
የፎቶው ባለመብት, EPA
ፓኪስታን የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚል ከረመዳን ወር አስቀድማ በመስጂዶች ለፀሎት መሰባሰብ ላይ ጥላ የነበረውን እገዳ ከሀይማኖት አባቶች በመጣ ጫና ምክንያት አነሳች።
በረመዳን ወር ማታ ማታ ሙስሊሞች ለፀሎት በመስጂድ ይሰባሰባሉ።
የፓኪስታን መንግሥት ከሃይማኖት አባቶች ጋር ባደረገው ስምምነት እድሜያቸው ከ50 በላይ የሆነ እና ሕጻናት እንዲሁም ጉንፋን ያዛቸው መስጂድ መግባት አይፈቀድላቸውም።
ሁሉም ምንጣፎች ተነስተው ወለሉ በፀረ ተዋህሲያን እንዲፀዳም ስምምነት ላይ ተደሰርሷል ተብሏል። ሙስሊሞች በመስጂድ ሲገኙ አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ እና መተቃቀፍና መሳሳም እንዲያስወግዱም ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
መንግሥት ከዚህች አንዷ እንኳ ዝንፍ ብትል መስጂዶቹን እስከመዝጋት የሚያደርስ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል አስጠንቅቋል።
በተጨማሪም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጨመረ ይህንን ውሳኔያቸውን ለማጤን እንደሚገደዱም ገልፀዋል።
የፓኪስታን ባለስልጣናት ለአርብ ፀሎት በመስጂድ መሰባሰብን ለማስቀረት የሰዓት እላፊና በመስጂድ የመሰባሰብ እገዳ ጥለው የቆዩ ቢሆንም ይህ ግን ተግባራዊ የሆነው በከፊል ነበር።