በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 92 ደረሰ

በዓለማችን ላይ ቢሊየኖች የኮቪድ-19ን እንቅስቃሴ ለመግታት ቤት ዘግተው ተቀምጠዋል። የዚህን ቫይረስ የስርጭት ሽክርክሪት ለመስበር ከሚረዱ መንገዶች አንዱ ራስዎን ሰዎች ከሚበዙበት ስፍራ ማራቅ ነው። አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን ደጋግሞ በሳሙናና በውሃ መታጠብ ደግሞ ሌላው መከላከያ ነው። እናንተም ጤና እኛም ደህና ሆነን እንድንውል እየተመኘን ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ የቀጥታ ዘገባችንን ይከታተሉ ግብዣችን ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በፈረንሳይ ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች ሞቱ

    በፈረንሳይ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 17,167 ደረሰ።

    10,643 የሚሆኑት ሕይወታቸው ያለፈው ሆስፒታል ሳሉ ነው።

    ባለፉት 24 ሰዓታት የሟቾች ቁጥር ከ500 በልጧል። ሆኖም ግን ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል ተብሏል።

    በፅኑ ህሙማን ክፍል ያሉ ሰዎች ቁጥርም ለሰባት ተከታታይ ቀናት ዝቅ ብሏል።

  2. ጋና ኮሮናቫይረስ ሊኖርባቸው ይችላል የተባሉ ሰዎችን በመተግበሪያ ልትከታተል ነው

    ጋና ኮሮናቫይረስ ሊኖርባቸው እንደሚችል የተገመቱ ሰዎችን የሚከታተል የስልክ መተግበሪያ መጠቀም ልትጀምር ነው።

    እስካሁን መተግበሪያውን በመጠቀም 100 በሽታው እንደያዛቸው የተጠረጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል። የጋና መንግሥት ወረርሽኙን ለመዋጋት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብሏል።

    መተግበሪያው የሰዎችን እንቅስቀሴ በስልካቸው ‘ጂፒኤስ’ ይከታተላል። በሽታው ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያደረጉ ሰዎችን መንግሥት እንዲያውቅም ያደርጋል።

    ራሳቸውን እንዲያገሉ የተነገራቸው ሰዎች መመሪያውን እየተከተሉ መሆኑንም ይከታተላል።

    መተግበሪያው በስድስት የአገሪቱ ቋንቋዎች ይሠራል። በእርግጥ የአገሪቱ ተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች 35 በመቶ ብቻ መሆናቸው ተደራሽነቱን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።

    ጋና 37,000 ሰዎችን መርምራ 636 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ስምንት ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

  3. በጣልያን የሟቾች ቁጥር በ578 ጨመረ

    በጣልያን ባለፉት 24 ሰዓታት የሟቾች ቁጥር በ578 ከፍ ብሎ፤ በአጠቃላይ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች 21,645 ደርሰዋል።

    አሁን በፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገኙት 3,079 ሰዎች ናቸው። ባለፉት 12 ቀናት ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎቹ ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል።

    በቫይረሱ ከተያዙት 38,092 ያህሉ አገግመዋል።

    ከአሜሪካ ቀጥሎ በርካታ ሰዎች የሞቱት በጣልያን ነው።

  4. የአፍሪካ ሕብረት ኃላፊ የትራምፕን ውሳኔ ኮነኑ

    የአፍሪካ ሕብረት ዋና ጸሐፊ ሙሳ ፋኪ ፕሬዝደንት ትራምፕ አገራቸው ለዓለም ጤና ድርጅት የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ታቋርጣለች ማለታቸውን ኮንነዋል።

    ሙሳ ፋኪ የትራምፕ ውሳኔን አሳዛኝ ካሉ በኋላ "ከመቼውም በላይ ዓለማችን በዓለም ጤና ድርጅት አመራር ላይ የምትመረኮዝበት ወቅት ነው" ብለዋል።

    ትራምፕ የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ኃላፊነቱን አልተወጣም በማለት አሜሪካ ለድርጅቱ ታደርግ የነበረውን ድጋፍ እንደሚያቋርጡ መናገራቸው ይታወሳል።

