፊ በሽታዎች ተቋም ቪሳል ሙላሳርት አስታውቋል፡፡

    በታይላንድ እስካሁን 2 ሺህ 826 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን የ49 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡

  11. የሕክምና ባለሙያዎችን አጥቅተዋል የተባሉት ኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

    የሕንድ የጤና ባለሙያዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሕንድ ውስጥ የሕክምና ባለሙያዎችን አጥቅተዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር የዋሉ አምስት ግለሰቦች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው።

    በሕንዷ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ነው ይህ የተከሰተው። ባለሥልጣናት ከአምስቱ ሰዎች ጋር ንክኪ ነበራቸው ያሏቸውን 70 ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ወስደዋል።

    አምስቱ ሰዎች በያዝነው ወር መባቻ የሕክምና ባለሙያዎችን አጥቅተዋል ተብለው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ ሰዎች መካከል ናቸው።

    ሰዎቹ ባሉመያዎቹ የታመመን ሰው ወደ ጤና ጣብያ ሊወስዱ ሲሉ አይሆንም ብለው ሲከላከሉ ነበር።

    ሕንድ ውስጥ በርካታ የጤና ባለሙያዎች ከነዋሪዎች ጥቃት ይደርስባቸዋል። ይህን የተረዳው መንግሥት ባለሙያዎችን የሚተናኮሱ እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እሥራት እንዲቀጡ ወስኗል።

  12. Ethiopia

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሰላም የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች፤ እንዴት አደራችሁ!

    ******************************************

    ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ከሃገር ቤትና ከመላው ዓለም ያገኘናቸውን ዘገባዎች በየደቂቃው የምናቀርብበት የቀጥታ ዘገባ ገፃችን እነሆ ተጀምሯል።

    ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት እንደተነሳ የሚነገርለት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ስጋት መሆኑ ቀጥሎ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.5 ሚሊዮን ልቋል።

    ኮሮናቫይረስ እስያን፣ አውሮፓን አሜሪካን አዳርሶ አሁን አፍሪካን ክፉኛ ያሰጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

    በመላው ዓለም ዜጎች እራሳቸውን እንዲጠብቁ እየተመከሩ ነው። ቢችሉ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡ፤ ከወጡ ደግሞ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲጠቀሙ፤ የተጨናነቁ ቦታዎች እንዳይሄዱ በመንግሥታት እየታገዱ ነው።

    እኛም ለእናንተ አስተማሪ ይሆናሉ ያልናቸውን ዘገባዎች በትኩስ በትኩስ ለማቅረብ ተዘጋጅተናል። እንደተለመደው በድረ-ገፃችንና በፌስቡክ ገፃችን ያገኙናል።

    መልካም ቀን!

  13. ኬንያ ከለይቶ ማቆያ ያመለጡ ሰዎችን እያደነች ነው

  14. የዓለም ጤና ድርጅት፡ 'ከማዳጋስካር ተገኘ ስተለባለው 'መድኃኒት' የማውቀው ነገር የለም'

    ፕሬዝደንት አንድሪ ራጆሊና

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, የ45 ዓመቱ ፕሬዝደንት ፈሳሹን የጠጡ ሁለት ሰዎች ከኮሮና ድነዋል ይላሉ።

    የዓለም ጤና ድርጅት ለኮቪድ-19 ከወደ ማዳጋስጃር ተገኘ የተባለው መድኃኒት ማስረጃ የሌለው ነው ብሏል።

    የማዳጋስካሩ ፕሬዝደንት ኮሮናቫይረስን 'የሚፈውስ' መድኃኒት ከቅጠላ ቅጠሎች ሠርተናል ማለታቸው ይታወሳል።

    ይሁን እንጂ የሃገሪቱ ሜዲካል አካዳሚም ቢሆን ፕሬዝደንት አንድሪ ራጆሊና ያስተዋወቁት 'መድኃኒት' ፈዋሽ ስለመሆኑ ማስረጃ የለም ብሏል።

    ሰዎች ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት በሳይንሳዊ መንገድ አልተመረመረም ሲል አካዳሚው ግኝቱን አጣጥሏል።

    አርቲሚሲያ ከተባለው ተክል የተሠራው ፈሳሽ መድኃኒት አቅም ለሌላቸው በነፃ ይሰጣል ተብሏል።

    የፕሬዝንቱ ፅ/ቤት ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት መድኃኒቱ በ20 ሰዎች ላይ ለሶስት ሳምንታት ከተሞከረ በኋላ በጠርሙስ ታሽጎ ለገበያ ቀርቧል።

