በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 965 ሰዎች ነጻ ሆነው ተገኙ

ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት የተነሳው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ስጋት መሆኑ ቀጥሎ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,501,156 ደርሷል። ኮሮናቫይረስ እስያን፣ አውሮፓን አሜሪካን አዳርሶ አሁን አፍሪካን ክፉኛ ያሰጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ምንም አንእኳ አገራት ቀድመው የተለያዩ እርምጃዎች ቢወስዱም የአፍሪካውያን አኗኗር ግን ጥግግት የበዛበትና አብዛኛውን ነገር በጋራ የመጠቀም ባህል ስር የሰደደ በመሆኑ ለቫይረሱ በቀላሉ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እዚህም እዚያም ይሰማል። እርስዎ ደህና ቤተሰብዎም ጤና እንዲሆኑ በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ሁሉ ይተግብሩ። መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል። የኮቪድ-19 የቀጥታ ዘገባችንን እዚህ ያገኛሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በየደቂቃው በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን የሚያሳይ ካርታ

  2. የኮሮናቫይረስ የክትባት ሙከራ በሰዎች ላይ ተጀመረ

    ክትባት የተሞከረባቸው ግለሰቦች

    በሰዎች ላይ የሚደረገው የኮሮናቫይረስ የክትባት ሙከራ በዛሬው እለት በእንግሊዝ፣ ኦክስፎርድ ተጀምሯል።

    ሁለት በጎ ፈቃደኞችም ክትባቱን ተወግተዋል። ለዚህ ሙከራም ስምንት መቶ ያህል ፈቃደኞች ተመልምለዋል።

    ከነዚህም ውሰጥ ግማሾቹ የኮቪድ 19 ክትባት ሙከራ የሚደረግባቸው ሲሆን፤ ግማሾቹ ደግሞ የማጅራት ገትር መከላከያ ክትባት ይሰጣቸዋል። የማጅራት ገትር መከላከያ ክትባት የሚሰጣቸው ፈቃደኞች የኮሮና መከላከያ አይከተቡም ተብሏል።

    በጎ ፈቃደኞቹ የተከተቡትን የሙከራ አይነት ማወቅ የማይችሉ ሲሆን ዶክተሮቹ ግን ለተለያዩ የክትባት አይነቶች ያላቸውን ምላሽ ይከታተላሉ።

    ክትባቱ የተሰራው ከደከመ የጉንፋን ቫይረስ ሲሆን አዴኖቪረስ ተብሎ ይጠራል። ቫይረሱ በዝንጀሮዎች የሚገኝ ሲሆን ሰዎችም እንዳይዛቸውም ባህርዩ ተቀይሯል ተብሏል።

  3. ዱባይና አቡዳቢ ወደ እንቅስቃሴ ሊመለሱ ነው

    ዱባይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ለ24 ሰዓት ጥላ የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለረመዳን ወር በመጠኑ አላላች።

    አዲሱ የእንቅስቃሴ ገደብ ከምሽቱ አራት ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ የሚዘልቅ ሆኖ ዜጎች ቀን እንዲንቀሳቀሱ ይፈቅዳል።

    ላለፉት ሦስት ሳምንታት ዱባይ በጣም ጥብቅ የተባለውን የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለች ሲሆን በዚያም ወቅት ዜጎች በቤታቸው እንዲቀመጡ ታዘው ነበር።

    ዱባይና አቡዳቢ በቅርቡ ሱቆቻቸውን ለመክፈት እቅድ እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል።

    የንግድ ማዕከሎቹ የሚከፈቱበት መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን የገበያ አዳራሾቹ ማስተናገድ ከሚችሉት 30 በመቶ ብቻ እንዲያስተናግዱ የማዕከላቱ አስተዳዳሪዎችም ይህን መፈፀሙን እንዲያረጋግጡ ታዝዟል።

    እንዲሁም በንግድ ማዕከላት ውስጥ በተገበያዮች መካከል የሁለት ሜትር አካላዊ ርቀት መኖሩን እንዲያረጋግጡ ተጠይቋል።

    እነዚህን ትልልቅ ከተሞች የሚጎበኙ ለሦስት ሰዓታት ብቻ መገበያየት የሚችሉ ሲሆን በዚህ ወቅትም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ነው ተብሏል።

