በዓለም ላይ ያሉ የኦሮቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓል አከባበር

በዛሬው ዕለት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የትንሳኤ በዓል ይከበራል። በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ አብይ በሆነው የትንሳኤ በዓል ብዙ ኢትዮጵያዊ በጉንም፣ ዶሮውን በቻለው አቅሙ ያርዳል። ዘመድ ለዘመድ መጠያየቅም ሆነ ከጎረቤት ጋር በአንድ ማዕድ መቋደስ፣ መጎራረረስ የበዓሉ አንድ ኣካል ነው። የኮሮናቫይረስ ስጋት ለዓለም ጠንቅ በሆነበት በዚህ ወቅት ከንክኪ ጋር የተገናኙ ልማዶችን ማስቀረት እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በተቻለ መጠን ሰብሰብ ብሎ በዓሉን ከማክበር መታቀብም ይመከራል። በሽታውን አካላዊ ርቀታችንን በመጠበቅ፣ መሰባሰባችንን በመቀነስ፣ እጃችንን በሚገባ በመታጠብ እንከላከል። መልካም የትንሳኤ በዓል እንዲሆን እየተመኘን የቀጥታ ዘገባችንን ከዚህ ገጽ ላይ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. "ክትባት ካልተገኘ በስተቀር የኦሊምፒክ ውድድር ላይካሄድ ይችላል"

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ወደ ቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት የተሸጋገረው የኦሊምፒክ ውድድር የመካሄዱ ነገር አጠራጣሪ እንደሆነ ተነገረ።

    በዓለማችን ካሉ ቀዳሚ የጤና ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ዴቪ ስሪድሃራ እንደተናገሩት አስከ ውድድሩ መካሄጃ ጊዜ ድርስ የኮሮናቫይረስ ክትባት ካልተገኘ የቶኪዮው ኦሊምፒክ ሊካሄድ ይችላል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።

    በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች ከተቋረጡ ወራት ተቆጥረዋል። በተጨማሪም በመጪዎቹ ወራት ይካሄዳሉ ተብለው የታቀዱ ውድድሮችም ተሰርዘዋል።

    የስፖርት ባላስልጣናት የዚህ ዓመት መረሃ ግብሮቻቸውን መቼ ማጠናቀቅ እንደሚችሉና ቀጣይ የሚደረጉ ውድድሮች መቼ ሊካሄዱ እንደሚችሉ ከወዲሁ እየመከሩ ነው።

  2. ከኮሮናቫይረስ የዳኑ ሰዎች ቁጥር ከ570 ሺህ በላይ ደረሰ

    በኮሮናቫይረስ እስካሁን ከተያዙት ሰዎች መካካል ከ570 ሺህ የሚበልጡት ከበሽታው መዳናቸውን ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰበ መረጃ አመለከተ።

    ከ185 አገራትና ግዛቶች በተሰባሰበው መረጃ መሰረት 570 ሺህ 716 ሰዎች እስካሁን ድረስ ከኮሮናቫይረስ በሽታ መዳናቸው ተረጋግጧል፤ ከዚህም በኋላ ከበሽታው የሚያገግሙ ሰዎች አሃዝ እንደሚጨምር ይጠበቃል።

    የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ በሽታው ከተመዘገበባቸው የዓለም አገራት የሚያሰባስበው መረጃ እንዳመለከተው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከበሽታው ድነዋል።

    ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ከበሽታው የዳነባት አገር ጀርመን ስትሆን 77 ሺህ 578 ሰዎች ማገገማቸው ተዘግቧል። ትናንት የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር እንዳስታወቁት ጀርመን በሽታውን ለመቆጣጠር በመቻሏ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በጣም ቀንሷል።

    በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ደግሞ በሽታው የተቀሰባት ቻይና ስትሆን 74 ሺህ 797 ሰዎች ከኮሮናቫይረስ አገግመዋል። ቻይና በሽታውን መስፋፋት በመቆጣጠር በኩል ስኬታማ እንደሆነች ይነግርላታል።