    የ45 ዓመቱ ፕሬዝደንት ፈሳሹን የጠጡ ሁለት ሰዎች ከኮሮና ድነዋል ይላሉ።

    የዓለም ጤና ድርጅት ማንኛውም ዓይነት ሳንይንሳዊ ድጋፍ ያላገኘ መድኃኒት ኮሮናቫይረስን ለማከም ጥቅም ላይ መዋል የለበትም ይላል።

  15. ዶ/ር ቴድሮስ ቫይረስ ከእኛ ጋር ገና ብዙ ይሰነብታል አሉ

    WHO DG

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በየቀኑ በሚሰጡት መግለጫ ላይ ኮሮናቫይረስ ገና ብዙ ይሰነብታል ብለዋል።

    ዳይሬክተር ጀነራሉ ምንም እንኳ በምዕራብ አውሮፓ የቫይረሱ ስርጭት የመቀነስ እና ባለበት የመቀጠል ሁኔታ ቢያሳይም በአፍሪካ፣ ማዕከላዊ እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በምስራቅ አውሮፓ የቫይረሱ ስርጭት በሚያስፈራ ሁኔታ እየጨመረ ነው ብለዋል።

    "ምንም አይነት ስህተት መሥራት የለብንም - ገና ብዙ የምንጓዘው መንገድ አለ። ይህ ቫይረስ ከእኛ ጋር ገና ብዙ ይቆያል" ብለዋል ዳይሬክተር ጀነራል ቴድሮስ አድሃኖም።

    ዶ/ር ቴድሮስ ሰዎች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በቤት እንዲቂዩ የሚተላለፉ ትዕዛዞች እንዳሰለቿቸው ተናግረው "ዓለም ከዚህ ቀደም ወደነበረችበት መመለስ አትችልም፤ መመለስም የለባትምም" ብለዋል።

  16. ኮሮናቫይረስ፡ የኒው ዮርክ ሞት መጠን ከ20 ቀናት በኋላ ቀነሰ

    NY

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኮሮናቫይስ ምክንያት ክፉኛ የተጎዳችው የአሜሪካዋ ኒው ዮርክ ግዛት ከቀናት በኋላ ረጋ የሚያደርግ ዜና ሰምታለች።

    በየቀኑ አንድ ሺህና ከዚያ በላይ ሰዎች ሲረግፉባት የነበረችው ኒው ዮርክ ከ22 ቀናት በኋላ ቁጥሩ ትንሽ ነው የተባለ የሞት መጠን አስመዝግባለች።

    የኒው ዮርክ ሃገረ ገዥ አንድሪው ኩሞ እንዳሉት በግዛቲቱ የሞት መጠን ቅናሽ አሳይቷል።

    ኩሞ፤ ባለፉት 24 ሰዓታት በግዛቲቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 474 መሆኑን አሳውቀዋል። ይህም ከ22 ቀናት በኋላ የታየ አነስተኛ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።

    በኒው ዮርክ የሞት መጠኑ ለተከታታይ ቀናት ከ500 በታች ሆኖ ተመዝግቧል።

    «በአንፃራዊነት የተሻለ ወቅት ላይ እንገኛለን» ሲሉ ገዢው ተናግረዋል።

  17. ጀርመን የአፍ እና አፍንጫ ማድረግ ግዴታ እንዲሆን አዘዘች

    Germany mask

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    16ቱም የጀርመን ግዛቶች ዜጎች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረጋቸው ግዴታ እንዲሆን እንዳርጋለን አሉ።

    ይህም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።

    የማስክ አጠቃቀም ከግዛት ግዛት ሊለያይ ይችላል ተብሏል። ይሁን እንጂ ዜጎች የህዝብ ትራንስፖርት አግልግሎት ሲጠቀሙ እና ወደ ገበያ ማዕከላት ሲጓዙ በሁሉም ግዛቶች ማስክ ማድረግ ግድ ይሆናል።

    ጀርመን እስካሁን ከ145ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ሲሆን 4879 የሚሆኑ ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል።

  18. 'ኮሮናቫይረስ የሶማሊያን ምጣኔ ሃብት እያደቀቀው ነው'