    ምግብ ቤቶችም ቢሆኑ መያዝ ከሚችሉት ተጠቃሚ 30 በመቶ ብቻ ማስተናገድ የሚኖርባቸው ሲሆን በጠረጴዛዎች መካከል ርቀት መጠበቅ እንዳለባቸው የተላለፈው መመሪያ ያዛል።

    በዱባይ የሚገኙ ባለስልጣናት በረመዳን ወቅት ነዋሪዎች ቤተሰቦቻቸውን ተቀብለው ማስተናገድ እንደሚችሉ የገለፁ ሲሆን ከቤታቸው ውጪ "አንድ እንቅስቃሴ ብቻ" ማካሄድ ይችላሉ ተብሏል። በዚህ ወቅት ግን የሚሰበሰበው ሰው ብዛት ከ10 መብለጥ የለበትም ተብሏል።

    መጨባበጥ፣ መተቃቀፍ እና ሕዝባዊ ስብሰባ አሁንም በጥብቅ የተከለከለ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም ቢሆን በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በመስጂዶች የጁምአ ፀሎት አልተፈቀደም።

    በዱባይ የትራንስፖርት አግግሎት በቅርቡ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

    እስካሁን ድረስ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች 8,756 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች እንዳሉ ስታረጋግጥ ከእነዚህ መካከል 56 ሰዎች መሞታቸውን መዝግባለች።

  4. በእንግሊዝ 103 የጤና ባለሙያዎች በኮሮና መሞታቸው ተገለፀ

    መፈክር የያዘችው ጥቁር ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንግሊዝ 103 የጤና ባለሙያዎችን ማጣቷን ቢቢሲ ባደረገው የምርመራ ዘገባ መረዳት ችሏል።

    ከነዚህም መካከል 53 ወንዶች እንዲሁም 49 ሴቶች ናቸው።

    ህይወታቸውን ያጡት በአብዛኛው ጥቁር፣ እስያና ከሌሎች አገራት የመጡ ነጭ ያልሆኑ የጤና ባለሙያዎች ሲሆኑ 65 በመቶ የሚሆነውን አሃዝ ይሸፍናል ተብሏል። ከነዚህም ውስጥ አስራ ሶስቱ የፊሊፒንስ ዜግነት ያላቸው ናቸው።

    ምንም እንኳን የጤና ባለሙያዎቹ በቫይረሱ መያዛቸውን ቢቢሲ ማረጋገጥ ባይችልም ለህዝቡ ይፋ ከተደረጉ ሪፖርቶች ላይ በሰበሰው መረጃ ሞታቸው በቫይረሱ መሆኑን ማወቅ ተችሏል። ሪፖርቶቹ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም የስራ ባልደረቦቻቸውን ዋቢ አድርገው የተሰሩ ናቸው።

    ከነዚህም ውስጥ በሆስፒታል ሲሰሩ የነበሩ 16 ዶክተሮች የሞቱ ሲሆን፣ ሁሉም ወንዶች፣ ነጭ ያልሆኑና አብዛኞቹ እድሜያቸው ከአምሳ በላይ መሆናቸውም ታውቋል።

    በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች 22፣ ነርሶችና አዋላጆች 34 እንዲሁም ሌሎች ድጋፍ ሰጪዎች 47 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

    የጤና ባለሙያዎቹ በቫይረሱ የተያዙት የኮሮና ህሙማንን እያከሙ በነበረበት ወቅት ስለመሆኑ የተገለፀ ዝርዝር መረጃ የለም።

  5. በጣሊያን በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 25,549 ደረሰ

    በጣልያን የሚገኝ መካነ መቃብር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ጣሊያን ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 464 ከኮሮና ጋር የተያያዙ ሞቶች መመዝገቧን አስታወቀች።

    ይህም በአጠቃላይ በአገሪቷ በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥርን 25,549 አድርሶታል።

    ጣሊያን በሟቾች ቁጥር ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ስትሆን ባለፉት 24 ሰአታት የመዘገበቻቸው አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 2,646 መሆኑን ባለስልጣናት ገልፀዋል።

    በጣሊያን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲሁም በጽኑ ሕሙማን ክፍል ያሉ ታካሚዎችም ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን ባለስልጣናቱ ጨምረው ገልፀዋል።

