በዓለም ላይ ያሉ የኦሮቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓል አከባበር

በዛሬው ዕለት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የትንሳኤ በዓል ይከበራል። በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ አብይ በሆነው የትንሳኤ በዓል ብዙ ኢትዮጵያዊ በጉንም፣ ዶሮውን በቻለው አቅሙ ያርዳል። ዘመድ ለዘመድ መጠያየቅም ሆነ ከጎረቤት ጋር በአንድ ማዕድ መቋደስ፣ መጎራረረስ የበዓሉ አንድ ኣካል ነው። የኮሮናቫይረስ ስጋት ለዓለም ጠንቅ በሆነበት በዚህ ወቅት ከንክኪ ጋር የተገናኙ ልማዶችን ማስቀረት እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በተቻለ መጠን ሰብሰብ ብሎ በዓሉን ከማክበር መታቀብም ይመከራል። በሽታውን አካላዊ ርቀታችንን በመጠበቅ፣ መሰባሰባችንን በመቀነስ፣ እጃችንን በሚገባ በመታጠብ እንከላከል። መልካም የትንሳኤ በዓል እንዲሆን እየተመኘን የቀጥታ ዘገባችንን ከዚህ ገጽ ላይ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ታይዋን 700 የባህር ኃይል አባላትን በለይቶ ማቆያ ውስጥ አስገባች

    ታይዋን 700 የሚሆኑ የባህር ኃይል ባለስልጣናት፣ አባላትና ሰልጣኖችን በለይቶ ማቆያ ውስጥ አስገብታለች።

    ይህም የሆነው 24 አባላት በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው።

    የታይዋን የጤና ሚኒስትር ሼን ሽ ቹንግ ከባህር ኃይል አባላቱ በተጨማሪ 22 ሰዎች መያዛቸውን የተናገሩ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 21ዱ የሰራዊት አባላት መሆናቸውም ታውቋል።

    እነዚህ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙት ባለፈው ወር በታይዋን የምትገኘውን ፖላው ደሴት ሊጎበኙ ከመጡ ሶስት መርከቦች ነው።

    መርከቦቹ ረቡዕ እለት ወደ ሃገራቸውም ተሸኝተዋል።

    በታይዋን ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በአጠቃላይ 420 የደረሱ ሲሆን ስድስት ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል።

  2. በአሜሪካ ቤት መቀመጥን የሚቃወሙ ሰልፎች እንደቀጠሉ ነው

    በኮሮናቫይረስ ክፉኛ በተጠቃችው አሜሪካ የቫይረሱን መዛመት ለመግታት የወሰደችው የቤት መቀመጥ ውሳኔ ተቃውሞችን እያስከተለ ነው። ከሰሞኑም የነበሩት የተቃውሞ ሰልፎች እንደቀጠሉ ነው።

    አንዳንድ የመብት አቀንቃኞችን ጨምሮ የቫይረሱን መዛመት ለመቆጣጠር እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ገደብ እንዳለፉና ትንሽ ላላ ማለት እንዳለባቸውም ጥሪ እያደረጉ ነው።

    እነዚህ የተቃውሞ ሰልፎችም ሆኑ ስብሰባዎች የበለጠ ቫይረሱን ሊያስፋፉት ይችላሉ የሚልም ፍራቻ አለ። በቫይረሱ ከተጠቁ ሃገራት የቀደመ ስፍራ ባላት አሜሪካ 735 ሺ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፣ 39 ሺ ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል።

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በነዚህ ተቃውሞ ሰልፎች ማዕከል ሆነዋል። በዚህ ሳምንት አርብ ለነበረው የተቃውሞ ሰልፍም አነሳስተዋል የተባሉት ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገፃቸው ላይ ህዝቡ "ግዛቶችን ነፃ ያውጣ" የሚል መልእክትም አስፍረዋል።

  3. በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች ቫይረሱ ተገኘባቸው

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳሳወቀው ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገ 667 የላብራቶሪ ምርመራ ሶስት ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ተረጋግጧል።

    በዚህም በአጠቃላይ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 108 አድርሶታል።

    ሶስቱም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ሁለት ሴትና አንድ ወንድ ናቸው።

    በበሽታው ከተያዙት መካከል የ62 አመት ሴት ከአሜሪካ የመጡና በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ሲሆኑ በሽታው ከተያዘ ሰው ጋርም ግንኙነት እንደነበራቸው ተረጋግጧል።