    'ኮሮናቫይረስ የሶማሊያን ምጣኔ ሃብት እያደቀቀው ነው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የሶማሊያ ፋይናንስ ሚኒስትር ኮቪድ-19 በሃገራቸው ምጣኔ ሃብት ላይ ከበድ ያለ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ሚኒስትር አብዲራህማን ዱዋሌ በይሌ በርካታ ሶሚሊያውያን ዳያስፖራ ሥራቸውን በማጣታቸው ምክንያት ወደ ሃገር ቤት ገንዘብ እየላኩ አይደለም።

    አክለውም መንግሥት ታክስ መሰብሰብ ባለመቻሉ ምክንያት ገቢው በ40 በመቶ ቀንሷል። በዚህ ምክንያት አቅም የሌላቸው ሶማሊያውያን ረሃብ ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    ሶማሊያ ከውጭ እርዳታ በላይ ዳያስፖራዎች ከተለያዩ ሃገራት ከሚልኩት ገንዘብ ትጠቀም ነበር። ከኮቪድ-19 በፊት ቢያንስ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወደ ሶማሊያ ይላክ ነበር።

    ከዩናይትድ ኪንግደም ብቻ ወደ ሶማሊያ የሚላከው ገንዘብ በኮሮና ምክንያት 50 በመቶ ቀንሷል።

    ምንም እንኳ ሃገሪቱ በወረርሽኙ ምክንያት ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳት ቢደርስባትም ተስፋ የሚሰጥ ነገር ግን አልጠፋም።

    የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ በጋራ በመሆን 5 ቢሊዮን ዶላር ሊለግሱ እንደሚችሉ ይገመታል። አልፎም ሃገሪቱ ከ30 ዓመታት በኋላ የዕዳ እፎይታ ሊደርግላት ይችላል እየተባለ ነው።

    ዓለም ባንክ ያወጣው አንድ መረጃ እንደሚያሳየው ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት በኮሮናቫይረስ ምክንያት 37 ቢሊዮን ዶላር 'ሬሚታንስ' ገቢ ሊያጡ ትችላለች።

  19. አሜሪካ፡ ከኮሮና ጋር በተያያዘ የተመዘገበው የመጀመሪያ ሞት ምርመራ ይፋ ሆኗል

    አሜሪካ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ካሊፎርኒያ ውስጥ የወጣው ይህ የአሥከሬን ምርመራ ውጤት እንዲሚያሳየው አሜሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገው ሟች ስህተት እንደሆነ ያሳያል።

    በዋሽንግተን ግዛት ሲያትል ከተማ ነበር የመጀመሪያው የኮሮናቫይስ ሟች የካቲት 18 የተመዘገበው።

    ነገር ግን ከዚያ ቀድም ብሎ ሁለት ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት እንደሞቱ ታውቋል። የመጀመሪያ ሟች ጥር 26 ሲሆን ሁለተኛው ሞት ደግሞ የተመዘገበው የካቲት 9 ነው ሲል ሪፖርቱ አስታውቋል

    በወቅቱ አሜሪካ ከውጭ ሃገር ለመጡ ሰዎች ብቻ ነበር የኮሮናቫይረስ ምርመራ ስታደርግ የነበረው። ካልሆነ ደግሞ የተለየ ምልክት ያሳዩ ብቻ ነበሩ ምርመራ እንዲደርግላቸው የሚፈቀደው።

    መርማሪዎቹ ተጨማሪ ግኝቶችን ከሌሎች ምርመራዎች በኋላ ይፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

  20. ኡጋንዳ፡ ከለይቶ ማቆያ ያመለጡት ቻይናውያን ተቀጡ

    ኡጋንዳ ውስጥ ተለይተው እንዲቆዩ ከተዘጋጀላቸው ሆቴል ያመለጡ ስደስት ቻይናውያን መቀጣታቸውን ደይሊ ሞኒተር የተሰኘው የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።

    ስድስቱ ቻይናውያን ባለፈው ወር ነበር ከዩጋንዳዊ ሹፌራቸውና ባለቤቱ ጋር ለእሥር የተዳረጉት። ሰዎቹ ወደ ጎረቤት ሃገር ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሊያመልጡ ሲሉ ነው እጅ ከፍንጅ የተያዙት።

    ቻይናውያኑ የሚጠበቅባቸውን 14 ቀናት ቆይታ ሳያጠናቅቁ ነው ከሆቴል ያመለጡት ተብሏል።

    ማክሰኞ ዕለት ለፍርድ የቀረቡት ስድስቱ ግሰለቦች ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነዋል። ከሁለት ሳምንታት በኃላ ብይን እንደሚሰጣቸውም ተነግሯል።