  6. በጋና ከስምንት ሺህ በላይ ፖሊሶች የኮቪድ-19 ምርመራ ሊያደርጉ ነው

    የጋና ፖሊስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከስምንት ሺህ በላይ የጋና ፖሊሶች አስገዳጅ የኮቪድ-19 ምርመራ ሊደረግላቸው መሆኑን የአገሪቱ ፖሊስ ባለስልጣናት ለቢቢሲ ገለፁ።

    የፖሊስ አባላቱ ጋና የጣለችውን ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ ለማስፈፀም የተሰማሩ ናቸው ተብሏል።

    ምርመራውን ለማድረግ ያስፈለገው በከፊል የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለማስፈፀም በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ለቫይረሱ ተጋልጠው ከሆነ ለመለየትና ለማከም እንደሆነ ተገልጿል።

    ባለስልጣናቱ ለቢቢሲ እንዳሉት ምርመራው መደበኛውን አሰራር ተከትሎ የሚካሄድ ነው።

    ከፖሊስ አባላቱ ናሙና ሲወሰድ በፖሊስ መኮንኖቹ እና በቤተሰቦቻቸው ዘንድ "ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል" የሚል ስጋት መፈጠሩን ለማወቅ ተችሏል።

    በቫይረሱ የተያዙ የፖሊስ አባላት አንዳንዶቹ እረፍት ተሰጥቷቸው ህክምናቸውን እንዲከታተሉ ሲደረግ፣ ቀሪዎቹ ግን ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ስራ ገበታቸው ላይ መሆናቸው ታውቋል።

    የፖሊስ አባላቱ በማይገኙበት ወቅት ክፍተት እንዳይፈጠር አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረጉን ባለስልጣናቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    በጋና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መስፋፋት ለመግታት የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለማስፈፀም ከ30ሺህ በላይ የፀጥታና ደህንነት አባላት በመላ አገሪቱ ተሰማርተዋል።

    ፕሬዝዳንት አኩፎ አዶ በቫይረሱ የተያዙ የፖሊስ ባልደረቦች ያሉበትን አክራን ጨምሮ ለሶስት ሳምንታት ተጥሎ የነበረውን ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ ማንሳታቸው ይታወሳል።

    ከስምንት መቶ በላይ ሰዎች የእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት የተላለፉ መመሪያዎችን በመጣስ በቁጥጥር ስር ውለው የፍርድ ሂደታቸውን እየተጠባበቁ ነው።

    በጋና አሁንም ቢሆን ሕዝባዊ ስብሰባዎችና ትምህርት ቤቶች እንደታገዱ ሲሆኑ የአገሪቱ ድንበርም ዝግ ሆኖ ይቆያል ተብሏል።

  7. የማላዊ ማረሚያ ቤት ጠባቂዎች ከኮሮና በጀት ይገባናል ብለው አድማ መቱ

    ኮሮና በማላዊ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በማላዊ ቺቺሪ ማረሚያ ቤት ጠባቂዎች መንግሥት ኮሮና ቫይረስን ለመታገል ከያዘው በጀት ላይ ገንዘብ ይገባናል በሚል የስራ ማቆም አድማ መትተዋል። በማረሚያ ቤቱ በር ላይ ጎማዎችን በማቃጠል ተቃውሟቸዋን ገልፀዋል።

    ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት እንዲለቀቁ ብሏቸው የነበሩ 184 ታራሚዎችን አንለቅም በማለት እንዳገቷቸውም የአገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።

    አገሪቷ የኮቪድ-19 በጀት ተጠቃሚ ይሆናሉ ብላ ከዘረዘረቻቸው የስራ ዘርፎች መካከል ፖሊስ፣ የስደተኞች ተቋም የሚገኝበት ሲሆን ይህም ሁኔታ በማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች ዘንድ ቅያሜን ፈጥሯል።

    "ልንካተት ይገባል፣ መገለላችን ተገቢ አይደለም" እያሉም ቅሬታቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።

    የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች ጎማዎችን ሲያቃጥሉ የሚያሳየው ቪዲዮው በትዊተር ተጠቃሚዎች ዘንድ ተጋርቷል።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    በፕሬዚዳንት ፒተር ሙታሪካ የተቋቋመው የኮሮና ልዩ በጀት አፈፃፀሙ ጋር ተያይዞም ከፍተኛ ትችቶችን እያስተናገደ ነው።

    ትችታቸውን ካሰሙትም መካከል የማላዊ የህግ ማህበር ይገኝበታል።

    በማላዊ 33 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ሶስት ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

    አገሪቷ ባለፈው ሳምንት አስገዳጅ የቤት ውስጥ መቀመጥ ውሳኔን ለማሳለፍ ተዘጋጅታ የነበረ ቢሆንም የአገሪቱ ፍርድ ቤት በመጀመሪያ ሌሎች እርምጃዎች መቅደም አለባቸው በሚል ውሳኔውን እንዲዘገይ አድርጎታል።

  8. ኮሮናቫይረስ ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን አብዝቶ የሚገድለው ለምንድን ነው?, በቻይና በተደረገ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ከሴቶች ይልቅ በኮሮናቫይረስ በብዛት የሚሞቱት ወንዶች መሆናቸው ተረጋግጧል። ለምን? የሚከተለው ቪዲዮ ይህንን ያብራራል።

    የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ኮሮናቫይረስ ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን አብዝቶ የሚገድለው ለምንድን ነው?
  9. አዲስ አበባ ውስጥ 31 ሰዎች በአንድ ቦታ ጫት ሲቅሙ ተያዙ

    የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አርማ

    የፎቶው ባለመብት, AAPC

    የኮሮናቫይረስ ለመከላከል የወጣውን ደንብ ተላልፈው በአንድ ቦታ በመሰብሰብ ጫት ሲቅሙ የነበሩ 31 ሰዎችን መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

    በአገሪቱ በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት ከአራት ሰው በላይ በአንድ ቦታ መሰብሰብ የተከለከለ ሲሆን ግለሰቦቹ የተያዙት ይህንን ደንብ ተላልፈው ነው ተብሏል።

    ሰላሳ አንዱ ሰዎች የተያዙት ለገሀር አካበቢ በሚገኝ አንድ ታዋቂ የጫት መቃሚያ ቤት ውስጥ ሲሆን ተጨማሪ የጫት መቃሚያ ቤቶች መታሸጋቸውን ፖሊስ ገልጿል።

  10. የዓለም ጤና ድርጅት ወባን በሚመለከት አስጠነቀቀ

    የወባ መከላከያ አጎበር ስርጭት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሊስተጓጎል ይችላል የሚል ፍራቻ አለ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የዓለም ጤና ድርጅት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በወባ የሚሞቱ ሰዎች በእጥፍ ሊጨምር ይችላል ሲል አስጠነቀቀ።

    ድርጅቱ ባጠናው አዲስ ጥናት በዚህ የፈረንጆች ዓመት የመከላከያ አጎበርና የመድሃኒት አቅርቦት ላይ መደናቀፍ ከተፈጠረ 760,000 ሰዎች ይሞታሉ ብሏል።

    ይህ የዓለም ጤና ድርጅት ማስጠንቀቂያ እንደሚለው አህጉሪቱ የዛሬ 20 ዓመት በወባ ምክንያት ያጣቻቸውን ሰዎች የሚስተካከል ሰው ልታጣ ትችላለች ብሏል።

    አፍሪካ ከዚህ ቀደም በየዓመቱ 400 000 ያህል ሰዎች በወባ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ። ነገር ግን በአሁን ሰዓት ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አገራት ድንበራቸውን ዘግተዋል፤ የአውሮፕላን በረራዎች ተቋርጠዋል እንዲሁም በከተሞች የሚደረጉ እንቅስቃሴ ተገድቧል። ይህም የወባ መከላከል ስራው ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥር ተሰግቷል።

    ድርጅቱ አገራት በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዝቅተኛ በሆነበት በዚህ ወቅት የወባ መከላከያና ለሕክምና የሚያገለግሉ ቁሶችን እንዲያቀርቡ ጠይቋል።

  11. በዩናትድ ኪንግደም በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 16,786 ደረሰ

