እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ ለአፍሪካ ምን ያክል ከባድ ነው?
ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ እና ኬንያ ሙሉ በሙሉና በከፊል እንቅስቃሴ የገደቡ የአፍሪካ አገራት ናቸው። ምክንያታቸው ደግሞ ዓለምን እያሸበረ ያለው የኮሮናቫይረስ ነው።
ነገር ግን በአህጉረ አፍሪካ ለሚገኙ በርካታ አገራት እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ መገደብ የማይታሰብና አስቸጋሪ ነው ይላሉ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች።
አብዛኛዎቹ አፍሪካውያን ከእጅ ወደ አፍ የሚባል አይነት ኑሮ ነው ያለቸው፤ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴን መከልከል ማለት ደግሞ ድህነት ላይ ረሃብን እንደ መጨመር ነው።
በማንኛውም ሁኔታ እንቅስቃሴዎች የሚከለከሉ ከሆነ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚደረግበት ስርአት መዘርጋት አለበት።
እንደ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ያሉ አገራት ለህዝባቸው ምግብ በነጻ ማከፋፈል ጀምረዋል። ጋና ደግሞ ውሃና መብራት በነጻ እንዲቀርብ እንዲሁም የግብር እፎይታ እንዲኖር ወስናለች።
ነገር ግን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የአፍሪካ አገራት ይህንን ኃላፊነት ብቻቸውን ሊወጡት አይችሉም። የዓለማቀፍ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።