    ሁለተኛው የ19 አመት ወጣት ሲሆን ከሳዑዲ አረቢያ የመጣና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ ሲሆን ሶስተኛዋ የ52 አመት ሴት የውጭ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ናቸው።

    ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን 7557 የኮሮናቫይረስ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጓል። በአጠቃላይ በቫይረሱ ተይዘው በህክምና ያሉ 87 ሰዎች ሲሆኑ፤ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች አሃዝ 16 ደርሷል። አንድ ግለሰብ በፅኑ ህሙማን ክፍል ናቸው።

    እስካሁን ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተረጋገጡት መካከል ሦስት ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው ማለፉን የሚኒስቴሩ መግለጫ ያመለክታል።

  4. "ሁሉም መንግሥታት ስህተት ይሰራሉ"የእንግሊዙ ሚኒስትር

    በእንግሊዝ ፖለቲካ ውስጥ አንጋፋ የሚባሉት ሚኒስትሩ ሚካኤል ጎቬ የእንግሊዝ መንግሥት የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመቆጣጠር የሄደበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነና መንግሥት ስህተት ፈጸሙን ተናግረዋል።

    ለቢቢሲ ጋዜጠኛ አንድሪው ማር በሰጡት ቃለ መጠይቅ " ሁሉም መንግሥታት ስህተት ይፈፅማሉ የኛንም ጨምሮ፤ ከስህተታችን ተምረን ልናስተካክል ይገባል" ያሉት ሚኒስትሩ አክለውም፤

    "ለወደፊቱ ያለፈ ስህተታችንን ዘወር ብለን የምናይበትና ጥሩ ትምህርት የምንወስድበት ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ" በማለት ተስፋቸውን ተናግረዋል።

    የእንግሊዝ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠርም ሆነ ያደረገው ዝግጀት በጣም የዘገየ ነው የሚሉ ከፍተኛ ትችቶችና ውግዘቶች መሰማታቸውን ተከትሎ ነው ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት።

  5. የሳዑዲ እምነት መሪዎች በረመዳን ፆም ወቅት ለፀሎት መሰብሰብ እንዲቆም አሳሰቡ

    የሳዑዲ አረቢያ የእምነት መሪዎች በመላው ዓለም ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች በረመዳን ፆም ወቅት ለፀሎት መሰባሳብ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

    የቫይረሱን መዛመት ለመግታት አካላዊ ርቀት መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል። በእስልምና እምነት ዘንድ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው የምሁራን ጉባኤ ባስተላለፈው መልእክት " መሰባሰብን አቁሙ፤ ምክንያቱም ለቫይረሱ መዛመት ዋነኛ ምክንያት ስለሆነ" ማለታቸውን የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ ዘግቧል።

    የሱኒ ሙስሊሞች በአብዛኛው በሚገኙባት ሳዑዲ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ቅዲስ ተብሎ የሚጠራውን መካን ጨምሮ በአገሪቷ ያሉ መስጊዶችን ዘግታለች።

    የሺአ ሙስሊሞች መሪና የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መስራች አያቶላህ ሆሚኒ በበኩላቸው ሙስሊሞች በአሁኑ የረመዳን ፆም መፆም ግዴታ አይደለም ብለዋል። ምክንያቱም ጤናን አደጋ ውስጥ የሚከት ከሆነ ሊፆሙ አይገባም በማለትም አሳስበዋል

  6. ስቲቪ ወንደር፣ ጆን ሌጀንድ፣ ሌዲ ጋጋ፣ በርና ቦይ... የጤና ባለሙያዎችን ያወደሱበት የቤት ኮንሰርት

  7. ኮሮናቫይረስ፡ በከፍተኛ ስጋት ላይ የምትገኘው ሃይቲ

    11 ሚሊዮን ህዝብ እንዳላት የሚነገረው በካሪቢያን ደሴት ላይ የምትገኘው ሃይቲ፣ በመላው አገሪቱ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ ወይም ቬንትሌተር ከ60 እንደማይበልጥ ተዘግቧል።