    የትራምፕ ውሳኔ በበርካታ አገራት እና ድርጅቶች ትችት ቀርቦበታል።

    የአውሮፓ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ ቻይና እና ጀርመን የትራምፕን ውሳኔ ከተቹት መካከል ይገኙበታል።

  5. በሊቢያ ግጭት መባባሱ የተባበሩት መንግሥታትን አስግቷል

    የተባበሩት መንግሥታት እና የተለያዩ የተራድኦ ድርጅቶች የሊቢያው ግጭት እንዲቆም ጥሪ ቢያቀርቡም፤ በዚህ ሳምንትም ግጭቱ ተባብሶ ቀጥሏል።

    ሰላማዊ ዜጎች እንዲሁም መኖሪያ አካባቢዎች ላይም ጥቃት ተሰንዝሯል።

    የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መግለጫ፤ አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ እንዳሳሰበው አስታውቋል። ነገሮች ባሉበት ከቀጠሉ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው እንደሚፈናቀሉም አስጠንቅቋል።

    በባህር ዳርቻ አካባቢ የሕዝብና የግል ንብረት ላይ በመንግሥት ደጋፊዎች ጥቃት መድረሱ በመግለጫው ተመልክቷል። ጄነራል ካሊፋ ሀፍታርም በመዲናዋ ትሪፖሊ ጥቃት ሰንዝሯል ተብሏል።

    ባለፈው ሳምንት ታጣቂዎች የውሀ መቆጣጠሪያ ጥሰው በመግባት፤ ታግተው የነበሩ የቤተሰብ አባላት እንዲለቀቁ ማስገደዳቸውንም የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።

    በዚህ ምክንያት ትሪፖሊን ጨምሮ በአብዛኛው ምዕራብ ሊቢያ ውሀ ተቋርጦ ነበር።

    በሊቢያ 29 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

  6. ዶ/ር ቴድሮስ በትራምፕ ውሳኔ ማዘናቸውን ተናገሩ

    የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አዽኃኖም አሜሪካ ለድርጅታቸው የምታደርገውን ድጋፍ አቋርጣለሁ ማለቷ እንዳሳዘናቸው ተናገሩ።

    በውሳኔው ቅር ተሰኝተናል ያሉት ኃላፊው፤ "ለህብረተሰብ ጤና፣ ለሳይንስ እና ለሁሉም የዓለም ሕዝብ ያለ አድልዎ እና ፍርሃት ማገልገላችን ፍጹም ሆኖ ይቀጥላል" ብለዋል።

    ዶ/ር ቴድሮስ አሜሪካ የምትሰጠውን ፈንድ ማቋረጧ በድርጅታቸው ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት እንደሚያጤኑ እና ሥራዎች ሳይቋረጡ መከናወናቸውን እንደሚያረጋግጡ ተናግረዋል።

  7. ጥቁሮችን አናስገባም ላለው ቅርንጫፍ ማክዶናልድስ ይቅርታ ጠየቀ

    በቻይና ጉዋንዡ ከተማ የሚገኝ አንድ የማክዶናልድስ ቅርንጫ ጥቁሮችን ወደ ምግብ ቤቱ አላስገባም ማለቱን ተከትሎ ማክዶናልድስ ይቅርታ ጠየቀ።

    በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት የተጋራ ተንቀሳቃሽ ምስል ወደ ማክዶናልድስ ቅርንጫፉ መግቢያ በር ላይ "ከአሁን በኋላ ጥቁሮች ወደዚህ ምግብ ቤት እንዳይገቡ ተነግሮናል" የሚል መልዕክት ለጥፏል።

    ማክዶናልድስ ይህን መረጃ እንደደረሰኝ ቅርንጫፉን ለግዜው ዝግ አድርጊያለሁ ብሏል።

    በጉዋንዡ ከተማ በእስያውያን እና በአፍሪካውያን መካከል መቃቃር መፈጠሩ ተነግሯል።

    ባሳለፍነው ሳምንት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ኮሮናቫይረስ በአፍሪካውያን ዘንድ እንደ አዲስ እየተሰፋፋ ነው የሚል ሐሰተኛ ወሬ መስፋፋቱን ተከትሎ በርካታ ጥቁሮች ተከራይተው ከሚኖሩበት ቤት በኃይል እንዲወጡ ሲደረግ ነበር።