    በሦስተኛ ደረጃ በርካታ ሰዎች ከወረርሽኙ ያገገሙባት አገር አውሮፓዊቷ ስፔን ስትሆን 59 ሺህ 672 ሰዎች ድነዋል። ስፔን አውሮፓ ውስጥ በበሽታው ክፉኛ ከተጠቁት አገራት መካከል አንዷ ናት።

    በኢትዮጵያም እስካሁን ድረስ በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጡት 105 ሰዎች መካከል 16ቱ ከበሽታው መዳናቸውን የጤና ሚኒስቴርና መረጃ አመልክቷል።

    እስካሁን በዓለም ላይ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡት ሰዎች አሃዝ ከ2 ሚሊዮን 250 ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን ቁጥሩ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።

  3. ከንቲባው መንገድ ላይ ቢራ በመጠጣታቸው በፖሊስ ተቀጡ

    በአውስትራሊያዋ ግዛት ቪክቶሪያ ውስጥ የምትገኝ የአንዲት ከተማ ከንቲባ የሆኑት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተጣለውን ዕገዳ ተላልፈው በጎዳና ላይ ቢራ ሲጠጡ የሚያሳይ ፎቶ በመውጣቱ ተቀጡ።

    ዋርናምቡል የተባለችው ከተማ አስተዳዳሪው ቶኒ ኽርበርት ከአንድ ሆቴል ውጪ ከሌሎች ሦስት ሰዎች ጋር ሆነው የሚያሳይ ፎቶ ነው እንደማስረጃ የቀረበባቸው።

    ፎቶግራፉ በአንድ መንገደኛ የተነሳ ሲሆን ከንቲባው መንግሥት ከሰጣቸው መኪና ጎን ሆነው ቢራቸውን ሲጎነጩ የሚያሳይ ነው።

    ከንቲባው መንገድ ላይ ቢራ ሲጠጡ የሚያሳየው ፎቶ ከመነሳቱ ከሰዓታት በፊት የከተማቸው ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ የሚጠይቅ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

    የወረርሽኙን መስፋፋት ለመግታት የወጣውን አካላዊ ርቀት የመጠበቅ ግዴታን ባለማክበራቸው የግዛቲቱ ፖሊስ ከንቲባውን ከአንድ ሺህ ዶላር በላይ መቀጮ ጥሎባቸዋል።

    ከንቲባው ስህተት መፈጸማቸውን አምነው ይቅርታ ጠይቀዋል። ነገር ግን ያገኟቸው ሰዎች የከተማዋ ነጋዴዎች ሲሆኑ በሥራ ኃላፊነታቸው ምክንያት እንደተገናኙም ተናግረዋል።

    "ሳላስበው ህበረሰቡን ለመጠበቅ የወጣውን ደንብ በመተላለፌ፤ ለድርጊቴ በእውነት ይቀርታ እጠይቃለሁ” ሲሉ መጸጸታቸውን ገልጸዋል።

    ፖሊስ እንዳለው ከከንቲባው ጋር የነበሩት ሦስቱ ሰዎችም የጤና ባለስልጣናት ያወጡትን ደንብ በመተላለፍ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።

  4. በእንስሳት ገበያ ውስጥ ማድረግ ያሉብን ጥንቃቄዎች

    ዛሬ የፋሲካ በዓል ዋዜማ ነው በርካታ ሰዎች ለበዓሉ የሚሆኑ ነገሮችን ለመሸማመት ወደ ተለያዩ ገበያዎች ያቀናሉ። በተለይ የእንስሳት ገበያው ከሌሎቹ በተለየ በርካታ ሰው የሚገኝበት እንደሆነ ይታወቃል።

    ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ስጋት የገበያተኛው መጠን ላይ መቀነስ ሊያጋጥም ይችል ይሆናል እንጂ በገበያዎች አካባቢ የተለመደው የሰዎች ብዛትና ግርግር መኖሩ እንደማይቀር ባለፉት ሁለት ቀናት የቢቢሲ ዘጋቢዎች በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች የታዘቡት ክስተት ያመለክታተል።

