በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሆነ

ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት የተነሳው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ስጋት መሆኑ ቀጥሎ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,501,156 ደርሷል።ኮሮናቫይረስ እስያን፣ አውሮፓን አሜሪካን አዳርሶ አሁን አፍሪካን ክፉኛ ያሰጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ምንም አንእኳ አገራት ቀድመው የተለያዩ እርምጃዎች ቢወስዱም የአፍሪካውያን አኗኗር ግን ጥግግት የበዛበትና አብዛኛውን ነገር በጋራ የመጠቀም ባህል ስር የሰደደ በመሆኑ ለቫይረሱ በቀላሉ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እዚህም እዚያም ይሰማል። እርስዎ ደህና ቤተሰብዎም ጤና እንዲሆኑ በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ሁሉ ይተግብሩ። መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል። የኮቪድ-19 የቀጥታ ዘገባችንን እዚህ ያገኛሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የእስልምና እምነት ተከታዮች ላልተለመደው የረመዳን ጾም ወር እየተዘጋጁ ነው

    መካ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የረመዳን ወር ሊጀምር የቀሩት ጥቂት ቀናት ናቸው። በዓለም ላይ የሚገኙ ሙስሊሞች ይህንን ወር አገራት ከጣሉት የእንቅስቃሴ ገደብና ማህበራዊና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አንጻር እንዴት አድርገው ማሳለፍ እንዳለባቸው እያሰቡ ነው።

    በረመዳን ወር ቀን ሲጾም ተውሎ ማታ ከቤተሰብና ከሌሎች ሙስሊም ወገኖች ጋር ሰብሰብ ብሎ ማፍጠር የተለመደ ነው። በርካቶች ምሽቱን አልያም ለሊት በጋራ የሚደረግ የፀሎት ስነስርዓትን ለመካፈል በመስጂዶች ይገኛሉ።

    ይህ ዓመት ግን እንደ ከዚህ በፊት እንደነበሩት ረመዳኖች ያለ አይደለም።

    በርካታ የሙስሊም አባቶችና ባለስልጣናት በረመዳን፣ ህዝበ ሙስሊሙ ከቤቱ ሆኖ እንዲፀልይ እና የአካላዊ ርቀቱን እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ለሳምንታት መካ ጭር ብሎ ታይቷል።

    በመካ ታላቁ መስጂድ ሙዘይን የሆኑት አሊ ሙላ መካን ያለ አማኘቹ ግርግር ሲመለከቱ " ልባችን ያለቅሳል" ሲሉ ተናግረዋል። " ቅዱሱ መስጂድ ቀን ማታ በሰዎች ተጨናንቆ ነበር የምናውቀው፤ አሁን ግን እንዲህ በመሆኑ ውስጤ ተሰብሯል"

  2. ቻይና ወደቀድሞ ህይወትዋ እየተመለሰች ነው

    ታላቁ የቻይና ግንብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቻይና ከሁለት ወር ላለፈ ጊዜ ዜጎቿ ቤታቸውን ከርችመው ከተቀመጡ በኋላ ህይወት ቀስ እያለ ወደ ነበረበት እየተመለሰ ይመስላል።

    እሁድ ዕለት ቤይዢንግ 73 ዋነኛ የቱሪስት መስህቦቿን ለእይታ ክፍት አድርጋለች። ከእነዚህ ክፍት የሆኑ ቦታዎች መካከል ታላቁ የቻይና ግንብ እንደሚገኝበት የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኀን ተናግረዋል።

    አሁን ክፍት የሆኑት የቱሪስት መስህቦች በሙሉ ከውጪ ሆነው የሚጎበኙ ሲሆኑ የከተማዋን 30 በመቶ ገቢ ይሸፍናሉ ተብሏል።

    የቤይዢንግ ቱሪዝም ቢሮ የጎብኚዎችም ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ዝቅ እንደሚል ተናግሯል።

    ሰዎች እንዲወጡና ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲቀላቀሉ የምታበረታታው ቤይዢንግ ብቻ ሳትሆን፣ ሻንጋይም ከግንቦት እስከ ሰኔ የለሊት ገበያዎች ዘመቻ ሊጀመር መሆኑን አስታውቃለች።