    በጉዋንዡ በርካታ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ጥቁር አፍሪካውያን ይገኛሉ።

  8. አይስላንድ፡ “ብቸኝነት እንዳይጎዳችሁ ዛፍ እቀፉ”

    የአይስላንድ ደን ጥበቃ፤ በኮቪድ-19 ምክንያት ሰዎች በብቸኝነት እና በመገለል እንዳይጎዱ፤ ዛፍ እንዲያቅፉ መከረ።

    በርግሩን አርና ቶርስቲንስድቶር የተባሉት ከፍተኛ የደን ጥበቃ ኃላፊ፤ ነዋሪዎች ደን ውስጥ እንዲናፈሱ እና ዛፍ በማቀፍ እንዲጽናኑም ጥሪ አቅርበዋል።

    በምሥራቅ አይስላንድ የደን ኃብት ኃላፊ ቶር ቶርፊንሰን፤ “አይናችሁን ጨፍናችሁ ዛፍ እቀፉ፤ ፊታችሁን ዛፉ ሲነካው ደስ የሚል ስሜት ይፈጥራል። ስሜቱ ከእግር እስከራሳችሁ ይሰራጫል። መንፈሳችሁም ይታደሳል” ብለዋል።

    በየቀኑ ለአምስት ደቂቃ ዛፍ ማቀፍ አንዳች ኃይል እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

  9. በግብፅ እና በሱዳን ሚሊዮኖች እጅ መታጠቢያ እንደሌላቸው ተገለጸ

    የተባበሩት መንግሥታት፤ ወደ 41 ሚሊዮን የሚጠጉ የግብፅ እና የሱዳን ዜጎች ውሃን ጨምሮ አስፈላጊው የንጽህና መጠበቂያ ስለሌላቸው፤ በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው ሰፊ መሆኑን ጠቆመ

    በድርጅቱ የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ በግብፅ 10 ሚሊዮን፣ በሱዳን ደግሞ 31 ሚሊዮን ሰዎች እጅ መታጠቢያ የላቸውም።

    ከኮሮናቫይረስ ራስን ለመከላከል ከሚረዱ ዋነኛ መንገዶች አንዱ እጅ መታጠብ መሆኑ ይታወቃል።

  10. በኮሮና ዘመን ገበያ የደራላቸው የዓለማችን ቁጥር አንዱ ቱጃር

    የዓለማችን ቁጥር አንድ ቱጃር ጄፍ ቤዞስ በከሮና ዘመን ገበያው ደርቶላቸዋል።

    የአማዞን መስራችን እና አለቃ ጄፍ ቤዞስ በወረርሽኙ ስርጭት ምክንያት የኢንተርኔት ገበያ በመድራቱ ተጨማሪ 24 ቢሊዮን ዶላር መሰብሰብ ችለዋል።

    ይህም ብቻ ሳይሆን የድርጅታቸው የገበያ ድርሻ ከፍ ብሏል።

    ቤዞስ የዓለማችን ቁጥር አንድ ሃብታም የሆኑት 138 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት በማከማቸታቸው ነው።

    በአሁኑ ወቅት የኢንተርኔት ግብይት እጅጉን በመጨመሩ አማዞን በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር ተገዷል።

    የብሉምበርግ ቢሊየነርስ ኢንዴክስ እንደሚያመላክተው፤ በዓላማችን ላይ የመጀመሪያዎቹ 500 ሃብታም ግለሰቦች ጠቅላላ የተጣራ ሃብት ከ553 ቢሊዮን ዶላር አይዘልም።

  11. የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ የጠየቀው አስቸኳይ ድጋፍ ውድቅ ተደረገበት

    የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ከገባበት ኪሳራ ለመውጣት የጠየቀው የገንዘብ ድጋፍ በአገሪቱ መንግሥት ውድቅ ተደረገ።

    አየር መንገዱ ቀድሞውኑ ኪሳራ ውስጥ የቆየ ሲሆን፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኘ መከሰት ችግሩን አባብሶበታል።

    የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በአየር መንገዱ የተጠየቀውን 500 ሚሊዮን ዶላር አልሰጥም ብሏል።