    ሌሎች አገራት በስፋት የተሰራጨውን የኮሮረናቫይረስ ለመቆጣጠር በሚታትሩበት በዚህ ወቅት ሃይቲ ከነጭራሹ ላታገግም ትችላለችም ተብሏል።

    ምንም እንኳን መንግኸሥት በርካታ ቬንትሌተሮችንና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አፍ መሸፈኛ ጭንብሎችን ለመግዛት ትረት እያደረገ ቢሆንም በአገሪቱ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ግን ውሳኔው በጣም ዘግይቷል እያሉ ነው።

    ‘’ እውነቱን ለመናገር ይህን ቫይረስ ለመከላከል ከነጭራሹ አልተዘጋጀንም’’ ብለዋል በመዲናዋ ፖርት ኦ ፕሪንስ የሚሰሩት ዶክተር ስቴፈን ድራገን።

    እስካሁን በሃይቲ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 40 ብቻ ሲሆን ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ይገመታል። ምክንያቱም በርካታ አገሪቱ ገጠራማ ክፍሎች ስላሉበት ሁኔታ በቂ መረጃ የለም።

    ነገሮችን ይበልጥ አስጊ የሚያደርጋቸው ደግሞ አብዛኛው የሃይቲ ዜጎች በስኳር በሽታና ሌሎች የጤና እክሎች የሚሰቃዩ መሆናቸው ነው።

    ቫይረሱ ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ ብዙ አገሬው ዜጎች ሕይወታቸውን ሊያጡም ይችላሉ።

  8. በኬንያ በኮሮና የተያዘ አሽከርካሪና ሶስት መንገደኞች የእንቅስቃሴ ገደቡን በመጣሳቸው በቁጥጥር ስር ዋሉ

    የኬንያ ፖሊስ በኮሮናቫይረስ የተያዘ አንድ አሽከርካሪና ሶስት መንገደኞች ባዶ የሬሳ ሳጥን ይዘው ለቀብር ነው የምንሄደው በማለት ከከተማ ውጭ በመንቀሳቀስ የተጣለውን እግድ በመተላለፋቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

    ግለሰቦቹ ለቀስተኛ በመምሰል ባዶ የሬሳ ሳጥን ተሸክመው ለ370 ኪሎሜትርም ያህል ተጉዘዋል፤ ፖሊስ ተጠራጥሮ ሆማ ቤይ በምትባለው ግዛት እስኪያቆማቸው ድረስ።

    የጤና ሚኒስትሩ ሙታይ ካግዌ በትናንትናው ዕለት እንደተናገሩት ተጓዦቹ ባዶ የሬሳ ሳጥን ተሸክመው በርካታ የድንበር መቆጣጠሪያዎችን ማለፍ ችለዋል።

    በሆማ የሚገኝ አንድ ፖሊስ ተጠራጥሮ የሬሳ ሳጥኑን ሲከፍተው ባዶ መሆኑ ታውቋል። በኮሮና የተያዘው አሽከርካሪ ተለይቶ ወደ ህክምና የተወሰደ ሲሆን፤ ሶስቱ መንገደኞች በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል።

    ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር የኬንያ መንግሥት የኮሮናቫይረስ እንዳይዛመት በሚል ከመዲናዋ ናይሮቢ ወደ ሌሎች ከተሞች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ያገደው።

    የጤና ሚኒስትሩ አክለው እንዳሳወቁትም አንዳንድ አሽከርካሪዎች ድንበር ላይ ያሉ ፖሊሶችን ጉቦ በመክፈል መንገደኞችን "በህገወጥ መንገድ" በመማላለስ ላይ መሆናቸው እንደተሰማና በዚህም ላይ አስፈላጊው ምርመራና ማጣራት እየተደረገ ነው ብለዋል።

    በኬንያ በትናንትናው ዕለት 16 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በአጠቃላይ ቁጥሩን 262 አድርሶታል።

  9. በዓለም ላይ ያሉ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ትንሳኤን እንዴት እያከበሩት ነው?

  10. የኮሮናቫይረስ ለሮቦቶች የሥራ ዕድል ይከፍት ይሆን?