    ከበዓሉ ጋር በተያያዘ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በእንስሳት ግብይት፣ እርድ፣ በምግብ ዝግጅትና አጠቃቀም እንዲሁም ከእንሰሳት አያያዝ እና እንክብካቤ አኳያ መደረግ ያለበትን ጥንቃቄን በተመለከተ የግብርና ሚኒስቴር መልዕክት አስተላልፏል።

    1. በገበያ ቦታና በግብይት ወቅት መደረግ ያለባቸዉ ጥንቃቄዎች

    • ርቀትን ጠብቆ መገበያየት

    • ከእንስሳት ጋር የሚኖር ንክኪ መቀነስ

    • የሽያጭ ገንዘብ ቅብብሎሽ የመጨረሻ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በገዥና ሻጭ መካከል ብቻ ቢወሰን

    • በገበያ ቦታዎች ለእጅ ማጽጃ ውሃና ሳሙና እንዲሁም ሳኒታይዘር መጠቀም

    • ነጋዴዎችና ሸማቾች ጭንብልና የእጅ ጓንት እንዲያደርጉ

    • የቁም እንስሳት መገበያያ ቦታዎ እንስሳቶች ከመግባታቸው በፊት በፀረ ተህዋስ ኬሚካል ማጽዳት

    • ሻጮች እና ረዳታቸው የእጅ ጓንት እና ጭንብል (ማስክ) ማድረግ አለባቸው

    • ወደ እንስሳ መገበያያ ማዕከል የሚገቡ እና የሚወጡ እጆቻቸውን በውሃና በሳሙና እንዲታጠቡ ማድረግ

    በዛሬው የገበያ ውሏችን መከተል ካለብን የጥንቃቄ እርምጃዎች መካከል እንዚህን በመተግበር እራሳችንንና ሌሎችን ከበሽታ ጠበቅ ይገባናል። መልካም በዓል!

  5. በአንድ ቀን ከ5 ሺህ በላይ ሞት ያስመዘገበችው አገር

  6. ኢንሹራንስና ቤት ለኮሮናቫይረስ ጤና አገልግሎት ሰጪዎች

    ከሰሞኑም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ድጋፍ ሰጪ አካላትም ሆነ የጤና ባለሙያዎች በኢንሹራንስ እንዲሸፈኑ ውሳኔ ላይ ደርሷል።

    ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎኞች ለስድስት ወር ያህል የኢንሹራንስ ሽፋን ለመስጠት ስምምነት ላይ መደረሱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።

    ኢንሹራንሱ ዶክተሮችና ነርሶችን ብቻ ሳይሆን በፅዳት ላይ የተሰማሩ፣ የአምቡላንስ አሽከርካሪዎች ወይም ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር በቀጥታ የሚሰሩ ሠራተኞችን በሙሉ ይመለከታል። ዘርዝሩን ለማንበብ፡ ኢንሹራንስና ቤት ለኮሮናቫይረስ ጤና አገልግሎት ሰጪዎች

  7. በፌስቡክ በኩል የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን መቆጣጠር

    ስለኮሮናቫይረስ ሐሰተኛ መረጃ ያነበቡ፣ የተመለከቱ እንዲሁም መረጃውን ለሌላ ሰው ያጋሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ሊላክላቸው መሆኑን ፌስቡክ አስታውቋል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ የተሳሳቱ መረጃዎችን "infodemic" የሚል መጠሪያ ሰጥቷቸዋል።

    ፌስቡክም የእነዚህን ሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭትን ለመግታት ሲል አዲሱን አሠራር ተግባራዊ እንደሚያደርግ ጠቁሟል። አንድ ገለልተኛ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ከወረርሽኙ ጋር የተያያዙ ሐሰተኛ መረጃዎች በዋናነት የሚሰራጩት በፌስቡክ ነው።

    በተለይ በስፓኒሽ ቋንቋ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ። ፌስቡክ በበኩሉ ጥናቱ ድርጅቱ አሁን የሚገኝበትን ደረጃ አያሳይም ይላል። ተጨማሪ ለማንበብ፡ ፌስቡክ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ሐሰተኛ መረጃዎችን ሊጠቁም ነው

  8. የቅዳሜ ሚያዝያ 10/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    እንደምን አደራችሁ!