    መንግሥት ባለፉት ሶስት ዓመታት አየር መንገዱን ለመታደግ 1 ቢሊዮን ዶላር ሰጥቷል ተብሏል።

    ይህንንም ተከትሎ አየር መንገዱ ሙሉ በሙሉ የመዘጋት እድል ይገጥመዋል የተባለ ሲሆን፤ በዚህም 5000 ሰዎች ከሥራቸው ይፈናቀላሉ።

    አየር መንገዱ ላለፉት 9 ዓመታት ትርፍ ሳያስመዘግብ መቆየቱ ተነግሯል።

    የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኘ መከሰቱን ተከትሎ አብዛኛውን የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ በረራዎቹን ለመሰረዝ ተገዷል።

  12. ሰበር, በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን አለፈ

    ከወራት በፊት ቻይና ውስጥ ተቀስቅሶ ዓለምን ያዳረሰው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች አሃዝ ከሁለት ሚሊዮን በላይ መድረሱ ተነገረ።

    የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሚያሰባስበው መረጃ እንዳመላከተው በዓለም ዙሪያ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው ሰዎች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን ተሻግሯል።

    ነገር ግን ይፋዊ ቁጥሩ ይህንን ያመለክት እንጂ በበሽታው የተያዙት ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ እንደሚሆን ወረርሽኙን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው።

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ ከሆነ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 600 ሺህ የሚሆኑት የሚገኙት በአሜሪካ ነው።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 128 ሺህን ተሻግሯል።

  13. ዩኬ የዓለም ጤና ድርጅትን መደገፏን አታቆምም ተባለ

    ዩናይትድ ኪንግደም የአሜሪካን ውሳኔ በመከተል የዓለም ጤና ድርጅትን መደገፍ ለማቆም "እቅድ የላትም" ሲሉ የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ተናገሩ።

    የጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን አማካሪ ዩኬ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ለሚደረገው ጥረት የ75 ሚሊዮን ፓዎንድ ድጋፍ ማድረጓን አስታውሰው፤ የዓለም ጤና ድርጅት "የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ዓለም አቀፍ ርብርቦች እንዲካሄዱ ቀዳሚ ሚና ተጫውቷል" ብለዋል።

    ቃል አቀባዩ ፕሬዝድንት ትራምፕ ለዓለም ጤና ድርጅት ፈንድ አላደርግም ስለማለታቸው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

  14. የመጀመሪያውን ኮሮናቫይረስ ስላገኘችው ሴት ያውቃሉ?

    የመጀመሪያውን ኮሮናቫይረስ ያገኘችው የስኮትላንዳዊ አውቶብስ ሾፌር ልጅ ናት።

    ጁን አልሜዳ ትባላለች። ትምህርት ያቋረጠችው በ16 ዓመቷ ነበር።

    ዶ/ር ጁን በቫይረስ ምርምር ፈር ቀዳጅ ከሚባሉት አንዷ ናት። የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ተከትሎም ከዓመታት በፊት የሠራቸው ሥራ ዳግም መነጋገሪያ ሆኗል።

    ኮቪድ-19 አዲስ ቫይረስ ቢሆንም ከኮሮናቫይረስ አይነቶች አንዱ ነው። የመጀመሪያውን ኮሮናቫይረስ ዶ/ር ጁን ያገኘችው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1964፣ በለንደኑ ሴንት ቶማስ ሆስፒታል ውስጥ በሚገኝ ቤተ ሙከራዋ ነበር።

  15. ካታር በርካታ ስደተኛ ሠራተኞችን አባራለች ተባለ

    የካታር አመራሮች፤ በርካታ ስደተኛ ሠራተኞችን አባረዋል። አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንዳለው፤ ሠራተኞቹ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሊደረግላቸው እንደሆነ ተነግሯቸው ነበር።

    የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ፤ ያናገራቸው 20 የኔፓል ዜጋ ሠራተኞች፤ ባለፈው ወር በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሠራተኞች ጋር እንደተያዙ ተናግረዋል።