    ይህም መደብሮች እስከ እኩለ ሊት ድረስ ክፍት እንዲሆኑ ያበረታታል ተብሏል።

  3. 'ትኩስ ውሃ ቤትዎ ድረስ እናመጣለን'

    'ትኩስ ውሃ ቤትዎ ድረስ እናመጣለን'

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ጃፓን ውስጥ የሚገኝ አንድ ስፓ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በትኩስ ውሃ ሰውነታቸውን ለማፍታት መምጣት ላልቻሉ ደንበኞቹ አዲስ መላ ዘይዷል።

    ድርጅቱ 'ደንበኞቼ ሃሳብ አይግባችሁ ትኩስ ውሃ ቤታችሁ ድረስ አመጣለሁ' እያለ ነው።

    ፉኩያ የተሰኘው ይህ የስፓ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ከምንጭ ያገኘውን ውሃ በትልቅ 'ታንከር' አስጭኖ ወደ ደንበኞቹ ቤት እየገሰገሰ ነው።

    ጃፓኖች የምንጭ ውሃ ወደ ቤታቸው ሲያስልኩ አየርላንድ ውስጥ ደግሞ ጊነስ ቢራ እየተቸበቸበ ነው።

    በቢራ ጥም ጉሮሯቸው የደረቀ አየርላንዳውያን የጊነስ ድራፍት ቢራን እየኮመኮሙ ነው። ቢራው እንደተጠመቀ በፕላስቲክ ቡትሌ የደንበኞች በር ላይ ይቀመጣል።

    የጃፓኑ ትኩስ ውሃ ብዙም ንክኪ ስለሌው ተቃውሞ የገጠመው አይመስልም። የአየርላንድ ባለሥልጣናት ግን ኮሮናቫይረስ ደግሞ በቢራ እንዳይተላለፍ የሚል ስጋት ወጥሮ ይዟቸዋል።

  4. ሐሰተኛ ወሬዎችና ኮሮናቫይረስ

    ሞባይላቸው ላይ ያተኮሩ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በተለያዩ ወቅቶች ስለኤድስ የሐሰት ወሬዎች ተሰራጭተው አይተናል። የኤችአይቪ ቫይረስ በመንግሥት በቤተ ሙከራ ውስጥ ስለተፈጠረ፤ የኤችአይቪ ምርመራዎች እምነት የማይጣልባቸው ናቸው ሲባሉ ሰምተናል።

    አልፎ ተርፎም ሊታመን በማይችል መልኩ በሽታው በፍየል ወተት ሊታከም እንደሚችል በስፋት ሲነገር ነበር። ነገር ግን እነዚህ ሐሰተኛ መረጃዎች የሰዎችን ተጋላጭነት ከማስፋት ባሻገር ቀውሱን ያባብሳሉ።

    አሁን ደግሞ ተራው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነው። ከፌስቡክ እስከ ዋትስአፕ ድረስ ከወረርሽኙ አመጣጥ ጀምሮ እስከ መከላከያው ብዙ የተጋሩ የተሳሳቱ መረጃዎችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

    ከፀሐይ ብርሃን አስከ ሞቃት የአየር ሁኔታ እንዲሁም ትኩስ ውሃ መጠጣት የኮሮናቫይረስ መስፋፋት ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩበት የተነገሩ በርካታ ሐሰተኛ መረጃዎችን ቢቢሲ አጋልጧል።

    ከዚህ አንጻር በጣም መጥፎው ነገር የሚሰራጩት የሐሰት ወሬዎች ራሳቸው ጎጂ መሆናቸው ነው። ከወደ ኢራን የተገኘ አንድ ሪፖርት እንዳመለከተው ከኮቪድ-19 ያድናል በሚል ብዙዎች ጠንካራ አልኮል በመጠጣታቸው ምክንያት ሞተዋል። እንዴት ግን እራስዎን ከተሳሳተ መረጃ መጠበቅ ይችላሉ?