  11. ኮሮናቫይረስ፡ ስፔን ሕጻናት ከቤት እንዲወጡ ልትፈቅድ ነው

    በስፔን የሚገኙ ህጻናት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ተብሎ ከመጋቢት 4/2012 ዓ.ም. ጀምሮ ከቤታቸው እንዳይወጡ ተደርገው ነበር።

    የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ደግሞ ህጻናቱ ወጣ ብለው ንጹህ አየር ይተንፍሱ በማለት ከሚያዝያ 19 ጀምሮ ውጪ እንዲወጡ ለማድረግ አስበዋል።

    በየባርሴሎና ከተማ ከንቲባዋ አዳ ኮላዉ እሳቸውም በቤታቸው ልጆች እንደላቸው በመግለጽ ህጉ እንዲላላ መጠየቃቸው አይዘነጋም።

    በስፔን እስካሁን 200 ሺ የሚሆኑ ሰዎች በዚሁ ቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከ20 ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ፓርላማ አጠቃላይ የእንቅስቃሴ ገደቡን እስከ ግንቦት 1/2012 ድረስ እንዲያራዝመው እጠይቃለሁም ብለዋል።

    ስፔን ውስጥ ስምንት ሚሊዮን ህጻናት ያሉ ሲሆን ላለፉት አምስት ሳምንታት ከቤታቸው ሳይወጡ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት ጤናቸው ላይ እክል እንዳይከሰት ተሰግቷል።

    የአገሪቱ የህጻናት መብት ጥምረት እንደገለጸው ህጻናቱ ከዚህ በላይ በቤት ውስጥ የሚቆዩ ከሆነ በርካታ አእምሯዊና አካላዊ ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል።

  12. እንኳን ለትንሳኤ በአል አደረሳችሁ

    እንደምን አደራችሁ!በዛሬው እለት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የትንሳኤ በአል ይከበራል።በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ወደ ምድር ወርዶ፣ ተሰቅሎ በሶስተኛው ቀን የተነሳበት እለት ነው- የትንሳኤ በአል።በክርስትያኖችም ዘንድ ታላቅ የሚባል በአል ነው።

    በቀደመውም ሁኔታ የእምነቱ ተከታዮች በየቤተክርስቲያናቱ በመሄድ በቅዳሴ፣ በፀሎት እንዲሁም በሌሎች አገልግሎቶች ያከብሩ ነበር።በአሁኑ ሰአት ግን ቫይረሱ እንዳይዛመት በሚል ስጋት ቤተክርስቲያናትም ሆነ ፤ሌሎች የአምልኮ ቦታዎች በሯቻቸውን ከርችመዋል።

    የኮሮና ቫይረስ ለአለም ስጋት ከሆነባት እለት አንስቶ የሰውን ልጅ የእለት ተእለት አኗኗር፣ ባህልና ሌሎችም መገለጫዎችን ቀያይሮታል።ከሰሞኑ ለበአል በጉንም፣ ዶሮውንም ለመሸመት ከወጡት መካከል ጭምብል አጥልቀው፣ ተራርቀው ይህንንም ባያደርጉ ብዙዎች የሄዱት በስጋት ነው።

    የበአላት መገለጫ የነበሩት ዘመድ ለዘመድ መጠራራት፣ ጎረቤቶች ጋር የተገኘውን መቋደስ ለኮሮና ቫይረስ መዛመት ስጋት በመሆኑ ብዙዎች በፍራቻ ላይ ናቸው።ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ማዕድ መቋደሱ፣ መጎራረሱ እንዲሁም የአብሮነት መንፈሱ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አደጋ ውስጥ ወደቀዋል።

    ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ በተያዘበት ሁኔታ፣ ከመቶ ሺዎች በላይ ህይወታቸው በተነጠቁበት ሁኔታ በአሉ የሚከበረውስ በምን መንፈስ ነው?እስቲ የበአሉ መንፈስ እንዴት እንደሆነ አጋሩን፣ በምንስ ሁኔታ እያከበራችሁት ነው? አስተያየቶቻችሁንም ሆነ ፎቶዎቻችሁን አጋሩን።

    ለመላው ክርስቲያን በሙሉ መልካም የትንሳኤ በአል እንዲሆንላችሁ እንመኛለን።ቢቢሲ አማርኛ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አገራት እየወሰዱት ስላለሉት እርምጃዎች፣ በአለማችን ከኮሮና ጋር ተያይዞ እየተከሰቱ ስላሉ ሁኔታዎች፣ እየተሞከሩ ስላሉ ክትባቶች እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን በቀጥታ ዘገባችን እናደርሳችኋለን። የትናንትና ዘገባችንንም በቀጣዩ ገፅ ታገኙታላችሁ

