የኮሮናቫይረስ ክትባት ጀርመን ውስጥ በሰው ላይ ሊሞከር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጀርመኑ ባዮኤንቴክ እንዲሁም የአሜሪካው ፋይዘር መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ያዘጋጁትን የኮሮናቫይረስ ክትባት በሰው ላይ ለመሞከር ፈቃድ ማግኘታቸው ተነገረ።
የሙከራ ክትባቱ እድሜያቸው ከ18 እስከ 55 ለሆኑ 200 ጤናማ ሰዎች በመስጠት ይጀምራል።
የጀርመን ጤና ሚኒስትር የንስ ስፓን ዛሬ እንደተናገሩት ይህ በአገራቸው የተጀመረው ለኮቪድ-19 የሚሆን ክትባት የማዘጋጀት ሥራ ውጤት እያሳየ መሆኑን አመላካች ነው።.
"ነገር ግን ይህ ሙከራ ውጤት ለማሳየት ወራት ሊፈጅ እንደሚችል መታወቅ አለበት። ይህ ክትባት በሰውነት ላይ በመርፌ የሚሰጥ ነው፤ ስለዚህም ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው” ብለዋል።
እስካሁን በዓለም ዙሪያ ክትባት ለመስራት ከሚደረጉት ጥረቶች መካካል የተወሰኑት ብቻ ናቸው በሰው ላይ ሙከራ እንዲደረግባቸው የተፈቀደው።
ባለሙያዎች እንደሚሉት አስተማማኝና ዘላቂ ክትባት ለበሽታው ለማግኘት ቢያንስ አንድ ዓመት ያስፈልጋል።
በብሪታኒያው ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ያሉ ተመራማሪዎችም ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የሚሆን ክትባትን በሰው ላይ በዚህ ሳምንት ሙከራ እንደሚያደርጉ ተገልጿል። ሌሎች የክትባት ሙከራዎችም በአሜሪካና በቻይና ውስጥ እየተካሄዱ ይገኛሉ።