  5. አሜሪካና የኮሮና ወረርሽኝ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኮሮናቫይረስ በአሜሪካ ከ41 ሺህ በላይ ሰዎች መግደሉን የጆንስ ሆፕኪንስ አሁናዊ መረጃ ያሳያል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ተጠቅታ ከነበረችው ኒውዮርክ ተስፋ ሰጪ ነገር እየተሰማ ነው።

    የግዛቲቱ አስተዳዳሪ አንድሪው ኩሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጣሪያውን ማለፋቸውን ገልፀዋል።

    ከዚህ በኋላ በግዛቲቱ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መረጋጋት ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የአንዳንድ ግዛት አስተደዳሪዎች አሁንም ፍጥጫ ላይ ናቸው። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ግዛቶች ያስቀመጧቸውን ከቤት ያለመንቀሳቀስ እገዳን የሚቃወሙ ሰልፈኞች ትራምፕን ደግፈው ድምፃቸውን አሰምተዋል።

    በሚኒሶታ፣ ቨርጂኒያና ሚሺጋን ግዛቶች የተቀመጡትን ክልከላዎች ”በጣም ጠንካራ” ሲሉ ተችተው ነበር።

    የዋሺንግተን አስተዳዳሪ በበኩላቸው የፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚዎችን መደገፍ ”አደገኛ” ሲሉ ገልፀውታል።

    ትራምፕ የተለያዩ ግዛት አስተዳዳሪዎች የኮሮና መመርመሪያ መሳሪያ እጥረት እንዳለባቸው ቅሬታ ካሰሙ በኋላ በስም ያልገለፁት ኩባንያ 20 ሚሊዮን ናሙና መሰብሰቢያዎችን እንዲያመርት ሊያደርጉ መሆኑ ተሰምቷል።

  6. ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ የትኞቹ አገራት ኢኮኖሚያቸው በቶሎ ያንሰራራል?

    ሲያትል

    የፎቶው ባለመብት, Getty

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አገራት ከበሽታ ጋር በሚያደርጉት ትግል በዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ አለመረጋጋትን ፈጥሯል። ከዚህ አንጻር ከወረርሽኙ በኋላ የትኞቹ አገራት በተሻለ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንደሚመለሱ ባለሙያዎች ለመገምገም ሞክረዋል።

    ይህንን በተሻለ ለመረዳት የኢንሹራንስ ኩባንያ የሆነው ኤፍ ኤም ግሎባል የ2019 ዓለም አገራት የምጣኔ ሃብት ፈተናን የመቋቋም አቅም አመላካች ደረጃን ተመለከትን።

    በዚህም አገራት ለቫይረሱ የሰጡትን የመጀመሪያ ምላሽ ከግምት በማስገባት ቀውሱን በተረጋጋ መንገድ የሚወጡበትን ሁኔታና የመቋቋም ዕድላቸው ተቃኝቷል። ማስፈንጠሪያውን በመጫን ያንብቡ

  7. ወደ ቢቢሲ አማርኛ ገጽ እንኳን ደህና መጡ

    ቢቢሲ አማርኛ በየዕለቱ ስለኮቪድ-19 የቀጥታ ዘገባ ወደሚያቀርብበት ገጽ እንኳን በደህና መጡ።

    ከአለማችን የተለያዩ አካባቢዎች ስለኮሮናቫይረስ ያሉ አዳዲስ መረጃዎችን አበይት አበይቶቹን እየመረጥን እናቀርባለን።

    • በአሜሪካ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር 40000 አልፏል።
    • በአውስትራሊያ ሲድኒ የተወሰኑ የባህር ዳርቻዎች ወደ ስራ እየተመለሱ ነው
    • ደቡብ ኮሪያ አካላዊ ርቀት ለቀጣዮቹ 15 ቀናት ተጠብቆ ይቆይ ብላለች
    • በላቲን አሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው። እስካሁን ድረስ 100000 ሰዎች ሲያዙ 5ሺህ ደግሞ ሞተዋል። ብራዚል ከሁሉም ከፍ ያለው ተጠቂ የሚገኝባት አገር ናት። እነዚህ ማልደን የቃኘናቸው ናቸው። አብራችሁን ዋሉ!