ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የፈረንጆቹ በጋ የቫይረሱን ሥርጭት ይገታው ይሆን?
ኮቪድ-19 የጀመረ ሰሞን ይሄ ቫይረስ ሙቀት አይስማማውም ሲባል ነበር። ከጤና አማካሪዎቻቸውም በላይ በኅብረተሰብ ጤና ጉዳይ እንደ ሳይንቲስት የሚያደርጋቸው ዶናልድ ትራምፕ እንዲያውም "በጋ ይግባ እንጂ ሙቀት ቫይረሱን አፈር ድሜ ያበላዋል" ሲሉ ነበር።
እውን የቫይረሱ ሥርጭት በሙቀት ወራት ይገታ ይሆን?
ሳይንቲስቶች ይህን ጥያቄ አፍ ሞልቶ ለመመለስ ጊዜው ገና ነው ይላሉ።
ይህ ቫይረስ ወቅት ይመርጣል አይመርጥም ጥናት ይሻል። ጥናቱን ለማድረግ ገና ወቅቶቹ ራሳቸው አልገቡም፤ በተለይ በአንድ አካባቢ በተለያየ ወቅት ኮቪድ-19 ምን የተለየ ባህሪ አለው የሚለውን ለማጥናት።
ምልክቶችን ለማየትም በተለያዩ አካባቢዎች በሽታው ያሳየው ባሕሪ በስፋት መጠናት ይኖርበታል።
ይህ ማለት ግን እስካሁን በዚህ ረገድ የተገኙ ምንም መረጃዎች የሉም ማለት አይደለም።
አንጀት የሚያርሱ ባይሆኑም ኮቪድ-19 ለቀዝቃዛና ደረቅ አየር እጅ እንደማይሰጥ ከወዲሁ ምልክቶች ታይተዋል።
አንድ ጥናት አማካይ ሙቀታቸው ዝቅ ያሉ አካባቢዎች ቫይረሱ ሥርጭቱ ብርቱ እንደነበር አመላክቷል።
ሌላ የጥናት ወረቀት ደግሞ በመቶ የቻይና ከተሞች የቫይረሱን ባህሪ የተመለከተ ሆኖ ውጤቱም ከፍተኛ የአየር ሙቀትና የእርጥበት መጠን (ሂሙዩዲቲ) ያለባቸው ቦታዎች ሥርጭቱ አዝጋሚ ሆኖ ታይቷል።
ተጨማሪ የጥናት ወረቀት (ምንም እንኳ ይህኛው ጥናት የተጓዳኝ ባለሞያ ግምገማ ገና ያልተደረገበት ቢሆንም) የሚከለተውን የድምዳሜ አንቀጽ ይዟል።
"ኮቪድ-19 በሁሉም የዓለም ክፍል በተለያዩ የአየር ጠባዮች መሠራጨቱ እሙን ቢሆንም ቀዝቃዛና ደረቅ የአየር ሁኔታ ባለባቸው ቦታዎች ግስጋሴው ኃያል ነበር።"
እርግጥ ነው የስርጭት ፍጥነቱና ስፋቱ ቢለያይም ኮቪድ እስካሁን ባሳየው ጉልበት በየትኛውም የወበቅ/እርጥበት (ሂይሙዩዲቲ) ሁኔታ፣ በየትኛውም የአየር ንብረትና በየትኛውም የዓለም ክፍል ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ እንደሚችል ተረጋግጧል።
በሌላ ቋንቋ ቫይረሱን ይህ የአየር ንብረት ይበግረዋል፤ አይበግረውም የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር ነው የሚሆነው።
ለጊዜው ቫይረሱንና የአየር ንብረትን ጉዳይ አድርገን ስናወራ የምናወራው ስለ ሥርጭት ፍጥነት ብቻ የሚሆነውም ለዚሁ ነው።
በሰሜንና በደቡብ እኩል አይሰራጭ ይሆን?