    ቅዳሜ ሚያዝያ 10/2012 ዓ.ም፤ የፋሲካ በዓል ዋዜማ።

    ቢቢሲ አማርኛ መልካም ዕለት እንዲሆንላችሁ እየተመኘ፤ የዕለቱን ከኢትዮጵያና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡ በኮሮናቫይረስ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ዜናና መረጃዎችን የሚያቀርብበትን የቀጥታ ዘገባ ገጽ እነሆ ጀመረ።

    የትናንት [አርብ] የቀጥታ ዘገባዎችን ለማንበብ ወደ ታች በመውረድ ይመልከቱ።

    መልካም የበዓል ዋዜማ!

  9. ሰው አንገላተዋል የተባሉ የላይቤሪያ ወታደሮች እየተመረመሩ ነው

    አንዲት ሴት ክንዷን በስለት መወጋቷን ተከትሎ ሦስት የላይቤሪያ ወታደሮች ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው።

    ወታደሮቹ የሁለት ሳምንት የእንቅስቃሴ ገደብን ተፈጻሚ ለማድረግ በመዲናዋ ሞንሮቪያ እየተዘዋወሩ ነበር።

    ጄነራል ፕሪንስ ጆንሰን ለቢቢሲ፤ “አሁን በሥራ ላይ ያለው ወታደራዊ ኃይል በጎ ነገር እንዲያደርግ የተሰማራ ነው። ደንብ ከጣሱ ግን አንታገስም” ብለዋል።

    ፕሬዘዳንት ጆርጅ ዊሀ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገጉት ከአስር ቀን በፊት ነበር። እንቅስቃሴ የመገደብ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ እየተሰራጩ የሚገኙ ምስሎች የጸጥታ ኃይሎች ዜጎችን ሲያንገላቱ ያሳያሉ።

  10. አሜሪካዊያን የእንቅስቃሴ እገዳው እንዲነሳላቸው በሰልፍ እየጠየቁ ነው

    አሜሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት በሽታውን ለመግታት በተጣለው የእንቅስቃሴ ዕቀባ ላይ የሚደረገው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በመላዋ አገሪቱ እየጨረ መጥቷል።

    እስካሁንም የተቃውሞ ሰልፎች በሚችጋን፣ በኦሃዮ፣ በሰሜን ላሮሊና፣ በዩታህ፣ በቨርጂኒያና በኬንተኪ ተካሂደዋል። በቀጣይ ቀናትም በሌሎች ግዛቶች ውስጥ ሰልፎች ይካሄዳሉ ተብሏል።

    የተቃውሞ ሰልፎቹ ተሳታፊዎች የእንቅስቃሴ ገደቡ በምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ የተነሳ ዜጎች እየተጎዱ መሆናቸውን ቢገልጹም፤ የጤና ባለስልጣናት ግን ገደቡ ከተነሳ በሽታው የበለጠ ሊዛመት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዋ እንድትመለስ ከፍ ያለ ፍላጎት እንዳለቸው በተደጋጋሚ ቢገልጹም የግዛቶች አስተዳዳሪዎች ግን ስለበሽታው የመስፋፋት ሁኔታ ከባለሙያዎች አስተማማኝ መረጃ ካላገኙ እገዳውን ለማላላት ፈቃደኝነት አላሳዩም።

    ፕሬዝዳንቱ ግን በቅርቡ የእንቅስቃሴ ገደቦቹ ተነስተው ወደ መደበኛ ተግባራት እንዲገባ ዕቅድ አውጥተው እየሰሩ መሆናቸውን አሳውቀዋል።

  11. አምነስቲ በጋና የተጨናነቁ መንደሮች መፍረሳቸውን ኮነነ

    በጋና መዲና አክራ ከሚገኙ የተጨናነቁ መንደሮች አንዱ መፍረሱን አምነስቲ አወገዘ።

    እንቅስቃሴ በተገታባት አገር ውስጥ መንደሩ በመፍረሱ ሳቢያ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት አልባ ይሆናሉ።