    በእንግሊዝ አንድ አምቡላንስ ህሙማንን ሲወስድ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዩናይትድ ኪንግደም ባለፉት 24 ሰዓታት የሞቱት ሰዎች 514 መሆናቸው ተገለፀ። ይህም በአጠቃላይ በአገሪቱ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥርን 16,786 አድርሶታል።

    እነዚህ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች እድሜያቸው ከ37 እስከ 92 ድረስ መሆኑም ተገልጿል።

    በተጨማሪም በአገሪቱ በኮሮናቫይረስ ተይዘው የታመሙ ሰዎች እድሜያቸው ከ31 እስከ 100 ድረስ መሆኑ ይፋ ሆኗል።

  12. የማሪያ ማኬባ ዘፈን ኮሮናን ለመታገል ዋለ

    ሚሪያም ማኬባ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የደቡብ አፍሪካ ጨቋኝ የአፓርታይድ አገዛዝ ወቅትን በመታገል ስመ ጥር የሆነችው የነፃነት ታጋይና ሙዚቀኛዋ ማሪያ ማኬባ 'ፓታ ፓታ' የተሰኘው ሙዚቃዋ ኮሮናን ለመታገል ዋለ።

    ዘፈኑ ላይ አዳዲስ ግጥሞችን በመጨመር እንደገና የተለቀቀ ሲሆን የኮሮና ቫይረስ መዛመትን ለመታገል ለማነሳሳትም አልሟል።

    አዲሱንም ሙዚቃ ቤኒናዊቷ ሙዚቀኛ አንጀሊክ ኪጆ የተጫወተችው ሲሆን፣ እጅ መታጠብን እንዲሁም አካላዊ ርቀትን የሚያበረታቱ ስንኞችንም አካቷል።

    "ጊዜው የመቀመጥ ነው፣ ቤት ተቀምጠን እናሳልፈው፣ መነካካት አያስፈልግም" የሚሉም ግጥሞች ተካትተውበታል።

    የዘፈኑን መለቀቅ ያስተባበረው የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት ኤጀንሲ በመላው አፍሪካ ሙዚቃው እንደሚጫወት አስታውቋል።

    "ፓታ ፓታ ጭቆናን ለሚታገሉ ህዝቦች በሙሉ መነሳሳትን ችሯቸዋል። በዚህም ወቅት የትግልን መንፈስ እንደሚያመጣ ተስፋ አለኝ። በያለንበትም ሆነን አብረን እንደንሳለን" ብላለች አንጀሊክ ኪጆ።

    ፓታ ፓታ ደስታን የሚለግስ ቢሆንም ጭቆናን የሚፀየፍ ነው።

    ከአስራ ሁለት አመታት በፊት በ76 አመቷ ህይወቷ ያለፈው ማሪያ ማኬባ የአፓርታይድን አገዛዝ ለመታገል በርካታ የፖለቲካ ዘፈኖችን አቀንቅናለች።

  13. በቺካጎ የኢትዮጵያውያን ማኅበር መስራች አቶ መንግሥቴ አስረሴ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው አለፈ

  14. በናይጄሪያ ከአንድ ግዛት ወደሌላው የሚደረግ ጉዞ ታገደ

    አሁን የ36 ግዛቶች አስተዳዳሪዎች በጋራ ተስማምተው የወሰኑት የእንቅስቃሴ ገደብ አገሪቱን ሙሉ በሙሉ ከእንቅስቃሴ ውጪ ሊያደርጋት ይችላል ተብሏል።

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የናይጄሪያ 36 ግዛቶች አስተዳዳሪዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭት ለመከላከል ለሁለት ሳምንት ያህል ከአንድ ግዛት ወደ ሌላ ግዛት የሚደረግ እንቅስቃሴን አገዱ።

    የግዛቶቹ አስተዳዳሪዎች በጋራ ያወጡት መግለጫ እንደሚለው አስፈላጊ የሆነ አገልግሎት ብቻ ከግዛት ወደ ግዛት እንዲንቀሳቀስ ይፈቀድለታል።

    በናይጄሪያ ከ36ቱ ግዛቶች በ25ቱ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

    በአፍሪካ በሕዝብ ብዛቷ ቀዳሚ የሆነችው ናይጄሪያ እስከአሁን ድረስ ከ800 በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የመዘገበች ሲሆን፤ በዚህ ሳምንትም የእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች በሚገኙበት ግዛትም አዲስ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አግኝታለች።

