ኤርትራ ላልተወሰነ ጊዜ የእንቅስቃሴ ገደቡን አራዘመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኤርትራ መንግሥት የኮሮና መከላከል ግብረኃይል በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላልተወሰነ ጊዜ የእንቅስቃሴ ገደቡን አራዘመ።
የኤርትራ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የ21 ቀን የእንቅስቃሴ ገደብ ያስቀመጠው ባለፈው ወር ነበር።
ግብረ ኃይሉ በሰጠው መግለጫ የእንቅስቃሴ ገደቡን ማራዘም ያስፈለገው የሕዝቦችንና የአገሪቱን ደህንነት ለመከላከል መሆኑን ከገለፀ በኋላ ከሶስት ሳምንት በፊት ተቀምጦ የነበረው መመሪያ ተግባራዊ ሆኖ እንደሚቆይ አስታውቋል።
የኤርትራ መንግሥት የእንቅስቃሴ ገደቡ የኮቪድ-19 ስርጭት መስፋፋት ያለበት ሁኔታ በሚገባ እስኪፈተሽና የሚገኘው ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ እስኪገለፅ ድረስ ይቆያል ተብሏል።
በዚህ የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ጊዜ ባለፉት ሰላሳ ቀናት ወደ ኤርትራ ከተለያዩ አገራት የመጡ 1660 ዜጎች፣ ከእነርሱ ጋር ንክኪ የነበራቸው ቤተሰቦችና ዘመዶቻቸው ለ21 ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቀመጡ ይሆናል ተብሏል።
መንግሥት አክሎም ማንኛውም በኮቪድ-19 መያዙ የተጠረጠረ ሰው አስፈላጊው ምርመራ እንደሚደረግለት ገልጾ ቫይረሱ የተገኘበት አስፈላጊውን ህክምና እንደሚያገኝ አስታውቋል።
ይህ የእንቅስቃሴ ገደብ “በዜጎች ህይወት ላይ ከፍተኛ ጫና ይኖረዋል” ያለው መግለጫው በንግድ ላይ ለተሰማሩም ሆነ ለሌሎች ምንም አይነት ድጎማም ሆነ ድጋፍ እንደሚሰጥ አልተጠቀሰም።
ኤርትራ በኮሮናቫይረስ የተያዙ 39 ሰዎች ማግኘቷን የገለፀች ሲሆን ከእነዚህ መካከል ስድስት ሰዎች ማገገማቸው ተገልጿል።