    ‘ኦልድ ፋዳማ’ በመባል የሚታወቀው መንደር የፈረሰው በመንግሥት ትዕዛዝ ሲሆን፤ አካባቢው የኤሌክትሮኒክስ ተረፈ ምርቶች የሚወገዱበት በመሆኑ ለአካባቢ ብክለት የተጋለጠ ነው።

    አምነስቲ ይህ መንደር መፍረሱን “ጊዜውን ያልጠበቀ እና ርህራሄ የሌለው” ሲል ተችቷል።

    መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚወስደው እርምጃ፤ ከሰብአዊ መብት ጋር የሚጣረስ መሆን እንደሌለበትም አምነስቲ ተናግሯል።

    ከሚኖሩበት ለተፈናቀሉ ዜጎች ማረፊያ እንዲዘጋጅና ከዚህ በኋላ ሌሎች የተጨናነቁ መንደሮች እንዳይፈርሱ ተጠይቋል።

    መንግሥት በበኩሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ አስተባባሪዎች መንደሩ እንዲፈርስ ተስማምተዋል ይላል።

    ጋና የኮቪድ-19ኝን ስርጭት ለመግታት ድንበሮቿን እንደዘጋች ናት።

    እስካሁን 641 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው፤ ስምንቱ ሕይወታቸው አልፏል።

  12. "ባለቤቴ ትናንት ነው የወለደችው፤ ቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ የለም" ቤት መቀመጥ በናይጄሪያ

    የናይጄሪያ ሁለተኛ ትልቋ ከተማ ካኖ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መዛመትን ለመቆጣጠር ለሰባት ቀናት ያህል አስገዳጁ የቤት መቀመጥ ትዕዛዝ ተላልፏል።

    ሃያ ሚሊዮን ያህል ህዝብ በሚኖርባት ይህች ከተማ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ለሆኑ ነዋሪዎች ውሳኔውን በረሃብ እንደማለቅ እያዩት ነው።

    "ባለቤቴ ትናንት ነው የወለደችው ቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ የለም። ወጥተንም ምግብ እንዳንፈልግ የትም እንዳትንቀሳቀሱ ተብለናል። የሚረዳንም የለም። ከዚህ የከፋ ምን አለ?" ብሏል አሮጌ እቃዎችን በመሸጥ የሚተዳደረው ያኩቡ አብዱ።

    ከአስከፊው ድህነት በተጨማሪ የእምነት መሪዎችም ሃሳቡ ሊዋጥላቸው አልቻለም።

    በአካባቢው ያሉ የእምነት መሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "መንግሥት መስጊዶችን መዝጋቱ አግባብ አይደለም። በእኔ አስተያየት ይሄ ተግባር ለኮሮናቫይስ መፍትሄ አይሆንም" ብለዋል።

    ለካኖ ሕዝብ ከአጎራባች አገራት ኒጀርና ቻድም ጋር ያለው የንግድ ግንኙነት የኑሯቸው መሰረት ነው። በታዋቂዎቹ ካንቲንና ክዋሪ የአልባሳት ገበያ እንዲሁም የእህል ገበያው ዳዋናው ለሦስቱ አገራት ድንበር ሕዝቦች የገቢ ምንጫቸው ነው።

    ሳኒ ሙሳ ከኒጀር ወደ ካኖ በየሳምንቱ አልባሳትና ጫማ ለመነገድ ይመላለሳል።

    "ይሄ የቤት መቀመጥ ውሳኔ በከፍተኛ ሁኔታ ነው የሚጎዳን፤ ምክንያቱም ምርታችንን ለመሸጥም ሆነ ለመግዛት ካኖ እንመላለስ ነበር" ብሏል።

    የካኖ ባለስልጣናት በበኩላቸው በቤት መቀመጥ ውሳኔው ለሚጎዱ አካላት 1 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ እንደተዘጋጀ ገልፀዋል።