  13. ኬንያ ትልቁን የገበያ ቦታ ለመዝጋት ወሰነች

    ኢስሊ በመባል የሚታወቀውና በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የሚገኘው ትልቁ የግብይት ቦታ የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት በሚል ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘጋ ተወሰነ።

    በገበያ ቦታው ያሉ ነጋዴዎች የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ያወጣቸውን አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣ ሳኒታይዘር መጠቀምና ጭንብል ማድረግን የመሳሰሉ በሽታውን የመከላከያ መመሪያዎችን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ነው ለመዘጋት የበቃው።

    ነገር ግን ይህ ውሳኔ መድኃኒት ቤቶችንና የምግብ ምርት መሸጫዎችን የመሳሰሉ የመሰረታዊ ፍላጎት አቅራቢዎችን አይመለከትም ተብሏል።

    ኢስሊ ውስጥ ከቻይና፣ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከአንዳንድ የምዕራብ አገራት የሚመጡ ኤሌክትሮኒክሶች፣ አልባሰት፣ ጌጣጌጦችና ጨርቃ ጨርቆች የሚሸጡባቸው 18 ሺህ የሚገመቱ ሱቆችና 60 የገበያ አዳራሾች ይገኛሉ።

    በሽታው በኬንያ መገኘቱ ከተረጋገጠ ከወር በኋላ በተለያዩ ስፍራዎች ባሉ ማኅበረሰቦች ውስጥ ቫይረሱ እየተገኘ በመሆኑ የበለጠ እንዳይስፋፋ ስጋት ተፈጥሯል።

    ይህንንም ተከትሎ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፍሬድ ማቲያንጊ በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ጭምር በሽታውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

    ኬንያ ውስጥ እስካሁን በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ 262 ሰዎች ተገኝተዋል።

  14. የናይጄሪያው ፕሬዝዳነት የቅርብ ረዳት በኮቪድ-19 ምክንያት ሞቱ

    የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ የቅርብ ረዳት የነበሩት አባ ኪያሪ በኮሮናቫይረስ ከተያዙ በኋላ መሞታቸው ተነገረ።

    ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ "የኪያሪ ህልፈትን ለሕዝቡ ሲያሳውቅ በጥልቅ ሐዘን" እንደሆነ ጠቅሷል።

    "ኪያሪ በተደረገላቸው ምርመራ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ህክምናም ሲከታተሉ መቆየታቸውን" መግለጫው ጨምሮ አመልክቷል።

    በናይጄሪያ ውስጥ እስካሁን 493 ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 17 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

  15. "መደብር ሄጄ የውጪ አገር ሰው አንቀበልም አሉኝ" ኢትዮጵያዊቷ በቻይና

  16. የአዲስ አበባ መስተዳደር ለሥጋ ቤቶች ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጠ

    የኮሮናንቫይረስ ወረርሽኝም ሆነ የሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመከላከል ሁሉም ሥጋ ቤቶች የሚከተሉትን እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ጥሪው አቅርቧል።