    ከዚህ ውሳኔ በፊት አቡጃ፣ ሌጎስና ኦጉን የተሰኙት ከተሞች ላለፉት አራት ሳምንታት ከእንቅስቃሴ ታግደው የቆዩ ሲሆን በቀጣይ ሁለት ሳምንትም ይኸው እንዲቀጥል መወሰኑ ተሰምቷል።

    ይህ የእንቅስቃሴ ገደብ ሌሎች ግዛቶችንም እንዲያካትት ይደረጋል የሚል ጥርጣሬ ያለ ሲሆን ካኖ የተሰኘችው ግዛት የናይጄሪያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማዕከል እንዳትሆን ስጋት አለ።

    ካኖ ግዛት እስካሁን ድረስ 73 ሰዎች መያዛቸውን የታወቀ ሲሆን ነገር ግን የኮሮና መመርመሪያ ሰራተኛው በቫይረሱ በመያዙ የተቋረጠው ምርመራ ከተጀመረና ብዛት ያለው ሰው ከተመረመረ ይህ ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል የሚል ፍራቻ አለ።

    አሁን የ36 ግዛቶች አስተዳዳሪዎች በጋራ ተስማምተው የወሰኑት የእንቅስቃሴ ገደብ አገሪቱን ሙሉ በሙሉ ከእንቅስቃሴ ውጪ ሊያደርጋት ይችላል ተብሏል።

    በአጠቃላይ በአገሪቱ የሚኖርን የእንቅስቃሴ ገደብ ማወጅ የሚችሉት ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ ብቻ ናቸው።

  15. ተጨማሪ 4.4 ሚሊዮን አሜሪካውያን በኮሮና ምክንያት ስራቸውን አጡ

    ኮሮና በአሜሪካ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኮሮና ክፉኛ እየተመታች ባለችው አሜሪካ ተጨማሪ 4.4 ሚሊዮን አሜሪካውያን ስራቸውን ማጣታቸው ተገልጿል።

    ይህ ቁጥር በባለፈው ሳምንት የተመዘገበ ሲሆን፤ በኮሮና ምክንያት ስራ በማጣታቸውም ለመንግሥታቸውም አቤቱታ አቅርበዋል።

    በባለፉት አምስት ሳምንታት 20 ሚሊዮን አሜሪካውያን በኮሮና ምክንያት ከስራ ተሰናብተዋል። መንግሥትም ኮሮና ያስከተለውን የስራ አጥነት ቀውስ ለመፍታት በተለይም ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች የሚውል 349 ቢሊዮን ዶላር ልዩ በጀት መድቦ ነበር። ይህም ገንዘብ በሁለት ሳምንታት ውስጥ መጨረሱም ተዘግቧል።

    በአሜሪካ የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ 26́.4 ሚሊዮን አሜሪካውያን ከስራ ተሰናብተዋል፤ ይህም ቁጥር 15 በመቶ የሚሆነው የአገሪቷ የሰራተኛ ኃይል ነው ተብሏል።

  16. የአውሮፓ የሴቶች እግርኳስ ሻምፒዮና 2021 በአንድ አመት ተራዘመ

    ስታዲየም

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአውሮፓ የሴቶች እግር ኳስ ሻምፒዮና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ አመት ተራዘመ።

    ውድድሩ የፊታችን ሐምሌ ይደረጋል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም አሁን ግን በጎርጎሳውያኑ በ 2022 ጁላይ ወር ላይ 6-31 ድረስ ይካሄዳል ተብሏል።

    ውድድሩ በእንግሊዝ አዘጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን በዚህ የበጋ ወራት ሊካሄድ ከነበረውና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከተራዘመው የአውሮፓ ወንዶች ሻምፒዮና ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ይካሄዳል።

    በዚህ ውሳኔ መሰረት ሻምፒዮናው፣ የሴቶች እግር ኳስ ውድድርን ከሚያካትተው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ጋር በተመሳሳይ ወቅት አይካሄድም ማለት ነው።

  17. የእስራኤል ፖሊስ በዜጎች እንቅስቃሴ ላይ በስልክ የሚያደርገውን ክትትል አቋረጠ

  18. ትዊተር ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ በስልክ ማማዎች ላይ ጥቃት እንዲደርስ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን እሰርዛለሁ አለ

