ማክሮን ቻይና ቫይረሱን ለመቆጣጠር በወሰደችው እርምጃ ላይ ጥያቄ አለኝ አሉ
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ቻይና የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በወሰደችው እርምጃ ላይ ጥያቄ እንዳላቸው ተናገሩ።
ማክሮን "እኛ የማናውቃቸው ነገሮች ተከስተዋል" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን ቻይና ቫይረሱን በተሻለ መንገድ ተቆጣጥረዋለች ብሎ ማሰቡ 'አለማወቅ' ነው ብለዋል።
ማክሮን ይህን አስተያያት የሰጡት በፈረንሳይ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ "ምዕራባውያን አገራት አዛውንቶች እንዲሞቱ በመጦሪያ ቤቶች ውስጥ ጥለዋቸዋል" የሚል ሃሳብ ያዘለ ጽሑፍ ማውጣቱን ተከትሎ ነው።
የፈረንሳይ መንግሥት የውጪ ጉዳይ ሚንስትር በጽሑፍ ቅሬታቸው ለማቅረብ የቻይናውን አምባሳደር አስጠርተው ነበር።
ቻይና በበኩሏ በኤምባሲው የወጣው ጽሑፍ በስህተት መሆኑን እና ፈረንሳይ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ስለምትወስዳቸው ተግባራት አሉታዊ አስተያየት አትሰጥም ብለዋል።
"እርግጠኛ የማንሆንባቸው ነገሮች አሉ። ስለተከሰቱ ጉዳዮች በትክክል የማናውቃቸው ነገሮች አሉ" ብለዋል ማክሮን።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዶሚኒክ ራብ ሐሙስ ዕለት ቫይረሱ እንዴት እንደጀመረ እና በፍጥነት ስርጭቱን እንዴት ማስቆም እንዳልተቻለ "ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች መጠየቅ አለባቸው" ብለዋል።
ፕሬደንት ትራምፕ በበኩላቸው በቻይና በቫይረሱ ስለተያዙ እና ስለሞቱ ሰዎች ቁጥር የተሰጠው ቁጥር ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በቫይረሱ ዉሃን ከሚገኝ ላብራቶሪ ነው ያመለጠው ስለሚባለው ያልተረጋገጠ ሪፖርት አሜሪካ እንምታጣራ ተናግረዋል።