    ለብዙዎች ግን ይሄ በቂ አይደለም የአፍሪካው ቱጃር ናይጄሪያው አሊኮ ዳንጎቴ እርዳታ ማድረግ አለበት የሚሉም አልታጡም።

  13. የትራምፕ የቀድሞ ጠበቃ ከእስር ሊፈቱ ነው

    በኮሮናቫይረስ ምክንያት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ ጠበቃ ማይክል ኮኸን ከእስር ሊፈቱ ነው።

    ጠበቃው የምርጫ ቅስቀሳ የፋይናንስ ሕግን በመጣስና ምክር ቤቱን በመዋሸት ጥፋተኛ ተብለው የሦስት ዓመት እስር ተፈርዶባቸው እንደነበር ይታወሳል። ከእስር የሚለቀቁትም በቀጣዩ ዓመት ነበር።

    የማይክል ጠበቃ እንዳሉት፤ የቀራቸውን የእስር ጊዜ ቤታቸው ሆነው ያጠናቅቃሉ። አሁን የሚገኙበት የኒው ዮርክ ማረሚያ ቤት ውስጥ ወረርሽኙ መግባቱ ተነግሯል።

    ኒው ዮርክ ከተቀሩት የአሜሪካ ግዛቶች በቀዳሚነት በቫይረሱ ተጠቅታለች።

    በአሜሪካ 473 ታራሚዎችና 279 የእስር ቤት ሠራተኞች በኮቪድ-19 መያዛቸውን የአገሪቱ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተናግሯል። 18 ታራሚዎች ደግሞ በቫይረሱ ሞተዋል።

  14. አውሮፓ እና አውስትራሊያ ወረርሽኙን ለመከላከል መተግበሪያ ሊጠቀሙ ነው

    በአውሮፓ ሕብረት አገራትና በአውስትራሊያ ኮሮናቫይረስ ከያዛቸው ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የሚጠቁም መተግበሪያ በቀጣይ ሳምንታት ተግባራዊ ይሆናል ተባለ።

    የጀርመን የጤና ሚንስትር መተግበሪያውን በቀጣይና ሦስትና አራት ሳምንታት ውሰጥ መጫን ይቻላል ብለዋል።

    መተግበሪያው በአውስትራሊያ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሥራ ላይ ይውላል ተብሏል።

    በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያደረጉ ሰዎችን የሚለዩ መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙ አገራት ቁጥር እጨመረ ነው።

    መተግበሪያዎቹ ብሉቱዝ በመጠቀም ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለይተው የማስጠንቀቂያ መልዕክት ይልካሉ።

    መተግበሪያዎቹ ዜጎችን ለመሰለልና ለመከታተል ሊውሉ ይችላሉ በሚል የሚተቿቸው አካላትም አሉ።

  15. መታሰሩን በመቃወም እርቃኑን የሆነው ሹፌር እስር ተፈረደበት

    በናይጄሪያ አቡጃ ከተማ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣሱ የታሰረው የታክሲ ሹፌር፤ እስሩን በመቃወም አስፋልት ላይ እርቃኑን በመቆሙ የስድስት ወር እስር ተፈርዶበታል።

    ኢማኑኤል ሊሞህዱ የተባለው ግለሰብ፤ ሦስት ክስ ቀርቦበት ነበር። እስሩ፤ በ78 ዶላርና በብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ይቅርታ በመጠየቅ ይቀየርልህ ተብሎም ነበር።

    “የምመግባቸው ልጆች አሉኝ፤ ሚስት አለችኝ፤ ገንዘብ ፍለጋ ነው ከቤቴ የወጣሁት። ከቤታችሁ አትውጡ አላችሁን። ምን እናድርግ? ረሃብ ከኮሮናቫይረስ ይከፋል” ያለው ኢማኑኤል፤ መላው ዓለም ያለበትን ሁኔታ እንዲረዳ እርቃኑን መሆኑን ተናግሯል።