    የስልክ ማማ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/REUTERS

    ትዊተር ባልተረጋገጡ ወሬዎች የተነሳ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ መልዕክቶችን እንደሚሰርዝ አስታወቀ።

    ይህንን አቋሙን ያስታወቀው በዩናይትድ ኪንግደም ወረርሽኙን በማሰራጨት ረገድ የ5ጂ ኔትወርክ አስተዋጽኦ አለው በሚል የስልክ ማማዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ነው።

    ትዊተር አክሎም 5ጂ እና ኮሮናቫይረስን የተመለከቱ "ሀሰተኛ መረጃዎችን አላጠፋም" ነገር ግን ቀጥታ ጥቃት እንዲያደርሱ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን እሰርዛለሁ ብሏል።

    ትዊተር ይህንን ፖሊሲውን የሚያሳዩ ሁለት ምሳሌዎችን ጠቅሷል።

    5ጂ ኮሮናቫይረስን ያመጣል! በአቅራቢያችሁ የሚገኘውን የስልክ ማማ ሂዱና አውድሙ የሚል መልዕክት በፍጥነት የሚሰረዝ ቢሆንም “ መንግሥት ከአሁን በኋላ ምግብ አቅርቦት ለሁለት ወር አይኖርም ስላለ ወደ መደብር በፍጥነት ሄዳችሁ ግዙ” ብሎ የሚለጥፍ የትዊትር ተጠቃሚ ግን መልዕክቱ ሳይነካ ይቆያል ብሏል።

    ተመራማሪዎች ኮሮናቫይረስና 5ጂ ኔትወርክ ግንኙነት እንዳላቸው ተደርጎ የሚወራው፣ "ፍፁም እርባና ቢስ ነው” እንዲሁም በስነህይወታዊ መንገድም ግንኙነት የላቸውም ሲሉ አጣጥለውታል።

    በእንግሊዝ የሕክምና ዶክተር የሆኑት ስቴፈን ፖዊስ ይህ መሰረት የሌለው ወሬ “ የመጨረሻው ቀሽሙ ሐሰተኛ ዜና” ሲሉ ተናግረዋል።

  19. "በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ የዜጎች መብት መጣስ የለበትም" ኢሰመኮ

  20. የስፔን ህፃናት በቤታቸው አቅራቢያ እንዲጫወቱ ተፈቀደላቸው

    የሚጫወት ታዳጊ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በስፔን ለስድስት ሳምንት ከቆየው የእንቅስቃሴ ገደብ በኋላ ታዳጊዎች ከቤት ወጥተው መጫወት ተፈቀደላቸው።

    እድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ከቤታቸው ውጪ እንዲጫወቱ የተፈቀደ ሲሆን ይህ እንዴት እንደሚተገበር መመሪያ ተያይዞ ተላልፏል።

    መመሪያው ሶስት ሕጻናት ከአንድ አዋቂ ጋር በመሆን እንዲጫወቱ የሚፈቅድ ሲሆን የጨዋታ ጊዜውም ለአንድ ሰዓት ያህል ከመኖሪያ ቤታቸው በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ክልል ውስጥ ነው ተብሏል።

    ይህ 1-1-1 የተሰኘው ህግ በአፓርትመንት (በጋራ መኖሪያ ቤቶች) ውስጥ ለሚኖሩ ከ6.8 ሚሊዮን በላይ ስፔናውያን እፎይታ ነው።

    ሕጻናቱ መሯሯጥ፣ ኳስና አሻንጉሊት መያዝ እንዲሆን ስኩተር መጠቀም ተፈቅዶላቸዋል።

    ነገር ግን የሕዝብ መናፈሻዎችም ሆኑ የጋራ መጫወቻ ስፍራዎች አሁንም እንደተዘጉ ይቆያሉ።

    ስፔናውያን አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁም ተመክሯል።

    የስፔን መንግሥት መጀመሪያ ህጻናት ከወላጆቻቸው ጋር መደብር መሄድ የፈቀደ ቢሆንም ከበርካታ ፖለቲከኞችና ዜጎች በደረሰበት ትችት በቤታቸው አቅራቢያ እንዲጫወቱ ፈቅዷል።