    1. ሥጋ ከማስገባታቸው በፊት ቤቱንና መጠቀሚያ ቁሳቁሶችን በውሃ ሳሙናና በበረኪና ማጽዳት አለባቸው

    2. የሚገባው ሥጋ ሕጋዊና ከታወቀ ቄራ ታርዶ የቀረበ መሆን አለበት

    3. ሠራተኞች ሥጋ በሚሸጡበት ጊዜ የአፍና የአፍንጫ ጭንብል፣ ቆብ፣ ጋዎን መጠቀም አለባቸው

    4. ገንዘብ የሚቀበልና ሥጋ የሚቆርጥ ሠራተኛ መለየት አለበት

    5. ሠራተኞች የእጅ ሳሙናና ውሃ ተዘጋጅቶ በየጊዜው እጃቸውን በመታጠብ አለባቸው

    6. በሽያጭ ጊዜ ተገልጋዮች ከመሸጫ መስኮቱ 1 ሜትር ርቀው እንዲቆሙ መደረግ አለበት

    7. የተገልጋይ ቁጥር ከሁለት በላይ በሚሆንበት ወቅት ርቀታቸውን መጠበቅ አለባቸው

    8. ሥጋ ቤቶች ውስጥ ያልበሰለ ሥጋ (ቁርጥ/ጥሬ ስጋ፣ ያልበሰለ ክትፎ) ለምግብነት ማቅረብ የተከለከለ ነው

  17. በኮሮናቫይረስ ምክንያት ስጋት ውስጥ የወደቀው የጃፓን የጤና ሥርዓት

  18. ግዛቶች 'ጥብቅ' እርምጃ ወስደዋል ያሉት ትራምፕ የሕዝቡን ተቃውሞ ደገፉ

  19. በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከአንድ መቶ አለፈ

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው የምርመራ ውጤት መሰረት የቫይረሱ ምርመራከተደረገላቸው 659 ሰዎች መካከል ዘጠኙ በሽታው እንደተገኘባቸው አመልክቷል።

    ይህም እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ቫይረስ የተገኘባቸውን ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር ከአንድ መቶ በላይ እንዲሻገር በማድረግ 105 አድርሶታል።

    በበሽታው ከተያዙት መካከል አንድ የ13 ዓመት ታዳጊ ያለበት ሲሆን ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር ንክኪ እንዳለው ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

    በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች እድሜያቸው ከ13 እስከ 73 ውስጥ ያለ ሲሆን ሦስት ሴቶችና 6 ወንዶች ናቸው። በየዕለቱ የሚወጣው የበሽታው ሁኔታ መግለጫ እንዳለው የኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 8 ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ አንዱ የኢኳቶሪያል ጊኒ ዜጋ ነው።

    ከዘጠኙ ሰዎች ሦስቱ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው፣ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ናቸው። አምስቱ ደግሞ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ መሆናቸውን ተገልጿል።

    ቫይረሱ ከተገኘባቸው አንዷ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ከመጀመሩ በፊት ወደ ኢትዮጵያ የገባች ስትሆን፤ ሦስቱ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከጅቡቲ የመጡ ናቸው። ሌላኛው ግለሰብ የኢኳቶሪያል ጊኒ ተወላጅ ሲሆኑ ከእንግሊዝ መምጣታቸው ተጠቅሷል።

    ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን 6890 የኮሮናቫይረስ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጓል። በሽታው የተገኘባቸው 84 ሰዎች ደግሞ ህክምና ላይ ሲሆኑ፤ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች አሃዝ በአንድ ጨምሮ 16 ደርሷል። አንድ ግለሰብ በፅኑ ህሙማን ክፍል ናቸው።

    እስካሁን ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተረጋገጡት መካከል ሦስት ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው ማለፉን የሚኒስቴሩ መግለጫ ያመለክታል።

  20. “ዩናይትድ ኪንግደም ክትባቱን ለመፍጠር እንጂ በስፋት ለማምረት አቅም የላትም”

    ዩናይትድ ኪንግደም ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል የክትባት መጠን ለማምረት አቅም እንደሌላት ነገር ግን ክትባቱን ለመፍጠር “አመቺ ቦታ” መሆኗን የአገሪቱ መንግሥት ግብረ ኃይል አባል ፕሮፌሰር ጆን ቤል ተናገሩ።

    በቅርቡ የኮሮናቫይረስ ክትባት ማምረት ይቻል እንደሆነ የተጠየቁት ፕሮፌሰሩ በሰጡት መልስ ላይ ጥያቄው መሆን ያለበት ውጤታማ ይሆናል ወይ ነው ካሉ በኋላ “እስከ ግንቦት ድረስ ሊገኝ አይችልም” ሲሉ ወቅቱ ገና መሆኑን አመልክተዋል።

    "ዋናው ጉዳይ ተገቢው ሙከራ መደረጉ ላይ ነው፤ ምክንያቱም ክትባትን በተመለከተ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑ በጣሙን አስፈላጊው ነገር ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ቤል ተናግረዋል።

    "ነገር ግን በግንቦት ወር አጋማሽ ወይም መጨረሻ ላይ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል ማስረጃ ማግኘት ከቻልን ሥራው የሚጀመር ይመስለኛል። ከዚያም ነሐሴ አጋማሽ ላይ ፍጻሜን ያገኛል” ሲሉ አመልክተዋል።