ጉንፋንን ጨምሮ በርካታ የቫይረስ በሽታዎች በሰሜንና በደቡብ ንፍቀ ክበብ እኩል የሥርጭት መልክና ባህሪ እንደሌላቸው ከዚህ ቀደም የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
ነገር ግን በምድር ወገብ አካባቢ ያሉትና በተለይም ቆላማ አካባቢዎች ከሌሎች የትሮፒካል አየር ከሌላቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ የሥርጭት መልክ ኖሯቸው አያውቅም።
ያም ሆኖ እንደ ማሌዢያና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ያሉ በምድር ወገብ ቀበቶ ሥር ያሉ አገራት ሞቃትና ወበቃማ-እርጥበት አዘል አየር ቢኖራቸውም ኮቪድ-19 ደፍሯቸዋል። የስርጭት መጠናቸው ስለሚለያይ ሁለቱ አገራትን ብቻ ወስዶ ድምዳሜ ላይ መድረስ ያዳግታል።
ወደ ደቡብ ንፍቀ ክበብ ስናማትር የምናገኘው አውስትራሊያንና ኒውዚላንድን ነው። ቫይረሱ ሲገባ እነሱ የበጋ ወራቸውን በማገባደድ ላይ ነበሩ።
በዚያ ወቅት ከሰሜኑ ንፍቀ ክበብ በተነጻጻሪ በኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ አካባቢ የወረርሽኙ ሥርጭት የተገደበ ነበር ማለት ይቻላል።
ነገር ግን የአየር ንብረትና የአገሮቹ መገኛ ብቻውን ሁሉን ነገር አይወስንም። ለምሳሌ ወደዚያ አገር የገቡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ብዛትና የሰዎች የጥግግት መጠን፣ እንዲሁም የአኗኗር ሁኔታ፣ የጤና አጠባበቅ ወዘተ ወሳኝ ነገሮች ናቸው።
በተለይም ቫይረሱ ሰዎች ከአገር አገር እየተዘዋወሩ ስላሰራጩት የአየር ንብረት ከቫይረሱ ጋር ያለውን ተዛምዶ ነጥሎ ለማጥናት ፈታኝ ያደርገዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ ቫይረሶች ባሕሪ ምን ያሳያል?
ኮሮናቫይረስ የቫይረሶች የወል ስም ነው። ኮቪድ-19 በሽታው ነው። ይህንን በሽታ የሚያመጣው ደግሞ ሳርስ-ኮቭ-2 የተባለ ቫይረስ ነው።
ኮቪድ-19 ከነሳርስ እና ሜርስ ጋር ተቀራራቢ ባህሪ ያለው ቫይረስ ነው። እነዚያ የኮሮናቫይረስ አባላት ያሳዩት ባህሪ ስለ ኮቪድ-19 የሚነግረን ነገር ይኖር ይሆናል።
የለንደን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ሳይንቲስቶች ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ኮሮናቫይረሶች በክረምት ስርጭታቸው ከፍተኛ እንደነበር ደርሰውበታል።
ከ2 ሺህ በላይ ሰዎችን ባካተተው በዚህ ጥናታቸው ከጉሮሮ በሚወሰድ ናሙና የደረሱበት ነገር ቢኖር ኮቪድ-19 ከመከሰቱ በፊት በነበሩ ኮሮናቫይረሶች የበሽታው የክረምት ስርጭት ከበጋው በእጅጉ የፈጠነ እንደሆነ አውቀዋል።
ከሳይንቲስቶቹ አንዷ ኤለን ፍርንጋዚ እንደምትለው ከዚህ በመነሳት ኮቪድ-19 በበጋው ወቅት ትንሽ እፎይታ ሊሰጠን ይችል ይሆናል ስትል ግምቷን ለቢቢሲ ተናግራለች።
ሆኖም ግን ትላለች ዶ/ር ኤለን፤ ምናልባት ኮቪድ-19 ባህሪው ከዚህ ቀደም ካሉት ተመሳሳይ ቫይረሶች በአንዳንድ ነገሩ የተለየ ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት የለብንም።
በሌላ በኩል በሽታው በስፋት በመላው ዓለም ስለተሰራጨና የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሲታይ ብዙም ተስፋ ማድረግ ላያስፈልግ ይችላል ስትል ትደመድማለች።
በሳውዝሀምፕተን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ማይክል እንደሚሉት ደግሞ ኮቪድ-19 በአፈጣጠሩ ከሌሎች የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች ተቀራራቢ ይሁን እንጂ የሚያድግበትና የሚሰራጭበት ፍጥነት እንዲሁም ያደረሰው ጥፋት ከሌሎች ኮሮናቫይረሶች ጋር አያገናኘውም።
ሆኖም ለአየር ንብረት ወቅቶች የሚያሳየው ባህሪ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።
የጥናት ወረቀቶች እየወጡ ነው። ዞሮ ዞሮ ኮቪድ-19 በአየር ንብረት መለወጥ አልያም በፈረንጆች በጋ ሊገታ ይችል እንደሆነ በጥቂት ወራት ውስጥ የምናየው ይሆናል።