    ናይጄሪያ ውስጥ የታክሲና አውቶብስ ሹፌሮች ፖሊሶች እንዳያስሯቸው ልብሳቸውን ያወልቃሉ።

  16. የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር፡ “ወረርሽኙ ሲገታ የዓለም ጤና ድርጅት መገምገም አለበት”

    የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር ሽንዞ አቤ፤ ወረርሽኙ ካለፈ በኋላ የዓለም ጤና ድርጅት መገምገም አለበት አሉ።

    ሆኖም ግን መንግሥታቸው ድርጅቱን መደገፍ እንደማያቆም ገልጸዋል።

    “አሁን የዓለም ጤና ድርጅትን የምንደግፍበት ወቅት ነው። ያለንበት ሁኔታ እልባት ሲያገኝ ግን ድርጅቱ መፈተሽ አለበት። እውነታው ብዙ ጉዳዮችና ፈተናዎች መኖራቸው ነው” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን አስተያየት የሰጡት፤ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ለድርጅቱ የምታደርገውን ገንዘብ ድጋፍ እንደምታቆም ይፋ ካደረጉ ከቀናት በኋላ ነው።

    ትራምፕ፤ የዓለም ጤና ድርጅትን ‘ቻይናን ከመጠን በላይ በማመንና ስህተት በመስራት’ ወንጅለዋል።

  17. የባህር ዳሩ የኮሮናቫይረስ ህክምና ማዕከል የመሳሪያዎች ጥያቄ

  18. በአፍሪካ ቢያንስ 300 ሺህ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ ተባለ

    አፍሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ቢያንስ 300 ሺህ ሰዎች እንደሚሞቱና ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ደግሞ ለድህነት እንደሚዳረጉ የተባበሩት መንግሥታት ገለጸ።

    በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እንዳለው፤ አህጉሪቷ 100 ቢሊዮን ዶላር መጠባበቂያ (ሴፍቲኔት) ያስፈልጋታል።

    አፍሪካ ውስጥ እስካሁን በቫይረሱ መያዛቸው ሪፖርት የተደረገው 20 ሺህ ሰዎች ቢሆኑም፤ የዓለም ጤና ድርጅት በቀጣይ ወራት ቁጥሩ ወደ 10 ሚሊዮን ሊያድግ ይችላል ብሏል።

    ከአህጉሪቱ ሕዝብ ከሲሶው በላይ ንፁህ ውሃ በማያገኝበት ሁኔታና 60 በመቶው የከተማ ሕዝብ በተጨናነቁ መንደሮች እየኖረ የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር መመሞከር ፈታኝ ይሆናል ተብሏል።

  19. ሀብታም ናይጄሪያውያን በድብቅ ያከሙ ክሊኒኮች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

    የናይጄሪያ መንግሥት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሀብታም ናይጄሪያውያንን በድብቅ የሚያክሙ የግል ክሊኒኮችን አስጠነቀቀ።

    አንዳንድ ባለሀብቶች መመሪያ በመጣስ ወደ ግል ህክምና ሰጪዎች እየሄዱ ሲሆን፤ መንግሥት ክሊኒኮቹ ሊዘጉ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

    በደንቡ መሰረት ኮሮናቫይረስ የያዘው ሰው ሪፖርት ማድረግ ያለበት ለአገሪቱ በሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ነው።

    የአገሪቱ የጤና ሚንስትር እንደተናገሩት፤ የግል የህክምና መስጫ ተቋማት ለተላላፊ በሽታ ህክምና ለመስጠት ፍቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

    የህክምና ባለሙያዎች ይህንን ደንብ መጣሳቸው፤ ቫይረሱ በተለያዩ ግዛቶች እንዲዛመት ምክንያት መሆኑም ተገልጿል።

    በሚስጥር ህክምና መሰጠቱ፤ ሀኪሞችን እንዲሁም ሌሎች ህሙማንን ለአደጋ ያጋልጣልም ተብሏል።

  20. በቻይናዋ ዉሃን ከተማ የኮሮናቫይረስ ሟቾች ቁጥር በ50 በመቶ ጨመረ