    አውሮፕላን ከመሳፈራቸው በፊት በማቆያዎች ውስጥ ለበርካታ ቀናት በአስከፊ ሁኔታ እንደተያዙም ተናግረዋል።

    ካታር ሕገ ወጥ ተግባር የፈጸሙ ሰዎችን ለይቻለሁ ብላለች።

    የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው፤ የውሃ አቅርቦት የሌላቸው ወደ 74 ሚሊዮን የሚሆኑ በአረቡ አገራት የሚሮሩ ሰዎች በኮቪድ-19 የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

    87 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በቤታቸው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የላቸውም። ውሃ ለማግኘት ከብዙኃኑ ጋር ወደሚጋሩት ስፍራ መመላለሳቸው በበሽታው የመያዝ እድላቸውን እንደሚጨምረውም ተጠቁሟል።

    በሌላ በኩል በኢራን ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሟቾች ቁጥር ከመቶ በታች ሆኗል። የጤና ሚንስትር እንዳለው፤ ባለፉት 24 ሰዓታት የሞቱ ሰዎች 94 ናቸው። ይህም አጠቃላይ የሟቾችን ቁጥር 4,777 አድርሶታል።

  16. ጀርመን ከሁለት ሳምንት በኋላ የእንቅስቃሴ ገደቧን ታላላለች ተባለ

    የጀርመን መራሄተ መንግሥት አንጌላ መርክል በጀርመን ተላልፎ የሚገኘውን ያለ መንቀሳቀስ መመሪያ ለማላላት ከ16 የአገሪቱ ገዢዎች ጋር ሊመክሩ መሆኑ ተነግሯል።

    የጀርመን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ የፌደራል መንግሥቱ የእንቅስቃሴ ገደቡ ሚያዚያ 25 ላይ እንዲያበቃ ይፈልጋል።

    ይሁን እንጂ ከአምስት ቀናት በኋላ አንዳንድ መደብሮች ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ ሊጀምሩ ይችላሉ ተብሏል።

    ጀርመን ምንም እንኳ 3254 ሰዎችን በቫይረሱ ብታጣም፤ ከተቀረው ምዕራብ አውሮፓ አገራት ጋር ስትነጻጸር የደረሰባት ጉዳት ከፍተኛ አይደለም።

    ዴንማርክ በበኩሏ ዕድሜያቸው ከ11 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች ትምህር ቤቶችን ከፍታለች። ኦስትሪያ ደግሞ ከትናንት ጀምሮ አነስተኛ ሱቆች በራቸውን እንዲከፍቱ ፈቅዳለች።

  17. የ99 ዓመት አዛውንት ከኮሮናቫይረስ አገግመው ከሆስፒታል ወጡ

    በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተዋጉት የ99 ዓመት አዛውንት ከኮሮናቫይረስ አገግመው ከሆስፒታል ወጡ።

    ኤርማንዶ ፒቬታ የተባሉት አዛውንት፤ ከሆስፒታል ሲወጡ በጭብጨባ እና በትራምፔት ሙዚቃ ታጅበው ነበር።

    በሌላ በኩል ብራዚል ውስጥ የሚገኙ ነዳጅ አውጪ ሠራተኞች ከዚህ ቀደም ከተገመተው በላይ በቫይረሱ ሊጠቁ እንደሚችሉ ተነግሯል።

    126 ሠራተኞች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ፤ 897 ደግሞ ተይዘው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

    በተለይም ሠራተኞች ተጠጋግተው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ስርጭቱ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል። ዝርዝሩን ለማንበብ የ99 ዓመቱ ሽማግሌ 4 ሚሊዮን ፓውንድ ሰበሰቡ

  18. ኢራን በ100 ሜትር ርቀት በኮሮናቫይረስ የተያዘን ሰው የሚለይ መሣሪያ ፈጠርኩ አለች

    ኢራን በ100 ሜትር ርቀት በኮሮናቫይረስ የተያዘን ሰው የሚለይ መሣሪያ ፈጠርኩ አለች።

    የኢራን ኢስላሚክ ሪቮሉሽን ጋርድ ኮማንደር ከ100 ሜትር ርቀት ላይ ኮሮናን ይመረምራል ያሉትን መሣሪያ ማሳየታቸውን ታስኒማ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

