የኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ በሆነቸው ባህር ዳር ያለውን የፋሲካ በዓል የገበያ ሁኔታ ለመቃኘት የቢቢሲ ሪፖርተር በከተማዋ የተለያዩ የገበያ ቦታዎች ተዘዋውሯል።
በባህር ዳር ለሁለት ሳምንት ያህል በሰውም ሆነ በተሽከርካሪ እንቅስቀሴ ላይ የተጣለው እገዳ ከተነሳ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑ ነው።
ከእገዳው በፊት ከነበረው በተሻለ ብዙ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ለብሰው ይንቀሳቀሳሉ። በታክሲዎችም ሆነ በባጃጆች የሚጫነው የሰው ቁጥር በግማሽ ቀንሷል።
በዋናው የገበያ ቦታ እንደዚህ ቀደሙ የሰው ቁጥር በብዛት ባይኖርም የበዓል ግብይቱ ግን ሞቅ ብሏል።
በተለይ ለበዓል የሚሆኑ ነገሮች የሚሸጡበት አካባቢ ያለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ነው። ዶሮ፣ እንቁላል፣ በግ እና ቅቤ መሸጫዎች ደግሞ ብዙ ሰዎች የተገኙበት ነው።
በዋናው ገበያ እንደዚህ ቀደሙ መግቢያ መውጫዎቹ ላይ የነበሩ ነጋዴዎች ወደ ገበያው መሃል እንዲገቡ ተደርጓል።
ነጋዴዎቹ በሚቀመጡበት መካከል ለመንቀሳቀስ የሚያስችል መንገድ ቢኖርም ነጋዴዎቹ እርስ በርስ ተጣብቀው በሚባል ደረጃ ነው የተቀመጡት።
በከተማዋ የፊት እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ያደረጉ ሰዎች ቁጥር ከፍ ቢልም በተለይ ነጋዴዎች ይህንን ሲያደርጉ ብዙም አይስተዋልም።
በተለይም አነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ እና ቁጭ ብለው በሚነግዱ ሰዎችና ቆመው በሚገዙት መካከል የመጠበቅ ነገር ብዙም ስለማይታይ የትንፋሽ ልውውጥ የመኖር ዕድሉ ከፍ ይላል።
አንዳንድ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች የያዙትን ዕቃ ሸጠው ከመጨረሳቸው የተነሳ መደርደሪያቸው ባዶ ሆኖ ይታያል።
ነጋዴዎቹም ሰዉ የሚገዛውን ነገር ማወቅ ባለመቻላቸው መያዝ ያለባቸውን ዕቃ እንዳያውቁ እና ከአዲስ አበባ የሚጫንላቸው ዕቃ መቀነሱን በስፍራው ለተገኘው የቢቢሲ ሪፖርተር ነግረውታል።
በከተማው የመንገድ ላይ ንግድ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያለው ትርምስ እንደዚህ ቀደሙ ባይሆንም አሁንም ንግዱ ከመቀጠሉም በላይ ጥንቃቄ የጎደለው ጭምር ነው።
የጀበና ቡና የሚሸጡ ሴቶች በገበያ ቦታዎቹ በብዛት ያሉ ሲሆን ቡናዎቹን የሚሸጡባቸው ሲኒዎችን ብዙዎች ስለሚጋሩት በንጽህናው ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል።
የክልሉ መንግሥት የገበያ ቦታዎች ቁጥርን በማስፋት ጥግግቱን በመበተን የበግ፣ የፍየል፣ የከብትና ዶሮ አነስተኛ ገበያ በማመቻቸት፣ የቤት ለቤት አቅርቦት ላይ እየሠራ መሆኑን አስታውቆ ነበር።
በሁሉም የገበያ ስፍራዎች የሚደረገው ግብይት ላይ የሚስተዋለው ሌላ የጋራ ጉዳይ የወረቀት ገንዘብ ልውውጡ አሁንም ከፍተኛ መሆኑ ነው።