    መሣሪያው 'ማግኔቲክ ፊልድ' በመፍጠር፤ አንቴናው በ100 ሜትር አከባቢ ውስጥ በቫይረሱ የተጠቃ ቦታን በአምስት ሰከንድ ውስጥ ይለያል ሲሉ ሜጀር ጀነራል ሁሴን ሳላሚ ተናግረዋል።

    ኮማንደሩ ጨምረውም መሣሪያው 80 በመቶ ትክክለኛ ውጤትን ያሳያል ብለዋል።

    ኢራን ይህ መሣሪያ ስለመሥራቱ ማረጋገጫ አላቀረበችም።

    ባለሙያዎች አንድ ሰው በኮቪድ-19 ስለመያዙ የሚረጋገጠው ከአንድ ግለሰብ አፍንጫ እና ጉሮሮ የሚወሰደውን ናሙና በላብራቶሪ በመመርመር ብቻ ነው ይላሉ።

  19. ቻይና እና ጀርመን ትራምፕን አወገዙ

    ቻይና እና ጀርመን፤ ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጀት የምታደርገውን ድጋፍ አቆማለሁ ማለታቸውን ያወገዙ አገራትን ዝርዝር ተቀላቅለዋል።

    ወረርሽኙ እጅግ አሳሳቢ በሆነበት በዚህ ወቅት ድጋፍ ለማቆም መወሰኑ በጣም እንዳሰጋቸው የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

    የጀርመን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሂኮ ማስ “መወቃቀስ ዋጋ የለውም” ብለዋል።

    ወረርሽኙን ለመግታት፤ የምርመራ መሣሪያና ክትባት በማሰራጨት ረገድ የዓለም ጤና ድርጅት እና የአውሮፓ ሕብረት የበለጠ መተባበር አለባቸው ብለዋል።

    የአውሮፓ ሕብረት የውጪ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል፤ “ከመቼውም በላይ በሽታውን ለመግታት ጥረት በሚያስፈልግበት ወቅት፤ ድጋፍ ማቆም ላይ የሚያደርስ አንዳችም ምክንያት የለም” ብለዋል።

  20. ደቡብ ኮሪያውያን ጭምብልና ክሊኒኮች በተዘጋጁበት ሁኔታ ምርጫ እያካሄዱ ነው

    ደቡብ ኮሪያ በኮሮና ወቅትም ቢሆን ምርጫው ይካሄዳል ብላ በመወሰኗ መራጮች ወደየጣቢያው እየመጡ ነው።

    ነገር ግን ዝም ብሎ በዘፈቀደ መምጣት የለም። ሁሉም የፊት ጭምብል ማድረግ እንዲሁም በአንድ ሜትር ተራርቀው መሰለፍ አለባቸው።

    ከዚያም የሙቀት መጠናቸው ይለካል፣ እጃቸውንም በሳኒታይዘር እንዲያፀዱ ይደረግና የእጅ ጓንት ያጠልቃሉ።

    እነዚህን ሁሉ ሂደቶች ካለፉ በኋላ ነው ድምፃቸውን ለመስጠት ወደተከለለው ሚስጥራዊ ቦታ የሚወሰዱት።

    በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ እየተዛመተ ባለበት ወቅት የብሔራዊ ጉባኤው ምርጫ በተያዘለት እቅድ መሰረት እንዲካሄድ እነዚህ ቅድመ ጥንቃቄዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

    ደቡብ ኮሪያ በታሪኳ ውስጥ ምርጫን አራዝማ አታውቅም። በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ በነበረው የኮሪያ ጦርነት እንኳን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተካሂዷል።

    በዚህ ወቅት ለባለስልጣኖቹ ዋነኛ ፈተና የነበረው ምናልባት ቫይረሱ ቢዛመትስ የሚል ነበር።

    እናም የሙቀት መለኪያው ጣቢያዎቹ ላይ አስገዳጅ የሆነበትም ምክንያት መከላከል ያስችል ዘንድ በሚል ነው።

    መራጮች የሙቀት መጠናቸው ከ37.5 ሴንቲግሬድ በላይ ከሆነ ከሌላው መራጭ ተነጥለው በተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲመርጡ ይደረጋሉ።